የዓለም ጫና በኢትዮጵያ ፖለቲካ እና መጪው ምርጫ ላይ

Views: 67

ምርጫ ቦርድ ምርጫው የሚካሔደው ነሐሴ መጨረሻ ላይ እንደሚሆን ካሳወቀ ጊዜ ጀምሮ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሚወዳደሩባቸው ቦታዎች እንዲሁም በአገሪቱ ዙሪያ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምረዋል። የአገር ውስጥ ጉዳዮች የምርጫውን ውጤት ለመወሰን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ሁሉ ዓለም አቀፍ ጉዳዮችም ከዚህ ያነሰ የማይባል ሚና ይኖራቸዋል። ባለፉት 50 ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ በምን መልክ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተፅዕኖ ስር እንደቆየ እና በመጪው ምርጫ የቶቹ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተፅዕኖ ሊኖራቸው እንደሚችል እንቃኛለን።

በነሐሴ መጨረሻ ሊካሔድ የታቀደው ምርጫ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተፍ ተፍ እንዲሉ መነቃቃትን የፈጠረ ይመስላል። ይህንንም ተከትሎ የፖለቲካችን መገለጫ የሆነው የመጠላለፍ እና የመወነጃጀል አካሔድ እየተጠናከረ እንደመጣ እየታዘብን ነው። ፓርቲዎች እርስ በእርስ ከመወነጃጀላቸው በተጨማሪ ለምርጫው የሚደረገው ዝግጅት በእቅድ መሠረት እየሔደለት ያልሆነው የምርጫ ቦርድንም በተለያየ መንገድ እየጎነታተሉት ይገኛሉ።

እንደ አሜሪካ ያሉ ኃያላን አገራት እንኳን ሳይቀሩ በምርጫ ወቅታቸው የውጭ አገሮች ምርጫቸውን ወደሚፈልጉት ወገን እንዲያዘም ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር በሚናገሩበት በዚህ ዘመን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ደሀ አገሮች ከውጭ የሚያጋጥማቸው ጫና ትንሽ አይሆንም። በተለይ የምርጫ ቦርድ በመጪው ምርጫ የለመድናቸውን ኮሮጆዎች ሳይሆን ሊጠቀም ያሰበው የድምፅ መስጫ ማሽኖችን መሆኑ ከግምት ውስጥ ሲገባ እነዚህ ማሽኖች በአሜሪካም ሆነ በደቡብ አሜሪካ ምርጫዎች ላይ አወዛጋቢ ሁኔታ እንዲፈጠር ሚና እንደነበራቸው ማሰባችን አይቀርም።

ምንም እንኳን አገራዊ ሁኔታዎች በምርጫ ወቅት የሕዝብን ውሳኔ የመቀየር አቅም ያላቸው ቢመስሉም በዓለም አቀፍ መድረክ የሚነሱ ለውጦች እና አካሔዶች ከዚያ ያነሰ ጫና እንደሌላቸው ልብ ልንል ይገባል። አገራዊ እውነታዎች የፖርቲዎችን የእንቅስቃሴ አድማስ ይዘው ይገኛሉ። አገራዊ ምርጫ ሲታሰብም ፓርቲዎች መራጮችን ማግባባት እንደሚጠበቅባቸው ገልጽ ነው። ነገር ግን የኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ፓለቲካን መለስ ብለን ብንቃኝ አገራዊ ምቹ ሁኔታ ከዓለም ዓቀፋዊው ጋር ሲሰናሰል ነው የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ሥልጣን የሚመጡት።

በ1966 ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ለሦስት ሺህ ዘመን የቆየውን ንጉሳዊ አስተዳደር ገርስሶ ሥልጣን ላይ የወጣው በዓለም ዙሪያ ከቅኝ ገዢዎች ነጻ የወጡ አገሮች በስፋት እየተቀበሉት የነበረውን የሶሻሊስት አስተሳሰብ አንግቦ ነበር። በጊዜው አገራዊው ሁኔታም በዚህ ርዕዮተ ዓለም የተቃኘ ስለነበር አብዮቱ የሥርዓት ለውጡን እውን ሊያደርግ ችሏል። አገራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎቹ ለለውጡ ምቹ ነበሩ ማለት ይቻላል።

