ለአማራና ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር መፈትሔ

Views: 137

ፖለቲካ በምኞት የሚሠራ ነገር ባይሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ፖለቲካ ተወግዶ የዜግነት ፖለቲካ ሰፍኖ ማየት እመኛለሁ የሚሉት መላኩ አዳል፤ የፓርቲዎች በጋራና በኅብረት መሥራት ያለውን የተሻለ ጥቅም ይዘረዝራሉ። ሥልጣን የመጋራትን ጥቅምም ጠቅሰው፣ ለአማራ ሕዝብም በብሔር ሳይሆን በጋራ መደራጀት ያለውን ጥቅም አንስተዋል። ራስን ማስከበር የሚቻለው ለብቻ በመቆም ሳይሆን ከሌሎች ተባብሮ ሲሠራ ነው ሲሉም ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

የአማራ መደራጀት እጅግ አስፈላጊና ጊዜው የሚጠይቀውም ነው። ነገር ግን የጎሳ ብሔርተኝነት አደረጃጀት ግን በምንም መንገድ የአማራ ምርጫ መሆን የለበትም። የሌሎች በዘውግ መደራጀት ለምን የአማራውን በዘውግ መደራጀት ግዴታ እንዳደረገው ግልፅ አይደለም። ሌላ መደራጃ ሐሳብ ጠፍቶ ወይስ የእኛና እነሱ ፖለቲካ ለማደራጀት ቀላል ስለሆነ? ይህን ጣልያን አገራችንን የቅኝ ግዛቱ አካል ለማድረግ የዘየደውን የዘውግ አደረጃጀት ቀድሞ በሻዕብያ፣ ሕወሓትና ኦነግ፤ አሁን ደግሞ በአብን መተግበሩ አሳፋሪ ነው። የዘውግ ፖለቲካ ማንንም ሕዝብ የማይመጥን፣ ብሔርተኞች በቆፈሩት ቦይ መፍሰስም ነው። ትናንት ጠባብ ብሔርተኝነትን ሲቃወም፣ ኢትዮጵያዊነትን ሲደግፍ፣ ትምክህተኛና የቀድሞው ስርዓት ናፋቂ ይባል የነበረው የአማራ ልሂቅ፣ አሁን ብሔርተኛ ሆኖ እንደማየት ምን የሚያሳፍር ነገር አለ? እንዴት የሚጠሉትን ሐሳብ የራስ የመደራጃ ርዕዮት ተደርጎ ይወሰዳል?
የአማራ ብሔርተኞች፣ በአንድ በኩል ሕገ-መንግሥቱና የፌዴራል መንግሥቱ አወቃቀር ችግር አለበት፣ ሕዝባችን ስላልተሳተፈበት እኛን አይወክልም እያሉ፣ በሌላ በኩል ግን እንደ መከራከሪያ ሕገ-መንግሥቱ ራሱ የዘውግ ፖለቲካና ብሔርተኝነትን በሚደግፍበት ሁኔታ ብሔርተኝነትን መቃውም ትክክል አይደለም ይላሉ። ትክክል ያልሆነን ነገር የሕዝብ ይሁንታ ያላገኘ ሕገ-መንግሥት ትክክል ሊያደርገው እንደማይችል ግን ሊሰመርበት ይገባል። የዜግነት ፖለቲካ አራማጆች ወደ ሥልጣን አለመምጣትን እንደ ምክንያት ማቅረብ አሁንም ይህንን የስህተት ፖለቲካ ትክክል አያደርገውም።

