ኮሮናን ተደግፈው ፎቶ የሚነሱት…!

Views: 268

በአገራችንና ዓለም ዙሪያ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ የጤና ባለሙያዎችና በጎ ፈቃደኞች ኮሮና ቫይረስ ያመጣውን አደገኛ ችግር ለመፋለምና የሰውን ሕይወት (የሰውን ዘርም ሊሆን ይችላል) ለመታደግ ሌት ተቀን ደፋ ቀና በማለት ላይ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና ስለ እምነት (ሐይማኖት) በጥልቀት እናውቃለን ባዮች ወዘተ… ‘በኮሮና ፎቶ በመነሳት’ ትልቅ ሰው መስለው ለመታየት እየተሯሯጡ ነው።

በአገራችንና ዓለም ዙሪያ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ የጤና ባለሙያዎችና በጎ ፈቃደኞች ኮሮና ቫይረስ ያመጣውን አደገኛ ችግር ለመፋለምና የሰውን ሕይወት (የሰውን ዘርም ሊሆን ይችላል) ለመታደግ ሌት ተቀን ደፋ ቀና በማለት ላይ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና ስለ እምነት (ሐይማኖት) በጥልቀት እናውቃለን ባዮች ወዘተ… ‘በኮሮና ፎቶ በመነሳት’ ትልቅ ሰው መስለው ለመታየት እየተሯሯጡ ነው።

በአገራችንና በሌላው ዓለም ባዶ እጃቸውን፣ ባዶ ጭቅላታቸውንና የተደፈነ ልባቸውን ይዘው ወደ መገናኛ ብዙኀን፣ ወደ ማኀበራዊ ሚዲያዎች ወዘተ ብቅ እያሉ ታላቅ፣ አዋቂና ሩሕሩሕ መስለው ለመታየት የሚጥሩ ጥቂቶችን እየታዘብን ነው። ከእነዚህ ለየት ያሉት ደግሞ ኮሮና የማይበግራቸውና ኮሮናን የሚዘርሩ ጀግኖች መስለው ለመታየት እየጣሩ ነው።

አገራችንን ጨምሮ በአንዳንድ አገራት የዓለም መጨረሻ መድረሱን ወይም አምላክ የሰውን ልጅ እቀጣለሁ ያለበት እቅዱ እየተፈጸመ መሆኑን የሚያስረዳ ስሌት ሊሠሩ እየሞከሩ መርዶ እያስተጋቡ ነው። ቀደም ብሎ ለእይታ የበቃውን 2012 የተባለውን የእልቂትና የፍጻሜ ፊልም እያወሱ፣ ፈረንጆች አቆጣጠሩ በእነሱ የጊዜ ቀመር የሚፈጸም መስሏቸው ያንን ፊልም በዚያ አርእስት መሥራታቸውን፤ ነገር ግን የእልቂቱ ጊዜ ሊሰላ የሚገባው በእኛው የዘመን አቆጣጠር ስለሆነ ይኸው የእኛ 2012 ከገባበት ጊዜ ጀምሮ እልቂቱ ተከሰተ እያሉ ወሬ እየነዙ ነው።

እንዳሰቡትም ይህን ወሬአቸውን ቁም ነገር ብለው የሚያስተጋቡ መገናኛ ብዙኀን አልታጡምና፣ ካባቸውን ደርበው በተለያዩ ሚዲያዎች ብቅ እያሉ ወሬአቸውን ነዝተውት፣ በጥቂት ሰዎች ቢሆንም እንደ አዋቂ ተቆጥረው በየመንደሩ ሥማቸው እየተነሳላቸው ነው። ከኮሮና ቫይረስ ያመለጠውን የሚያጠፋ ተወረዋሪ አካል ከወዲያኛው አጽናፈ ዓለም ወደ ምድራችን እየተወነጨፈ በመምጣት ላይ መሆኑን የሚናገሩም አሉ።

መሰል ዜናዎች መርዶ በማወጅ ታላቅ ለመባል በሚፈልጉ ሰዎች አማካኝነት እየተሰራጩ ነው። አንዲትን ደራሲ እየጠቀሱ ‘ኮሮና’ በሚል ሥያሜ የሚጠራ አጥቂ ሕዋስ እንደሚመጣ ትንበያ ነበረ የሚሉና ኮሮና የሚባል ወረርሽኝ ሕዝብ እንደሚጨርስ ከ500 ዓመታት በፊት ተተንብዮ ነበር እያሉ የእልቂቱ ጊዜ ደረሰ ወዘተ የሚሉ ብዙዎች ናቸው።