ይህ የሶሻሊስት ስርዓት ደግሞ ለ17 ዓመታት ከቆየ በኋላ በ1983 ሲወድቅ ዓለማቀፋዊው ሁኔታ የርዕዩተ ዓለሙ ዋነኛ አራማጅ የሆነችው ኀያል አገር ሶቭዬት ሕብረትን መበታተን ያካተተ ነበር። ጊዜው የአሜሪካ እና የምዕራባውያን ካፒታሊዝም በሶቭዬት እና አጋሮቿ ሶሻሊዝም ላይ ድልን የተቀዳጀበት የነበረ ሲሆን ይህ ዓለማቀፋዊ ሁኔታ በኢትዮጵያ ፓለቲካ ውስጥ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) እንዲተካ አድርጓል።

በሶሻሊዝም መርሆዎች ተወልዶ ያደገው ኢሕአዴግ ምንም እንኳን ጥርስ የነቀለባቸውን እሴቶቹን እስከመጨረሻው ለመተው የተቸገረ ቢሆንም በተወሰነ መልኩም ቢሆን “ነጭ ካፒታሊስት” ለመባል ደፋ ቀና ማለት ነበረበት። ይህም ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ዓለምን በካፒታሊዝም ርዕዮተ ዓለም ጠርንፋ ያነጎደችው ብቸኛዋ ኀያል አገር አሜሪካን ይሁንታ ለማግኘት እንዲሁም ከዚያ አካሔድ ውጭ በመሆን የሚደርሰውን መገለል ለመከላከል ነው። እንዲህ ባለው የዓለም ስርዓት ውስጥ ሶሻሊዝምን የሙጥኝ ያሉት አገሮች ምን እንደሆኑ ሲታይ የኢሕአዴግ ካፒታሊስት ሆኖ ለመገኘት መጣር የሚያስገርም አይደለም።

ከዚህም ባሻገር በሕውሃት የሚመራው ኢሕአዴግ ግብዓት ላይ ብልጽግና ከመሰልጠኑ ከዓመታት በፊት የኀያልዋ አገር ሰዎች እንዲሁም ምዕራባዊያን ከኢሕአዴግ ጋር በዘላቂነት መሥራት እንደሚቻል ጥርጣሬ ገብቷቸው እንደነበር በሰፊው ሪፖርት ተደርጓል። ዶናልድ ያማሞቶ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ተደርገው ከተሾሙ በኋላ የዚያን ጊዜውን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን አቋም በቅርበት በመፈተሽ “አብረናቸው ልንሠራ የምንችል ሰው አይደሉም” የሚል ሪፖርት ወደ አገራቸው እንደላኩ ሚኪሊክስን በመጥቀስ አንዳንድ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኋን ዘግበው ነበር። የዚያን ጊዜው ኢሕአዴግ ከአሜሪካ ይልቅ ወደ ቻይና ያጋደለ አመለካከት ያለው መሆኑም ለምዕራባዊያኑ ጥርጣሬ በምክንያትነት ይጠቀሳል።

ከዚህ ድምዳሜ ጥቂት ዓመታት በኋላ ከፓርቲው ውስጥ የወጣ የለውጥ ኃይል እንደምናየው ሕውሃትን በቃኝ ከእናንተ ጋር መሆን አስብሎ ጥጉን አስይዞታል። የዚህ ለውጥ ኃይል የመጀመሪያ ውሳኔዎች መካከል ደግሞ ፊቱን ከቻይና ወደ አሜሪካ ማዞር እና ሕውሃት መራሹ ኢሕአዴግ አልለቅም ያላቸውን የአገሪቱን ትላልቅ ተቋማት ለሽያጭ ማቅረብ ይገኙበታል።

በመሆኑም በጥናት በተደገፈ መልኩ ለመደምደም ባይቻልም የዓለም አቀፉ ሁኔታ ከቅርብ ጊዜው የአገራችን የሥልጣን ሽግግር ጋር ሊያያዝ እንደሚችል መገመት ይቻላል። ከፊታችን የሚጠብቀን ምርጫ ወሳኝ የፖለቲካ እርከን መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ የዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ምን ዓይነት ተጽዖኖ ሊኖራቸው እንደሚችል አስቀድሞ ማሰብ እና ተጽዕኖው ውስን ወይም የአገራችንን ቀጣይነት እና ደህንነት የሚያስጠብቅ እንዲሆን ቀድሞ መዘጋጀት ያስፈልጋል።

