‹‹የእርሻ መሬት ሊስፋፋ የሚችልበት ቦታ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም››

Views: 176

ትውልዳቸው ናዝሬት ከተማ ነው፤ የ80 ዓመቱ አዛውንት ደሳለኝ ራኽመቶ። ከመሬት ጋር በተገናኙ ጉዳዩች ሐሳብና አስተያየት እንዲሰጡ ቀድመው ሊጠሩ ከሚችሉና በጉዳዩም የበሰለ እውቀትና መረጃ ካላቸው ሰዎች መካከል ናቸው። አብዛኛውን እድሜያቸውን ለጉዳዩ ሰጥተው የተለያዩና ሰፋፊ ጥናቶችን በግብርናው ዘርፍ አካሂደዋልና የመሬት ጉዳይ ከእግር እስከ ራሱ አጣርተው የሚያውቁት ሆኗል። በዚሁ ዙሪያ የሠሯቸው ጥናቶቻቸውም በአገር እንዲሁም በዓለም ዐቀፍ የጥናት መጽሔቶች ታትመው ለንባብ በቅተዋል።

የፖሊሲ ቀራጮችን፣ የተማሪዎችና የተለያዩ ባለድርሻዎችን ዐይን የገለጡ የመጽሐፍ ሥራዎችንም አቅርበዋል። ከዚህ መካከልም ‹‹Land grabbing in Ethiopia›› የተሰኘው መጽሐፋቸው ተጠቃሽ ነው።

ደሳለኝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለበርካታ ዓመታት በመምህርነት ያገለገሉ ሲሆን፣ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎ፣ ራሱን የቻለ የጥናት ተቋም መሥርተዋል። ከ23 ዓመት በፊት የተቋቋመው የማኅበራዊ ጥናት ፎረም እንደ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ እና ገብሩ ታረቀ ያሉ ምሁራንን ጨምሮ በድምሩ ስምንት መሥራቾች መካከል አንዱ የሆኑት ደሳለኝ፣ በኃላፊነትም ተቋሙን መርተዋል። በኋላም የመጽሐፍት አርትዖት ሥራ በመሥራትና ጥናቶችን በማካሄድ፣ የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችንም ለመንግሥት በማቅረብ ተጠምደው አገራቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ።
የመሬት ፖሊሲ ባለመሻሻሉ ምክንያት መሬት አልባነት፣ ሥራ አጥነት እና ዝቅተኛ የግብርና ምርት በጣም አስቸጋሪ ደረጃ ላይ ደርሷል ሲሉ ይሞግታሉ። ለችግሩም ዘላቂ መፍትሔ ነው የሚሉት የአገር ውስጥ አርሶ አደር ገበሬን ማገዝና ማበረታታትን ነው። ከመሬት ባለቤትነት በላይም ለገበሬው የመሬት ይዞታ ዋስትና ወሳኝ ነው ይላሉ።

የአዲስ ማለዳው አሻናፊ እንዳለ በኢትዮጵያ ያለውን የመሬት ይዞታ ስርዓትና ያንንም ተከትሎ ያለውን መሬት አልባነት በሚመለከት ከደሳለኝ ራኽመቶ ጋር ተከታዩን ቆየታ አድርጓል።

አሁን በኢትዮጵያ ያለውን የመሬት ይዞታ እንዴት ያዩታል?
የኢትዮጵያ መሬት ፖሊሲ ባለፉት 60 ዓመታት በብዙ ለውጦች ውስጥ አልፏል። አሁን ያለው የመሬት ይዞታ እና አመራር ፖሊሲ በ2005 የወጣውን የፌዴራል የመሬት ይዞታ እና አስተዳደር አዋጅ ተከትሎ በ1990 የወጣ ነው።የክልል መንግሥታትም የየራሳቸውን የመሬት ፖሊሲ በማውጣትና ከፌዴራሉ ጋር የተሰናኘ በማድረግ የየራሳቸውን የመሬት ሕግ አውጥተዋል።
አሁን ግን ይህ የመሬት ፖሊሲ መሬት አልባነት ሊፈታ ባለመቻሉ ወሳኝ ነጥብ ላይ ነው ያለው። የከፋው ደግሞ አሁን ላይ ምንም ዓይነት እርምጃ ሲወሰድ አለማየታችን ነው። አሁን ግን በተባራሪ እንደሰማሁት ከሆነ፣ የመሬት ይዞታና አስተዳደር ስርዓትን በሚመለከት አሠራሩን ዘመናዊ ለማድረግ አዲስ ሐሳብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል።

ብዙዎች አሁን ያለውን የመሬት አልባነት ችግር ለመፍታት የግል የመሬት ይዞታ መፈቀድ አለበት የሚል ሙግት አላቸው። እርስዎስ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
መሬት የግል ይሁን አይሁን የሚለው አይደለም ችግሩ። የመሬት ዋስታና ላይ ያጠነጠነ ነው። የመሬት ዋስትና በግልም አልያም በመንግሥት ይዞታ ስርዓት ወይም በሌላ ሊሆን ይችላል፤ ዋናው እሱ አይደለም ዋናው የመሬት መጠቀም ዋስትና ነው። እና ሙሉ ዋስትና ማግኘት ከተቻለ የእገሌ ይሁን የሚለው የሚወዛግበን አይደለም።
ማተኮር ያለብን የመሬት ዋስትና ላይ ነው። ችግር በአጭሩ ሊስተካከል የሚችል አይደለም፤ የተወሳሰበ ነው። ምን ላይ እናተኩር የሚለው ቢነሳ የመሬት ዋስትና እንዲዳብር ለማድረግ መንቀሳቀስ ትልቁ መንገድ መሆን አለበት ነው የምለው።

አሁን የግል የመሬት ይዞታ ስርዓትን ማስተዋወቅ ከባድ ሥራ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም ላለፉት ኹለት ዐስርት ዓመታት የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ የብሔር ፖለቲካ አንዱ አካል ሆኗል። አሁን የመሬት ባለቤትነት ከማንነት እና ብሔር ፖለቲካ ጋር በኃይል ተሳስሯል። ከባለሙያዎች በላይ ምሁራን እና አክቲቪስቶች ናቸው ተሰሚነት ያላቸው።ለዛም ነው መንግሥት ጉዳዩን ለመንካት የፈራው።
ለንባብ ባበቁት መጽሐፍዎ፣ መሬት አልባነት በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ ለሚሰደዱና መዳረሻቸውን ደቡብ አፍሪካ ላደረጉ ወጣቶቸ ይልቁንም ከደቡብ ክልል ለሚነሱት ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የመሬት አልባነት ዋና መንስኤዎች ምንድን ናቸው?
የመሬት ጥበት በጣም እየከፋ እየመጣ ነው። ዋናው ወይም አንደኛው ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ያለው የሕዝብ ቁጥር ነው። ኹለተኛ የሕዝብ ብዛት ጨምሮ የሚታረሰው መሬት መጠን ከዛ ጋር በተጣጣመ መንገድ እያደገ አይደለም፤ ጥቂት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታረሰው መሬት መጠንና የሕዝቡ መጠን ሲታይ፣ በጣም ብዙ ታሪክ የሚናገር ነው።
አራሹ ሕዝብ ሰፍሮ ያለው በአገሪቱ ከጠቅላላው መሬት ከ20 እስከ 25 በመቶ በሚሆነው መሬት ላይ ነው። ሌላው ወይ በአርብቶ አደሮች ነው ወይም ድርቅ የሚያጠቃው ነው፤ አልያም ተራራና ወንዙ ያለበት ነው። ስለዚህ የሕዝብ ብዛት እያደገ ሲሄድ የመሬት ጥበትን እየፈጠረ ይሄዳል።

ሌላው የመሬት መበጣጠስ አለ። ለዚህ ብዙ ምክንያት ቢኖርም አንዱ የውርስ ጉዳይ ነው። አንድ ቤተሰብ አባት ወይ እናት ሲሞቱ መሬቱ ለልጆች ሁሉ ነው የሚከፋፈለው፣ አራትና አምስት ልጅ ካሉም ለሁሉም ይካፈላል። ይዘቱ ትንሽ ስለሆነ ያ ለሦስትና ለአራት ሲከፋል ጭረሽ በጣም ይበጣጠሳል። እና ይህ በምግብ ዋስትና ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ አለ።

