ኮሮና ቫይረስን መዳፈር ይብቃ!

Views: 208

ከቀን ወደ ቀን ዓለምን በከፍተኛ ፍጥነት በማዳረስ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ የሚገኘው ኮሮና፤ ኮቪድ-19 አሁንም ግስጋሴውን እንደቀጠለ ነው። የዓለም አገራት በሽታው በቻይናዋ ዉሃን ግዛት ከተከሰተ ጀምሮ ድንበራቸውን ተሻግሮ እንዳይገባ እና የተፈራውን ጉዳት እንዳያደርስም ጠንካራ ጥረቶችን ሲያደርጉ ተስተውለዋል። ይሁን እንጂ ምንም ያህል ቁጥጥር እና ጥንቃቄ ቢያደርጉም፤ ቫይረሱ ወደ አገራቸው ገብቶ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎቻቸውን ለሕልፈት በመዳረግና ከዛም የሚልቁትን በሕመም በማሰር እንደቀጠለ ነው።

በሽታው ከተከሰተበት የቻይናዋን ዉሃን ከተማን ጨምሮ፣ እስከ ዛሬ ድረስ በ169 አገራት፣ ግዛቶችና አካባቢዎች ላይ መዛመቱን የዓለም ጤና ድርጅት ያስታወቀ ሲሆን፤ ድርጅቱ በመጋቢት 11/2012 ባወጣው ሪፖርት መሰረት በተጠቀሱት አገራት ውስጥ 209 ሺሕ 839 የተረጋገጡ በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ቁጥር ይፋ ያደረገ አድርጓል። ከእነዚህም ውስጥ 8 ሺሕ 779 ደግሞ ለሕልፈት መዳረጋቸውን ይፋ አድርጓል።

ዓለም ዐቀፋዊው ወረርሽኝ አገራችን ኢትዮጵያንም ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ቀናት ላይ ከቡርኪናፋሶ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አዲስ አበባ በመጣ የ47 ዓመት ጃፓናዊ ምክንያት የጎበኛት ሲሆን፣ አዲስ ማለዳ ለሕትመት እስከገባችበት ሰዓት ድረስ ዘጠኝ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎችም እንደሚገኙ ከኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በአገር አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን ይህን አደገኛ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ውስጥ ግን ተገቢው ትኩረት እየተሰጠው እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች። እስከ እለተ አርብ ምሽት ድረስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን መቀጠሉ የሚታወቅ ሲሆን፣ አርብ ምሽት ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የወጣውን መግለጫ ተከትሎ፣ በረራዎች ለጊዜው እንዲቆሙ መደረጉና ከውጪ የሚገቡ ሰዎችም በራሳቸው ወጪ በተመደበላቸው ስፍራ ለ15 ቀናት ራሳቸውን ለይተው እንዲያቆዩ ተብሏል።
ይህ የኮቪድ 19 መከላከል ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተገናኝተውና ተወያይተው ያስተላለፏቸው ውሳኔዎች በአግባቡና በስርዓት ተግባራዊ የሚሆኑ ከሆነ፣ አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡና ከኅብረተሰቡ ጋር ንክኪ እንዳይኖራቸው፣ ተያይዞም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እንደሚረዳ አዲስ ማለዳ ታምናለች። ለዚህም ተግባራዊነት ክትትልና ድጋፍ ያስፈልጋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ማኅበራዊ ፈቀቅታዎችም በሕዝቡ ዘንድ እየተተገበሩ እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ ተገንዝባለች። በአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው እና የሕዝብ አገልግሎት በሚሰጡ ስፍራዎች የተጀመረው የእጅ ንጽሕና አጠባበቅና ስለ ወረርሽኙ የሚሰጡ ግንዛቤዎች፣ መልካም ጅማሬዎች ቢሆኑም አጥጋቢ እና ለውጥ አምጪ እንዳልሆኑ ትገልጻለች።

ወረርሽኙን ለመከላከል በዓለም የጤና ድርጅት ባለሙያዎች፣ በአገራችን በጤና ሚኒስቴር እንዲሁም በኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሚጠቀሱት እርምጃዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ማኅበራዊ ፈቀቅታ በማኅበረሰቡ ዘንድ እየተከወነ አይደለም። ምንም እንኳን መንግሥት ትምህርት ተቋማትን ለአስራ አምስት ቀናት እንዲዘጉ ቢያደርግም፣ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸው ቤታቸው ሆነው እንዲሠሩ ቢያደርጉም፤ የሚበዛው ሕዝብ ግን ከማኅበራዊ ፈቀቅታ በመታቀብ በመድኃኒት ቤቶች፣ በገበያ ማእከላት፣ በትራንስፖርት እንዲሁም በምሽት መዝናኛ ቤቶች የቀደመውን የመጠጋጋት ኑሮ እየገፋ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ የትኛውም ዓይነት ሰፊ ስብሰባ እንዳይካሔድ ቢያስታውቁም፤ በቀጣዩ ቀን የሸማቾች ቁጥጥርና ውድድር ባለሥልጣን በኢትዮጵያ ሆቴል ውስጥ ሰፊ ስብሰባ ሲያካሂድ እንደነበር አዲስ ማለዳ ታዝባለች። በተመሳሳይም በሐዋሳ ከተማ የኢትዮጵያ ታላላቅ ባለሃብቶችና የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት የኢትዮጵያን ሆቴልና ቱሪዝም ላይ መሠረት ያደረገ ሰፊ ስብሰባ ሲካሔድ ተስተውሏል።

ይህ ኹሉ በመንግሥት እና ሕዝብ በኩል ለወረርሽኙ የተሰጠው አናሳ ትኩረት ነው ስትል አዲስ ማለዳ ትገልጻለች። በዚሁ ረገድም በአማራ ክልል በተለያዩ ወረዳዎች ከመጋቢት 10 እስከ 14 /2012 የሚቆይና 10 ሺሕ ያህል የብልጽግና ፓርቲ የታችኛው አመራሮች ይሳተፉበታል የተባለ ሥልጠና በይፋ መጀመሩ፣ ወረርሽኙን በአገር ዐቀፍ ደረጃ ለመግታት እየተወሰደ ያለውን አናሳ ትኩረትና ግዴለሽነት የሚያሳይ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች።

በማኅበራዊ ፈቀቅታ እና አብሮነት የአኗኗር ዘይቤ የምትታወቀው አውሮፓዊቷ አገር ጣሊያን፣ የቫይረሱ ወረርሽኝ በስፋት ጉዳት ካደረሰባቸው አገራት ግንባር ቀደም የምትጠቀስ ናት። በተለይም ደግሞ በመጀመሪያ ደረጃ በቂ ትኩርት በመንፈጓ ከ3 ሺሕ 400 በላይ ዜጎቿን ልትነጠቅ በቅታለች። አሁንም የቫይረሱ ስርጭት በአገረ ጣሊያን እየጨመረ ይገኛል። ለዚህ ደግሞ ከመጀመሪያው ተገቢውን ትኩረት አለመስጠቷ ዋነኛው ምክንያት ነው።

ታላላቅ እና በቴክኖሎጂ እንዲሁም በምጣኔ ሃብት ከኢትዮጵያ እጅጉን የሚልቁ አገራት ሊቆጣጠሩት ያቃታቸውን ወረርሽኝ ኢትዮጵያ እንደ አገር በመጀመሪያው ደረጃ ላይ ትገኛለችና ሳይቃጠል በቅጠል እንድትል አዲስ ማለዳ ለመንግሥትና ለሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት መልዕክት ታስተላልፋለች።

ከዚሁ ባለፈም ታላላቅ ዓለም ዐቀፍ የዜና አውታሮች በየሰዓቱ እና ደቂቃው ዓለም ላይ ስለተከሰተው ወረርሽኝ ጠቃሚ መረጃዎችን ወደ ሕዝብ በሚያሰራጩበት በአሁኑ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ እና ጉዳዮን በቅርበት እንዲሁም በኃላፊነት የሚከታተሉት የመንግሥት ተቋማት በራቸውን ለመገናኛ ብዙኀን ክፍት ባለማድረጋቸው የመረጃ እጥረቶች እየተከሰቱ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታዝባለች።

ይህ ደግሞ ሕዝብ መረጃ የማግኘት መብቱን ከመጋፋት ባለፈ በዚህ ወሳኝ ሰዓት ኅብረተሰቡ ራሱን ከወረርሽኙ እንዲከላከል ጠቃሚ መረጃ እንዳያገኝ እና ለተለያዩ ያልተጣሩ መረጃዎች፣ ሐሰተኛ ዜናዎችና ውዥንብሮች የሚዳርግ ነው ስትል አዲስ ማለዳ ታምናለች። በዚህም በመመርኮዝ የሚመለከታቸው አካላት በየጊዜው ስለ ኮሮና ቫይረስ የደረሱበትን መረጃ እና ግኝት ለኅብረተሰቡ በማድረስ ቁጥጥሩን እና መከላከሉን ማገዝ እንደሚኖርባቸው አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ አድኀኖም (ዶ/ር) በመጋቢት 9/2012 በጽሕፈት ቤታቸው ለዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኀን በሰጡት መግለጫ፣ አገራት የዓለም የጤና ድርጅት ምክርን ተግባራዊ እያደረጉ እንደሚገኙ እና ለአብነትም ኮሪያን አንስተው፤ ቀሪው የዓለም አገራትም ይህን እንዲተግበሩ አጽንኦት ሰጥተዋል። አዲስ ማለዳም እንደመንግሥት በሕዝቡ ዘንድ ትክክለኛውን ግንዛቤ የመፍጠር ሂደት ከመቼውም በበለጠ አጠናክሮ እንዲሠራ ታሳስባለች።

በተለይም ደግሞ በተለያዩ አጋጣሚዎች ባለድርሻ አካላት በይፋ መደንገጥ ሳይሆን መጠንቀቅ ነው የሚያዋጣው በሚል ያልጠራ ሐሳብን ወደ ሕዝቡ በመስደድ ጥንቃቄን በሕዝቡ ዘንድ በስፋት እንዳይተገበር ማድረጋቸው ሊቆም ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ አጽንኦት ሰጥታ ታስገነዝባለች። ሕዝብም ሆነ መንግሥት ወረርሽኙን ለመግታት እንደ ሞዴል የተጠቀሱ አገራትን ልምድም እንዲቀስሙ ስትል ታሳስባለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com