መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናሕወሓት በታች አርማጭሆ አካባቢ ሠዎችን ወደ ሱዳን እያስወጣ መሆኑ ተገለጸ

ሕወሓት በታች አርማጭሆ አካባቢ ሠዎችን ወደ ሱዳን እያስወጣ መሆኑ ተገለጸ

-የአካባቢው ባለሥልጣናት ሠዎች ወደ ሱዳን እየወጡ መሆኑን አረጋግጠዋል

ሕወሓት በአማራ ክልል በማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ ታች አርማጭሆ ወረዳ ሳንጃ ቀበሌ ለሚገኙ ድንበር ጠባቂ የፀጥታ አካላት ገንዘብ በመክፈል ሠዎችን ለሥልጠና ወደ ሱዳን መላኩ ተሰማ፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው የሕወሓት ቡድን፣ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ ታች አርማጭሆ ወረዳ ሳንጃ ቀበሌ ለሚገኙ ለቀበሌ፣ ለፌደራል ፖሊስና ለጉምሩክ ድንበር ጠባቂ የፀጥታ አካላት በአንድ ሰው ከ120 ሺሕ ብር በላይ ገንዘብ በመክፈል፣ ከአንድ ሳምንት በፊት ከ60 በላይ ሠዎችን ለሥልጠና ወደ ሱዳን ማስወጣቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ፣ ሕወሓት ከአንድ ሳምንት በፊት ሠዎችን በ‹ሲኖትራክ› ጭኖና በታጣቂዎቹ አሳጅቦ ወደ ሱዳን ያስወጣ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ የወጡት እነዚህ ሠዎች ሱዳን ከሚገኘው “ሳምሪ” ከተባለው የሕወሓት ቡድን ጋር ሳይቀላቀሉ እንዳልቀሩ ተጠቁሟል፡፡

በሳንጃ ቀበሌ የሚኖሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ከኢትዮጵያ የወጡት ሠዎች “በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ጦርነት ውስጥ ለመግባት ኃይላችንን አጎልብተን እንመለሳለን፤ ጠብቁን” የሚል ዛቻና ማስፈራሪያ በተባባሪዎቻቸው በኩል በየቀኑ እየላኩብን ነው ብለዋል፡፡

አዲስ ማለዳ መረጃውን እስካጠናቀረችበት ጊዜ ድረስ፣ ከተጠቀሱት ሠዎች በተጨማሪ ሌሎች ኃይሎች የውትድርና ሥልጠና እንዲያገኙ ወደ ሱዳን ለመላክ ሕወሓት የሚያደርገው እንቅስቃሴ እንዳልተገደበና በአርማጭሆ ሳንጃ ቀበሌና በሌሎች ቦታዎችም ጭምር ከተባባሪ ግለሰቦች፣ ኃይሎችና የፀጥታ አካላት ጋር እየተመሳጠረ ሠዎችን እያስወጣ ነው ተብሏል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች ጉዳዩን ለወረዳ፣ ለቀበሌና ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አሳውቀው ውይይት ቢያደርጉም፣ ዕርምጃ ይወሰዳል ከሚል ምላሽ በስተቀር ለውጥ አለመምጣቱን እና የተቀናጀ የሕገ-ወጥ የሠዎች ዝውውሩ እንዳልቆመ ተናግረዋል።

“ሳምሪ” የተባለው የሕወሓት ታጣቂ ቡድን፣ ከአምስት ወር በፊት 400 የሚሆኑ ታጣቂዎቹን በመተማና ቋራ አካባቢ አሥርጎ በማስገባት ጥቃት ለማድረስ እንቅስቃሴ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ከግማሽ በላይ የሆኑት መደምሰሳቸውና የተቀሩት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የሚታወስ ነው፡፡

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የታች አርማጭሆ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ሙላቱ ጌቱ፣ ከአንድ ሳምንት በፊት የፀጥታ አካላት ባልተመደቡባቸው ድንበሮች አድርገው ወደ ሱዳን የገቡ ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች አሉ ብለዋል። ይሁን እንጂ፣ የተጠቀሰውን ብር ከፍለው የሳንጃ ቀበሌ ጉምሩክ ኬላን አልፈዋል የሚል መረጃ ቢኖራቸውም፣ የመረጃው እውነተኛነት እንዳልተረጋገጠ ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ከአካባቢው ነዋሪዎች በደረሳቸው ጥቆማ መሠረት እንጨት በጫነ ‹ሲኖትራክ› ተደብቀው ድንበሩን አቋርጠው ሊያልፉ የነበሩ የኦሮሚያ፣ የደቡብና የሱማሌ ክልል መታወቂያ የያዙ 58 ሰዎች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል፡፡ የኤርትራ ስደተኞች ነን የሚሉና ሐሰተኛ የሆነ የአዲስ አበባ ከተማ መታወቂያ የያዙ 55 የትግራይ ክልል ወጣቶች የሳንጃን ቀበሌ ግምሩክ ለማለፍ ጥረት ሲያደርጉ በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው ጉዳያቸው በሕግ ዕየታየ መሆኑንም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ከአንድ ሳምንት በፊት አንዳንድ የፀጥታ አካላት በፍተሻ ወቅት በፈጠሩት ቸልተኝነት ምክንያት ደንበር አልፈው ወደ ሱዳን የገቡ የኤርትራ ስደተኞች መኖራቸውን የታች አርማጭሆ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ድግስ መለሰ ጠቁመዋል፡፡

አያይዘወም፣ በተያዘው ዓመት ብቻ የሳንጃ ቀበሌ ድንበር አቋርጠው ሱዳን ሊገቡ የነበሩ ከስድስት መቶ በላይ የሚሆኑ የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የደቡብና የሱማሌ ክልል መታወቂያ የያዙ እና የኤርትራን መታወቂያ የሚጠቀሙ ሥደተኞችን በሕግ ቁጥጥር ሥር በማዋል ወደ መጡበት አካባቢ እንዲመለሱ አድርገናል ብለዋል።

ድምበር አቋርጠው ወደ ሱዳን ለመግባት ጥረት የሚያደርጉ አካላት አሁንም አሉ የሚሉት ዋና አስተዳደሪው፣ ከፌዴራልና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የተቀናጀ የቁጥጥር ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 173 የካቲት 19 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች