ዳሰሳ ዘ ማለዳ (መጋቢት 16/2012)

Views: 431

 

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተቋማት ከነገ መጋቢት 17/2012  ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ስራ እንዲያቆሙ ወሰነች

 

ቋሚ ሲኖዶሱ ዛሬ መጋቢት16/2012 ባደረገዉ ስብሰባ ከጠቅላይ ቤተ-ክህነት ጀምሮ የመንበረ ፓትሪያርክ ቅርሳ-ቅርስ ቤተ-መጻህፍት ወመዘክር፣ጉብኝትና የንባብ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ላልተወሰነ ጊዜያት ተዘግተዋል።

በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስር ከአዲስ አበባ እስከ አህጉረ ስብከት ያሉ፤መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲዎች፣መንፈሳዊ ኮሌጆች፣ስልጠና ያልጀመሩ የካህናት ማሰልጠኛዎች፣መዋዕለ ህጻናትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ላልተወሰነ ጊዜ የመማር ማስተማሩ ስራ እንዲቆም ተወስኗል።

ከዚህ ባሻገር ግን ከመንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እስከ መላዉ አህጉረ ስብከት ጽ/ቤት፣ለአስቸኳይ ስራ ከሚፈለጉና ተለይተዉ እንዲቆዩ ከሚደረጉ ሰራተኞች በስተቀር መላዉ ሰራተኞች በቤታቸዉ ስራቸዉን እንዲያከናዉኑና ሲፈለጉና ጥሪ ሲደረግላቸዉ ከሚመጡ በስተቀር በቤታቸዉ እንዲቆዩ ተወስኗል።(ኢትዮኤፍኤም)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..

ብልጽግና ያካሄደው ውህደት ህጋዊና በአብላጫ ድምጽ ድጋፍ ያገኘ በመሆኑ ህወሃት ሊያቀርብ የሚችለው የሃብት ጥያቄ የለም ሲል የብልፅግና ፓርቲ አስታወቀ::
የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ  አወሉ አብዲ እንደተናገሩት አሁን ላይ ኢህአዴግ የሚባል ፓርቲ ፈርሷል፤ በእርሱ ምትክ ደግሞ በህጋዊነት ብልጽግና ፓርቲ ተቋቁሟል ስለዚህ ህወሃት ከማዕከል የሚካፈለው ምንም ዓይነት ንብረት የለም ብዋል:: (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..

የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በፌደራል ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ከ4ሺህ በላይ ታራሚዎች ሊለቀቁ መሆኑን የጠቅላይ አቃቤ ሕግ አስታወቀ። አቃቢተ ሕጓ አዳነች አቤቤ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኀን እንዳስታወቁት እስረኞቹ የሚፈቱት በይቅርታ ነው ያሉ ሲሆን ከሚፈቱት ታራሚዎች መካከል ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኀተመወርቅ እንደሚገኝበት ለማወቅ ተችሏል። በይቅርታው የተካተቱት ታራሚዎች በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ስር ባሉ አምስት ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ታራሚዎች ሲሆኑ በይቅርታው ከተካተቱት መካከል በግድያ ወንጀል ያልተሳተፉ የውጭ ሀገር ዜጎች እንዲለቀቁ እና ወደ የመጡበት ሀገሮች እንዲላኩ መወሰኑን  አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።ከእነዚህም ውጪ እስከ ሶስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት የተፈረደባቸው፣ በማረሚያ ቤት ሆነው አንድ ዓመት የአመክሮ ጊዜ የሚቀራቸው እንዲሁም በግድያ ወንጀል ያልተከከሰሱ የሚያጠቡ እና ነፍሰ ጡር እናት ታራሚዎች እንደሚገኙበት አቃቢተ ህጓ በመግለጫቸው ላይ አስታውቀዋል።(ቢቢሲ አማርኛ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለኮቪድ19 ድንገተኛ ሁኔታ ዝግጅት የሚውል ገንዘብ እና ሌሎች አቅርቦቶችን የሚያሰባስብ ብሔራዊ የአቅርቦት አፈላላጊ ኮሚቴ አቋቁመዋል። መንግሥት ጠቀም ያለ በጀት መደቦ የመጨረሻው አስከፊ ሁኔታ ቢከሰት ለመቋቋም የሚያስችሉ ግብአቶችን በማሰባሰብ ላይ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን ነገር ግን እንዲህ ያለው ጊዜ የእያንዳንዱን ግለሰብ አስተዋጽኦ የሚፈልግ ነው ተብሏል። ተረጋግቶ አስተዋጽኦ ማድረግ’ን በቀዳሚነት ተግባራዊ በማድረግ የብሔራዊ ኮሚቴው አባላት የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለብሔራዊው የኮቪድ19 አቅርቦት ማሰባሰቢያ ለግሰዋል።(ኢዜአ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..

የደቡብ ክልል የአስተዳደር ምክር ቤት ዛሬ መጋቢት16/2012  ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባው ለ3642 የህግ ታራሚዎች ምህረት እንዲደረግላቸው የወሰነ ሲሆን በክልሉ የሚደረጉ ማንኛውም ስብሰባዎች እንዲቆሙ፣ የህዝብ ትራንስፖርት የሚሰጡ ተቋማትም የትራንስፖርት ዘርፉ የሚያወጣው መመሪያ ተግባራዊ እንዲያደርጉ እና ይህን በማያደርጉ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ተነግሯል።እንዲሁም  ጫት ቤቶች፣ ጭፈራ ቤቶች፣ ሺሻ ቤቶች እንዲዘጉ ተወስኗል፤ መዝናኛ ቦታዎች በቀጣይ እየታየ ውሳኔ እንዲተላለፍባቸው ምክር ቤቱ ወስኗል።(ኢቲቪ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..

በአሁኑ ሰዓት 9 ሰዎች የበሽታው ምልክት ታይቶባቸው በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆነው የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤታቸውን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

እስከ አሁኑ ሰዓት አራት መቶ አርባ ስድስት (446) ሰዎች የበሽታው ምልክት ታይቶባቸው በተለያየ ጊዜ በለይቶ መቆያ ማእከል እንዲቆዩ ተደርጎ የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን አራት መቶ ሰላሳ አንድ ሰዎች (431ዎቹ) ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው በመረጋገጡ ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል።(ጤና ሚንስቴር)

 

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..

ሕብረት ባንክ የኮቪድ19 ሥርጭትን ለመከላከል የአምሥት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ድጋፉም የቫይረሱን ሥርጭትት ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት የሚውል እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ ላይ ገለጸ።ለጤና ሚንስትር አምስት ሺህ ብር ድጋፍ ያደረገው ባንኩ፣ በዚህ ብቻ እንደማይቆምና ቫይረሱን ለመግታት ከሚሰሩት ባለድርሻ አካላት ጋር ቀጣይነት ያለው ሥራ እንደሚሰራም ገልጿል።ባንኩ ጨምሮም፣ ደንበኞቹ ከቫይረሱ እራሳቸውን እንዲከላከሉ ባንክ ድረስ መምጣት ሳይጠብቅባቸው የኤሌክትሮኒክስ ባንክ፣የኦንላይን እንዲሁም የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት እንዲጠቀሙም አሳስቧል።(አዲስ ማለዳ)

 

 

 

 

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com