የመንገድ የትራፊክ አደጋ – መቋጫውን ፍለጋ

Views: 142

የትራፊክ አደጋ የእለት ከእለት አስደንጋጭ ክስተት ከሆነ ሰነባብቷል – በኢትዮጵያ። ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ በትራፊክ አደጋ ከ5 ሺሕ 118 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። በዚህም ሳብያ በየቤቱ የቤተሰብ አባል የሆነ፣ እናት ወይም አባት፣ ሴት አልያም ወንድ ልጅ፣ እህት ወይም ወንድም፤ የልጅ ልጅ፣ አብሮ አደግ ወይም የክፍል ጓደኛ የአደጋው ሰለባ ሊገኝ ይችላል።

ዮናስ መላኩ (ሥሙ የተቀየረ) የእህቱን ልጅ በትራፊክ አደጋ ያጣበትን ክስተት እስከዛሬ አልረሳውም፤ መቼም እንደማይረሳውም እርግጠኛ ነው። ከአደጋው በኋላ እህቱ ያሳለፈችው ሕይወት፣ ቤተሰባቸው በጠቅላላ ያለፈበትን መከራ ማስታወስም ልብ የሚሰብርና የሚያሳዝን ነው።

የ32 ዓመቷ የዮናስ እህት ሰሎሜ መላኩ (ሥሟ የተቀየረ) እንዲሁም ቤተሰቧ የማይሽርና የማይዘነጋው ጠባሳ ያረፈባቸው ወርሃመስከርም ላይ 2011 ነበር። እንደ ቤተሰብ ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍም ሰሎሜ እና ቤተሰቦቿ ከአዲሰ አበባ 50 ኪሎሜትር ርቃ ወደምትገኘው ደብረዘይት ከተማ ያቀናሉ። እቅዳቸው በከተማዋ በሚገኘው ኩሪፍቱ ሪዞርት ለመዝናናት፣ ከተለመደው የኑሮ ሩጫ አረፍ ለማለት ነበር።

ሰሎሜ እንደ ወትሮውና እንደተለመደው መኪናውን ስታሽረክር፣ ባለቤትዋ ከጎና እንዲሁም የኹለት ዓመት ከመንፈቅ እድሜ ያለው ልጃቸው ደግሞ ከኋላ ይቀመጣሉ። ይህ ሁኔታና ጉዞ በመስከረም ወር መጨረሻ የሰሎሜና የቤተሰቦቿ የተለመደ ድርጊት ነው። ወደ ደብረዘይት የሚያደርሳቸውን መንገድም ቀድመው የመረጡ ሲሆን፣ ይህም በየረር ጎሮ በኩል ወደ ፈጣን የክፍያ መንገዶች በኩል የሚጀምር ነው።

መንገድ ተጀመረ፤ በሰሎሜ አሽከርካሪነት ቀሪዎቹ ቤተሰቦች ደግሞ የተለመደውን ጨዋታቸውን ተያይዘውታል። መንገዱ ክፍት መሆኑና ሰሎሜም ጠንካራ አሽከርካሪ በመሆኗ፣ ጉዞው ቀና መንገዱም የተረጋጋ ነበር። በእርግጥ ደግሞ ፈጣን የክፍያ መንገዱም ቢሆን አስተማማኝ እና ለብዙ ተሸከርካሪዎች አመቺ የሚባል ነው። ከባድ ተሽከርካሪዎች፣ የሕዝብ ማማላሻ አነስተኛ ባሶች፣ አገር አቋራጭ እንዲሁም አነስተኛ መኪናዎች በዚህ መንገድ በትንሹ በሰዓት 80 ኪሎ ሜትር እንዲጓዙ ያስችላቸዋል።

