የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ ዐዋጅ ምን ይላል?

0
965

በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የፖለቲካ ችግር በውይይት እና በብሔራዊ መግባባት እንዲፈታ ብዙዎች ሲወተውቱ ቆይተዋል። በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሠተ የጸጥታ ችግር ለዓመታት ዕልባት ሳያገኝ እስካሁን ዘልቋል።
በተለያዩ አካባቢዎች ለዓመታት የዘለቁት የጸጥታ ችግሮች መነሻቸው የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሲሆን፣ እንደ አገር የሚታዩትን ልዩነቶች መፍታት ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን እንደሚችል የፖለቲካ ልኂቃን ይገልጻሉ።

በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ልዩነት የፈጠረው ችግር በምርጫ ብቻ የማይፈታ መሆኑን መንግሥት ከስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ማግሥት መግለጹን ተከትሎ፣ ይህንኑ አገራዊ ውይይትና መግባባት ለመፍጠር የያዘውን ውጥን ለማሳካት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ ዐዋጅ ቁጥር 1265/2014 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁ የሚታወስ ነው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቀው ዐዋጅ በተለያዩ የፖለቲካ እና የሐሳብ መሪዎች እንዲሁም፣ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሐሳብ ልዩነት እና አለመግባባት እንደሚታይ ጠቅሷል። የሚታየውን ልዩነት እና አለመግባባት ለማርገብ እና ለመፍታት ሠፋፊ አገራዊ የሕዝብ ምክክሮችን አካታች በሆነ መንገድ ማካሄድ አስፈላጊ መሆኑ የታመነበት ሲሆን፣ መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ አካታች አገራዊ ምክክሮችን ማካሄድ የተሻለ መግባባትን ለመገንባት እና በሒደትም መተማመንን ለመፍጠር እንደሚያስችል ተጠቅሷል።

አገራዊ ምክክሮች ተቀባይነት እና ተዓማኒነት ያላቸው እንዲሆኑ ከሚያስችላቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ምክክሮቹን የሚያመቻቸውና የሚመራው አካል ብቃትና ገለልተኝነት ነው። ምክክሮቹን በብቃትና በገለልተኝነት ለመምራትና ለማስተባበር የሚችል ሠፊ ቅቡልነት ያለው ተቋም ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ በዐዋጁ ተመላክቷል። በረቂቅ ዐዋጁ ላይ የአገራዊ ምክክሩ እና አጠቃላይ የኮሚሽኑ ሥራዎች የሚመሩባቸው መርኾዎች የተጠቀሱ ሲሆን፣ አካታችነት፣ ግልፅነት፣ ተዓማኒነት፣ መቻቻል እና መከባበር፣ ምክንያታዊነት፣ የምክረ ሃሳቦች ተግባራዊነት እና አውድ ተኮርነት፣ ገለልተኛ አመቻች፣ የአጀንዳዎች ጥልቀት እና አግባብነት፣ ዲሞክራሲ እና የሕግ የበላይነት የሚሉት ተካተዋል።

በዐዋጅ የተቋቋመው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከፖለቲካ ወገንተኝነት፣ ከማንኛውም የመንግሥት ወይም ሌላ አካል ተጽዕኖ ነፃ የሆነ ራሱን የቻለ የሕግ ሰውነት ያለው አካል ሆኖ፣ ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሆነ በዐዋጁ ላይ ተጠቅሷል።

በዐዋጁ መሠረት ኮሚሽኑ ሰባት መሠረታዊ ዓላማዎች ያሉት ሲሆን፣ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች ወሳኝ ምክንያቶችን እና ውይይቶቹ የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በመለየት ምክክር እንዲደረግባቸው ማመቻቸት፤ የሚካሄዱት አገራዊ ምክክሮች አካታች፣ ብቃት ባለውና ገለልተኛ በሆነ አካል የሚመሩ፣ የአለመግባባት መንስዔዎችን በትክክል በሚዳስስ አጀንዳ የሚያተኩሩ፣ ግልፅ በሆነ የአሠራር ሥርዓት የሚመሩ እና የምክክሮቹን ውጤቶችን ለማስፈፀም የሚያስችል ዕቅድ ያላቸው እንዲሆኑ በማድረግ ውጤታማ የሆኑ አገራዊ የምክክር ሒደት ተግባራዊ ማድረግ፤ የሚካሄዱት አገራዊ ምክክሮች በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል እንዲሁም በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል እና መተማመን የሠፈነበትና አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር በሚያስችል አግባብ ውይይቶቹ እንዲካሄዱ ሥርዓት መዘርጋት ናቸው።

