የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ 20 ሚሊዮን ብር መደበ

Views: 110

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚውል 20 ሚሊዮን ብር መመደቡን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አስታወቀ፡፡
ማህበሩ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ከዓለም አቀፍ የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽን እንዲሁም ከእህት ማህበራት ጋር በመሆን የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጿል፡፡

በዚህም 5 ሺህ የፊት መሸፈኛ ማስኮች፣ 6 ሺህ የሰርጅካል ጓንቶች፣ 1 ሺ 500 የህክምና ጫማዎች፣ 1 ሺህ የፕላስቲክ የፊት መከላከያ እና 5 ሺህ የመለያ ገዋኖችን ለመግዛት መታቀዱንም ማህበሩ አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም ከ500 በላይ አምቡላንሶች አስፈላጊው የሕክምና ቁሳቁስ ተሟልቶላቸው ዝግጁ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

ማህበሩ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በፌዴራል እና በክልል ያሉት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቹን በማስተባበር እየሰራ ሲሆን የማህበሩ በጎ ፍቃደኞች ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን በአየር ማረፊያዎች፣ ከአጎራባች አገራት ወደ ኢትዮጵያ መግቢያ ኬላዎች ለሚገቡ ሰዎች የሙቀት ልየታ እየሰሩ መሆኑ ተገልጿል።

የማህበሩ አባላት የጤና ሚኒስቴር እና የክልል ጤና ቢሮዎች ባቋቋሟቸው አብይና የቴክኒክ ኮሚቴዎች ውስጥም በመሳተፍ ላይ ናቸው ያለው ማህበሩ ከ4ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ከባለድርሻ አካላት ለተውጣጡ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠቱንም ገልጿል።
በኢትዮጵያ አሁን ላይ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 9 መድረሱ ይታወቃል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com