ሦስተኛ በግሉ እንዲሁም በመንግሥት በኩል ያለውና እየጨመረ የመጣው የመሬት ፍላጎት በሚታረስ መሬት ላይ ጫና እያሳደረ ይገኛል። ይህም ያለውን የመሬት አልባነት ችግር ጭራሽ ያብሰዋል።
በመንግሥት በኩል ያለውን ስናይ ለመሠረተ ልማት ማለትም ለመንገድ፣ ድልድይ፣ ግድብና አየር መንገድ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶች ቀላል የማይባል መሬት ይወስዳል። እነዚህ ጠቃሚ መሆናቸው ይታወቃል። ነገር ግን ለም የሆነውና ሊታረስ የሚችለውን መሬት መውሰድ የለባቸውም።

በኢንዱስትሪ ደረጃም ፋብሪካዎች፣ ኢንደስትሪያል ፓርኮች በተለይ የውጪ ኢንቨስተሮች በየቦታው አሉ። እነርሱም ቀላል የማይባል መሬት ነው የሚወስዱት። ለምሳሌ በደብረ ብርሃን እና ቢሾፍቱ የእርሻ መሬቶች ፋብሪካዎች እየተገነቡባቸው ነው። ለዛም እንግዲህ የገበሬውን መሬት ነው የሚወስዱት። መጀመሪያም የተጣበበውን የመሬት ሁኔታ ይህ ደግሞ ይበልጥ እንዲጣበብ ያደርገዋል።
በተጨማሪ ሰፋፊ የእርሻ ሥራዎችም መሬት እየወሰዱ ነው። እርግጥ እነዚህ የሚያፈናቅሉ አይደሉም፣ ሆኖም የገበሬውን መሬት እየተሻሙ ነው። ገበሬው የእርሻ መሬት ብቻ አይደለም፣ ግጦሽ መሬትም ይፈልጋል፣ ማቋረጫ መንገድ፣ ውሃና ደን የመሳሰሉትን ይፈልጋል። በመጨረሻ የከተሞች መስፋፋት ነው። ከተሞች እንዲስፋፉ መንግሥት ባወጣው ፖሊሲ መሠረት የግብርና መሬትን ነው ወደ ከተማ የሚቀይሩት።

በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች፣ የእርሻ መሬቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሱ ነው፣ የመሬት ጥበቱም እየናረ ነው። ስለዚህ ገበሬው በተበጣጠሰና በጠባብ መሬት መካከል ሆኖ ነው ምግብ የሚያመርተው። ይህ ለምግብ ማምረት ትልቅ ተግዳሮትና እንቅፋት ነው።

አሁን የሕዝብ ብዛት ጨመረ ስንል፣ ልጆች ለሥራ እድሜያቸው ሲደርስ መሬት ይሰጠን ይላሉ። ነገር ግን የሚሰጥ መሬት የለም። አልፎ አልፎ አንዳንድ ቦታ ተዳፋት የሆነው አካባቢ ይሰጣቸዋል፤ እሱ ግን ጥቅም የለውም። አልፎ አልፎም ለደን ተብሎ የተከለለ ቦታን አልያም የግጦሽ መሬት ይሰጧቸዋል፤ አሁን ብዙ አካባቢ የግጦሽ መሬት የለም።
ይህ ግን ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን አይችልም። በዚህም ምክንያት ደግሞ ባለፉት ዐስርት ዓመታት የደን እና ግጦሽ መሬቶች በከፍተኛ ደረጃ ቀንሰዋል።
ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት አሁን ያለሥራ እንዲሁም ያለገቢ ሥራ ፈትቶ ተቀምጧል። ኑሮውን ለመለወጥ፣ ጥሩ ሕይወት እንዲኖረው የሚፈልገውና ገንዘብ ማግኘት የሚፈልግ ይህ ወጣት፣ በዚህ መልክ መገኘቱ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ለሚሠሩት እንደ ጥሩ አጋጣሚ የሚቆጠር ነው። አንዳንዱ ይሳካለታል ግን ከስንት አንድ ነው።

