የኮቪድ19 ግፍ እና ‹ውለታ›

Views: 217

በነገር ሁሉ ልጇን እንደምታነሳ ከወለደች ሳምንት እንዳልሞላት ወላድ፣ ዓለም ነጋ ጠባ ስለኮሮና ቫይረስ መነጋገሯን አልተወችም። ቫይረሱም ከማንምና ከምንም በላይ ከጥግ እስከ ጥግ ሥሙ ናኝቷል። እንደው ከአንዳች ፍጡር አካል ነስቶ ቢታይ፣ ዝነኛ ነኝ ብሎ ሳይኮራ አይቀርም። ታድያ ይህ የዘመናችን ዝነኛ ቫይረስ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ነጥቋል፣ ሕይወትን አናግቷል።

ብዙዎች ከሥራቸው ተፈናቅለው ቤታቸው ተለይተው እንዲቀመጡ ተገደዋል። ተሯሩጠው ይኖሩ የነበሩ የሌሎች እጅ ጠባቂ ከመሆን ውጪ አማራጭ አላገኙም። አዛውንት ባልቴቶች በቤታቸው ለብቻቸው እንዲቀመጡ ግድ ብሏቸዋል። ሰርግና ለቅሶን መጋራት ተናፍቋል። ምግብና መጠጥ ቤቶች ተዘግተዋል። ጭፈራ ቤቶች በብርሃንም ይሁን በጨለማ በራቸው እንደተቆለፈ ነው። ዓለም ልማዷ ሁሉ ቀርቶባታል።

በሌላ በኩል ደግሞ ‹ውለታ› እየዋለም ይመስላል። ‹‹ስታለቅሺ ደስ አልሽኝ›› እንዳለው ዘፋኝ፣ ዓለም በቫይረስ የታመመችበት ይህ ጊዜ የሰውነት ውበት ቁልጭ ብሎ ታይቶበታል፤ ሰብአዊነት። መገናኛ ብዙኀንም በቫይረሱ ምክንያት የደረሱ ሞቶችንና ሐዘኖችን፣ ጉድለትና ኪሳራዎችን የበለጠ ሽፋን ይስጡ እንጂ፣ እነዚህን በጎነቶችም እየለቀሙ ማስቃኘታቸው አልቀረም።

የሚገርመው ደግሞ መተቃቀፍ፣ መጨባበጥ፣ መነካካት የሚባለው ነገር ተከልክሏል። እንደወትሮው ቢሆን ‹‹ሰው እንዴት ላለመነካካት እንዲህ ተራርቆና ተፈራርቶ በጎ ነገር ሠራ ሊባል ይቻላል› እንል ነበር። እግር ኳስ ሜዳ ላይ ሳይቀር ዘረኝነት ልባቸውን ያጠቆረው ሰዎች፣ ‹አንጨብጥም› ሲሉ ወቀሳና ስድብ እንደጉድ ይዘንብባቸው ነበር።

አሁን ግን ቫይረሱ ሰዎች በአካል እንዳይቀራረቡ በማድረጉ ውስጥ፣ ሰዎች ለመገናኘት አዲስ ዘዴ እንዲፈጥሩ አድርጓል። አሁን በሐሳብና በልብ እየተግባቡ ነው። አገራት አንዳቸው ለሌላቸው መቆማቸው አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንደሆነ ያመኑ ይመስላሉ። ፀባቸውን ትተው፣ እርስ በእርስ መገዳደላቸውን ገትተው፣ ‹የጋራ ገዳያችንን እንታገል› ብለው የጦር መሣሪያውን አስቀምጠዋል።

ፖሊሶች ቤታቸውን ዘግተው የተቀመጡ ሰዎችን ለማዝናናት ሲዘፍኑ ታይቷል። አሸባሪ ቡድኖች ‹መሣሪያችንን ለአፍታ አስቀምጠን እጃችንን እንታጠብ› ሲሉ ተሰምተዋል። እንግዲህ ይልመድብን ማለት ነው! ምድሪቱም ብትሆን አረፍ ብላለች። ይበክላት የነበረ የፋብሪካ ጭስ ሠራተኞች ወደ ሥራ ባለመግባታቸው ሥራውን ገትቷል። በምጥ መካከል እንደሚገኝ የአጭር ደቂቃ እንቅልፍ፣ ዓለም ከቆየችበት የሽብርና የመከራ ምጥ ለአፍታ አረፍ ያለች፣ እንደው ለቅጽበት ጋብ ያለላት ይመስላል።
በአገራችንም ቢሆን የብሔር ጉዳይ ዝም ብሏል። ፖለቲካ ፓርቲዎች አቋማቸውን የሚገልጹት ኮሮናን በሚመለከት ነው። የተቃረበው የ2012 ምርጫ ‹ይራዘም፤ አይራዘም› አሁን ክርክር አይነሳም። ሕዝቡ ራሱ ‹‹ፖለቲካ የትኛው ቫይረስ ነው?› ብለው ሳይጠይቅ ይቀራል!

ከምንም በላይ ግን የበጎ አድራጎት ሥራዎች ከወዲሁ ተጀምረዋል። ‹ቅድሚያ ለሰብአዊነት› ብለው በየጊዜው የሚንቀሳቀሱ ወጣቶች፣ አሁንም ቫይረሱ የበለጠ ቢስፋፋ እንኳ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ለመድረስ እንንቀሳቀስ ብለው ጥሪያቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።

በተጓዳኝ መንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ተማሪዎች በቀናት ውስጥ ወደየቤታቸው እንዲገቡ ማዘዘኑን ተከትሎና እንዲደረጉ የተባሉ የተለያዩ ጥንቃቄዎችን በማንሳት፣ ‹‹ቫይረሱ ከሚነገረን ቁጥር በላይ ተሰራጭቷል ማለት ነው›› ብለው ስጋታቸውን የገለጹ አልጠፉም። ‹‹መንግሥት የደበቀን ነገር ያለ የሚመስለኝ እኔን ብቻ ነው?›› ብሎ አንድ የፌስቡክ ተጠቃሚ በለቀቀው ጽሑፍ ስር፣ ብዙዎች ይህን ስጋታቸውን አስፍረዋል።

ኮሮና አንድም ሰው ይያዝ መቶ ላይ፣ ጥንቃቄ ካልተደረገ ጥፋቱ እኩል ነውና፤ ሳይቃጠል በቅጠል ብሎ ለክፉም ለደጉም መዘጋጀቱን ግን ብዙዎች አድንቀውታል። እንግዲህ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ጀመርን ማለት አይደለ? ‹‹እድሜ ለኮሮና›› አይባልም እንጂ!

ቅጽ 2 ቁጥር 73 መጋቢት 19 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com