ልዩ የበአል ቃለ መጠይቅ

Views: 203

ታኅሳስ 28/2012 የሚከበረው የገና በዓል መዳረሱን ምክንያት በማድረግ አዲስ ማለዳ የተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ስኬታማ የሆኑ ሰዎችን በአሉን የሚመለከቱ ቀለል ያሉ ጥያቄዎችን ጠይቃለች። ጥያቄዎቹም በበዓል ጊዜ የቤት ውስጥ የሥራ ድርሻዎት ምንድን ነው? የበዓል ቀን ከቡና እና ከዶሮ አንዱን ምረጡ ቢባሉ የቱን ይመርጣሉ? የበዓል ቀን ማለዳ ስንት ሰዓት ይነሳሉ? የገና በአልን የት ማክበር ይፈልጋሉ? በገና በዓል ወቅት በኪስዎ 3 ሺሕ ብር ብቻ ቢኖርዎ በዓልን እንዴት ያሳልፋታል? እንዲሁም የበዓል ማግስት ቀንዎ ምን መልክ አለው? የሚሉ ነበሩ። እነዚህ አንጋፋና በተለያየ መስክ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ ግለሰቦች ተከታዮቹን መልሶች ሰጥተዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር፣ ታዋቂ የውል ሕግ ባለሞያ፣ ተመራማሪ እና በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ብቸኛው ሙሉ የሕግ ፕሮፌሰር

ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ

በበዓል ቀን የተለየ ድርሻ የለኝም፣ ያው የሚያስፈልገውን ሁሉ ግን በአቅሜ አሟላለሁ። የሚገዙ ነገሮችን እገዛለሁ፤ በተለይ ደግሞ በግ። ግን ሔጄ አልገዛም፣ የማምናቸው ልጆች አሉ። በበዓልም ሆነ በአዘቦት እነርሱ ያመጡልኛል፤ አርደው ጨርሰው ይሔዳሉ። እኔ በሕይወቴ በግም ዶሮም አርጄ አላውቅም። የእንስሳት መብት ጉዳይ አሁን እየመጣ ነው፣ እኔ ግን እንደው ከድሮም ነፍስ ማጥፋት አልወድም። ዶሮ የሚያርድ ሰው ከተፈለገ ጎረቤት ተጠርቶ ነው አሁንም የሚያሳርዱት።

ኹለት አገር ነው ማክበር የምፈልገው፤ አንዱን አክብሬአለሁ ሌላው ይቀረኛል። በእኛ ጊዜ ካሉት እኔ ነኝ እዚህ የቀረሁት እንጂ አብዛኞቹ ጓደኞቼ አሜሪካ ነው። እና እነሱ ጋር ሔጄ አክብሬአለሁ። ኹለተኛው እስራኤል አገር ቤተልሔም ከተማ ነው። ለፋሲካ ሔጄ አክብሬአለሁ፤ አሁን ገና ይቀረኛል። በቅርቡ ሔጄ አከብራለሁ ብዬ አስባለሁ። እኛ አገር ላሊበላ ባከብር ደስተኛ ነኝ። ለነገሩ በቅርቡም ሄጄ አይቼዋለሁ፣ ግን የልደት በዓልን እዛ አክብሬ አላውቅም። በአልን ግን ሁሌም ከቤተሰቦቼ ጋር ማክበር ነው ደስታዬ። እስከ አሁን ወላጆቼ ቤት ነው እኔም ልጆቼም የምናከብረው። በዚህ ዓመት መጀመሪያ ግን እናቴ አርፋለች፣ አባቴም ከዛ ቀደም ብሎ እንደዚሁ። ስለዚህ ከዚህ በኋላ ያው ቤት ነው የማከብረው ማለት ነው። የቤቱ ታላቅ እንደመሆኔ ታናናሾቼንም ሙሉ ቤተሰቡን እሰበስባለሁ። ብቻ ከ 30 በላይ ሆነን ነው የምናከብረው።

እኔ አገሬም ትውልዴም ፈረንሳይ ለጋሲዮን ነው። አያቶቼ ጭምር የፈረንሳይ ተወላጅ ናቸው። የአሁን ዘመን ያመጣውን ነገር አላውቀውም፣ እኔ ፈረንሳይን ይዤ ነው የምገነጠለው (ሳቅ)።

