የአፓርታይድ መንፈስ በኢትዮጵያ….. ?!?!

Views: 245

በኦሮሚያ ሚድያ ኔትወርክ ቀጥታ ስርጭት ይተላለፍ በነበረ ስብሰባ፣ አንድ አስተያየት ሰጪ ባደረገችው ንግግር አልፎም በሐሳቧ ብዙዎች ደንግጠው ነበር። ጉዳዩም የብዙኀኑ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። ግዛቸው አበበ በበኩላቸው፣ ከዚህች ሴት ሐሳብ ባልተናነሰ አልፎም በባሰ መልኩ የሚደረጉ የጥላቻ ንግግሮች እንዳሉ አንስተዋል። እንደውም ከኢትዮጵያ አንድነት በራቀና በብሔር በጠበበ ደረጃ በሚደረጉ ንግግሮችና በሚሰጡ ሐሳቦች፣ በድርጊቶችም ጭምር በባለሥልጣናት ደረጃ ራሳቸው የሚገኙበት መሆኑ አስወቃሽ ነው በማለትም ማሳያ ነጥቦችን ጠቅሰዋል።

በኦሮሚያ ሚድያ ኔትወርክ (ኦኤምኤን) ላይ በቀጥታ ሲተላለፍ በነበረ ስብሰባ ላይ ተካፋይ የነበረች አንዲት ወጣት የኦሮሞ ሕዝብ ጋብቻ ምን መምሰል እንዳለበት አስደንጋጭ ሐሳቧን መሰንዘሯን ተከትሎ፣ ብዙ ደግ አሳቢ ኢትዮጵያውያን ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። ቁጥራቸው የዚያኑ ያህል አስመሳይ ሰዎች ደግሞ ባዶ ጫጫታ፣ የሐሰት ኡኡታ ሊባል የሚገባውና አጋጣሚውን በመጠቀም ጥላቻን ለመዝራት የታሰበበት የሚዲያ ግርግር ፈጥረው ታይተዋል።

ከእነዚህ ሰዎች ብዙዎቹ ሐይማኖትንና ብሔርን ሽፋን አድርገው፣ ወጣቷ ከተናገረችው የከፋ ከፋፋይና ነጣጣይ ትምህርት በዕምነት ተቋማት በአዳራሾች፣ በሕትመት ሥራዎቻቸው ወዘተ… ሲያስተምሩ የታዘብናቸው ናቸው። እነዚህ ሰዎች እኩይ ትምህርታቸው ወደ መሬት ወርዶ ክፉ ፍሬ ሲያፈራም እያየን ነው። አሁንም ደግሞ ጀሌዎቻቸውን፣ ተከታዮቻቸውን፣ አድናቂዎቻቸውን ወዘተ… እየጠሩ መቶ ብርና ከዚያም በላይ እያስከፈሉ፣ ያሻቸውን ሲናገሩ፣ የፈለጉትን ሲዘረጥጡ፣ የወደዱትን ሲያወድሱ ይታያሉ። እነዚሁ ሰዎች የኢትዮጵያን የቀድሞ ነገሥታት ይዘረጥጣሉ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ በጅምላ ይዘልፋሉ፣ አድናቂዎቻቸው፣ ጀሌዎቻቸው፣ ተከታዮቻቸውም እግራቸውን እያነሱ ከጣራ በላይ ይስቁላቸዋል፣ ያጨበጭቡላቸዋል።

ከእነዚህ ሰዎች አንዳንዶቹ አምላካቸውን ፈርተው ብዙ ኃላፊነት ሊሰማቸው የሚገባ ዲያቆናት፣ ኡስታዞች፣ የሐይማኖታዊ ማኅበራትና ተቋማት አባላት ወይም አመራሮች ናቸው። እነዚህ ሰዎች አንድን ቦታ (የቀድሞ ክፍለ አገሮችን) ለይተው እየጠሩ፣ በዚህ አገር ይኸኛው እምነት እንጂ ያኛው እምነት ኖሮ አያውቅም፣ የዚያ ሐይማኖት ሰዎች በዚህ ቦታ ከተገኙ ይሰየፉ ነበረ፣ እያሉ ሰብከዋል ወይም የሕትመት ሥራ አሰራጭተዋል። ይህ ስብከታቸው ደግሞ ሰዎችን ለሞት፣ የእምነት ተቋማትን ለጥቃት ዳርጎ እያየን ነው።