ችግሩን ከእምነትና ከአምላክ ቁጣ ጋር ስለሚያገናኙ አዋቂ ነን ባይ ግለሰቦችና ስለ ጭፍን ተከታዮቻቸው አንድ ነገር ማለት ተገቢ ነው። ችግሩን ከእምነት ጋር የሚያያይዙ የእምነት መሪዎችና ተከታዮቻቸው፣ የእምነት መጽሐፎቻችን ናቸው የሚሏቸውን ጽሑፎች መለስ ብለው ይመልከቱ። አምላክ ቁጣውን ሲልክ ሁሉንም አብሮ የሚጨፈልቅ አለመሆኑን፣ የኖህ ዘመንና የሰዶምና ጎሞራ የቅጣት ታሪኮች ውሃውና እሳቱ ለቅጣት ከመውረዱ በፊት አምላክ ሕዝቦቹን አስቀድሞ እንደሰበሰበ (የኖህንና እና የሎጥን ቤተሰቦችን) እንደሚናገሩ ማስታወስ ተገቢ ነው።

የኖህ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስና በቅዱስ ቁርዓን ላይ ብቻ ሳይሆን ከመጠነኛ ወይም ከሰፊ ልዩነቶች ጋር በኤዥያና በላቲን አሜሪካ በሚገኙ የጥንታዊ ሐይማኖታዊ አስተምህሮዎችና አፈ-ታሪኮች ውስጥም ይገኛል።

ከዚህ ቀደም በሩሲያና በአንዳንድ የኤዥያ አገራት የዓለም መጨረሻ መጣ የሚሉ ግለሰቦችን ስብከት አሰምተው ብዙዎች ተስፋ በመቁረጥ ለችግር መዳረጋቸው (ራሳቸውን በጅምላ ያጠፉ ሰዎችን ጨምሮ)፣ አላስፈላጊና የማያዋጣ ከለላ ፍለጋ ተሰባስበው ለእልቂት የተዳረጉ መኖራቸው፣ ለብዝበዛና ለኪሳራም የተጋለጡ እንደነበሩ ወዘተ… ታሳቢ ተደርጎ ሕዝብ ሊጠነቀቅ ይገባዋል።

ማስተዋል በጎደለው እምነት ወይም ‹እምነተ ደካማ› ይሉኛል በሚል ይሉኝታ፣ ራስን ለአደጋና ለችግር ማጋለጥ ተገቢ አይደለም። ከሁሉም በላይ ፈጣሪህን አትፈታተን የሚለው ሕግ መቼ እንደሚሠራ በጽሞና ማሰብ ተገቢ ነው። ራስን በአጉል ድፍረት ወይም በደካማ (እውቀት በጎደለው) እምነት፣ አደጋ ውስጥ እየወረወሩ ስለ መዳን ማሰብ አጠያያቂ ነው። ይህን ማለት ያስፈለገው ሳይንሳዊ የጥንቃቄ ጥሪዎች በተደጋጋሚ ሲጣሱ ከሚስተዋሉባቸው ቦታዎች ውስጥ የእምነት ተቋማት ተጠቃሾች በመሆናቸው ነው።

ጀርመን ለበሽታው ከፍተኛ ክብደት በመስጠት፣ ቫይረሱ ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ዜጎቼን ሊያጠቃ ይችላል ብላ ችግሩን በሰፊው አይታ ሕመሙን ለመዋጋት 500 ቢሊዮን ዩሮ መድባ ሰፊ ዝግጅት አድርጋለች። ከዚህ ውስጥ ወደ 160 ቢሊዮን ዩሮው ከቤት እንዳትወጡ፣ ሥራ አቁሙ የሚል ክልከላ ሲመጣ ገቢአቸው ለሚመናመንና እጅ ለሚያጥራቸው ጀርመናውን መደጎሚያ የሚውል ነው። አሜሪካ ለተመሳሳይ ተግባር ወደ አንድ ትሪሊዮን ዶላር ለመመደብ የኢኮኖሚ ዘርፍ ባለሙያዎቿና ፖለቲከኞቿ ውይይት ላይ ናቸው።

አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሚሴ፣ ጋርዲዮላና ሌሎች የስፖርቱ ዓለም ቤተሰቦች እያንዳንዳቸው አንድ ሚሊዮን ዩሮ ለሕክምና ማእከላትና ለዕርዳታ ሰጭ ተቋማት ለግሰዋል። ክርስቲያኖ ሮናልዶ ቅንጡ ሆቴሎቹን ለማገገሚያነት አበርክቶ፣ በእነዚያ ሆቴሎች ለሚገለገሉ ታማሚዎችና በዚያ ለሚሠሩ የሕክምና ባለሙያቸው የሚያስፈልገውን ወጭ ራሱ ሮናልዶ እየሸፈነ መሆኑ ተሰምቷል።

