ከምን ነፃ ልውጣ?!

Views: 90

በነፃነት ሥም የሚደረግ ትግል መነሻው ክብርና ዕውቅናን መሻት ነው የሚሉት ይነገር ጌታቸው፣ በዚህ መነሻ የተነሱ ጥያቄዎች በኢትዮጵያ ታሪክ መንግሥታትን የቀያየሩበትን ሁኔታ አብራርተዋል። ነፃነት ለሁሉም ነገር ምላሽ ይሰጣል በሚል፣ ነፃ ገበያ ለአዳጊ አገራት የችግር መውጫ ተደርጎ በኃያላኑ ቀርቦ ተቀባይነት ቢያገኝም፣ አካሔዱ አገራቱን ስለከተተበት ቀውስ ይጠቅሳሉ። በዚሁ ጽሑፋቸው ላይ ወደ ነፃነትና እኩልነት የሚደረገው ጉዞ መነሻው ከየት ነው? ሲሉም ይጠይቃሉ።

‹ከምን ነፃ ልውጣ?› የቤቲ ጂ እና ቤሪ አልበም የሚጋሩት የወል ግዛት ነው። ኹለቱ ድምፃውያን በሥራዎቻቸው ውስጥ ፍልስፍናዊ የመሰለውን የነፃነት ጉዳይ አንስተው ያንጎራጉራሉ። ዜማቸው ግለሰባዊ ብቻ አይመስለኝም፤ እንደ ማኅበረሰብም ሆነ እንደ አገር ከምን ነፃ ለመውጣት እንደምንሞክር አናውቀውም። ጥያቄያችን የቱን ጠልቶ የቱን ለመውደድ እንደሆነም ግልፅ አይደለም። ታሪካችን ለሄግሊያን ትርጓሜ የሚመች ስለሆነ እሱን ልዋስ። ፍሬድሪክ ሄግል ‹የሰው ልጆች የዘመናት የነፃነት ትግል ዋና ግቡ ዕውቅና እና ክብርን ማግኘት ነው› ይላል።

የኢትዮጵያም የዘመናት ሂደት ከዚህ እውነት አያመልጥም። የእርስ በእርስ ጦርነታችንም ሆነ አብዮታችን ግቡ ክብርና ዕውቅናን መሻት ነበር። የሩቅ ቅርብ የሆነውን የተማሪዎችን ጥያቄ እናንሳ። የ1960ዎቹ ፈናኖች መሬት ላራሹ፣ ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም እና የብሔሮች ጭቆና ይቅር የሚል ሙግት ማንሳታቸው ይታወሳል። ይህ ደግሞ የሰርኩን ዓለም ነቅንቆ ንጉሡን ከዙፋናቸው አሽቀነጠረ፤ ደርግንም አራት ኪሎ ደጃፍ አደረሰ።

ለብሔራችንም ሆነ ለመሬታችን ዕውቅና ይሰጠው የሚለው ጥያቄ ግን ለሌተናትንት ኮለኔል መንግሥተ ኃይለማርያም የሚመለስ አልነበርም። እናም የአገሪቱ የፖለቲካ ልኂቅ በአካሄዱ ላይ ቢለያይም ስርዓቱን ለማስወገድ ተረባረበ። ከፊሉ ብረት አንግቶ ከገጠር ተንስቶ ወደ አዲስ አበባ ገሰገሰ፤ የቀረው የከተማ ውስጥ አብዮት ለድል ያበቃል ብሎ ተገዳደለ። ነፃነት የሚል የዳቦ ስም የተሰጠው ትግል በሕወሓት አሸናፊነት ተገባደደ።

ሦስቱ ጥያቄዎች አሁንም የምኒልክን ቤተ-መንግሥት እንደከበቡ ናቸው። የአቶ መለስ አስተዳደር ለዚህ ማስተንፈሻ ቦይ ካልፈጠረ በቀር የ17 ዓመት የጫካ ኑሮው ዋጋ እንደሌለው ተረድቶታል። እናም የተማሪው ትግል የፈጠራቸው ኦነግ፣ ሕወሓትና ኢሕዴን በጉልህ የተጫኑት ሕገ-መንግሥት የሕዝብ ዕውቅናና ክብርን አስቀድሜያለሁ አለ።

ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤቶችም ‹ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች› መሆናቸውን አወጀ። የሕዝቦች የነፃነት ጥያቄም በሕግ ደረጃ መመለሱ ተበሰረ። ውጤቱ ግን እንደሰመመን መርፌ ጊዜያዊ ማስታገሻ እንጂ ፈዋሽ አልሆነም።
ለምን?

