ዳሰሳ ዘ ማለዳ (መጋቢት15/2012)

Views: 151

የኮቪድ19  ሥርጭትን ለመከላከል 20 ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ሊሰማሩ ነው

የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላም እና ብልጽግና ተልእኮ ሊግ የኮቪድ19 ን ለመከላከል 20 ሺህ በጎ ፈቃደኞችን በመላ አገሪቱ ሊያሰማራ መሆኑን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላም እና ብልጽግና ተልእኮ ሊግ ፕሬዚዳንት ወጣት ብርሃኑ በቀለ፣ ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ኢትዮጵያ 20 ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ሊሰማሩ መሆኑን ገልጸዋል። (ኢዜአ)

……………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

 

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮቪድ19 ወረርሽኝን ተከትሎ የቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ አዘጋጆች ጨዋታው ለአንድ ዓመት እንዲራዘም ተስማሙ። የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ  ዓለም አቀፉ የኦሎፒክ ኮሚቴ በመራዘሙ መስማማቱን ለጋዜጠኞች ይፋ አድርገዋል። “ጨዋታዎች ለአንድ ዓመት እንዲራዘሙ ያቀረብኩትን ሐሳብ ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ቶማስ ባች ሙሉ በሙሉ ተቀብለውታል” ብለዋል። የዘንድሮው የኦሎምፒክ ውድድር ከሐምሌ 24-ነሐሴ 09 ቀን 2020 መርሐ ግብር ተይዞለት እንደነበር ይታወሳል (ኢቢስ)

……………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

 

መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ በሀገራችን ከተገኘ ወዲህ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ አንድ (1) ተጨማሪ ሰው በመገኘቱ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አስራ ሁለት (12) መድረሱን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል።ኢንስቲትዩቱ እንዳለው ይህ ታማሚ የ 34 ዓመት ኢትዮጵያዊ ሲሆን መጋቢት 10 ቀን 2012 ዓ.ም ከዱባይ ወደ ሀገር ውስጥ የገባ ነው።ግለሰቡ የህመም ምልክት የነበረው በመሆኑ በመጋቢት 13 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ጤና ተቋም የሄደ ሲሆን ተቋሙም ለሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሪፖረት በማድረጉ በተደረገለት የላቦራቶሪ ምርመራ በቫይረሱ መያዙ ተረጋግጧል።(ፋና ብሮድካስቲን ኮርፖሬት)

……………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

በአዳማ ከተማ “በኮሮናቫይረስ ምክንያት ረዳቱን መልስ አይጠይቁ” የሚል መልዕክት ለጥፈው የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩት አሽከርካሪ እና ረዳት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፖሊስ አስተወቀ። የምዕራብ ሸዋ ዞን የትራፊክ ቁጥጥር ክፍል ኃላፊ የሆኑት ኢንስፔክተር እስማኤል አባድር “አሽከርካሪው ከተሳፋሪዎች በሕገ-ወጥ መንግድ ገንዘብ ለመሰብሰብ ጥረት አድርጓል” ያሉ ሲሆን “መልስ አጥጠይቁ ማለት ዘረፋ ነው” ያሉት ኢንስፔክተሩ፤ ረዳቱ እና አሽከርካሪው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን እና ምረመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ተናግረዋል። ማህብረሰቡ የትራንስፖርት አገልግሎት ሲጠቀም እራሱን ለቫይረሱ እንዳያጋልጥ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርበት ኢንስፔክተሩ ጨምረው ተናግረዋል። (ቢቢሲ አማርኛ)

……………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

የኮቪድ19 ስርጭትን ለመከላከል በአማራ ክልል ከዛሬ መጋቢት 15/2012 ጀምሮ ምንም ዓይነት ስብሰባዎች እንደማይካሄዱ ተገለጸ። በክልሉ ከዛሬ ጀምሮ በጸጥታ ጉዳይ በጥንቃቄ ከሚከናወኑ ምክክሮች ውጭ ምንም ዓይነት ስብሰባ እንደማይካሄድ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ፈንታ ማንደፍሮ (ዶ/ር) ገልጸዋል።በተጨማሪም በክልሉ የሚገኙ የመጠጥ እና ጭፈራ ቤቶች ላልተወሰነ ጊዜ ሙሉ በሙሉ እንዲዘጉ ተወስኗል።

የክልሉን ህዝብ ህልውና የሚፈታተኑ የጸጥታና ጤና-ነክ ውይይቶች እንደ የአስፈላጊነቱ ቁጥራቸው ከ15 ባልበለጡ ሰዎች በየቀኑም ቢሆን በጥንቃቄ ሊከናወኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል። (ኢዜአ)

……………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

64 ኢትዮጵያዊያን ከማላዊ ወደ ሞዛቢክ በከባድ ተሽከርካሪ ኮንቴይነር ውስጥ በመጓዝ ላይ ሳሉ ታፍነው መሞታቸው ተገለጸ። ኢትዮጵያዊያኑ ህይወታቸው ያለፈው ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት በማሰብ ከማላዊ ወደ ሞዛምቢክ በአንድ የእቃ መጫኛ ተሽከርካሪ ውስጥ ተደብቀው ሲጓዙ በተፈጠረ መታፈን መሆኑ ተገልጿል።በአጠቃላይ 78 ኢትዮጵያያን በተሽከርካሪው ወስጥ ሲጓዙ የነበረ ሲሆን 64ቱ ሲሞቱ 14ቱ በህይወት የተረፉ ሰዎች ከጭነት መኪና ውስጥ ዛሬ ጠዋት ተገኝተዋል።(ኢትዮ ኤፍ ኤም)

……………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የእጅ ማፅጃ ሳኒታይዘር ማምረት መጀመሩ የተገለጸ ሲሆን ምርቱን የሚሰራው የዩኒቨርስቲው የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ነው ተብሏል።

የእጅ ማፅጃው የኮሮና በሽታን ለመከላከል አገልግሎት ላይ እንደሚውልም የተነገ ሲሆን  ዩኒቨርስቲው በኢትዮጵያ የእጅ ማፅጃ ሳኒታይዘር እጥረት መኖሩን ከግምት በማስገባት መስራቱን የኮሌጁ የፋርማሲ ትምህርት ክፍል ኃላፊ መምህር ታምራት ባልቻ መናገራቸውን ወላይታ ታይምስ ፅፏል።(ሸገር ኤፍ ኤም)

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com