በተጨማሪም አማራ ተጨቁኗል የሚለው ትክክል ነው፣ ግን ማን ጎሳ ነው ያልተጨቆነውና ችግር ያልደረሰበት? ለጊዜው ባለው ሕገ-መንግሥት እየተመራን፣ ነገር ግን ሕገ-መንግሥቱ እንዲሻሻል፣ የፌዴራል አወቃቀሩ እንዲስተካከል ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፤ ብዙ ችግር ያለበት ሕገ-መንግሥትና የፌዴራል አወቃቀር ነውና። በብሔር ፖለቲካ የተደራጀሁበት ምክንያት የመተግበር አስገዳጅነት እንጂ የብሔር ፖለቲካም ሆነ የብሔር ፌዴራሊዝም በዘላቂነት ለአገር ህልውና አዋጭ ስለሆነ አይደለም ማለትና ለሕዝብም ማሳወቅ አለባቸው። ይህ አይነቱ አስተሳሰብ ከሌሎች ፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ስትራቴጂካዊ ትብብር ፈጥሮ ለመሥራት ያስችላልና።

ከዚህም በተጨማሪ የብልጽግና እና የኢዜማ የመሃሉን ፖለቲካ መያዛቸው ለዴሞክራሲያዊ መንግሥት ምሥረታ የራሱን በጎ ጎን እንደሚጫወት ብዙዎቻችን ተስፋ እንድንሰንቅ አድርጓል። ሁሉንም ጎሳዎች አቃፊና አሳታፊ የሆነ መንግሥት ይኖረናል፤ ፍታኀዊ የሆነ የሥልጣንና የሃብት ክፍፍልም የሚኖርበት መንገድ ይፈጠራል ብለን እንጠብቃለን። የፌዴራል ሥልጣንን በመቆጣጠር የአገሪቱን ዋና ዋና ባህሎችና እሴቶችን ለማፍረስ እየተሠራ ያለው ሥራ አፋጣኝ የተግባር እርማትም ይደረግበታል ብለን እንጠብቃለን።

ምርጫውን በተመለከተ፣ ለተወሰነ ጊዜ ቢራዘምና የአገር ሰላም ማረጋገጡ ቢቀድም የተሻለ ነው። ይህ በዚህ እንዳለ፣ የተለያዩ የምርጫ ስርዓቶች አሉ። ተመጣጣኝ (proportional)፣ አብላጫ (majoritarian) እና የኹለቱም ቅልቅል (mixed) ብለን ለሦስት ልንከፍለው እንችላለን። በኢትዮጵያ የምርጫ ስርዓት በአንድ የምርጫ ቀጠና ከፍተኛ ድምፅ ያገኘ አሸናፊ ይሆናል። በዚህ ስሌት መሰረት ለምሳሌ ባህር-ዳር ላይ አብን፣ ብልጽግና፣ ኢዜማ ቢወዳደሩ አንደኛው ድርጅት በ1 የድምፅ ልዩነትም ካሸነፈ ሙሉ በሙሉ የዛ ምርጫ ጣቢያን እንዳሸነፈ ነው የሚሰላው።

ይህ የምርጫ ቀመር ግን አማራ ክልል ተብሎ ከተሰየመው ውጭ ወዳለው መሃል አገር እና ደቡብ ኢትዮጵያ ሲመጣ በተለያዩ ቦታዎች ተበታትኖ የሚኖረው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠረውን አማራ ውክልና እንዳይኖረው የሚያደርግ ነው። ይህ ሕዝብ ተገቢው ውክልና ሊኖረው የሚችለው የሌሎችን ኢትዮጵያውያንን ድምፅ አንድ ላይ ሲደምር ነው። ስለዚህ እንደ አብን ያሉ ለአማራ እታገላለሁ የሚሉ ድርጅቶች፣ ከዜግነት ፖለቲካ አራማጅ ኃይሉ ጋር ግንባር ፈጥሮ የአማራውን ጥቅም እና ተገቢውን ውክልና ማስከበር ሲገባው ራሱን ነጥሎ አማራውን የፖለቲካ ድምጽ አናሳ እንዲሆን የሚያደርግ የስህተት መንገድ መርጠዋል።