እውቁ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ፍራንሲስ ፉክያማ ዓለም ላይ ያሉ የሕዝቦች እውቅና እና ክብር መሻት ጥያቄዎች በማያዳግም ሆኔታ ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉት ስርዓተ መንግሥቱ ሌበራሊዝምን ከተከተለ ብቻ መሆኑን ይጠቅሳል። ፉክያም THE END OF THE HISTORY AND THE LAST MAN በተሰኘ መጽሐፉ፣ የሌበራል ስርዓተ ማኅበር እኩልነትን፣ ነፃነትን የሚያጣጥም በመሆኑ ችግር ፈችነቱ አያጠያይቅም ሲል ይሞግታል። የትውልደ ጃፓናዊው ምክረ ሐሳብ የምዕራቡ ዓለም የፖለቲካ አስተምሮ አዕማድ ከሆነም ውሎ አድሯል።

በመሆኑም አሜሪካም ሆነ እንግሊዝ ዓለም ባንክም ሆነ IMF ታዳጊ አገራት ከችግሮቻቸው ለመውጣት ከፈለጉ ሌበራሊዝም ብቸኛ መዳኛቸው እንደሆነ ጎትጉተዋል። ነፃነት ለሁሉም ነገር ምላሽ ይሰጣል በሚል መርህም ነፃ ገብያ፣ ነፃ ብሔር (ከጭቆና የተላቀቀ) እና ነፃ መንግሥት (በኢኮኖሚው ውስጥ ገብቶ የማይፈተፍት) እንዲመሠረት ጥረት አድርገዋል። ድሃ አገራት በዚህ ዘርፍ ለሚያደርጉት ተነሳሽነትም የሚችሉትን ሁሉ ለመደገፍ ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።

የቀዝቃዛውን ጦርነት ፍፃሜ ተከትሎ በዋሽንግተን የተካሔደው ስምምነትም ለዚህ ፕሮጀክት ዋና ማስፈፀሚያ ሆነ። ዓለም ባንክና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የሚመሩት የአገራት የመዋቅር ማስተካክያ ፕሮግራምም ይፋ ተደረገ። በርካታ ታዳጊ አገራት ‹ገቢያችሁንም ሆነ ስርዓታችሁን ነፃ አድርጉ› የሚለውን ቅደመ ሁኔታ በማሟላት ቢሊዮን ዶላሮችን ተበደሩ። የምዕራቡን ዓለም የተስፋ ቃል ሰመተው ‹እንደኛ ያለ አገር ምን ሉዓላዊነት አለው!› ብለው በራሳቸው ላይ ተዘባበቱ። ይሁን እንጂ ይመጣል የተባለው ብልፅግና የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ።

በአንፃሩም የከፋ ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ ተፈጠረ። ‹በሩን ከፋፍቱልን፤ እኛ ባደግንበት መንገድ እናንተን እንምራችሁ› ያሉት ግዙፍ ተቋማትም ብድራችንን መልሱልን ብለው ድሆች መንግሥታት ላይ በረቱ። ውስብስብ ችግር ውስጥ የተዘፈቁት መንግሥታት ለዕዳ ክፍያ አይደልም ለሠራተኞቻቸው የሚሆን ገንዘብ በማጣታቸው ተጨማሪ የገንዘብ ኖቶችን ማተም ጀመሩ። እሱ ደግሞ የኑሮ ውደነቱን አንሮ በሕዝባዊ አመፅ መንግሥታቱን ማሰናበት ቀጠል።
በዓለም የገንዘብ ድርጅት ውስጥ የሠራው በኢኮኖሚክስ ኖቬልን ያሸነፈው ጆሴፍ ስትግሊዝ ቀድሞ ንስሃ ገባ። ‹‹የእኔና የባልደረቦቼ ምክር ፈፅሞ ስህተት ብቻ ሳይሆን፣ የምዕራባውያን መንግሥታት ራስ ወዳድነት የተጫነው ነበር›› አለ። ተቋሙም ወቀሳ ሲበረታበት ‹መዋቅራዊ ማሻሻያ በሚል ለድሃ አገራት ያበደርኩት ገንዘብ ችግር ፈች ሳይሆን ችግር አባባሽ በመሆኑ ይቅርታ እጠይቃለሁ› አለ። ፀፀቱ ግን ስላለፈው እንጂ የወደፊት ስህተቱን ላለመድገሙ ዋስትና የሚሆን አልነበረም። በዚህ የተነሳም የተመሠረተበትን ለምዕራቡ ዓለም የሚመች የፖለቲካል ኢኮኖሚ ስርዓትን መፍጠርን አላቆመውም። እናም ሌበራላይዜሽን የሚል አስተምሮውን ይዞ ዛሬም መባዘኑን ቀጥሏል።