ወጣቱ ለመሰደድ አልያም እየሞከረ ለመሞት ፈቃደኛ ነው። ከድህነት ሞት ነው የመረጡት። እንደ ማሳያ እንደውም አሁን በጦርነት ጠርዝ ላይ በሆነችው የመን ሦስት ሺሕ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በእስር ቤቶች ተገኝተዋል። ብዙዎች በስደት ስቃይ ይገጥማቸዋል፣ እስር ቤት ይገባሉ፣ ታፍሰውም ወደ አገር ቤት ይመለሳሉ።

ከሰሜን ኢትዮጵያ በርካታ ወጣቶች ቀይ ባህርን እንዲሁም ሜድትራንያንን ሲያቋርጡ፣ በደቡብ ኢትዮጵያም በዛው ልክ ወጣቶች ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚፈልሱ ናቸው። ቁጥራቸውን መንግሥትም ሆነ ማንም ይህን ያህል ባይልም በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ናቸው።

በ1990 እና በ2010 መካከል፣ የኢትዮጵያ የሚታረስ መሬት በ3.8 ሚሊዮን ሔክታር እድገት አሳይቶ ነበር። ከዛ በኋላ ግን ይህ ነው የሚባል ለውጥ አልታየም። በደጋማ አካባቢዎች የግብርና መሬትን ማስፋፋት ከዚህ በኋላ አይቻልም ብለው ያስባሉ?
ላለፉት ኹለት ዐስርት ዓመታት የእርሻ መሬት መስፋፋት ይታይ የነበረው፣ በተለይ በአገሪቱ ያለውን ትንንሽ ደን በመመንጠር የተካሄደ ነው። ግን ያም በራሱ አሁን የመጨረሻው ደረጃ ላይ ደርሷል። በከፍተኛ ቦታዎች ላይ ለእርሻ የሚሆንና ሊስፋፋበት የሚችል ቦታ ከዚህ በኋላ አይኖርም። የተረፈችውን ደን በማጥፋት እንጂ ከዚህ በላይ ለመስፋት አመቺ ሁኔታም የለም።

ስለዚህ ለኢትዮጵያ ያለው አማራጭ ምንድን ነው? ምን አልባት ቆላማ ቦታዎች ላይ የእርሻ መሬቶችን መፈለግ አማራጭ ይሆን ይሆን?
እርሻን ወደ ቆላማ አካባቢዎች ማስፋፋት ቀላል ሥራ አይደለም። ቆላማ ቦታዎች በተለያዩ አርብቶ አደር ማኅበረሰብ የሚገኝባቸው ናቸው። እነዛን አርብቶ አደሮች ገፍቶ ቦታውን ማረስ አስቸጋሪ ነው። በሌላ በኩል ቆላማ ቦታዎችን ለእርሻ እንዲሆኑ አድርጎ ለማልማት፣ ተለቅ ያለ ሀብት እና አቅም ይፈልጋል። የውሃ እንዲሁም በዘመናዊ መሣሪያ የታገዘ እርሻም ያስፈልጋል፣ ሕዝብን ለማስፈር ከፍተኛ ውጪ ይጠይቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ሐሳብ አቅርበዋል። ይሁንን ተከትሎ አሁን ባለው አስተዳደር ቆላማ ቦታዎችን በመጠቀም ለማረስና እንደ ስንዴ ያሉ ምርቶችን ለማምረት የሚደረጉ ጥረቶች ይታያሉ። የት ቦታ? በምን ሁኔታ? ምን ተደርጎ? የሚለው ላይ ዝርዝር ነገር አልተነሳም፣ ገና ለውይይትም አልቀረበም።

መንግሥት ደጋማ በሆኑ አካባቢዎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ይመስላል። ይህ አካሄድ ያዋጣል?
የኢትዮጵያ የግብርና ፖለሲ ከዘመነ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጀምሮ ብንመለከት፣ ዋና ዓላማ ተብሎ የተያዘው የግብርናውን ዘርፍ ስለማዘመን ነው። ያኔ እንደውም ቀስ በቀስ በትላልቅ እርሻዎች ዘመናዊ መሣሪያዎችን በመጠቀም ዘመናዊ የእርሻ ሁኔታ እንፈጥራለን የሚል ነው። ለባለሀብት በመስጠት አንዱ ነው። ለምሳሌ አዋሽ አካባቢ ግዙፍ የእርሻ ልማት እንዲንቀሳቀስ ማድረግ የተጀመረው በዚያ አጋጣሚ ነው።