የሕክምና ባለሙያዎች ኮሮናን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመዋጋት ‘ምን ዓይነት’ የጥንቃቄ እርምጃ ተወሰደ በሚለው ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን የጥንቃቄ እርምጃው ‘መቼ’ ተወሰደ የሚለው ጥያቄ በጣም ወሳኝ መሆኑን እየተናገሩ ነው። መከረኛዋ ጣሊያን የጎደላት ይህ መሆኑንም ጣሊያናውያኑን ጨምሮ የሌሎች አገራት ባለሙያዎች ሲናገሩ ይሰማሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት የሚወስደውን እርምጃ የጎረቤት ኬንያ መንግሥት ከወሰደው እርምጃና እርምጃዎች ከተወሰዱበት ጊዜ ጋር ማነጻጸሩ ኢትዮጵያ ምን ያህል ወደ ኋላ እንደቀረች ያሳያል። የኬንያው መሪ ኡሁሩ ኬንያታ ባለሥልጣኖቻቸው የሥራ መስካቸው፣ የሙያና የኃላፊነት ደረጃቸው፣ መንግሥትና ሕዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት መሰረት አድርገው የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደርጉ ዘንድ መመሪያና መሳሰቢያ ሰጡ እንጂ፣ ራሳቸውን የአገሪቱ ብቸኛ አዳኝና አዋቂ አድርገው ለማሳየት ድራማ መሥራቱን አልወደዱትም። ኡሁሩ በዚህ በሽታ ምንም ዓይነት ታዋቂነትንና ለማግኘትና የፖለቲካ ቁማር ለመጫወት ሲፈልጉ አልታዩም።

ሁሉም የኬንያ ባለሥልጣናት የተመደቡበት ሙያ፣ ኃላፊነትና የግል ሕሊና ተገቢ ነው ብሎ የነገራቸውን ሥራ በጥድፊያ በመሥራት ላይ ናቸው። ኡሁሩ ኬንያታም በሙያና በዕውቀት ዘርፎች ጣልቃ እየገቡ ባለሙያዎችን ለማዘዝና የባለሙያዎችን ውሳኔዎች አሽቀንጥረው በመጣል፣ የሕዝብ ሕይወት በእሳቸው እጅ ውስጥ ያለ፣ ሁሉንም እንዳሻቸው ሊያደርጉ የሚችሉ፣ ሁሉን ቻይ መሪ የሚል ሥም ለማትረፍ የሚዲያ ላይ ድራማዎችን አልሠሩም። ሕይወት ለማትረፍ በመሯሯጥ ላይ ናቸው። ኡሁሩ ኬንያታ በእውቀትና በሙያቸው (በትምህርትና በተሞክሯቸው) ተማምነው በሚኒስቴርነትና በሌሎችም የሥራ ዘርፎች ለኃላፊነት ካበቋቸው ባለሥልጣኖቻቸው ጋር በመሆን የሰው ሕይወት ለመታደግ፣ ፈጥነውና ተባብረው በመሥራት ላይ ናቸው።

‘አትሌቲክስ ኬንያን’ የተባለው የኬንያ አትሌቶች ተጠሪ (የኢትዮጵያ እትሌቲክስ ፌዴሬሽን አቻ ተቋም ነው) የኬንያ አትሌቶች ወደ የትኛውም አገር በመጓዝ ውድድር እንዳያካሂዱ ያገደው ቀድሞ ነው። ይህም የአውሮፓ እግር ኳስ ጨዋታዎችን ማካሄድ ሳያቋርጡ፣ ጣሊያንን የመሳሰሉ አንዳንድ አገራት በዝግ ስቴዲዮም ጫዋታዎችን የማካሄድን አማራጭን እንደ አዋጭ ዘዴ ቆጥረው በነበሩበት ጊዜ ነው። ይህ የኬንያ የስፖርት ተቋም ሕዝብና መንግሥት የሰጡትን ኃላፊነት የመወጣት መብቱን ተጠቅሞ፣ ለአገርና ለአትሌቶች የሚጠቅም ውሳኔ ሳይረፍድ በጊዜ አስቀምጧል።

የኬንያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የነበረበትን አኅጉር ዐቀፍ ጨዋታ ሰርዞ፣ የጨዋታ ፕሮግራሞች እንዲቀየሩ ወደ ካፍ ጥያቄ ሲልክ ፎርፌ ከተሰጠም፣ ዋንጫ ከሕዝብ ደኅንነት አይበልጥም የሚል ግልጽ አቋም ይዞ ነው። የኬንያው እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይህን ውሳኔ ባሳለፈበት ጊዜ፣ በአፍሪካ ቀርቶ በአውሮፓ ውድድሮችን ለማቆም የሚያስብ ብዙ የስፖርት ተቋም አልነበረም።

እነሆ ዛሬ በአውሮፓ ምድር ብዙ እግር ኳስ ተጫዋቾች፣ አሠልጣኞች፣ የቡድኖች ኃላፊዎችና የመሳሰሉት የስፖርቱ ቤተሰቦች የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ሆነው ዜና ለመሆን በቅተዋል።

ገቢው በመዳከሙ ምክንያት በመንገዳገድ ላይ ያለው የኬንያ አየር መንገድ፣ በረራዎችን ለመሰረዝ ዳተኛ ሆኖ የተወሰኑ ጊዜያትን በነበረበት ሁኔታ መብረሩን ቀጥሎ ነበር። በዓለም ዙሪያ የኮሮና ቫይረስ ችግር መስፋፋትን የታዘበው የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ አየር መንገዱን ችሎት ፊት አቅርቦ ሥራውን በነበረበት መቀጠሉ በኬንያና በሕዝቦቿ ላይ አደጋ እንደማይጋርጥ ያስረዳ ዘንድ የጠየቀው ከብዙ ሳምንታት በፊት ነው። አየር መንገዱ የተወሰኑ ማስተካከያወችን ለማድረግ የተገደደውም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነበር።

ኬንያ ጥቅጥቅ ብለው በተሠሩ ቤቶችና በተጨናነቁ መንደሮች ውስጥ የሚኖሩ፣ ሳሙናና ሌሎች የንጽሕና መጠበቂ ኪሚካሎች ገዝተው እየተጠቀሙ ረዥም ጊዜ መዝለቅ የማይችሉ ዜጎቿን እንዴት መርዳት እንደሚቻል በጽሞና እያሰበች ያለች አገር ናት። በአሜሪካና በአውሮፓ ሲደረግ እንደሚሰማው፣ ሰዎችን ለወርና ለኹለት ወራት ከቤት አትውጡ ብሎ ትዕዛዝ ማስተላለፍ ቀላል ቢሆንም፣ ይህን ትዕዛዝ መተግበርና ማስተግበር ግን በጣም ከባድ ነው። ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ የሆኑ ወገኖችን ለተራዘመ ጊዜ ከቤት አትውጡ ማለት በኮሮና ከምትሞቱ በቤታችሁ ውስጥ በረሀብ ጠውልጋችሁ እለቁ ብሎ እንደ ማዘዝ ያህል የሚቆጠር ነው።

በተጠጋጉ ቤቶች፣ አዳራሽ የመሳሰሉ ሰፋፊ ሕንጻዎችን እንደ ነገሩ ከፋፍለውና ተጋርተው የሚኖሩ ወገኖችን ወዘተ… እዚያው ታፍናችሁ ተጨራረሱ ብሎ እንደ መፍረድ የሚቆጠር ነውና፣ የኬንያ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ አስቀድሞ መጨነቁ ለሌላውም ትምህርት ሊሆን ይገባል። መንግሥታዊ ጭካኔው ባለበት አገር፣ ያለ ምንም ተጨማሪ ዝግጅት ይህን ትዕዛዝ በአስገዳጅ ሁኔታ ጥቅም ላይ ማዋል ሌላ ችግር እንዲከሰት ያደርጋል። ከቤት እወጣለሁ ለሚለው ከኮሮናና ከረሃቡ በተጨማሪ በጥይት የማሰናበትን ሦስተኛ አማራጭ ለማዘጋጀት የሚጋብዝ ሊሆን ይችላልና ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግርን ለማቃለልና ከልክ በላይ የሚጭኑ የትራንስፖርት ዘርፎችን ለማስተካከል የመንግሥት መኪናዎች ይመደባሉ ቢባልም፣ ይህ እየተስተዋለ አይደለም። የመንግሥት መኪኖችን ወደዚህ ሥራ ከማስገባት የንግድ መኪኖችን በሥራው ላይ ድጎማ እየሰጡ ማሰማራት ጥሩ አማራጭ ሊሆን ይችላል። በትራንስፖርት ለመጠቀም ተጠጋግቶ መሰለፍ ይቀራል ቢባልም፣ ይህን የሚያሳካ ተጨማሪ ዝግጅት ስለሌለ ሲተገበር አይታይም። ወደ ብዙ ብዙ አቅጣጫዎች የተከማ አውቶብሶችና ታከሲዎች ጉዞ ለመጀመር የሚያሳፍሩባቸው ቦታዎች ያው የቀድሞወቹ ስለሆኑ፣ ተራርቆ መሰለፍን ከባድ አድርጎታል።

