እቴጌ የሴቶች ባንድ ጉዞ

Views: 189

ጀግና ሴቶች ይዘርዘሩ የተባለ እንደሆነ ከቀዳሚዎቹ መካከል እቴጌ ጣይቱ ብጡል ተጠቃሽ ናቸው። ታድያ በእኚህ ጀግና እና ብርቱ ሴት ሥም የተለያዩ ሥራዎች ይሠራሉ፣ ተቋማት ይመሠረታሉ። ከእነዚህ መካከል በእቴጌ ጣይቱ መጠሪያ የተቋቋመው ‹‹እቴጌ የሴቶች ባንድ›› ወይም እቴጌ የሴቶች የሙዚቃ ቡድን አንዷ ናት።

ቡድኗ ከተቋቋመች አራት ዓመት ሆኗታል። ስምንት ሴት አባላት ያሏት ስትሆን፣ ይህች ባንድ በተለያዩ መድረኮች ላይ በመታደም የተለያዩ መርሃ ግብሮችን ለማድመቅ፣ ሥራዎቿን በሁሉንም የሙዚቃ ስልቶች ትጫወታለች። ‹ሴት በዛ ጎመን ጠነዛ› የሚል ብሂል ባለበትና ሴቶች እርስ በእርስ ተስማምተው መሥራት አይችሉም ተብለው በሚታሙበት ጊዜ፣ እቴጌዎች ይህን አስተያየት ፉርሽ ያደረጉ ይመስላሉ።

አዲስ ማለዳም ከዚሁ ጋር በተያያዘ የእቴጌ የሴቶች የሙዚቃ ቡድን ጉዞ ምን ይመስላል? የወደፊት እርምጃቸውስ ወዴት ይሆን? በማለትና ሌሎች ጥያቄዎችንም በማንሳት ከቡድኗ አባላት ጋር ተከታዩን አጠር ያለ ቆይታ አደርጋለች።

እቴጌ የሙዚቃ ቡድን፣ እንዴት ተቋቋመች?
አጋጣሚው እንዲህ ነበር፤ የቅድስ ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እና የጃዝ አምባ የሙዚቃ ተማሪዎች ለአንድ የሙዚቃ ሥራ ይገናኛሉ። ይህንን አጋጣሚ ግን አጋጣሚ ብቻ ብለው እንዲሁ አላሳለፉትም፤ ተጠቀሙበት እንጂ። ለምን የሴቶች ባንድ አናቋቁምም ሲሉ መከሩ። መምክር ብቻ አይደለም ከውሳኔ ላይ በመድረስ ስድስት በመሆን ባንዷን ይመሠርታሉ። ሳይውሉ ሳያድሩም ሥሟን ‹እቴጌ› ይሏታል።

ከባንዷ መሥራች አባላቶች ውስጥ ሦስቱ በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች ቡድኗን ለቅቀው ቢወጡም፣ ዛሬ ላይ ግን ስምንት አባላቶች በቡድኗ ይገኛሉ።
የባንዱ የኪቦርድ ተጫዋች እና ሜዲካል ዳይሬክትር መሰረት ሥሜ፣ ከዚህ በፊት በሌሎች የሙዚቃ ቡድኖች የመሥራት አጋጣሚ እንደነበራት ትናራለች። ‹‹ነገር ግን እቴጌ ጣይቱ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያላቸው ድርሻ ቀላል የሚባል አይደለም። ለሴቶችም ፈር ቀዳጅ ናቸው። ሴቶች ነጻነታቸውን እንዲቀዳጁ ለማድረግ የሠሩት ሥራ እንኳን በቀላል የሚታለፍ አይደለም።›› ትላለች።