መኪናዋ የኮዬ ፈጬን አደባባይ እንዳለፈች፣ ሰሎሜ በእርጋታ ስትነዳ ከቆየችበት መስመር ወደሚቀጥለው ተሻገረች። ያቺ ቅጽበት ግን አጥፊና አስከፊ መዘዝ ይዛ መጣች። ያልታሰበ ነገር ተፈጠረ፤ አንድ ከመጠን ባለፈ ፍጥነት ሲበር የነበረ ከባድ ተሽከርካሪ የእነ ሰሎሜን መኪና ከኋላ ክፉኛ መታት። መኪናዋም ለክስተቱ ታዛዥ ሆኖ ከመኪና መስመር ውጪ ወጣች።

በዛች ቅጽበት የቤተሰቡ ሕይወት ፍጹም ሌላ መልክ ያዘ። የኹለት ዓመት ከመንፈቅ እድሜ ያለው ሕጻን ልጃቸውና ሞግዚቱ ወዲያው ሕይወታቸው አለፈ፤ ሰሎሜ እና ባለቤቷ ደግሞ በአደጋው ራሳቸውን ሳቱ። ይህ ኹነት ካለፈ ከሦስት ቀናት በኋላ ከመጠነኛ ጉዳት ጋር ነቁ።

‹‹የሰሎሜ እና ባለቤቷ የጤንነት ሁኔታ አስቸጋሪ አልነበርም›› የሚለው ዮናስ ‹‹በጣም አሳስቦንና አስጨንቆን፣ ግራ አጋብቶንም የነበረው ሕጻኑ ልጃቸው በአደጋው ሕይወቱ እንዳለፈ እንዴት እንደሚነገራቸው ነበር።›› በማለት የሚያስረዳው የሶሎሜ ወንድም እንዲህ ሲል ይቀጥላል፣
‹‹ሰሎሜ እና ባለቤቷ እንደነቁ የመጀመሪያ ጥያቄያቸው ልጃንስ የሚለው አስጨናቂው ጥያቄ ነበር። እኛም የተለየ ሕክምና ስለሚያስፈልገው የጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ነው አልናቸው። ነገር ግን እነሱ እኛን ሰምተው ቁጭ አላሉም። ይልቁንም በተደጋጋሚ ልጃችንን አሳዩን ነበር ጥያቄያቸው።››

ይህ ተደብቆ የሚቆይ ጉዳይ አልነበረምና፣ በመጨረሻም ከኹለት ቀናት በኋላ ዮናስ እና ሌሎች የቤተሰቡ አባላት ተሰባስበው ሊነግሯቸው ወሰኑ።
‹‹ሰሎሚ እና ባለቤቷ የልጃቸውን ሞት ሲሰሙ የነበረው ሁኔታ በጣም ከባድ እና ልብ የሚሰብር ነበር። የልጃቸውን መሞት መቀበል አቅቷቸው ባለቤቷ በጣም ልቡ ተሰብሮ በሀዘን ከመጎዳቱ በተጨማሪ፣ ድብታ ውስጥ ገብቶ ነበር። ከወር በኋላም ባለቤቷ ራሱን አጠፋ›› ሲል ዮናስ በተሰበረ ልቡ ስለተፈጠረው ሁኔታ በሃዘን ስሜት ውስጥ ይናገራል።

ከዚህ በኋላ የሰሎሜ የጤና ሁኔታ ተቀየረ። የአእምሮ ህመም ገጠማት። እስከ አሁን ድረስም ለ24 ሰዓት ወይም ሰባቱንም ቀን በቤተሰብ ክትትል ወስጥ መሆኗን ዮናስ ያስረዳል። ‹‹እኛ እሷን ለማዳን እና ጤንነቷም ላይ መሻሻል እንዲኖር በጣም ደክመናል፤ ብዙም አድርገናል። የሥነ አእምሮ እና ሥለ ልቦና ሕክምና እንድታገኝም ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ወስደናታል። ሆኖም ምንም ዓይነት ለውጥ አላየንባትም። በአሁን ወቅት በጸበል እና በጸሎት መንፋሳዊ ሕክምናዋን እየተከታተለች ሲሆን፣ በዚህም ትንሽም ቢሆን ለውጥ አይተንባታል።›› ሲል ዮናስ ተናግሯል።
እንዲህ ዓይነት መጨረሻውቸው እጅግ አሳዛኝ የሆኑ ታሪኮች ለኢትዮጵያ ጎዳናዎችና መንገዶች እንግዳ መሆን ትተዋል፣ ተለምደዋል።