ኮቪድ-19 ቫይረስና ተከትሎት የሚከሰተው ችግር በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር ከኅዳር 2019 ጀምሮ የተነሳ በመሆኑ፣ የእጭር ጊዜ እርምጃ መፍትሔ ላይሆን ይችላል። በአገራችን የሚካሄዱ የጥንቃቄ እርምጃዎች ታድያ ለ15 ቀናትና ለአንድ ወይም ኹለት ወር ብቻ እንደሚካሄዱ ተደርጎ በማሰብ የዘመቻ ሸብ-ረብ ዓይነት ሥራዎች ሊታሰብባቸው ይገባል። እነዚህ የጥንቃቄ እርምጃዎች በቻይና እስከ አሁን ወደ 5 ወራት ለሚሆን ጊዜ እየተወሰዱ መሆኑን በማወቅ በእኛ አገርም የረዥም ጊዜ ሥራዎችን ሊጠይቅ እንደሚችል በመገመት ወገብን ጠበቅ ማድረግ ተገቢ ነው።

ስለዚህ በታክሲዎችና በአውቶብሶች ውስጥ ከልክ በላይ ተጠጋግቶ መጓዝ ይቀር ዘንድ አንበሳና ሸገር የሚሠሩት ሥራ የሚመሰገንና በዚሁ ሊቀጥል የሚገባው ነው። ቢሆንም ድርጅቶቹ አቅም እንዳያንሳቸውና ሥራ ለማቆም እንዳይዳረጉ የመንግሥት ድጎማ ያስፈልጋቸው እንደሆነ፣ ተጨማሪ አውቶብሶች ወደ ሥራ ገብተው አሽከርካሪዎችና ረዳቶቻቸው ረዘም ያለ ሰዓት የሚሠሩ ከሆነም፣ ለእነሱም የጥንቃቄ መሣሪያዎችና ማበረታቻ ሊያስፈልጋቸው ስለሚችል፣ ከወዲሁ ሊጤን ይገባዋል።
የአንበሳና የሸገር አውቶብሶች፣ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ደግሞ ለመንግሥት ሠራተኞች አገልግሎት የሚሰጡ የፐብሊክ ሰርቪስ አውቶብሶች በወንበር ልክ ብቻ እየጫኑ እንደሚሠሩ ይታወቃል። ይህም ጥሩ የጥንቃቄ እርምጃ ነውና ሊመሰገን ይገባዋል። ነገር ግን እነዚህ የሸገርና የአንበሳ አውቶብሶች ብዙዎቹ ከመነሻ ቦታቸው ስለሚሞሉ በመንገድ ላይ ባሉ ፌርማታዎች ትራንስፖርት የሚጠብቁ ዜጎች ችግር ውስጥ እየወደቁ ነው።

የመንግሥት ሠራተኞችም ተጨማሪ የፐብሊክ ሰርቪሰ አውቶብሶች ሳይመደቡ በልክ ስለሚጭኑ ብዙ ሠራተኞችን ጥለው ለመሄድ ይገደዳሉ። ስለዚህ ይህ ጥሩ ጅምር ‘መመሪያዬ ከተተገበረልኝ ሌላው የራሱ ጉዳይ’ በሚል ሳይሆን፣ ክፍተቱ ተቀርፎለት ቢቀጥል ውጤታማ ይሆናል። በመገናኛ ብዙኀን ላይ ሕዝቡ በእግሩ መሄድ አይወድም እየተባለ ክፍተቱን ለማቃለል የሚሞክሩ ወገኖችና እነሱን የሚያስተናግዱ ጋዜጠኞች፣ የስህተት አበረታቾች እየሆኑ መሆኑን ሊያውቁት ይገባል።
እነሱ ልብ ያላሉት ጉዳይ ጸሐይና ዝናብ በማይኖርበት ጊዜ ድሮውንም ቢሆን እጅግ በጣም ብዙ ሕዝብ በእግሩ የሚጓዝ መሆኑን ነው። ከፒያሳ አዲሱ ገበያ፣ ከአብነት/መርካቶ ጦር ኃይሎች፣ ከፒያሳ አራት ኪሎ፣ ከአራት ኪሎ ቀበና፣ ከአራት ኪሎ ስድስት ኪሎ ወዘተ…እና በተቃራኒው አቅጣጫ የእግር ጉዞ ማድረግ የተለመደ ነው። ከፒያሳ ዓለም ባንክ፣ ከገደራ መርካቶ፣ ከመገናኛ ጦር ኃይሎች ወዘተ ግን የሚሞከሩ አይደሉም። ከድካሙ በተጨማሪ ከሥራ ወጥቶ ረዥም መንገዶችን በእግር መጓዙ ይልቁንም ሲጨላልም፣ ለችግር ያጋልጣል።