በዚህ ላይ ለአብነት ያህል የጠቀሰችው በጣም ቀላል የሚመስል ግን አሁንም ድረስ ሴቶች ሊያደርጉት ሲፈሩ እና ሲያፍሩ የምንመለከወት ጉዳይ ሲሆን፣ ይህም ሴቶች ብቻቸውን ምግብ ቤት ገብተው እንዲመገቡ ያደረጉ መሆናቸው ነው። ይህ ቀላሉ ሲሆን፣ ያበረከቷቸውን አስተዋጽኦ እና ታላላቅ ተግባራትን በማከናወናቸው፣ እርሳቸውን ማስታወሻ ለእነርሱም ክብር የባንዷን ሥያሜ በእቴጌ ጣይቱ እንደሰየሙ ትጠቅሳለች።
እኛም ጥንካሬያችንን ለማሳየት ሥያሜውን ልንጠቀም ችለናል፣ ስትል ለአዲሰ ማለዳ ታብራራለች።

ፈተና እና እድል
መሠረት ገዛኸኝ በባንዱ ውስጥ የቤዝ ጊታር ተጫዋች ስትሆን በአሁን ወቅትም በአንድ የመገናኛ ብዙኀን ድርጅት ውስጥ በጋዜጠኝነትም እየሠራች ትገኛለች። በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት መመረቋን የምትናገረው መሠረት፣ ‹‹እኛን ጨምሮ ሴቶች ብቻ ተሰባስበው በሚሠሯቸው ሥራዎች፣ ከዚህ በፊት አትችሉም የሚል እሳቤ ነበር። በአሁን ወቅት ግን ለውጦች አሉ›› ስትል አስተያየቷን ትሰጣለች።

ከዚህ በፊት የነበረውን ነገርም ስታስታውስ፣ ገና በተቋቋሙበት ወቅት የተለያዩ የመድረክ ሥራዎች ላይ ለመሥራት እንዲሁም ለመሳተፍ አስቸጋሪ ነበር። ከሰዎች ጋር የነበረን ቀረቤታ እና ግንኙነት ብሎም የተለያዩ ሰዎችን አለማወቃችንም ሥራችን ላይ በትንሹም ቢሆን አስቸጋሪ ሆኖ ነበር ስትል ታስረዳለች።

መሰረት አክላ ስታገልጽም፣ ሴቶችን ይመለከታቸዋል የሚባሉት የመንግሥት ተቋማትም ቢሆኑ ተገቢው ትኩረት እና ቦታ እንደማይሰጧቸው ታነሳለች። ‹‹እራሳችን ነን ሥራዎችን እየፈለግን ያለነው። ይሁን እና አሁን ላይ ግን የተሻለ እድል እየመጣ ነው›› ስትል በማነጻጸር ሁኔታውን ትገልጻለች።

ሌላዋ የእቴጌ የሴቶች የሙዚቃ ቡድን የሊድ ጊታር ተጫዋች ነጻነት ጌታቸው፣ ከሰባት ዓመት በፊት ነበር ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ወደ አዲስ አበባ የዘለቀችው። ለዚህም ምክንያቷ የሙዚቃ ትምህርት ለመማር አዲ አበባ አመቺ ናት። በሙዚቃው ዘርፍም ጥሩ አጋጣሚ አላት ብላ በማሰብ ነው። አዲ አበባም ያሳፈረቻት አይመስልም፣ በመልካም አጋጣሚዎች ተቀብላታለች።

ይሁን እንጂ ለነጻነት ነገሮች በቀላሉ አልጋ በአልጋ ሆነው አልጠበቋትም። እንዲህም ስትል ትቀጥላለች፣ ‹‹የተሟላ የሙዚቃ መሣሪያ እና መለማመጃ ቦታ የለንም። ቡድናችን የበለጠ ጎልታ እንዳትወጣ እና እንዳትሄድ ያደረጋት አንዱም ቦታ ያለመኖሩ ነው።›› ስትል ታስረዳለች።

ለልምምድም ለኹለት ሰዓት አገልግሎት ሦስት መቶ ብር እየከፈሉ እንደሚያጠኑ ጠቅሳለች። በመንግሥት በኩልም የሚጠበቀውን ያህል ድጋፍ እየተደረገልን አይደለም ስትልም እይታዋን ትገልጻለች።