በመሆኑም በሚመጣው አገራዊ ምርጫ ላይ ከፍተኛ ተፅዖኖ የሚያሳድሩ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ አመለካከቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል። የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኝ የሆኑት ይታገሱ ዘውዱ (ዶ/ር) በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ እየተቀነቀነ ያለው እና በአገራችንም ጫና ሊኖረው ይችላል ብለው የሚያምኑት አመለካከት ሕዝበኝነት ወይም ብሔርተኝነት ነው። እርሳቸው እንዳሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ ብሔርተኝነት አገራዊ ሲሆን በእኛ አገር ያለው ግን ንዑስ ብሔርተኝነት ወይም ጎሰኝነትን የሚገልፅ በመሆኑ አተረጓጎሙ ላይ ለውጥ አለ። በሌላው ዓለም ብሔርተኝነት የአንድ አገር የበላይነትን በማሳየት ከሉላዊነት ጋር በተቃርኖ የሚቆም መሆኑን ያስረዳሉ። ለዚህም የእንግሊዝን ከአውሮፓ ሕብረት መውጣት እንደማሳያ ያነሳሉ።

በመሆኑም የዓለም አቀፉ ሁኔታ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ይታገሱ ያምናሉ። በአገር አቀፍ ደረጃ ባይሆንም እንኳን የብሔርተኝነት እና ሕዝበኝነት አካሔድ በንዑስ ብሔርተኝነት ወይም በዘውገኝነት በሰፊው እየተቀነቀነ ይገኛል ይላሉ ይታገሱ። በዓለም አቀፍ ደረጃ ቅድሚያ ለአሜሪካ ሲባል የሰማነው መፈክር ቅድሚያ ለኦሮሚያ፣ ቅድሚያ ለትግራይ፣ ቅድሚያ ለአማራ፣ ቅድሚያ ለሱማሌ በሚል እየሰማነው ነው ሲሉም ወደ አገር ውስጥ እንደገባ ያሳያሉ።

በዚህ ሁኔታ ሁሉም ሰው አካባቢውን ከአገር በላይ አስበልጦ የራሱን ጎሳና ዘውግ የበላይነት ለማረጋገጥ ጥረት ማድረጉ የሚታወቅ ነው ብለዋል። የሚቀነቀኑት የፖለቲካ መልዕክቶችም በዋነኛነት ሕዝበኝነት ላይ የተመረኮዙ እንደሆኑ ያስረዳሉ። ይህም የዓለም አቀፍ አውዱ ያቀረበው አማራጭ ይመስላል ወይም ዓለም አቀፍ ፋሽን ነው ይላሉ ይታገሱ። ኢትዮጵያ ውስጥም ከእውነታው ባፈነገጠ መንገድ የአንድን አካባቢ እና የአንድን ማህበረሰብ ጥቅም ለማስጠበቅ ብቻ ሲባል ሌሎቹ የራሳቸው ጉዳይ የሚል ዓይነት የሕዝበኝነት እንቅስቃሴ መንግሥት ውስጥም ባሉ ሆነ ተቃዋሚ ነን በሚሉ ሰዎች በስፋት ይስተዋላል ብለዋል።

የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ዳርእስከዳር ታዬ (ዶ/ር) በዋናነት በምዕራባዊያኑ ፖለቲካ ውስጥ የሚታይና የእነሱም ምርጫዎች ላይ ጫና እያሳደረ ያለው የቀኝ ጽንፍ አገራዊ ብሔርተኝነት ነው ብለው ያምናሉ። ነገር ግን ከይታገሱ በተለየ ዳርእስከዳር ከዓለም አቀፉ ይልቅ የመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ተጽዖኖ ያሳድራል ብለው ያምናሉ።

በመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ ውስጥ በሳዑዲ አረቢያ እና በኢራን የሚመሩ ሁለት ተፎካካሪ ኃይሎች አሉ ይላሉ ዳርእስከዳር። በሳዑዲ ስር ዋነኛ ተጠቃሽ አገር የተባበሩት አረብ ኤመሬትስ ስትሆን በኢራን ስር ደግሞ ኳታር አለች ያሉት ዳርእስከዳር በአፍሪካ ቀንድ ልዩ ፍላጎት ያለው የሳዑዲ መራሹ ቡድን ነው ይላሉ።

ከዚህም ቡድን በዋነኛነት የተባበሩት አረብ ኤመሬትስ በዚህ አካባቢ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንደምታደርግም ያብራራሉ። “ዱባይ ኤርትራ ላይ አሰብ ወደብን እያለማች ነው፤ ጅቡቲ ጋር ጠብ ውስጥ ገብታለች፤ ሱማሌላንድ ላይ በርበራ ወደብን እያለማች ነው።” እነዚህን ወደቦች ስታለማ የኢትዮጵያ ገበያ ላይ አልማ ነው ሊሆን የሚችለው ባይ ናቸው ዳርእስከዳር። ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት እነዚህ ኃይሎች ለሚመርጡት ቡድን የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ በቀጥታ የምርጫው ውጤት ለእነሱ የሚመቻቸው እንዲሆን ሊሠሩ እንደሚችሉም ያምናሉ።