በትራንስፖርት ለመጠቀም ተጠጋግቶ መሰለፍ ይቀራል ቢባልም፣ ይህን የሚያሳካ ተጨማሪ ዝግጅት ስለሌለ ሲተገበር አይታይም። ወደ ተለያዩ አቅጣጫወች የከተማ አውቶብሶችና ታክሲዎች ጉዞ ለመጀመር የሚያሳፍሩባቸው ቦታዎች ያው የቀድሞዎቹ ስለሆኑ፣ ተራርቆ መሰለፍን ከባድ አድርጎታል።

ለምሳሌ በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ ዙሪያ፣ ቁጥር 3፣ 5፣ 37፣ 59፣ 103 የሚመጀምሩት አንድ ቦታ ላይ ሲሆን፣ ከእነዚህ በተጨማሪ ከአዲሱ ገበያ፣ ከሽሮ ሜዳና ስድስት ኪሎ፣ ከመገናኛ፣ ከፈረንሳይና ከጉራራ ወዘተ… መጥተው ወደ መርካቶ፣ ለገሐር ወዘተ.. የሚቀጥሉ አውቶብሶችም በዚሁ ቦታ እየቆሙ ሰው ያወርዳሉ ይጭናሉ። ስለዚህ መራራቅ የሚባለው ነገር አይታሰብም። የእነዚህ አውቶብሶች መቆሚያ ዘርዘር ካልተደረገ በዚሁ ይቀጥላል።

ይህን መሰል ችግር በመገናኛ፣ በጀሞ ቁጥር አንድ፣ በሜክሲኮ፣ በጦር ኃይሎችና በመሳሰሉት ቦታዎች መመልከት ይቻላል። እነዚህ ጉዳዮች ችላ ተብለው ሕዝቡ አልሠለጠነም፣ ሕዝቡ ግድ የለውም፣ ሕዝቡ ግንዛቤ ይጎድለዋል ወዘተ… እያሉ፣ በየሚዲያው ማቅራራት የራስን ግንድ የሚያክል ስህተት ችላ ብሎ በሌሎች ጉድፍ የምታክል ስህተት እንደ መሳለቅ ይቆጠራል።

የፍጆታ አስቤዛዎችንና ሌሎችንም አስፈላጊ ነገሮች በሚያቀርቡ መደብሮችና የገበያ ስፍራዎች፣ ሰልፎች የተለመዱ ናቸው። ሰልፉን ተራርቆ መሰለፍና አለመሰለፍ ደግሞ ቦታ፣ ጊዜ፣ የአቅርቦቱ መጠንና የአስተናጋጆች የሥራ ሥነ ምግባር ይወስነዋል። የአስፈላጊ ነገሮች እጥረት ሳይቀረፍና ስርጭቱንም በየአቅራቢያውና በየአካባቢው ማድረግ ሳይቻል ስለሰልፍ ስነ-ስርዓት ብቻ ማውራት ተገቢ አይደለም። የተሰለፈ ሰው የፈለገውን ሳያገኝ አቅርቦቶች እያለቁና በድጋሚ ለመምጣት ኹለትና አራት ሳምንት እየተጠበቀ ሰው ተረጋግቶ እንዲገበያይ ማድረግ አይቻልም።

አልኮል፣ ሳኒታይዘር፣ ማስክ ወዘተ…. ለአፍታም ሳይቆዩ ከገበያ የታጡት መንግሥት ምንም ዓይነት ዝግጅት ሳያደርግ በመቆየቱ መሆኑን መካድ አይገባም። መንግሥት የአልኮል መጠጥ ፋብሪካዎችና ሌሎች እነዚህን ማምረት የሚችሉ ኢንዱስትሪዎችን በዘመቻ መልክ እነዚህን ተፈላጊ ነገሮች እያመረቱ እንዲቆዩ አድርጎ ቢሆን ኖሮ፣ እስከ አሁን አልፈታ ያለው ችግር አይኖርም ነበር። አሁንም ቢሆን፣ ኢንጅነር ታከለ ዑማን የመሳሰሉ ባለሥልጣናት አልኮልና ሳኒታይዘር እየተሸከሙ ሚዲያ ላይ የመታየት ሥራ ከሚሠሩ ለኬሚካሎቹ በበቂ መጠን መመረት ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር እየተመካከሩ መመሪያና ትዕዛዝ ቢሰጡ የበለጠ ጠቃሚ ይሆናል።