በተጨማሪም፣ ከምክክሮቹ የተገኙ የመፍትሔ ምክረ ሃሳቦች በሥራ ላይ እንዲውሉ ድጋፍ በማድረግ በዜጎች መካከል፣ እንዲሁም በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መተማመን የሠፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲገነባ ማስቻል፤ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል የፖለቲካ ባህል ለማዳበር እና ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ምቹ መደላደል መፍጠር፤ ወቅታዊ ችግሮች ዘላቂ በሆነ መንገድ ተፈተው አስተማማኝ ሠላም የሚረጋገጥበትን የፖለቲካ እና የማኅበራዊ መደላደል ማመቻቸት እና ለአገራዊ መግባባት እና ጠንካራ ቅቡልነት ያለው አገረ መንግሥት ለመገንባት ፅኑ መሠረት መጣል የሚሉት ናቸው።

የኮሚሽኑ የሥራ ዘመን ሦስት ዓመት ሲሆን፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የኮሚሽኑ የሥራ ዘመን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊራዘም እንደሚችል ተመላክቷል። ወደ ፊት ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው አገራዊ ምክክርና ብሔራዊ መግባባት የሚቋቋመው ኮሚሽን የተለያዩ ተግባር እና ኃላፊነቶች ይኖሩታል ተብሏል።
በዚህም መሠረት ምክክሮችን የሚያመቻቹና የሚያስፈፅሙ፣ የተለያዩ ጥናቶችን የሚያካሄዱ እና ምክረ ሃሳቦችን የሚያመነጩ ኮሚቴዎችን እና የባለሙያ ቡድኖችን ያቋቁማል። ከዚህ በፊት በመንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት የተደረጉ አገራዊ የምክክር ሒደቶችን እና የተገኙ ውጤቶችን ያጠናል። ግኝቶቹን በቀጣይ በሚያካሄዳቸው አገራዊ ውይይቶች በግብዓትነት ይጠቀማል፤ በልኂቃኖች መካከል አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያሉትን ልዩነቶች በጥናት፣ በሕዝባዊ ውይይቶች ወይም ሌሎች አግባብነት ያላቸውን መንገዶች በመጠቀም ይለያል፤ የምክክር አጀንዳዎችን ይቀርፃል፤ ምክክር እንዲደረግባቸው ያመቻቻል። ከዚያም ባለፈ ምክክሮችን እና ውይይቶችን ማዘጋጀትና ማሠልጠን ይገኙበታል።

እንዲሁም ከመላ ኢትዮጵያ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እና አካላትን የሚወክሉ ተሳታፊዎች የሚገኙባቸው፣ አገራዊ መግባባት ለማምጣት የሚያስችሉ የተለያዩ የምክክር ስብሰባዎችን በፌዴራል እና በክልሎች ደረጃ እንዲካሄዱ ያመቻቻል። በአገራዊ የምክክር ጉባዔ ላይ የሚሳተፉ ተሳታፊዎችን ግልፅ በሆኑ መሥፈርቶች እና የአሠራር ሥርዓት መሠረት ይለያል፤ በምክክሮች ላይ እንዲሳተፉ ያደርጋል፤ ምክክሮቹ በኮሚሽነሮች ወይም የኮሚሽነሮች ምክር ቤት በሚሠይማቸው አወያዮች አማካይነት እንዲመሩ ያደርጋል። በምክክር ሒደቶች የሚደረጉ ምክክሮችን ቃለ ጉባዔ የሚይዙ፣ የቀረቡ ምክረ ሃሳቦችን የሚያጠናቅሩ እና አደራጅተው ለኮሚሽነሮች ምክር ቤት የሚያቀርቡ ባለሙያዎችን ይመድባል። የጽሕፈት ቤቱን የውስጥ የአሠራር ሥርዓት፣ የምክክር አጀንዳዎች ወይም አርዕስት የሚመረጡበትን የሚመለከት፣ በአገራዊ ውይይቶች ላይ የሚሳተፉ አካላት የሚለዩበትን ሥርዓት ለመዘርጋትና መሠል ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችሉ ውስጠ ደንቦችን እና መመሪያዎችን የማውጣትና በሥራ ላይ የማዋል ሥልጣንና ተግባር ተሰጥቶታል።