እነዚህ ሰዎች በእምነት ቦታዎች በሚያደርጉት ስብከቶች፣ ቤት ያላቸው የእምነታቸው ተከታዮች እነማንን ብቻ ማከራየት እንዳለባቸው፣ እነማንን ደግሞ ማከራየት እንደማይገባቸው ትምህርት ሲሰጥ በቸልታ ተመልክተዋል። ኢትዮጵያውያን በአንድ ግቢ መኖር ካልቻሉ በአንድ አገር አብሮ መኖርንም ከባድ ወይም የማይቻል እንደሚያደርግ ቢያውቁም፣ ሰባኪዎችን ከማስቆም ወደ ኋላ ብለዋል። እነዚህ ግለሰቦች ኢትዮጵያን የሐይማኖት መቻቻል የሌለባት፣ የሐይማኖት መቻቻል አለ የሚባለው የውሸት መሆኑን ለእምነት ተከታዮቻቸው ነግረዋል። የኢትዮጵያን ነገሥታት በሙሉ ጸረ-እምነታቸው አድርገው ያዩ ዘንድ የሚገፋፋ መጽሐፍ አሳትመው፣ በእምነት ተቋማቸው በር ላይ ቸርችረዋል፣ እየቸረቸሩም ነው።

እንግዲህ እነዚህ ሰዎችና ተከታዮቻቸውም ጭምር ናቸው ያችን ወጣት ለመተቸት፣ ለመዝለፍ፣ ለማጣጣል ወዘተ… ሲጣደፉ ያየናቸው። ለመሆኑ እነዚህ ግለሰቦች እያንዳንዱን ሰው መቶ ብር እያስከፈሉ ከሚያካሂዱት ስብሰባ ወጣ ብለው በሕወሐት/ኢሕአዴግ ዘመን ተወልደው የጎለመሱ ወጣቶችን ሰብስበው ትክክለኛ ታሪካቸው ያውቁ ዘንድ፣ በሐይማኖት እንዲናቆሩ ለማድረግ ሆነ ተብሎ ተቀምሞ የተዘራውን አናቋሪ ትርክት ለማጋለጥ ስብሰባ አካሂደው ያውቃሉ? መጽሐፍ አሳትመው ለማስተማርስ ሞክረዋል? በመጽሔትና በጋዜጦችስ ትምህርት ሰጭ ጽሑፎችን ለማሰራጨት ሞክረዋል?

እነዚህ ሰዎችና ጀሌዎቻቸው ኢትዮጵያዊነት በአማራ ክልል እንዳይሰበክ የሚቀሰቅሱ ወገኖችን ዝም ብለው ከርመው፣ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ፓርቲ በአማራ ክልል እንዳይንቀሳቀስ ጓንዴና ጎራዴ ይዘው የሚከለክሉ ሰዎች ሲበዙ፣ ምንም ሳይተነፍሱ የኦሮምያዋ ወጣት ‘ከሐበሻ ጋር አትጋቡ’ ስትል መደንፋታቸው የጤና ነውን? ድንፋታቸው የራሳቸውን የዘር ጥላቻ የሚያጋልጥ አይደለምን?
እነዚህ ሰዎችና ጀሌዎቻቸው የልጅቱን የኦሮምኛ አባባል ተርጉመውና አስተርጉመው እንደ ተንጫጩት ሁሉ፣ የልጅቱን ሐሳብ ያስተላለፉ ሚዲያዎችን እንዳብጠለጠሉት ሁሉ፣ ከወደ ትግራይ ከዚህ የከፉ አገር የማፍረስ ዛቻወች ያለ ማቋረጥ ሲስተጋቡ ለምን ያልሰሙ መስለው አለፉት? አገር አፍራሽ ሐሳቦችን ዘወትር የሚያስተጋቡ የትግርኛ ሚዲያዎችንስ ለምን አልተቹም? ይህ አካሄዳቸው የሕወሐት ሎሌነታቸውን ወይም ሕወሐትን መፍራታቸው ያልለቀቃቸው መሆኑን አያሳይምን?