እዚህ ላይ አንድ አስገራሚ እውነትን መጥቀሱ ተገቢ ይመስለኛል። ለዓለም አቀፍ ተቋማት የቃል ኪዳን ሰንድ ሆኖ የሚያገለግለው የፍራንሲስ ፉክያማ ድርሳን፤ አሁንም ያላባራው የሰው ልጆች ዕውቅናና ክብርን የመሻት ጥያቄ የሚታከመው በሌበራል ዴሞክራሲ ብቻ ነው ብሎ ማመኑን ከላይ ጠቅሻለሁ።

ይሁን እንጅ እንዲህ ያለው ፍኖት በአደጉት አገራትም ውጤት ማስመዝገብ ተስኖታል። እራሱ ፉክያማ ባለፈው ዓመት ለንባብ ባበቃው “ማንነት” በተሰኘ መጽሐፉም ውስጥ ዛሬም በሌበራል ዴሞክራሲ ግማሽ ምዕተ ዓመት የተጓዙ አገራት ሳይቀር በሕዝቦች የማንነት ጥያቄዎች ተወጥረው መያዛቸውን አምኗል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ለጽሑፌ ርዕስ ያደረኩት ‹ከምን ነፃ ልውጣ?› የሚለው ጥያቄ ነው። ሌበራል ዴሞክራሲ ካላይ እንደጠቀስኩት የሕዝብን እኩልነትና ነፃነትን የሚያውጅ በመሆኑ የዜጎችን ፍላጎት የመመለስ ትልቅ መደላድል ይፈጥራል።
ነገር ግን ወደ ነፃነትና እኩልነት የሚደረገው ጉዞ መነሻው ከየት ነው? በፍፁም ድህነት ውስጥ ያለን ሰው ከአንድ ባለሀብት ጋር ‹ከዛሬ ጀምሮ እኩል ነህ› ብለን ጉዞ ብንጀምር፣ ውጤቱ የድሃውን ባርነት ከማወጅ ውጭ ምንስ ዕርባና ይኖረዋል? በፖለቲካው መስክም የደሰነችን ሕዝብ ከአሁን በኋላ ከትግራይ ጋር እኩል ነህ ብለን ብንራመድ፣ ቀዳሚው ልዩነት እንዴት ይጠባል? ከዚህ አንፃር እኩልነትና ነፃነትን ለማስፈን በቅድሚያ ሁሉም ተሳታፊዎች በሚቀራረብ ደረጃ ላይ ሊገኙ ይገባል።

የአቶ መለስ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፅንሰ ሐሳብ ዋና ዓላማው እንዲህ ያለውን መደላድል አስቀድሞ መፍጠር ነው። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በጻፏቸው ድርሳናት ኢሕአዴግ መክሰሙ አይቀርም የሚል ሟርት አዘል አስተያየትን የሚሰነዝሩትም ሌበራል ዴሞክራሲን መገንባት የምንችልበት ደረጃ ላይ ከደረስን በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ግንባር አላስፈላጊ አይደለም ብለው በማመናቸው ነው። ጉዞቸው እሱን ያደርግ ነበር? የሚለውን ጥያቄ ለአንባቢው ትቼ ዛሬ እየጀመርነው ያለነው ሌበራል ዴሞክራሲ መደላድሉ ስለተፈጠረ የምንገባባት ነው ወይንስ ተገደን የሚለውን ላንሳ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተረከቧት ኢትዮጵያ በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚው ዘርፍ እጅግ የሚያስፈራ ገፅታ ውስጥ የነበረች መሆኑ አያከራክርም። እንዳንዶች እንደሚሉት ዐቢይ አሕመድ የተረከቡት ካዝና ሌላው ቀርቶ ለመንግሥት ሠራተኛው የኹለት ወር ደሞዝ እንኳን የማይበቃ ነበር። ችግሩ ግን ምጣኔ ሃብታዊ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊም መሆኑ አያከራክርም።