ከዛ ደርግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ መሠረታዊ የመሬት ለውጦችን አደረገ። ለገበሬዎች መሬቱን ሰጠ። ከኹለት ሦስተኛ በላይ መሬት በመንግሥት ይዞታ ስር ከመሆኑ በላይ ለገበሬዎች ተከፋፈለ። ክፍፍሉም ለአንድ አባወራ ከግማሽ እስከ ኹለት ሔክታር የደረሰ ነበር። ከዚህ በኋላ ግን ገበሬው ኃላቀር ስለሆነና ወደ ዘመናዊነት ለማምራት ሰፊ የሆነ እርሻ እና ዘመናዊ መሣሪያ ነው የሚያስፈልገው ብሎ ወደ የግብርና ኅብረት ወስዶታል፤ ደርግ። ይህም ገበሬዎቹን አንድ ላይ በማሰባሰብ አንድ ላይ እንዲያርሱ ማድረግ ነው። ከዛ የመንግሥት እርሻ ተብሎ ሰፋፊ እርሻ መጣ፤ ይህም አልሠራም።
ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ፣ ሰፋፊ እርሻ ማስፋፋት አለብን ብሎ ለባለሀብት ሰፋፊ መሬት ይሰጣል። ብዙዎቹም ከስመዋል። ከውጪ የመጡት ኢንቨስተሮች፣ ዘመናዊ እርሻ ከማድረግ ይልቅ፣ ከገበሬው እየተማሩ ነበር። አንዳንዶቹ ስለ ግብርና የማያውቁ የውጪ ኢንቨስተሮች ቦታውና አካባቢውን ስለማያውቁ ብዙ አጥፍተው አገር ጥለው ሄዱ። መንግሥትም ይህን ገምግሞ ወድቅ ናቸው፣ ውጤታማ አልሆኑም ብሎ ራሱን ወቅሶ ሪፖርት አውጥቷል።

የእርስዎ ምክረ ሐሳብ ምንድን ነው?
እስከ አሁን ድረስ በእኔ ግምት፣ ባቀረብኩትም ሐሳብ ሙሉ ለሙሉ ሰፊ እርሻዎቸን እናጥፋ ባንልም ትልቅ ትኩረት ማድረግ ያለብን አነስተኛ ገበሬው ላይ ነው። ገበሬውን ዘመናዊ እናድርገው። ሌሎች ኢንቨስተሮች ዘመናዊ እርሻ ይዘው ይምጡ ከማለት፣ ገበሬውን ማዘመን።

እኔ የምለው ኢትዮጵያ ትኩረቷን በእነዚህ ገበሬዎች ላይ ማድረግ አለባት ነው። ይህም የንግድ የሚሆነውን ሳንዘነጋ ነው። አዳዲስ ገበሬዎች በአዲስና ዘመናዊ አሠራር እንዲመጡ ከመጠበቅ ይልቅ ያለውን በአነስታ ደረጃ እያረሰ ያለ አርሶ አደር ዘመናዊ ማድረግ ይሻላል።ከ ውጪ ለሚመጡ የንግድ ገበሬዎች የሚሰጠው ድጋፍና ማበረታቻ ለአገር ውስጥ ገበሬ የሚሰጥ ቢሆን ኖሮ፣ የግብርና ዘርፉ እስከ አሁን ይዘምን ነበር።