መሠረት ለዚህ የመንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ማነስ ማሳያ በቅርቡ ቡድኗ የገጠማትን ታቀርባለች። ይህም የአዲሰ አበባ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ወጣቶች ቢሮን ለማርች ስምንት፣ በኢትዮጵያ ለ44ኛ እና በዓለም ለ109ኛ ጊዜ ለሚከበረው የሴቶች ቀን ሥራዎች እንዲያሠሯቸው ጠይቀው እንደነበር ትጠቅሳለች። ይሁንና በተደጋጋሚ ተመላልሰው ለማናገር ቢሞክሩም ሊሳካላቸው አልቻለም። ‹‹እኛን ለማነጋገር ፈቀደኛ አይደሉም›› ስትል መሠረት የሆነውን ትገልጸዋለች።

ነገር ግን የኢፌዴሪ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር የዓለም ጸጋዬ፣ አምነውባቸው ሥራዎችን እንዲሠሩ እንዳደረጉ አውስተዋል። ይሁንና ግን የሙዚቃ ቡድኗ ስለሚገጥማት ችግርና ፈተና ከዚህም በላይ እንደሆነ መሠረት ታብራራለች።

ጂቱ ተፈራ በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ውስጥ የአራተኛ ዓመት ተማሪ ስትሆን፣ ባንዱን ከተቀላቀለች ዓመት አልሞላትም። በአዳማ የኒቨርስቲም በኮምፕዩተር ሳይንስ ትመረቅ እንጂ፣ በዚሁ ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት እንደሌላት በመናገር፣ ፍላጎቷ ዓለማዊ ሙዚቃ እና ሙዚቃ ብቻ በመሆኑ፣ የሙዚቃ ትምህርቱን ለመማር እንደወሰነች ታስረዳለች።

በቤተሰብ በኩል ድጋፍ እንደሚደረግላት የምትገልጸው ቱጂ፣ በሙዚቃ ቡድኗ ውስጥ የተለያዩ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች መኖራቸው ልምዳቸውን በቀላሉ ለመረዳት እንዳስቻላት ትገልጻለች። ለወደፊትም እንደ እቴጌ የሴቶች የሙዚቃ ቡድን ይሁን በግሏ ብቁ ባለሙያ ሆና፣ ለሌሎችም አረአያ የመሆን ህልም እንዳላትም ነው የምትገልጸው።

በሙዚቃ ውስጥ ለመሰማራት የሚፈልጉ ሴቶችም ቢሆኑ ራሳቸውን ብቁ በማድረግ ፍላጎታቸውን ለማሟላት መጠንከር እንዳለባቸውም መልዕክቷን አስተላልፋለች።
የሙዚቃ ቡድኑን ከመሠረቱ አባላት መካከል ይርጋሸዋ ደብሩ የሙዚቃ ትምህርት ተምራለች። ከተለያዩ ባንዶች ጋር እየሠራሁ ነው የምትለው ይርጋሸዋ፣ ከወንዶች ጋር የመሠራቱ አጋጣሚ እንዳላትም አስታውሳለች። ይሁንና ‹‹ምንም የተለየ ነገር የለም።›› ያለች ሲሆን፣ እንደውም በሴቶች በኩል የሚገርም መነቃቃትን እንደምትመለከት ትገልፃለች።

በእቴጌ የሴቶች የሙዚቃ ቡድን ውስጥ የሳክስፎን መሣሪያ ትጫወታለች። እናም ቡድኗ ስትመሠረት ጀምሮ ያለፈችበትን ብዙ ፈተናዎችና እንደ ቡድን የገጠማቸውን በማውሳት፣ ከሙዚቀኞች ጀምሮ ሴቶችም ጭምር፣ ሴቶች በጥሩ ሁኔታ ይሠራሉ ብለው አያምኑም ነበር። ዛሬ ግን ይህ ተቀይሯል ባይ ናት።