የአገራዊ ምክክር ጉባዔ አጀንዳዎችን፣ የምክክሮቹን ሒደት፣ በምክክሮቹ የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን እንዲሁም ምክረ ሃሳቦቹ በተግባር ላይ ሊውሉ የሚችሉበትን ሥልት የሚገልጽ ዝርዝር ሪፖርት በማዘጋጀት ለመንግሥት ያቀርባል፤ ለሕዝብም ይፋ ያደርጋል። መንግሥት ከአገራዊ ውይይቶች የሚገኙ ምክረ ሃሳቦችን በተግባር ላይ ለማዋል እንዲችል ግልጽ እና ተጨባጭ የሆነ ዕቅድ እንዲያዘጋጅ አስፈላጊውን ዕገዛ ያደርጋል። የምክረ ሃሳቦቹን ተግባራዊነት ለመከታተል የሚያስችል ሥርዓት ይዘረጋል፤ ዓላማውን ለማስፈፀም የሚያስፈልጉ ሌሎች ተግባራትን ያከናውናል ተብሏል።

ኮሚሽኑን የሚመሩ አካላት በሕዝብ ጥቆማ እንዲቀርቡ መደንገጉን ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባዘጋጀው የመጠቆሚያ ቅጽ (ፎርም) ከተጠቆሙ 632 ሰዎች መካከል ምክር ቤቱ 42 ሰዎችን መለየቱን አስታውቋል። ዐዋጁ ለአፈ ጉባኤውና ለአፈ ጉባኤው ጽሕፈት ቤት በሠጠው ሥልጣን፣ እንዲሁም በዐዋጁ በተቀመጠው መስፈርት መሠረት ከቀረቡት 632 ሰዎች መካከል 42ቱ መለየታቸውን ምክር ቤቱ ገልጿል።
በተለዩት ሰዎች ላይ የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች፣ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጋራ ምክር ቤት አመራር አካላት በሚገኙበት በዕጩዎች የትምህርት ዝግጅትና የሥራ ልምድ ላይ ምክክር ተደርጎ ግብዓት የሚሰበሰብ መሆኑንም ተጠቁሟል። በተጨማሪም በምክር ቤቱ ድረ ገጽና በማኅበራዊ ሚዲያው የዕጩዎችን ማንነት በመግለጽ በቂ ግብዓት ከተሰበሰበ በኋላ፣ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢን ጨምሮ 11ዱ ዕጩ ኮሚሽነሮች ለምክር ቤቱ ቀርበው ከፀደቀና ዕጩዎች ከተሰየሙ በኋላ፣ ኮሚሽኑ ወደ ሥራ እንደሚገባ ምክር ቤቱ ገልጿል።
ብሔራዊ ውይይት በአንድ አገር ውስጥ ችግር በሚያጋጥምበት ወቅት በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ለመፈለግና ችግሩን ለማስቀረት የሚጠቅም የጋራ መድረክ መሆኑን ብዙዎች ይገልጻሉ። ብሔራዊ ውይይት ለዘላቂ የግጭት አፈታት፣ ለፖለቲካዊ ለውጥና ለኹሉን አሳታፊ ፖለቲካዊ ሥርዓት ግንባታ ተመራጭ መንገድ መሆኑ ይገለጻል።
ብሔራዊ ውይይትና መግባባት በኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ታሪካዊ ጉዳዮች ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት እና ችግሮችን ወደ ኋላ በመተው አዲስ ምዕራፍ ለመጀመር በር ከፋች መፍትሔ እንደሆነም ይነገርለታል።
በኢትዮጵያ ያሉት ችግሮች ያለ ውይይት እና የጋራ መግባባት እንደማይፈቱ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ሲገልጹ ይደመጣል። በብሔራዊ ምክክሩ ከፖለቲካዊ ችግሮች እስከ ሕገ መንግሥት ድረስ ያሉ ችግሮች በውይይት መሻሻል እንደሚገባቸው ብዙዎች ይጠቁማሉ።
በብሔራዊ ውይይቱ የተለያዩ ሐሳቦች የመንጸባረቅ ዕድል እንዲያገኙ ምቹ ኹኔታዎችን መፍጠር እና ውይይቱ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት በሚፈጥር ሁኔታ ተቀርጾ መመራት እንዳለበት ብዙዎች ይስማማሉ። የብሔራዊ ውይይት ሒደቱን ሊያስፈጽም የሚችል ኮሚሽን ለማቋቋም በመንግሥት በኩል የተጀመረው ሥራ ወሳኝ መሆኑም ብዙዎች እየገለጹ ነው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here