ሦስት ሺሕ ብር ከሆነ ትንሽ ጠቦት ገዛለሁ፤ ሌላውን ልጆቼ ያሟሉታል። ድሮ የገና ዛፍ እና ይሄ የፈረንጅ ጌጣጌጡ ከሌለ ቅር ይላቸዋል፤ አሁን ግን ስላደጉ ራሳቸው ይገዛሉ።

ያው እንደ በዓሉ የምንነሳበት ሰዓት ይለያያል። ፋሲካ ከሆነ ከባለቤቴ ጋር ቤተ ክርስቲያን ነው የማድረው። ከዛ አስቀድሰን ጠዋት 11 ሰዓት አካባቢ ነው የምንመጣው። ትንሽ አርፈን አረፋፍደን ወደ ወላጆቼ ቤት ሔደን እናሳልፋለን። ልደት ሲሆን ያው በአዘቦት በምንነሳበት ኹለት ሰዓት አካባቢ ተነስተን የተለመደ ፀሎት አድርሰን በዓሉን እንጀምራለን። ከዛ ረፋድ ላይ እንዳልኩሽ ወደ ወላጆቼ ቤት እንሔዳለን። እኔ አገር ውስጥ ባልኖር እንኳን ባለቤቴ እና ልጆቼ ይሔዳሉ። ይሄ የማይቀር ነበር።

እንዴ! ዶሮ ነው እንጂ፤ ቡናማ በየቀኑ አገኘው የለ!
ያው በዓሉን ቤታችን ስለማንውል በበዓል ማግስት በጣም አስቸኳይ ነገር ካልመጣ በስተቀር ጠዋት ከቤቴ አልወጣም። ቤታችን ተሰብስበን እናከብረዋል። ከሰዓት አንገብጋቢ ነገር ካጋጠመኝ ቢሮ ደረስ ልል እችላለሁ እንጂ ማግስቱም በዓል ነው። በተረፈ በበዓል ዋዜማ ጫጫታ ሰፈር መሔድ አልወድም። አሁንማ አርጅቼ አያምርብኝም። ግን እንደው ድሮም ወጣት ሆኜ በበዓል ዋዜማ ወጥቶ መዝናናትን አልወደውም። በአዘቦቱ ግን አልፎ አልፎ እዝናናለሁ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን
ኮሚሽነር

አበበ አበባየሁ

በዋናነት መብላት ነው የእኔ የሥራ ድርሻ። ነገር ግን በግ በመግዛት እና በጉን አሳርጄ ጨርሼ ወደ ቤት ይዤ እመጣለሁ። ከዛ ባለፈ ግን ምንም የሥራ ድርሻ የለኝም። ከመብላት ባለፈ፤ እንዲህ ከባለቤቴ ጋር ዶሮ ማጠብ ወይም ማረድ ምናምን እንግዲህ…

እንዴ! ምን ይገናኛል? ዶሮ ቢቀር ነዋ የሚሻለው። በበዓል ቀን ቡና ከሌለማ ምኑን በዓል ሆነው። ቡና አስቀርተህ በምን ታካክሰዋለህ? ለእኔ ሌሎች አማራጮችም ስለሚኖሩ ዶሮ ቢቀርና ቡና ቢኖር እመርጣለሁ።

በመሠረቱ እኔ የጠዋት ሰው ነኝ። በበዓልም ሆነ በሥራ ቀን ስፖርት ስለምሠራ በጠዋት ነው የምነሳው። ግን በበዓል ቀን አንዳንዴ 1 ሰዓት ላይ ልነሳ እችላለሁ።

አገር ውስጥ የመጀመሪያ ምርጫዬ የሚሆነው ላሊበላ ሔጄ ማክበር ነው። ሁኔታዎች ተመቻችተውልኝ ውጭ አገር ሔዶ የማክበር ዕድሉን ካገኘሁ ግን፤ እየሱስ ክርስቶስ በተወለደባት የቤተልሔም ከተማ ባከብር ደስ ይለኛል።
ይሄማ አያድርስ ነው። ጭራሽ የልጆች ስጦታ እኮ ኹሉንም ገንዘብ ይወስደዋል። ብቻ ግን የግድ በዓሉ መከበር ካለበት፤ ዶሮ ከአስፈላጊ ግብዓቶች ጋር እገዛለሁ። እንግዲህ ግማሹ (1500) ብር ጠፋ ማለት ነው። እንደምንም ለማጣጣም ከተሞከረ በቀረው ደግሞ ለልጆች የበዓል ስጦታ በመግዛት አከብራለሁ ብዬ አስባለሁ።