ወደ ኦሮሚያ እንመለስ። አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ “ኦሕዴድ ሲፋቅ ኦነግ ይሆናል!” ሲሉ ተሰምተው ነበር። ይህ አባባላቸው ኦሕዴዶች ሕወሐት ከሚፈልገው በላይ ፈጥነውና በልጠው (ልክ እንደ ኦነግ) ጸረ-ኢትዮጵያና ጸረ-ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን የሚያሳይ ተደርጎ ተወስዷል።

ምርጫ 1997ን ተከትሎ በአዲሰ አበባ ሽንፈትን የተከናነበው ሕወሐት/ኢሕአዴግ፣ አዲሰ አበባን የንትርክ ከተማ ለማድረግ ሲል የኦሮሚያን ዋና ከተማ ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ ማዛወሩ የሚዘነጋ አይደለም። ሕወሐት ኢትዮጵያን እንደተቆጣጠረ የኦሮሚያ ቢሮዎች በሙሉ አዲስ አበባ ውስጥ እንዲሆኑ አድርጎ ነበር። ከዚያም ወደ አዳማ አዛወራቸው። እንደገና ደግሞ የምርጫ 1997 ሽንፈቱን ተከትሎ፣ ወደ አዲስ አበባ መለሳቸው። በዚህ ጊዜ በ1997 ክረምትና በ1998 መባቻ ላይ፣ በርካታ ስብሰባዎች በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች ተካሂደው ነበር።

በአዳማ ከተማ በተደረገ አንድ ስብሰባ ላይ ተሰብሳቢዎች ስብሰባውን ለሚመራው ከፍተኛ የኦሕዴድና የፌዴራል ባለሥልጣን “…እናንተ ኦሕዴዶች የራሳችሁ የሆነ አስተሳሰብና አቋም የላችሁም፣ ውጡ ስትባሉ ትወጣላችሁ፤ ተመለሱ ስትባሉ ትመለሳላችሁ… የአሁኑ ውሳኔ ለአሮሞ ሕዝብ ታስቦ ሳይሆን ኦሮሞውን ከሌላው ወገኑ ጋር ለማጋጨትና የሕወሐትን ውጥረት ለማርገብ ሲባል የተወሰነ ነው….” በማለት የኦሕዴድን አሻንጉሊት መሆን ተቃወሙ። በዚህ ጊዜ የኦሕዴዱ ባለሥልጣን “… ሁሉንም ነገር የወሰንነው እኛ (ኦሕዴዶች) ነን… ከፈለግን ኦሮሚያንም መገንጠል እንችላለን …” ሲሉ አንባርቀው ነበር። መለስ ዜናዊ ኦሕዴድን በጅምላ የዘረጠጡት ይህን መሰሉን የኦሕዴዳውያን ችኩል መንፈስ ታሳቢ አድርገው ነው። ቢያንስ የያኔው ኦነግ ዓላማ ግልጽ ነበረና።

ኦሕአዴድም ሆነ ሌሎች የኢሕአዴግ አባል እና አጋር የሚባሉ ድርጅቶች ሕወሐትን ለማገልገል የተፈጠሩና ለሕወሐት ጥቅም ሲባል የቆሙ ናቸውና እንደ አብቹ፣ እንደ በላይ ዘለቀ፣ እንደ ዘርዓይ ደረስ፣ እንደ አላሉላ አባ ነጋ፣ እንደ ዑመር ሰመተርና እንደ ሌሎቹ ከየብሔረሰቡና በአራቱም ማዕዘናት እየተነሱ ለውድ አገራቸው ጠበቃ እንደሆኑት፣ ለኢትዮጵያውያን ‘ኢትዮጵያ ወይም ሞት!’ ብለው መቆም አይጠበቅባቸውም።