ከትራፊክ አደጋ ሕይወታቸው የተረፈ ወይም የተጎጂ ቤተሰቦች እንደሚያነሱት ከሆነ፣ ደካማ እና የዘገየ የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት ምላሽ እንዲሁም በቂ ሆስፒታሎች እና ለረዥም ጊዜ ማገገሚያ ማእከላት ያለመኖራቸው ችግሩን የበለጠ አባብሰውታል።

ከመኪና አደጋ ሕይወታቸው የተረፈና በኑሮ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ተርታ የሚመደቡ ሰዎች እና ቤተሰቦች፣ በተከሰተው አደጋ ከሚደርስባቸው ሐዘን እና ድንጋጤ በተጓዳኝ፣ በኢኮኖሚም ሆነ በመንፈስ የሚደግፋቸው አለመኖሩ ስሜታቸውን ይጎዳዋል። ከሚደርስባቸው አካላዊ እና ሥነልቦናዊ ጉዳት በተጨማሪም፣ የዳኝነት ስርዓቱ አደጋ አድራሾችን በአግባቡ ተጠያቂ አያደርግም።
በኢትዮጵያ የትራፊክ አደጋ እንደ አገር የሚያሳስብ ጉዳይ ሆኗል። የዓለም የጤና ድርጅት ሪፖርት፣ በኢትዮጵያ የትራፊክ አደጋ በየዓመቱ እየጨመረ እንደሆነ ይገልጻል። ከላይ እንደተጠቀሰውም ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ብቻ በአደጋው ከ5 ሺሕ 118 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በአብዛኛው የሰዎች ሕይወት የጠፋው ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ሲሆን፣ በክልሉ በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፣ ጉዳትም ገጥሟቸዋል።

በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ ወደ አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ተሽከርካሪዎች መግባታቸው ተመዝግቧል። ይህም ማለት ዘጠኝ ተሽከርካሪዎች ለአንድ ሺሕ ሰዎች ያገለግላሉ ማለት ነው። በአዲስ አበባ ሦስት አራተኛ ተሽከርካሪዎች እንደመገኘታው፣ ከፍተኛ የመኪና አደጋ የሚከሰተውም በዚህችው በአዲስ አበባ ከተማ ነው።

የመኪና አደጋዎች በብዛት የሚከሰቱት ምሽቱ ገፋ ካለ በኋላ እንዲሁም በእረፍት ቀናት (ቅዳሜ እና እሁድ) ነው። የእነዚህ በመዲናይቱ አዲስ አበባ የሚደርሱ አደጋዎች ምክንያትም በአብዛኛው የግለሰቦች ስህተት ነው። የአሽከርካሪዎች የግል ባህሪ ለአደጋው የራሱ ድረሻ እንዳለውም ይታመናል።

ብዙ ጊዜ እንደሚሰማውም ለእግረኛ ቅድሚያ አለመስጠት በአሽከርካሪዎች የሚታይ ችግር ሲሆን፣ እግረኞችም የእግረኛ መንገድ አክብሮ አለመጓዝ እና ዜብራ ላይ አለመሻገር ለሚደርሰው አደጋ ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው።

ተመስገን በየነ በአዲስ አበባ ከተማ በሚከሰተው የትራፊክ አደጋ ዙሪያ ባደረጉት ጥናት፤ በትራፊክ አደጋ ለሚደርስ የሰዎች ሞት ለእግረኛ ቅድሚያ መከልከል 53 ነጥብ 8 በመቶ ድርሻ ሲኖረው፣ ያልተገባ ወይ ሞገደኛ የአሽከርካሪ ባህሪ ደግሞ 102 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ወስዷል።