የለውጥ ኃይል በሚል አራት ኪሎን የተረከበው ቡድን አገረ መንግሥቱን ለማፅናት ጠንካራ ምርኩዝ መደገፍ ነበረበት። ለኹለቱም ስር የሰደዱ ችግሮች ደግሞ ከኹለቱ የዓለም ኀያላን አንዱን መምረጥ ያስፈልጋል። ቻይና ከሕወሓት መራሹ መንግሥት ጋር ስትሠራ በመኖሯ ተፈላጊ የሆነች አይመስልም። በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከምዕራቡ ዓለም እና ሸሪክ የዓረብ መንግሥታት ጋር ወዳጅነታቸውን አጠናከሩ።

አሜሪካ የምትዘውራቸው የዓለም ገንዘብ ድርጅትና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋማም የለውጡ ምጣኔ ሃብታዊ አማካሪ ሆነው ከፊት ተሰየሙ። እውቁ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ እንደሚሉት ደግሞ፣ አራት ኪሎ የሚገቡ የኢኮኖሚ አማካሪዎችን በመምረጥ ደሞዝ እስከመክፈል ደረሱ።

እንዲህ ያለው መንገድም ሌበራሊዝምን አክነፎ ኢትዮጵያ አደረሰው። አቶ መለስ ፊት ድቅን ያለው ጥያቄ ግን አሁንም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገሸሸ አላለም። ኢትዮጵያ መዳረሻዋ ሌበራል ዴሞክራሲ ቢሆንም ዛሬ ላይ ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ግን ለእሱ የሚያበቃ አይደለም። ከዚህ አንፃር የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የ“መደመር” እሳቤ እንደ አብዮታዊ ዴሞካራሲ ሁሉ ወደ ሌበራል ዴሞክራሲ ለሚደረገው ሽግግር ድልድይ ሆኖ እንዲያገለግል የታሰበ ይመስላል።

ነገር ግን “መደመር” እንደ አብዮታዊ ዴሞክራሲ መሸጋገሪያ ነው ቢባል እንኳን መንግሥታዊ መልክን የያዘ አለመሆኑ ያደናግራል። ብልፅግና ፓርቲ የኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለሜ አካታች ካፒታሊዝም ነው ሲል እኔን ጨምሮ ብዙ ሰው ግራ የተጋባውም በዚህ ምክንያት መሆኑ አያጠራጥርም። የብልፅግናው አካታች ካፒታሊዝምን መምረጥ አንድ ሀቅን ገሃድ ያወጣ ይመስለኛል። እሱም አራት ኪሎን የሚዘውሩት የምጣኔ ሀብት አማካሪዎች የዓለም አቀፉ ገንዘብ ተቋም ምርኮኞች መሆናቸው ነው።

የአካታች ካፒታሊዝም ርዕዮት በዓለም የገንዘብ ድርጅት ተነድፎ በአገራት እንዲተገብር ሲሰበክ የቆዬ መሆኑ የሚያከራክር አይደለም። አስገራሚው ነገር ግን ምክረ ሐሳቡ ከምዕራቡ ዓለም መምጣቱ አይመስለኝም። ትኩረት የሚሰብው ጉዳይ የአካታች ካፒታሊዝም የድህረ ካፒታሊዝም ውጤት ተደርጎ የሚወሰድ ከመሆኑ ነው። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ቅደመ ካፒታሊስት የሆነችው ኢትዮጵያ፣ የድኅረ ካፒታሊስቱን ርዕዮት እንዴት ተቀበለች የሚል ጥያቄ ያስነሳል። በሌላ በኩል የካፒታሊስቱ ዓለም የሀብት ልዩነትን እንዲሰፋ አድርጓል የሚለው አካታች ካፒታሊዝም፣ በኢትዮጵያ የትኛውን አርሶ አደር የሀብት ልዩነት ለማጥበብ ሥራ ላይ እንደሚውል ግልፅ አይደለም።
የሌበራል ዴሞክራሲ ኢትዮጵያን የት ያደርሳታል?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መራሹ አስተዳደር በቀጣዮቹ 20 እና 30 ዓመታት ወደ ብልፅግና የሚያሸጋግረኝን አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አዘጋጅቻለሁ ብሎ ለሕዝብ አስተዋውቋል። የማክሮ ኢኮኖሚውን መዛነፍ ስር ነቀል በሆነ መንገድ ለመፍታትም ለዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የገንዘብ ጥያቄን ካቀረበ ውሎ ማደሩ ተሰምቷል። የድርጅቱ ሰሞነኛ መግለጫም በሐሳቡ መስማማቱን አስታውቋል። በዚህ መሰረትም 700 ሚሊዮን ዓመታዊ ኮታ የተያዘላት ኢትዮጵያ 2.9 ቢሊዮን ዶላር ተፈቅዶላታል። ይህም አገራዊ የብድር መጠናችንን ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያደርገዋል። ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነውን በዕዳ የተያዘ የአገሪቱ አጠቃላይ የምርት መጠን አሃዝም ያሳድገዋል።