ሌላዋ የቡድኑ አባልና በቡድኗ የሳክስፎን ተጫዋት መልዕክት ፍቅሬ፣ ቡድኗ ከተመሰረተች ኹለት ዓመት በኋላ የተቀላቀለች ናት። የሙዚቃ ትምህርትና ከሙዚቃ በተጨማሪ ከኮምፕዩተር ጋር የተያያዘ ትምህርት ለመማር ብትሞክርም፣ ዝናባሌዋ ወደ ሙዚቃ ስለሆነ በሙዚቃው ቀጥላ ዛሬ በእቴጌ የሴቶች ባንድን እንድትቀላቀል ሆናለች።

እቴጌ የሙዚቃ ቡድን ውስጥ በመሥራት ከትምህርት ቤት ሊገኙ ከሚችሉ እውቀቶች በተጨማሪም ብዙ እውቀቶችን ልምዶችን ማግኘት ችያለሁ። በሴትነቴም ጠንክሬ እንድሠራ አድርጎኛል ስትል ታስረዳለች።

በያዝነው 2012 ቡድኑን የተቀላቀለቸው ሌላዋ የቡድኗ አባል ሐወኒ ኢተፋ (ሀዊ) ናት። ሐወኒ በተለያዩ ሆቴሎች ላይ ፒያኖ በመጫወት ትሠራለች። በኮሌጅ ውስጥም የኤሌክትሮኒክስ ጥገና ትምህርት ብትማርም፣ እርሷም ለሙዚቃው ካላት ፍላጎት የተነሳ እቴጌን በመቀላቀል እየሠራች ትገኛለች። አሁን በሙዚቃ ቡድኑ ኪቦርድ በመጫወት እያገለገለች ሲሆን፣ እንደ ቡድን የተሻለ ለማድረግ እሠራለሁም ትላለች።

በጥቅሉም እቴጌ የሴቶች የሙዚቃ ቡድን፣ ያሰባሰበቻቸው ሴቶች በሚወዱት የሙዚቃ ሥራ የልባቸውን እንዲያደርሱና በነጻነት እንዲሠሩ ችለዋል። በዚህም በሁሉም ገጽ እና ንግግር ላይ ደስታ ይነበባል። ሴቶች አንድ ላይ በመሥራታቸው የተለየ ነገር እንደማይፈጠርና፣ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉት እቴጌዎች ማሳያ ይሆናሉ። እነርሱም እንዲህ ላለ አረአያነት እንደሚተጉ ነው የሚናገሩት።

ተቀባይነት
በባንዱ ውስጥ የኪቦርድ መሣሪያ ተጫዋችዋ ትዕግስት ሥሜ፣ ከያሬድ ሙዚቃ እና ጃዝ አምባ ትምህርት ቤት የተመረቀች ሲሆን በአሁን ወቅት ከእቴጌ የሴቶች ባንድ በተጨማሪ በአዲስ አበባ ቴአትር ባህል አዳራሽ ውስጥ በሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋችነት ትሠራለች። ትዕግስት ስትናገር፣ በአሁኑ ወቅት ብዙ መሻሻሎች አሉ ትላለች። ይልቁንም በመድረኮች ላይ ባህል – ዘመናዊ፣ ዘመናዊ ብቻ እና በሙዚቃ መሣሪያ ብቻ ስትሠራ ብዙ ሰዎች ማመን እንደሚያቅታቸው ትናገራለች። አሁን ግን ሙዚቀኞችም ቢሆኑ ከእኛ ጋር መሥራትን እየመረጡ፣ አሁን አሁን ተቀባይነታችን እየጨመረ ነው ትላለች።