እንዳለመታደል ሆኖ ሥራ ላይ ሆኜ ነው የማሳልፈው። ድሮ ድሮ ስንሰማ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጊዜ ከበዓል ማግስት በተለይ ደግሞ በፋሲካ ማግስት ሥራ ዝግ ይሆን እንደነበር ይታወቃል። ነገር ግን ያው የአሁኑ ሩጫችን አንድ ቀን ለመዝጋት እንኳን የሚያስችል አይደለም። ስለዚህ እኔ በዓል ማግስትን ቢሮ ውስጥ በሥራ ነው የማሳልፈው።

የዓለም ዐቀፉ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሴቭ ዘ ቺልድረን የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ፣ ደረሲ እንዲሁም የማኅበራዊ ሚዲያ ጸሐፊ

ሕይወት እምሻው

እኔ እና ባለቤቴ በዓል በተለመደው ሁኔታ አናከብርም። በተወሰነ መልኩ ደግሞ መተው የማልፈልጋቸው ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ቄጤማ መግዛት፣ ቡና ማፍላት፣ ዶሮ ወጥ መብላት የመሳሰሉት ነገሮችን ማንሳት ይቻላል።

ዶሮ ወጥ እንኳን አልፍ አልፎ ነው የምሠራው፤ ቄጤማ መግዛትና ቡና ማፍላት ግን የማይቀሩ ናቸው። ከዚያ ውጪ ቤቴን አፀዳለሁ፤ ቤተሰብ ጥየቃ መሔድም አለ። ከተለመደው ውጪ ያልኩት ብዙ ጊዜ በበዓል ቀን ቤት ውስጥ የሚዋል ቢሆንም እኛ ግን ፊልም እንገባለን። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከከተማ እንወጣለን።
ከከተማ ወጣ እንልና ከማናውቃቸው ሰዎች ጋር እናከብራለን። ብዙ ጊዜ ዘንድሮ ፋሲካን ወይም ሌላ ዓመት በዓል ጎንደር እንሒድ ወይስ አርባ ምንጭ ብለን ከዚህ በፊት ያልሔድንበት ከተማ ለመሄድ እቅድ እንይዛለን። ስንሔድም አዝማሪ ቤት እናመሻለን፣ ወይም በፌስቡክ ምክንያት ብዙ ሰው ስለማውቅ እመጣለሁ ብዬ ተናግሬ ሰው ቤት እሔዳለሁ። ባለፈው ለምሳሌ ጎንደር እና መቀሌ ስሔድ ጠላ ቤት ገብቻለሁ። ቤት ከሆንን ግን በግ ማረድ ዓይነት ከባባድ ሥራዎችን አናደርግም።

በአሁኑ አርባ ምንጭ እንሔዳለን ተባብለን ነበር፤ አልተሳካልንም። ስለዚህ አዲስ አበባ ነው የምንሆነው።
ሦስት ሺሕ ብር ብቻ ቢኖረኝ ቄጤማ፣ እጣን፣ ቡና፣ ድፎ ዳቦ [የሀበሻው ማለት ነው]፣ ግማሽ ኪሎ የተነጠረ ቅቤ፣ ዶሮ እና ግብዓቶቹ (ሽንኩርት፣ እንቁላል)

ከዶሮ እና ከቡና ቡናን ነው የምመርጠው። ያለቡና በዓል እንዴት ደስ ሊል ይችላል? ሽታው ደስ ይላል። ከሌሎች ሽታዎች ጋር ሲቀላቀል ደስ የሚል የበዓል መዓዛን ይፈጥራል። በጠረን ትዝታ በጣም አምናለሁ።
እየሰከነ ያለ ዶሮ ወጥ ትንሽ ከፈት ተደርጎ፣ ተቆርሶ የተቀመጠ ድፎ ዳቦ እና የትኩስ እንጀራ ሽታ ጋር ቡና እና እጣን ካልገባበት ትክክለኛው የዓመት በዓል ሽታ የለም። አሁንም ቢሆን እነ ኩበትን ተነጥቀናል። አሁን ደግሞ ይህንን ስንቀጥል በጣም ያስቸግራል።