መንግሥት ይህን ምክረ ሐሳብ ከግምት ውስጥ ያስገባል ወይም አያስገባም የሚለውን አላውቅም፣ ግን ለመንግሥት አቅርቤአለሁ። አንዳንዶች ይህን አጨቃጫቂ ነው ይላሉ፣ ያልተቀበሉትም አሉ። በበኩሌ ግን ምክንያታቸው አይታየኝም።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አርሶ አደሮች ከግማሽ ሔክታር በታች መሬት ነው ያላቸው። እንዲህ መጡኑ እያነሰ በሚሄድበት ቦታና መሬት ተከፋፍሎ ባለበት ሁኔታ፣ እንዴት በአነስተኛ ደረጃ የሚያመርቱ አርሶአደሮችን እንዴት ነው ሊደገፉ የሚገባው?
የመሬት ፖሊሲው ቢሻሻል፣ ምቹና ተለዋዋጭ ፖሊሲ ከሆነ እንዲሁም ገበሬው እንደ ልቡ እንዲንቀሳቀስ ቢደረግ ከመሬት አልባነት የሚወጣበትን መንገድ ራሱ ገበሬው ያገኛል። ገበሬዎች እርስ በእርሳቸው እንዲሁም ስለመሬት አጠቃቀምና ስለ ግብርና በደንብ ያውቃሉ። ስለዚህ መፍትሔ ማምጣት ይችላሉ። የሰፋፊ እርሻ መሬቶች ኪራይ እገዳ ሲነሳም ለመሬት አልባነት ችግር ጥሩ መፍትሔ ይሆናል።

በዚህ ላይ የተደረገ ጥናት ባላይም፣ አንድ አካባቢ ያሉ ኩታ ገጠም ገበሬዎች አንድ ላይ መሬታቸውን አድርው ትራክተር ተከራይተው ያሳርሳሉ። አዋጭ ሆኖ አግኝተውታል። የፈጠራ አቅማቸውን የሚያዳብር ፖለሲ ቢቀረጽ ውጤታማ መሆን ይቻላል ነው። በዚህ መንገድ ዘመናዊነትን እንዲያመጡ ማድረግም ይቻላል።

ትልቁ ችግር ግን ግብርናም እንዳይዘም የሚያደርገው፣ ገበሬው ከባንክ የገንዘብ ብድር አገልግሎት የሚያገኝበት መንገድ አለመኖሩ ነው። የኢትዮጵያ ገበሬዎች ብድር የማግኘት ምንም ዓይነት እድል የላቸውም። ሆኖም ለምሳሌ አንዳንድ ክልሎች ላይ እንዳየሁት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በእርሻ መሬት በያዘው ሀብት የብድር አገልግሎት መሰጠት ተጀምሯል። ይህም ግብርናን በማዘመን በኩል ለገበሬዎች ቴክኖሎጂውን ለማቅረብ ያገለግላል።

በእርግጥ ብድር የሚሰጡ ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት አሉ። እነርሱ ግን ትንንሽ ናቸው። አቅም የላቸውም። ለዚህ ለማናውቀው ኢንቨስተርኮ፣ ራሱ በተናገረው ቃሉን በማመን ብቻ፣ አለኝ ያለው ሁሉ ይኑረው አይኑረው ሳይጣራ ነው በገፍ ብድር የሚያገኘው። ከመንግሥት ጋር ግንኙነት የነበራቸው ኢትዮጵያውያን ባለሀብት ነን ብለው ብድር ያገኛሉ። ግን ለሌላ ጉዳይ ነው የሚያውሉት። የኢትዮጵያ ልማት ባንክም በዚህ ያልተከፈለ ብድር ምክንያት ሊወድቅ ደርሶ ነበር።

ከዚህ ይልቅ ለገበሬው ይህ እድል ቢሰጠው። ለባለሀብቶች የታክስ፣ የካፒታል እቃዎችን ለማምጣት ያለ ቀረጥ የማስገባትና መሰል የተለያዩ ጥቅማ ጥቅምና መብት አላቸው። ለገበሬው ግን ምንም መብት የለውም። እነዚህ የተዛቡ ጉዳዮችን አስተካክሎ ቢያንስ እንዲህ ዓይነቱን ለባለሀብት የተሰጠ ጥቅም ለገሬውም ሊሰጠው ይገባል።

በእኔ ግምት ለገበሬው የተሻለ ጥቅምና ማበረታቻ ተሰጥቶ ዘመናዊ እንዲሆን ቢደረግ አዋጭ ነው ባይ ነኝ። እንዲህ ከሆነ ሰፋፊ እርሻም ላያስፈልግ ይችላል። አልፎ አልፎ ዘመናዊ አሠራር የሚጠይቅ ከሆነ የውጪ ባለሀብት መጠቀም አለንን። በእኔ አመለካከት ግን በራሳችን ገበሬ ላይ ነው መተማን ያለብን።