ትዕግስት መለስ ብላ በፈረንጆቹ 2019 ዓለም አቀፉ የሚዲያ ተቋም የሆነው ሲ.ኤን.ኤን. የዓመቱ ጀግና ብሎ የሸለማትን ፍሬወይኒ መብራቱ ጋር የተገናኘችበትን አጋጣሚ ታነሳለች። ‹‹ከፍሬወይኒ ጋር በአንድ መድረክ ላይ ተገናኝተን ሥራዎችን የማቅረብ አጋጣሚው ነበረን። እና ፍሬወይኒም አበረታታናለች። አገራችንን ብዙ ጀግኒት ሴቶች ያሏት መሆኑንም ነግራናለች።›› ብላለች።

ተቀባይነታችን ከዕለት ዕለት በመጨመሩም በተለያዩ የባዛር ሥራዎች፣ ሆቴሎች እና ጥበባዊ የሆኑና ያልሆኑ ሁነቶች ላይም ሥራዎችን እያሳዩ ስለመሆኑን ጠቅሳለች፤ ትዕግስት።

የነገ እቅዶች
እቴጌ የሴቶች የሙዚቃ ቡድን አባላት በተደጋጋሚ ሲናገሩት ከነበሩት ጉዳዮች መካከል ቡድኗን ለማቋቋም አልፎም ጉዞዋን ለማቀጠል ገና ከጅምሩ ብዙ ፈታናዎች እንደነበረባቸው ነው። ምንም እንኳን የቤተሰብ ድጋፍ ቢኖራቸውም፣ ታዋቂ ባለሙያዎችን ጨምሮ ለሥራቸው ዋጋ አለመስጠት የሚታይባቸው መሆኑና በእነርሱም ላይ እምነት የነበራው ብዙዎ አለመሆናቸው ለአባላቶቹ የሚያሳስባቸው የቤት ሥራ ነበር።

ዛሬ ግን ታሪክ እንደተቀየረ የሚናገሩት የሙዚቃ ባለሙያዎቹ፣ እቴጌም በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘቷን ያነሳሉ። እናም እጅ ሳይሰጡ መሥራታቸው፣ ለወደፊት የሚጠብቃቸው ረጅም ጉዞ እንዳለ፣ በዚህ እንደማይቆሙ እና ብዙ ርዕይም እንዳላቸው ነው የሚያስረዱት።

በሥራ ላይ የሚገኙትም ይሁኑ ተማሪዎቹ አሁን ላይ ሥራቸውን ፈታኝ የሚያደርግባቸው የጊዜ እጥረት ቢሆንም፣ ዛሬን ጨምሮ በግልም ይሁን በቡድን አቅማቸውን እና ብቃታቸውን እያሳዩ እንደሆነ ነው ለአዲስ ማለዳ ደጋግመው የሚናገሩት።

ምንም እንኳን ቋሚ የመለማመጃ ቦታዎች እና የሙዚቃ መሣሪያዎች የሌላቸው በመሆኑ በኪራይ እየሠሩ ቢሆንም፣ በአሁን ከፋሲካ በኋላ በአንድ ሆቴል ውስጥ በቋሚነት ለመሥራት መስማማታቸውን ጠቅሰዋል። ይህም የነበሩትን ችግሮች በተወሰነ መልኩ በቋሚነት የሚፈታላቸው እንደሆነ ተስፋ አድርገዋል።

በዚህ ብቻ የመቆም ሐሳብ የሌላቸው የእቴጌ የሴቶች የሙዚቃ ቡድን አባላት፣ በመሣሪያ ብቻ የተቀነባበሩ አልበሞችን ለማሳተም እቅድ ላይ መሆናቸውንም ይናገራሉ። ልክ እንደ እቴጌ ጣይቱ ጠንካራ በመሆን ብዙ እቴጌዎችን ለማፍራት እና ለሌሎች ሴቶችም ምሳሌ ለመሆን፣ በኢትዮጵያም ቀዳሚ የሚሆን የሴቶች የሙዚቃ ቡድን ለመሆን እየሠሩ እንደሆነ፣ በእምነትና በተስፋ በእርግጠኝነትም የተናገሩት ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 70 የካቲት 28 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com