ጥናቱ እንደማጠቃለያ ካስቀመጣቸው ሐሳቦች መካከል፣ የመኪና አደጋ ሰለባ ከሚሆኑት አብዛኛዎቹ ሰዎች እግረኞች ናቸው። አደጋው የሚደርስባቸውም ከዜብራ ውጪ አስፋልት በሚሻገሩ ጊዜ ሲሆን፣ ለንግድ ሥራ የሚንቀሳቀሱ ተሸከርካሪዎች ደግሞ በአደጋ አድራሽነት የተመዘገቡ ናቸው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ባወጣው መረጃ መሠረት፣ በፈረንጆቹ ከ2016/17 ጀምሮ የትራፊክ አደጋ በየዓመቱ ስድስት በመቶ ይጨምራል። አደጋውን ለመቀነስ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የንቅናቄ ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነ ኤጀንሲው ይገልጻል። በኤጀንሲው የኮምዩኒኬሽን ቡድን መሪ ብርሃኑ ኩማ ‹‹በ2017/18 በጀት ዓመት በአዲስ አበባ የተመዘገበው አደጋ 478 ሲሆን በ2018/19 ደግሞ በአንድ ቁጥር ብቻ ብልጫ አሳይቷል›› ብለዋል።

በተያዘው ዓመት 2012፣ እስከ ኅዳር ወር ድረስ በአዲሰ አበባ 132 የመኪና አደጋ መመዝገቡን የገለጸው ኤጀንሲው፣ ይህን ለመቅርፍ የተለያዩ ውይይቶችን እና መገናኛ ብዙኀንን በመጠቀምም ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቅሷል። ከዚህም አልፎ የትራፊክ ሕጎች እና የመንገድ አጠቃቀምን ትምህርት ለመስጠትም መንግሥታዊ እንዲሁም የሀይማኖት ተቋማት ጋር በጥምረት እየሠሩ ይገኛሉ፤ እንደ ኤጀንሲው ገለጻ።

ከዚህ ባሻገር ኤጀንሲው በትምህርት ሚኒስቴር እና በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በኩል፣ ጉዳዩ በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ተካትቶ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ግንዛቤ እንዲኖር ትምህርቱን ለመስጠት ምላሽ እየተጠባበቀ ነው። ብርሃኑ እንደገለጹት፣ ኤጀንሲው የትራፊክ አደጋን 50 በመቶ የመቀነስ ሥራን በአምስት ዓመት ውስጥ ለመከወን ማቀዱን ጠቅሰዋል። እቅዱ ከወጣ በ2012 ኹለት ዓመት አልፎታል።

ብርሃኑ አክለው ሲናገሩም ‹‹በከተማዋ የመኪናዎች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም የትራፊክ አደጋን መቀነስ እንችላለን ብለን እናምናለን። ምንም እንኳን ቀላል ባይሆንም በስድስት በመቶ ጭማሪ እያሳየ ያለውን አደጋ እንቀንሳለን›› ብለዋል።

በአዲስ አበባ የፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ ፖሊስ ኢንስፔክተር ቶማስ እሸቴ በበኩላቸው ‹‹ከትራፊክ አደጋ በስተጀርባ የምናገኘው አንዱ እና ተጠቃሹ ምክንያት አልኮል ጠጥቶ ማሽከርከር ነው›› ይላሉ። አደጋውን ለመቀነስም የወጣቶችን ግንዛቤ ከፍ ማድረግ አስፈላጊ ነው ሲሉ አሳስበዋል።
ለኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው በኤርምያስ ሙሉጌታ ተጽፎ፣ ለአዲስ ማለዳ በእየሩስ ተስፋዬ የተተረጎመ

ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com