አሁን ሕዝብ የሚፈልገው ሳኒታይዘር፣ አልኮል፣ ማስክ ተሸክመው የሚታዩ ሰዎች፣ ፎቶዎችና ቪዲዮዎች ሳይሆን፣ በሸማቾች ማኅበራት ሱቆች ዙሪያ የተሠሩ ስለ እነዚህ ቁሳቁሶች ስርጭት የሚሠሩ የፕሮፓጋንዳ ወሬዎችን አይደለም። ይልቁንም ራሳቸውን ቁሳቁሶቹንና ኬሚካሎቹን ነው። ምክንያቱም ሕይወቱን የሚታደጉለት እነሱ ራሳቸው እንጂ የእነሱ ፎቶና የእነሱ ወሬ አይደለም። ባለሥልጣናትና ካድሬዎች በዚህ ዓይነት ሕዝብን ደልለን፣ አጃጅለን፣ አሳምነን እንወደዳለን፣ እንከበራለን ብለው ማሰብ አይገባቸውም። እነ ፋና፣ ዋልታ፣ ኢቲቪ፣ የኢትዮጵያ ሬዲዮም ሆነ ሌሎች መገናኛ ብዙኀን ሕዝብን እያታለሉ እንዳልኖሩ ከ2008 እስከ 2010 የታየው ሕዝባዊ ተቃውሞ ትልቅ ማስረጃ ነው።

አሁንም በዚህ የችግር ወቅት የሚሠሩ ፕሮፓጋንዳዎች፣ ገጽታን የማሳመር ወሬዎች፣ ብልጽግና ፓርቲንና ባለሥልጣናቱን አሳቢና ተቆርቋሪ ለማስመሰል የሚሠሩ ድራማዎች በደልን፣ ግፍን፣ ኢ-ተአማኒነትን ከመከመር ያለፈ ውጤት አይኖራቸውም።

በክልሎች የሚገኙ አንዳንድ የወረዳዎችና የከተሞች የብልጽግና ፓርቲ ሹመኞች በኮሮና ቫይረስ ለየት ያለ ፎቶ ተነስተው ለመንጎማለል የሚሞክሩ ዓይነት ሰዎች ሆነው ከርመዋል። ኮሮናን ክፉኛ የመዳፈር ሥራ እየሠሩ ነው የሰነበቱት። ከየገጠሩና ከየመንደሩ የጠሯቸውን በመቶዎች የሚቆጠሩ የብልጽግና ፓርቲ አባላትን በሥልጠና ሥም በአንድ አዳራሽ አጉረው ሥልጠና ሲሰጡ ታይተዋል። ከነዚህ የብልጽግና ሹመኞች አንዱ፣ ብልጽግና ለኮሮና እንደማይበገር ይህ አይበገሬነት በብልጽግና ስብሰባዎች እየተገለጸ መሆኑን በመጎረር የጻፈው መልዕክት ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ተቀባብለውት ሕዝብን አሳዝኖና አስደንግጦ ከርሟል።

የብልጽግና ካድሬዎች አጉል ድፍረት ለሥልጠና የተገኙ ሰዎችን፣ እነሱ ወደ መኖሪያቸው ሲመለሱም የአካባቢያቸውን ኅብረተሰብ፣ ከዚም አለፍ ብሎም በዙሪያቸው የሚገኙ የሌሎች ወረዳዎች ኅብረተሰብን ለአደጋ የሚጋብዝ ነውና፣ በአስቸኳይ ሃይ ባይ ያስፈልገዋል። በዚህ ዓይነት መንገድ ታዋቂነትንና ጀግንነትን ለማግኘት መባዘን አላዋቂነትንና ቂልነትንና ከማሳየት ያለፈ ፋይዳ የለውም።