አብን መቶ በመቶ ሙሉ የክልሉን ድምፅ ማሸነፍ ቢችልም፣ 28 በመቶ የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ብቻ በሚያስገኝ የዘውግ ፖለቲካ ውስጥ መዋኘቱ ጥቅሙ ምንድን ነው? ይህ ለመንግሥትነት የማያበቃ የዘውግ ፖለቲካም፣ ሌሎችን የሚገፋ በመሆኑ በረዥም ጊዜ አማራን ከሥልጣን የሚያርቅ ነው። ሌሎች ብሔርተኞች የአማራውን ብሔርተኝነት የሚፈልጉበት ምክንያት፣ የኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ደጋፊዎችን አስተባብሮ ከሥልጣን ውጭ እንዳያደርጋቸውና ኢትዮጵያዊ ርዕዮትን ለማጥፋት ነው።

በዓለም ላይ ማንኛውም ኃይል ተባባሪ አጋር ይፈልጋል። ልዕለ ኀያላን አገሮች ሳይቀር ኀያል የሆኑት፣ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ ጥቅሞች ላይ ከሌሎች አገራት ጋር ትብብር (alliance) በመፍጠር ነው። በኢትዮጵያ አንድ ድርጅት ብቻውን ምርጫውን ማሸነፍ የሚችልበት የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ የለም። ስለዚህ ሁሉም አጋር ይሻል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ እውነተኛ ፉክክር (competitive) የሆነ ምርጫ ያደረገችው በ1997 ነበር።
ይህ ምርጫ ከፍተኛ ፉክክር ሊኖርበት የቻለው በወቅቱ ‹መድረክ› የተሰኘ የብሔር ድርጅቶች ግንባር ተፈጥሮ ነበር። ኢህአዴግ የአራት የብሔር ድርጅቶች ግንባር ነበር። በኋላ ላይ የኢትዮጵያ አንድነት አቀንቃኝ ፓርቲዎች የሆኑት መኢአድ፣ ኢዴፓ፣ ቀስተዳመና እና ሌሎችን ጨምረው ቅንጅት ብለው ግንባር ፈጠሩ። ምርጫውም በሦስት ጠንካራ ግንባሮች መካከል ተደረገ። ስለዚህ በኢትዮጵያ ምርጫን አሸንፎ ሥልጣን ለመያዝ የሥልጣን ተካፋይ አጋር ተባባሪ ያስፈልጋል።

የፖለቲካ ድርጅቶችን አሰላለፍ ካየን፣ በመንግሥትነት ሥልጣን ላይ ያለው ብልጽግና የተባለው ውህድ አገራዊ ፓርቲ አለ። በሌላ በኩል በኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ መረራ ጉዲና የሚመራ እነ አረናን እና ሌሎችንም የብሔር ድርጅቶች ያቀፈ መድረክ የተሰኘ ስብስብ አለ። የአንድነት አቀንቃኝ የሆነው ውህድ ፓርቲ ኢዜማም ተመሥርቷል። በሌላ በኩል ሕወሓት፣ አብን እና ኦነግ የተባሉት የፖለቲካ ድርጅቶች አሉ። ማንም ፓርቲ ምርጫ ተወዳድሮ መንግሥት ለመሆን የሚያስችል ድምፅ አይኖረውም። አብን ሥልጣንን ካልተጋሩ ደግሞ የአማራውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ጥያቄዎች መመለስ አይችልም።

