የመጀመሪያው የዲያስፖራ ባንክ አክሲዮን መሸጥ ጀመረ

Views: 217

በዓለም ዐቀፉ ውድድር ላይ የራሱን ፈተና ይዞ መምጣቱ አይቀርም

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ባንክ 70 በመቶ አባላቱን በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማድረግ እና ቀሪውን ከአገር ውስጥ በማሰባሰብ፣ በአጠቃላይ ስድስት ቢሊዮን ብር ካፒታል አዲስ ባንክ ለማቋቋም ፈቃድ አግኝቶ ከመጋቢት 4/2012 ጀምሮ አክሲዮን መሸጥ ጀመረ።

የአንድ አክሲዮን ዋጋ 20 ሺሕ ብር ሲሆን፣ አንድ ሰው በትንሹ 10 ድርሻዎችን ወይም የ6000 ዶላር አክሲዮን መግዛት ይጠበቅበታል። የባንኩ 70 በመቶ መስራቾች ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሆኑ የሚያደርግ ሲሆን፣ ቀሪውን አገር ውስጥ የሚሸጥ አክሲዮን ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ባንክ ከመጋቢት 4/2012 ጀምሮ አክሲዮን መሸጥ የጀመረ ሲሆን፣ ሽያጩ ለኹለት ዓመት እንደሚቆይ ለማወቅ ተችሏል። የመሥራች ቦርዱ ሰብሳቢ ጋሻው የትዋለ ዓለሙ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ ባንኩ በውጪ አገር የሚኖረው ትውልደ ኢትዮጵያዊ በአገሩ ላይ ባዳ እንዳይሆን ያደርጋል።

በስምንት ባንኮች የአክሲዮን ሺያጩ እየተከናወነ ሲሆን፣ ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ፣ የኢትዮጵያ ንግድ፣ አዋሽ፣ ቡና፣ ዳሽን፣ ዘመን፣ ንብ እና አቢሲኒያ ባንኮች በአገር ውስጥ አክሲዮኑ የሚሸጥባቸው ናቸው። ትውልደ ኢትዮጵያውያን አክሲዮኑን በውጪ ምንዛሬ የሚገዙ ይሆናልም ብለዋል።

ተሻሽሎ በወጣው የባንክ ሥራ አዋጅ መሠረት ብሔራዊ ባንክ የአፈፃፀም መመርያ አውጥቶ ከዚህ ቀደም ተከልክሎ የቆየውን የውጪ አገር ዜጋ የሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባንክ መመስረት እንዲችሉ ፈቅዷል። በዚህ ለውጥ መሠረት የሚቋቋመው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ባንክ በዋናነት መካከለኛ እና ከፍተኛ ገቢ ያላቸውን እንዲሁም ባለሃብቶችን በማሳተፍ በጋራ የሚያቋቁሙት ባንክ ይሆናል በሚል እየተሠራ መሆኑንም ጋሻው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

‹‹በአሁን ሰዓት የኢትዮጵያን የባንክ ገበያ ስናይ የሥራ ፈጠራን አያበረታታም›› ያሉት ሰብሳቢው፣ ባንኩ ያለማስያዣ አዋጪ የሥራ እቅድ ይዘው ለሚመጡ የሥራ ፈጣሪዎች ብድር በመስጠት ይህንን ለመቀየር እንደሚሠራም ገልጸዋል።

ይሄን ባንክ ማቋቋም ያስፈለገበት ዋና ምክንያትም ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የውጪ ምንዛሪ የማመንጨት አቅም እና አሁን በሥራ ላይ ያሉት ባንኮች የውጪ ምንዛሬ አቅማቸው ዝቅተኛ በመሆኑ ምክንያት መሆኑንም አክለዋል።

አሁን ላይ ባለው ሁኔታ አዲስ የሚመሠረቱ ባንኮች ያለውን ሁኔታ ተቋቁሞ ለመቀጠል ይከብዳቸዋል የሚሉት በባንክ እና በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ትንተና የሚሰጡት አብዱልመናን መሐመድ ናቸው። አንደ ማንኛውም አዲስ ባንክ ሃብት ማሰባሰብ ላይ ክፍተት ሊኖር እንደሚችል የሚናገሩት አብዱልመናን፣ ይህንን ሃብት ደግሞ ከውጪ አገር ማሰባሰብ ቀላል አይሆንም ይላሉ። በተለይም አክሲዮኖች በውጪ ምንዛሬ የሚገዙ መሆኑ እና ከዚህ ቀደም በዳያስፖራው የተያዘ ባንክ ስላልበረ እና አዲስ በመሆኑ ሌላ ተግዳሮት ይሆናል ሲሉም ያክላሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ቁጥሩ ቀላል የማይባል ብዙ ባንክ ገበያውን በመቀላል ላይ በመሆኑ፣ ፉክክሩን ቀላል አያደርገውም ሲሉ አብዱልመናን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
‹‹ምንም እንኳን አዳዲስ ባንኮች መምጣታቸው እና ፉክክር መኖሩ መልካም ቢሆንም፣ የተረጋጋ የባንክ ኢንዱስትሪ እና ፀንተው የቆዩ ባንኮች መኖር ግን እጅግ ወሳኝ ነው›› ይላሉ አብዱልመናን። ‹‹ስለዚህም ብሔራዊ ባንክ ቁጥጥርን በተመለከተ ጥብቅ መሆን ይጠበቅበታል።›› ሲሉ አሳስበዋል።

የኮቪድ19ኝ የኮሮና ቫይረስን መከሰት ተከትሎ፣ ዓለማቀፍ የኢኮኖሚ ድቀት የሚያስከትል ከሆነ፣ ኢትዮጵያም የወጪ ንግዷ መቀዛቀዙ እና የውጪ ምንዛሬ እጥረቱም መባባሱ አይቀርም፤ እንደ አብዱልመናን ገለፃ።

‹‹ከዚህ ባሻገርም ብድር እና እርዳታም ማሽቆልቆሉ ስለማይቀር ይህ ለባንኮችም በተለይ በዓለም ዐቀፉ ውድድር ላይ የራሱን ፈተና ይዞ መምጣቱ አይቀርም። ይህ በአገር ውስጥም የማድረግ አቅማቸውን መፈታተኑ እና የቁጠባ መጠንንም መቀነሱ አይቀሬ ይሆናል›› ሲሉ አብዱልመናን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com