ነገር ግን ሕወሐት ኢትዮጵያን ለመዝረፍ፣ የራሱን ክልል ለማበልጸግና ኢትዮጵያን አፈራርሶ ታላቅ አገሩን (የትግራይ ሪፐብሊክን) ለመገንባት ደረጃውን ጠብቆ እርምጃ ሲወስድ፣ እነዚህ ሕወሐት ሠራሽ ድርጅቶችም ያንኑ እርምጃ ጠብቀው መጓዝ ይጠበቅባቸዋል። እናም ኦሕአዴድ ሕወሐት ኦሮምያን እየዘረፈ ሃብት በሚያከማችበት ጊዜ፣ ኦሮሚያን የመገልንጠል ሩጫ ስላበዛ አቶ መለስ የኦነግ ባህሪውን ቀነስ እንዲያደርገው በግልጽ ተናገሩ።

ሲፍቁት ኦነግ የሚሆነው ኦሕዴድ በ1983 እና ከዚያ በኋላ ተወልደው አሁን ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሆኑትን የኦሮሚያ ወጣቶች፣ በአንድ በኩል ሕወሐትን አስደስታለሁ ብሎ በሌላ በኩል ደግሞ ከኦነግ ጋር በጸረ-ኢትዮጵያዊነት ውድድር ገጥሞ፣ እንዴት አድርጎ እንደቀረጻቸው አሁን በአደባባይ የሚታየው ነገር ሁሉ ምስክር ነው። ከቀበሌ ስብሰባዎች ጀምሮ እስከ አደባባይ ሰልፎች፣ ከመዋዕለ ሕጸናት ጀምሮ እስከ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምን ዓይነት ታሪክ እየነገረ (እያስተማረ) እንዳሳደጋቸው የታወቀ ጉዳይ ነው።

በ1983 ዕድሜያቸው እስከ 12 እና 13 ዓመት የነበሩ ልጆች ብዙ ሳያውቁና ሳይረዱ ነው የሕወሐት/ኢሕአዴግ ዘመን የመጣባቸው። እነዚያ ልጆች አሁን 39 እና የ40 ዓመት ወጣቶችና ጎልማሶች ናቸው። እነርሱም ዕውቀት የሚገበዩበትን፣ ብስለትን የሚጎናጸፉበትን ጊዜ ያሳለፉት ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት መጥፎ መጥፎው በሚሰበክበት በዘመነ ሕወሐት/ኢሐአዴግ ነው። እነዚህ ወጣቶችና ጎልማሶች የኢትዮጵያን ባንዲራ ሲጸየፉ፣ የኢትዮጵያን ነገሥታትና ጀግኖች ሲያንቋሽሹ፣ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ጠላታቸው አድርገው ለማሳደድና ለመግደል ሲነሳሱ፣ ዩንቨርሲቲ ተማሪ ሆነው በዘርና በሐይማኖት ከእነሱ የተለየውን (ምን ያልበደላቸውን) ጓደኛቸውን ለመግደል ቀን ከሌት ሲያደቡ፣ ከእነሱ የተለየ ቋንቋ ተናጋሪውን ከክልሌ/ከከተማየ ውጣ ማለትን ባህል ሲደርጉ፣ ስለ ወረዳና አውራጃ ድንበር ውዝግብ ሲፈጥሩ፣ ለክልል ድንበር ብለው ለግብግበ ሲዘጋጁ ወዘተ… ብዙም ያልተቆጡት፣ ጋብቻን በብሔር ለመከለል በተነሳሳችው ልጅ ላይ ብቻ ሳይሆን በዚያ ስብሰባ ላይ በነበሩ ሌሎች ሰዎች ላይ ዘመቻ መክፈቱን ለምን ፈለጉት?

አዎ! ወጣቶቻችን ክፉ ክፉው ተነግሯቸው ነው ለዚህ የበቁት። የሕወሐት/ኢሕአዴግ መርዘኛ ትምህርቶችን ማስወገድ ብዙ ሥራ የሚጠይቁ፣ ብዙ ጊዜ የሚፈጁ፣ ከፍተኛ ትዕግስትና ማስተዋል የሞላበት ጥረት የሚሹ ናቸው።

ለዚህ ነበር አቶ ለማ መገርሳ ወጣቶችን አሳስተናቸዋል፣ እውነተኛ ታሪካቸውን እንዳያውቁ አድርገናል፣ ለግጭት የሚያነሳሳና ለሕወሐት ዕድሜ መራዘሚያ የሚጠቅም ሥነ ልቦና ቀርጸን አሳድገናቸዋል ብለው ለመናገር የደፈሩት። እናም አቶ ለማ የኦሮም ወጣት ኢትዮጵያ አባቶቹና አያቶቹ ያቆዩለት አገሩ መሆኗን፣ ለብዙ ዓመታት የኦሮሞ ልጆች ለኢትዮጵያ የተዋደቁትና የተሰውት በቅጥረኛት ተሰልፈው ሳይሆን ምትክ የሌላት አገራቸው ስለሆነች ነው ብለው ማስተማር ጀምረው የነበሩት። ለዚህ ነው በሕወሐት/ኢሕአዴግ ዘመን የተፈጠረውን ቁርሾ ለማስወገድ ባህር-ዳር ድረስ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ሕዝብ ተወካዮችን ይዘው ባሕር-ዳር ድረስ ተጉዘው ልብ የሚነካ ሥራ ያካሄዱት።

አሁን ግን አቶ ለማ ‘የሉም’፣ የኦሕዴዶች የ27 ዓመታት ስህተቶችን እየነቀሰ ጥፋቶችን አምኖ፣ የኦሮምያ ወጣቶችን ሳይታክት በማስተማር ወደ ኢትዮጵያዊነታቸው ለመመለስ በርትቶ የሚሠራ ሰው የታጣ ይመስላል። የቀድሞ ኦሕዴዳውያን የአሁን የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ አባላት በቀድሞው ትምህርታቸው አንዳች ጥቅም ለማግኘት የፈለጉ ይመስላሉ። በሕወሐት ዘመን ሲማሩትና ሲያስተምሩበት የቆዩትን አናቋሪ ታሪክ እንደ ቀልድ ሲያወሱት ይሰማሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በባሌ የመስኖ ግድብ ሲመርቁ፣ ሽመልስ አብዲሳ በአዲስ አበባ ኢሬቻ ሲከበር ‘አንገትህን ያስደፉህን አሸንፈህ….’ እያሉ ሕዝብ ወደ ድሮው ቁዘማ እንዲመለስ እየነገሩት ነው። ኦሮሞ ብቻውን አንገቱን አልደፋም፣ ኦሮሞ እንደ ሌሎች ሕዝቦች በገዥዎች ተረግጦና ተገፍቶ ኖሯል። ከግንቦት 1983 እስከ 2010 አጋማሽ ለነበረው አንገት ማስደፋት፣ ረገጣ፣ ግድያና ወደ ዘብጥያ መወርወር ደግሞ የኦሕዴዳውያን ድርሻ በጣም ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ሽመልስ አብዲሳ፣ በዚህ ድርጅት ውስጥ በነበሩባቸው ዓመታት ለተፈጠረው ግፍ ተባባሪም ተጠያቂም ናቸው። አማራውንም ሆነ ትግሬውን እንደ ሕዝብ የመወንጀል ሞራል የላቸውም።
ግዛቸው አበበ / gizachewabe@gmail.com

ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com