ስለዚህም ይህ ፓርቲ የግዴታ በትብብር (alliance) ለምርጫም፣ ከምርጫ በኋላም መንግሥት ለመመስረት የሚያስችል ኅብረት (grand coalition) አስቦ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል። ያለዚያ ግን አብን የተወሰኑ ድምፆችን ይዞ እንደ አማራ ወኪል ሁኖ ተላላኪ ከመሆን የዘለለ ተጽእኖ አይኖረውም። በሕዝብ ዐይን አማራም ተወክሏል የሚል ሕጋዊ እውቅና ከመስጠት ባለፈ የመሪነት ሚና ሊጫወት የሚችልበት ቁመና አይኖርም።
በፖለቲካ ሥልጣን ውስጥ ወሳኝ ሳይሆን አንዱንም የአማራ ጥያቄ መፍታት አይቻልም። ቁልፉ ያለው ሥልጣን ተጋሪ ከመሆኑ ላይ ነው። ሥልጣን ተጋሪ የሚሆነው ደግሞ ከሌሎች ጋር በመተባበር ብቻ ነው። ጉራጌውን፣ ከንባታውን፣ ከፋውን፣ ጋሞውን፣ ኢትዮጵያዊውን ሁሉ በጋራ ጥቅም ላይ በማስተባበር ነው። አማራው እራሱን ማስከበር የሚችለውና ከማኅበራዊ ስብስቡ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚሆነው ብቻውን ሲቆም ሳይሆን ከሌሎች ጋር ተባብሮ ሲሠራና አጋሮችም ማፍራት ሲችል፣ ብሎም የፖለቲካ ሥልጣኑን ሲጋራ ብቻ ነውና።

አብን አጋር መሆን የሚችለው ከማን ጋር ነው? ከዜግነት ፖለቲካ ወይስ ከብሔር ፖለቲካ አራማጁ ጋር? ከዐቢዩ ብልጽግና ጋር? ከመድረክ ጋር? ከኦነግና ከሕወሓት ጋር? የአብን ተፈጥሮአዊ አጋር ሊሆን የሞችለው ኢዜማ ነው። ምክንያቱም የአማራው የፖለቲካ ፍልስፍና ከመሃል ወደ ቀኝ ነውና። ይህም በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ተበትኖ የሚኖረውን አማራና ሌሎችን ጎሳዎች በማስተባበር ስርአትን ለማስተካከል የሚያስችል ድምጽ ለማግኘት እድል ይከፍታል። እናም ለአማራ የሚሻለው በታሪኩ የመጣበት ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነቱና ሁሉንም የአገሪቱ ዜጎች አሳታፊ የሆነ መንግሥት መመስረት የሚያስችል የፖለቲካ ስርዓት ነው።

ከነዚህ ጋር አብሮ መተባበርና መሥራት ሳይችል ብቻውን ተነጥሎ በመቅረት አሁን ባለው የብሔር ፖለቲካ አማራን አቅመ ቢስ እና ወሳኝ ሚና የሌለው እንዲሆን ያደርገዋል። አብን በኢትዮጵያ አንድነት ዙሪያ ከአማራው ጎን ከሚሰለፉት ጋር አብሮ መሥራት ካልቻለ ለአማራው ጉዳት ነው። አዴፓ ከብልጽግና ጋር መወሃዱና የአብን ከኢዜማ ጋር ከተቻለ መዋሃድ፣ ያለዚያ ግን አብሮ የሚሠራበትን ትብብር መመስረቱ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር መሆን አለበት። ይህም የመሃሉን ፖለቲካ በመቆጣጠር የሁሉም ሕዝብ ችግር በአንድነት የሚፈታበትን መንገድ ለመተለምና ለመፍታት ይረዳል።