ይህ ግን አገሪቱ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር እንደነውር ሊታይ የሚጋባው አይደለም። በእኔ ዕይታ ሰሞነኛው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ብድርና ድጋፍ ስጋት የሚያጭረው አገራዊ ችግራችን ሊፈታ የመጣ ነው አልያስ ሊያባባስ ከሚል ወሳኝ ጥያቄ ጋር በመተሳሰሩ ነው። እንዲህ ያለው ሐሳብ በአግባቡ ሊመለስ የሚችለው ግን የምጣኔ ሀብት ህመሙና መድኀኒቱ ሊገናኙ መቻላቸውን እርግጠኛ ስንሆን ነው።

ታዋቂው ኢኮኖሚስት ዓለማዬሁ ገዳ፣ ችግርና መፍትሄው አለመገናኘቱን ደጋግመው ይገልፃሉ። ምጣኔ ሃብታዊ ቀውሱ መዋቅራዊ ነው የሚሉት ዓለማዬሁ፣ የተቀመጠው አቅጣጫ ግን ሌላ ስለመሆኑ ያብራራሉ። ነገርዬው የሞተረ ብልሽት የገጠመውን መኪና ጎማውን በመቀየር ለመንዳት ከመሞከር ጋር የሚመሳሰል ነው። ጥቂት ማሳያዎችን ልጥቀስ።

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት አንዱና መሠረታዊ ተብሎ የሚጠቀሰው ችግር ግብርናው የሚጠበቅበትን ያህል ለኢኮኖሚው ሞተር አለመሆኑ ነው። አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ግን ለዚህ የሚሆን አንድም መፍትሔ በግልፅ አላስቀመጠም። ከዛ ይልቅ ቢሮክራሲውን ማዘመን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቢዝነስ የሚጀመርበትን ዕድል ማመቻቸት ወዘተ በሚሉ ምክረ ሐሳቦች የተተበተበ ነው።

እንዲህ ያለው የችግሩና መፍትሄ መተላለፍ ደግሞ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው መሠረት ምንድን ነው የሚለውን እንድንጠይቅ ያደርጋናል። አንጋፋው ኢኮኖሚስት ዶክተር በፍቃዱ ደግፌ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የእኔ ነው ብሎ የሚያወራለት አገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ሙሉ በሙሉ የተኮረጀ መሆኑን ያነሳሉ።ዓለማየሁ ገዳም የዓለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ፓምፕሌት ቁጥር 2009/47 መንግሥት አዲስ ይፋ አደረኩት የሚለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዋና ቅጅ መሆኑን ይመሰክራሉ።

እውነታው እንዲህ ከሆነ ትናንት አገራት ተፈትነው በወደቁበት መንገድ መጓዛችን ቀቢፀ ተስፋን ያላብሳል። በምዕራቡ ዓለም የማንነት ጥያቄዎችን ያልመለሰው ሌበራሊዝም፣ ወዲህ ማዶ አስጨናቂ የሆነውን የማንነትና የፖለቲካ ጥያቄ መመለሱ ላም አለኝ በሰማይ ይሆናል።

ይነገር ጌታቸው ተለያዩ መገናኛ ብዙኀን በማገልገል ላይ የሚገኙ ባለሙያ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው mar.getachew@gmail.com ሊገኘኙ ይችላሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com