እኛ ከፋሲካ ውጪ የበዓል ማግስት በአዘቦት ቀን ከዋለ ሥራ ስላለን ሥራ መግባት ነው የሚሆነው። ሁሉም ሰው ቢሮ ዳቦ እና የበዓል ምግብ ይዞ ይመጣል። ሥራ ከሌለ ደግሞ ምናልባት ጠዋት ላይ ረፈድ አድርጌ ቁርስ መሥራት፣ የበዓል ቀን ደክሞኝ ስለማላይ ደኅና ነበር የተባለውን የሚደገም የበዓል ቀን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ማየት ይሆናል።

በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎችን በማጣራት በማኅበራዊ ሚዲያ የሚያገለገሉ እና በመደበኛ ሥራቸውም የአሶሺየትድ ፕሬስ የኢትዮጵያ ዘጋቢ ናቸው

የበዓል ቀን የቤት ውስጥ የሥራ ድርሻዬን በተመለከተ፣ ከዚህ ቀደም የምኖረዉ ብቻዬን ስለነበረ በዓልን ቤተሰቦች ጋር ነበር የማከብረው። ያው የበዓል ምግብ እየበላሁ፣ እየተጫወትኩ ተመልሼ ቤት እየሄድኩ እተኛ ነበር። ነገር ግን በዚህ ዓመት ባለ ትዳር ሆኛለሁ። ስለዚህ የሥራ ድርሻዬ እንደ አባወራ ለበዓል የሚያስፈልጉ እንደ በግ እና ዶሮ ያሉትን መግዛት ነው።
እኔ በአዘቦትም በበአልም ጠዋት አንድ ሰዓት ነው የምነሳው።
ከደሮ እና ከቡና ከተባልኩ ደግሞ ያው በዓልን በዓል የሚያስመስለዉ ወደ ሆድ የሚገባ ነገር ነው። ስለዚህ ዶሮ ይሻላል።

እንደ ጋዜጠኛ ብዙ ቦታ የማየት ፍላጎት እና እድል አለኝ። ነገር ግን ገናን ላሊበላ ላይ ሲከበር ደስ ይለኛል። ሄጄ ስለማላውቅ፣ እዛ ሄጄ ባየው እና ባከብር ደስተኛ ነኝ። በዚህኛዉ በዓል ግን ከነባለቤቴ ቤተሰብ ቤት ሄደን አንደምናሳልፍ ነው የማውቀው።

ሦስት ሺሕ ብር ብቻ ቢኖረኛ እና ቤት ውስጥ ምንም ነገር ከሌለ …. በጣም ከባድ ነው። የሚቻል ከሆነ ምናልባት ዉጪ ሄደን ክትፎም ሆነ ዶሮ መመገብ ነው። ካልተቻለ ግን ቤት ዉስጥ ሆነን ምግብ በተለይም ዶሮ ነገር አስመጥቶ መመገብ ይሻላል።

ካልሆነ ካልሆነ ግን ካልተቻለ፣ በቃ ለአንድ ቀን ተብሎ አይሞት ነገር! አንድ ኪሎ ስጋ፣ ሽንኩርት እና ድፎ ዳቦ ከሱፐር ማርኬት ገዝቶ ለእንጀራም ለቡናም ለፈንድሻ ብሩ ይብቃቃል። እንደዛ ማሳለፍ ነው እንግዲህ።
(ከሌሎች ተጠያቂዎች በተለያ ለኤሊያስ የቀረበ ጥያቄ)

በበዓል ቀን የሐሰት መረጃ አንዲያጣሩ ጥያቄ ቢቀርብልዎ ምን ያደርጋሉ?
እውነቱን ለመናገር በቀላሉ እና በግሌ ላጣራው የምችል ነገር ከሆነ መረጃን በበዓል ቀንም ቢሆን የማጣራ ይመስለኛል። ሌሎች ሰዎች ጋር መደወል ያለብኝ ከሆነ ግን በበዓል ቀን ሰው ማስቸገር አግባብ ስላልሆነ እተወዋለሁ።
ከዛ ውጭ ግን ብዙ ጊዜ ሥራ በበዓል ቀን ሠርቼ አውቃለሁ፣ የምሠራው ለውጭ ሚድያ ስለሆነ። እኛ ጋር በአል ሲሆን እነሱ ጋር ብዙ ጊዜ የሥራ ቀን ነው። በጋዜጠኝነት ደግሞ ‘ለበዓል ቀን አልሠራም’ የሚል ነገር የለም።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com