የአማራ ሚዲያና የሚዲያ አጠቃቀም ኢትዮጵያዊነትን ዋናው መርሁ አድርጎ የአማራውን ሕዝብ የፖለቲካ ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጥያቄዎች የሚፈቱበትን መንገድ አቅጣጫ ጠቋሚ፣ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር መልካም ግንኙነት እንዲፈጠር የሚረዳ፣ ከጥላቻ ስብከት የራቀ መሆን ይኖርበታል። ካልሆነ ከትርፉ ኪሳራው ያመዝናል። ስለዚህ ጥንቃቄ ያሻዋል። በተጨማሪም፣ የአማራው አክቲቪዝም መሬት የረገጠ፣ እያንዳንዱን ድርጊት የሚያመጣው አውንታዊና አሉታዊ ጎን በተጠና ሁኔታ መንቀሳቀስን ይጠይቃል። እንዲያውም፣ በአንድ ቋት የሚመራ፣ ለየቀኑ ድርጊቶች ባልተጠና መንገድ መልስ የማይሰጥ፣ ከንትርክ የጸዳና መሠረታዊ ጥያቄዎችን ያነገበ መሆን ይኖርበታል።
እኔ የምመኘው ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ፖለቲካ ተወግዶ የዜግነት ፖለቲካ ሰፍኖ ማየት ነው። ነገር ግን ፖለቲካ ምኞት አይደለም። ነባራዊ ሁኔታው የሚያሳየው በመጪዎቹ አስርት ዓመታት የብሔር ፖለቲካ በኢትዮጵያ ፖለቲካ እየተዳከመም ቢሆን መቀጠሉን ነው። ነገር ግን፣ ተራው የእኛ ነው የሚሉ ኃይሎችን አደብ ማስገዛት የሚቻለው ደግሞ የአማራ ፖለቲካ ከዜግነት ፖለቲካ አራማጅ ኃይሉ እና ከሌሎች በእኩልነት ከሚያምኑ ኢትዮጵያውያን ኃይሎች ጋር የጋራ ግንባር እንዲፈጥር በማድረግ ነው። ይህ የሚሆነው ደግሞ የኢትዮጵያዊነት አቀንቃኝ ሁሉ የአማራው ስትራቴጂክ አጋር ይሆናል ብሎ ማመን ሲቻል ነው። ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተባብሮ ለመሥራትም ራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ስለዚህ የአብን አማራን ከሌሎች አጋር ሃይሎች የመነጠል ሂደት በፍጥነት መስተካከልና መቆም አለበት።

አሁንም ‘’ተራው የእኛ ነው’’ የሚልን አስተሳሰብ መግታት፣ ሥልጣን የሁሉም ኢትዮጵያዊ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። የአገራችን ወቅታዊ ችግሮች ይህን ተከትለው የተፈጥሩ ናቸውና። በኦነግና በሕወሓት በኩል ያለው ከፖለቲካው ወደ ዳር መገፋትና እሱን አምኖ ለመቀበል አለመቻል፤ ይህንንም በሕዝብ ሞት፣ በሰላም መደፍረስ፣ ሲቀጥልም አገርን ለማፍረስ የመጣር ሒደት አለ። ሌላው የኢኮኖሚውን መዳከምና ለውጡን ተከትሎ እየተደረገ ያለው የፕራይቬታዜሽንና የገንዘብ ምንዛሬን የማድከም ግፊት ነው።

የአገር እሴትን መሸጥ ድሃው ሕዝብ እንዳይደጎም፣ እዳችንንም የምንከፍልበትን መንገድ ስለሚዘጋ ጥንቃቄና የእርምት እርምጃ ያስፈልጋል። ይህ 3፣ 6፣ 9 ቢሊዮን ዶላር በብድርም ሆነ በእርዳታ ተገኘ የሚባለው ነገር በጣም ሊታሰብበት ይገባል። መቼም ነጻ የሚባል ነገር የለምና ተያይዞ የሚመጣውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተጽእኖ በደንብ ልናስብበት ይገባል። በተለይም ይህ የገንዘብ ምንዛሬ አቅምን ማድከም (devaluation) ጉዳይ በጣም ሊታሰብበት የሚገባ ነው። አሁን ድሃው ሕዝብ በኑሮ ውድነት መኖር በተቸገረበት ሁኔታ፣ የገንዘብ ምንዛሬ ጥንካሬ ማድከም ሕዝብን ወደ ባሰ ችጋር መምራት መሆኑንም ልናስብበት ይገባል።

ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁላችንንም በእኩልነት የሚያስተናግድ ስርዓት ለመዘርጋት አሁኑኑ እየሔድንበት ያለውን መስመራችንን እንመርምር!!!

መላኩ አዳል የዶከትሬት ዲግሪ በባዮ ሜዲካል ሳይንስ በማጥናት ላይ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው melakuadal@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com