በምርጫው ላይ ጫና ሊያሳድሩ ከሚችሉ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች መካከል በቅርቡ ከአካባቢያዊ ወደ ዓለም አቀፋዊነት ያደገው የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ይገኝበታል። ይታገሱ ዘውዱ (ዶ/ር) ግብፅ በሕዳሴው ግድብ ምክንያት የተዳከመችና የተከፋፈለች ኢትዮጵያን ማየት ፅኑ ምኞቷ በመሆኑ የኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልጉ፤ ከዚያ ይልቅ ወደ ክልላዊነት ላይ ያተኮሩ ፓርቲዎች ቢመጡ ምርጫዋ ሊሆን ይችላል ብለው ያምናሉ። ይህንን ለማሳካት ደግሞ በተለያዩ ይፋ ባልሆኑ መንገዶች ልትሠራ እንደምትችል ይታመናል ብለዋል።

ይታገሱ ሌሎች አገራት ደግሞ የርዕዮተ ዓለም ምርጫቸውን አስመልክቶ የሚፈልጉት ዓይነት ስርዓት እንዲመጣ የሚንቀሳቀሱበት መንገድ እንደሚኖር ጠቁመዋል። ይህም ይላሉ ተንታኙ የእጅ ጥምዘዛ ድረስ ሊደርስ የሚችል ነው። በአጠቃላይ ዓለም አቀፍ ጫናው አሉታዊም አዎንታዊም ሊሆን ይችላል ያሉት ይታገሱ አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ጥሩ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያለን አገራት ደግሞ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ እንዲካሔድ ባላቸው ፍላጎት እያደረጉ ያለውን የገንዘብ፣ የቴክኒክ እና የልምድ ድጋፍ አድንቀዋል።

መደምደሚያ
ከላይ እንዳየነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለዓለም አቀፍ የፖለቲካ ለውጦች ምላሽ የሚሰጥ እና ራሱን ከዚሁ አዲስ አካሔድ ጋር የሚያዛምድ እየሆነ መጥቷል። በዓለም አቀፉ ስርዓት ውስጥ የሚታየው ብሔርተኝነት በአገራችን ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮለት ከመቆየቱ ጋር ተዳምሮ በንዑስ ብሔርተኝነት መልክ ገንኖ የወጣበት ሁኔታ ይታያል። ይህን ሁኔታ በአካባቢው ላይ የተለያየ ጥቅም ያላቸው አገሮች ሊጠቀሙበት የሚችሉ መሆኑ ሲታሰብ ጉዳዩ ከቁጥጥር እንዳይወጣ እና አንድ የምታደርገን አገር ጉዳይ ቸል እንዳይባል የሚያሳስብ ነው። በመሆኑም ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ የዓለም አቀፉን ስርዓት ለውጦች ተከትሎ ሲቀየር የቆየው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ አካሔዱን አሁን ሊቀይር ይገባዋል። ኢትዮጵያ ላይ ከሌሎች አገሮች ፍላጎት ይልቅ የኢትዮጵያውያን ፍላጎት ይበልጥ ተግባራዊ እንዲሆን የአንድነት ስሜት ከመቼውም የበለጠ ሊታይ ይገባዋል።

ይህ ሳይሆን የዓለም አቀፉ ስርዓት የወረወረብንን ተቀብለን የምንቀጥል ከሆነ ደግሞ በቀኝ አክራሪ ንዑስ ብሔረተኞች የተሞሉ የክልል ምክር ቤቶች እና ከጋራ ጉዳይ ይልቅ ለክልላዊ ጥቅም ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ የሕዝብ ተወካዮች ይኖሩናል። ይህም የአገሪቱን የወደፊት ጥንካሬ የሚያናጋ በመሆኑ ክልላዊነት ከአገራዊ ብሔረተኝነት ጋር ሚዛናዊ ቢደረግ ጥሩ ይሆናል።

በተጨማሪ የውጭ ኃይሎች ፍላጎታቸውን በድብቅ የሚያራምዱ በመሆኑ ይህንን ለማስፈፀም ሊጠቀሙባቸው የሚችሉት ፖለቲከኞችን ነው እና ፖለቲከኞቻችን ታማኝነታቸውን ለሕዝብ እና ለአገር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የዓለማቀፍ ለውጦችን እየተከተሉ በደመነፍስ መወዝወዙ ወደባሰ ችግር እየከተተን መሆኑን ማየት ስለሚቻል በእቅድና ታስቦበት ለሕዝብ የሚያስፈልገውን ነገር መሥራት ከፖለቲከኞች ይጠበቃል።

ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com