በኢትዮጵያ አሁን ላይ ሥራ አጥነት እንዲሁም መሬት አልባነት በጣም የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው። ኹለቱ የሚገናኙበት መንገድ ይኖር ይሆን?
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ግብርና ለብዙ ሕዝብ መተዳደሪያ በሆነበት አገር፣ ሥራ አጥነት ከመሬት አልባነት ጋር በቀጥታ ይገናኛል። ምንም እንኳ መንግሥት ያደረገው ጠቅላላ የዳሰሳ ጥናት የተደረገ አይመስለኝም፣ አንዳንድ አካባቢዎች የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ግን መሬት አልባነት በኢትዮጵያ በጣም በፍጥነት እየጨመረ ነው። ባሉት ውስን ጥናቶች መሠረትም፣ በክልሎች የሚገኘው ወጣት መሬት አልባ ነው። ይህም ከ20 እስከ 40 በመቶ ይጠጋል።

ወጣቶች መሬት አልባ ሲሆኑ፣ ወደ ከተማ ነው የሚፈልሱት። በየሁኔታው ለተለያየ ሥራ ወደ ከተማ ይገባሉ፤ እነዚህ ልጆች ከገጠር መሬት አለባ እና ሥራ አጥ ሆነው ወደ ከተማ የመጡ ናቸው። ችግሩም በጣም የከፋ ነው።

ይህን ችግር ለመቅረፍ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ያስፈልጋታል?
በመጀመሪያ ደረጃ በጣም ወሳኝ ቢሆንም፣ እስከ አሁን ኢትዮጵያ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ የላትም ወይም በኢትዮጵያ የመሬት ፖሊሲ አልወጣም። ትልቅ ፖሊሲ መውጣት ያለበት የመሬት አጠቃቀም ላይ ነው፤ መሬት መለየትም አለበት። ለደን የሚሆነው፣ እንክበረካቤ የሚፈልገው፣ ለውሃ የሚሆን፣ ለከተማ ማስፋፊያ ወይም ለኢንዱስትሪ ወዘተ ተብሉ በጥናት መሠረት እንዲለይ ፖሊሲ መሠራት አለበት። አሁን ግን በዛ መልክ በደንብ አልለየንም። ይህ ጥናትን መሠረት አድርጎ በፍጥነት መሠራት ያለበት ነው።

እንደሰማሁት ከጀርመን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ዝግጅት እየተካሄደ ነው። ጉዳዩንም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፍት ቤት ነው የያዘው። ተነሳሽነቱም አሁን ባለው አመራር የተጀመረ ነው። ነገር ግን አሁን ያለበትን ደረጃ አላውቅም። ይህን ፖሊሲ ማዘጋጀት በጣም ውስብስብ ሥራ ነው የሚሆነው፣ ከተሠራም ጥቂት ጊዜ ሳይሆን ቢያንስ አምስት ዓመትም የሚፈልግ ነው።

በአፍሪካ በሚገኙ ሌሎችም አገራትም መሬት አልባነትን ጨምሮ የመሬት ፖለሲ አለመኖርና መሰል ችግሮች አሉ። ኢትዮጵያ ከማን ልምድ ልትወስድ ትችላለች?
የእኛና የሌሎች አፍሪካ አገራት ሁኔታ ይለያያል። ኬንያ ለምሳሌ በዚህ ምክንያት እንደ እኛ ወደ ውጪ የመፍለስ ነገር የለም። የመሬት ይዞታ ፖሊሲያቸውም ለየት ያለ ነው። ወደ ምዕራቡ አፍሪካ ስንሄድ፣ ውስብስብ ናቸው ሁኔታዎቹ። ችግሩን ለመፍታትም ብዙ ዓይነት መንገድ እየተፈለገ ነው። ግን ከዚህ እንማርበታለን የምለው ለሞዴል ሊጠቅም የሚችል የአፍሪካ አገር የለም። በአንዳንድ ነገሮች ለምሳሌ ለብድር ጉዳይ እያልን ካልዘረዘርን በቀር፣ ሞዴላችን ልለው የምችለው የለም።

ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com