መንግሥት እያንዳንዱን ነገር ለመወሰን ጭራ በሆነበት በዚህ የአደጋ ጊዜ፣ ደኅና አቅም አላቸው የሚባሉት የሕክምና ማእከላትና በርካታ የሕክምና ባለሙያዎች ከሚገኙባቸው አዲስ አበባን ከመሳሰሉ ከተሞች ርቀው በሚገኙ ወረዳዎችና ገጠር መንደሮች የኮሮና ቫይረስ መዛመት የሚያስከትለውን ችግር አቅልሎ መመልከት ከቁጥጥር ውጭ የሆነ እልቂትን ሊስከትል እንደሚችል መዘንጋት አይገባውም። አንዳንድ የሐይማኖት ሰዎች ‹ኮሮናን እንበትነዋለን፣ ሰይጣንን ያሸነፈ እምነታችን ሰይጣን የፈጠረው ኮሮና ድራሹን ያጠፋዋል› እያሉ ትንንሽና ታላላቅ ስብሰባዎችን መጥራት መጀመራቸው አይዘነጋም። በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ዳርና ዳር የሰቀሏቸው ግዙፍ የጥሪና የቅስቀሳ ፖስተሮች አሁንም ባሉበት አሉ። የእነዚህ ሰዎች ግርግር ሳይበቃው ሕዝብ በብልጽግና ካድሬዎች ጀብደኝነት ስጋት ላይ ሊወድቅ አይገባውም።

በቤተ-መንግሥት አካባቢም በኮሮና ፎቶ የመነሳት አዝማሚያ አለ። ከጥቂት ቀናት በፊት ፋና የተሰኘው የብልጽግና ፓርቲ መገልገያ ሚዲያ ‘ዐቢይ-ጃክ ማ ኢንሽዬቲቭ’ ለኢትዮጵያና ለሌሎች የአፍሪካ አገራት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያዎችን፣ የምርመራ ቁሶችንና የአፍ መሸፈኛ ጭምብሎች የሚገኙባቸው ቁሳቁሶች በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሊያሰራጭ ነው የሚል ዜና አሰምቶን ነበረ። ይህን ዜና ተቀብለው አንዳንድ ሬዲዮ ጣቢያዎች የአዲስ አበባ ወኪሉን ወሬ ተቀብሎ ጉዳዩን ዜና ያደረገው ቪኦኤን ጨምሮ ‘የዐቢይ-ጃክ ማ ፋውንዴሽን’ አፍሪካን ስለ መርዳቱ ወሬ አሰራጭተዋል።

የባለጸጋው የጃክ ማ ሥም በዚህ ጉዳይ ውስጥ የገባው እሳቸው ካላቸው የግል ሃብት ዘግነው የገዙትን ለእርዳታ ስለለገሱ ነው። ታዲያ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሥም በዚህ ጉዳይ ውስጥ እንዴት ገባ? እርዳታው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ስለሚሰራጭ ነው? ከሆነም አየር መንገዱ የሕዝብ ሃብት ነውና፣ መጠቀስ ያለበት የኢትዮጵያ ሥም ወይም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊሆን አይገባውምን?

ለመሆኑ ይህን ‘የዐቢይ-ጃክ ማ ፋውንዴሽን’ ወይም ‘የዐቢይ-ጃክ ኢንሼቲቭ’ ሚስተር ጃክ ማ ወይም የቻይና ሕዝብ ያውቀው ይሆን? ነገሩ እንደዚህ አይመስልም። ዥንዋ (XINHUA) የተሰኘው የቻይና መገናኛ ብዙኀን ዜናውን “Jack Ma Foundation donates masks, testing kits to Africa for COVID-19 control” በሚል አርእስተ ዜና ነው ያሰራጨው። ዐቢይን አልጠቀሰም።

ይህ የዥንዋ ዜና ጃክ ማ ልገሳውን ያደረጉት ያለ ማንም ጥያቄና ጉስጎሳ፣ በገዛ ፈቃዳቸው አፍሪካን ከእልቂት ለመታደግ በመነሳሳት መሆኑን ያስረዳል። እርዳታውም ለ54 የአፍሪካ አገራት የሚሰጥ ሆኖ ለእያንዳንዱ አገር 20 ሺሕ የኮሮና ሕመም መመርመሪያ ኪት፣ 100 ሺሕ ማስኮችን፣ አንድ ሺሕ ለሕክምና ባለሙያዎች የተዘጋጁ ሙሉ አካልን የሚሸፍኑ ልብሶችንና የፊት መከለያዎችን ያካተተ እርዳታ እንደሚደርሰው ያበስራል።

ይህን የጃክ ማ እርዳታ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አስተባባሪ ሆነው ለአፍሪካ አገራት እንደሚከፋፈል ዥንዋ ያሳውቃል። ከዚህ አልፎ ግን ‘ዐቢይ-ጃክ ማ’ የሚል ነገር አይናገርም። የኢትዮጵያ መንግሥትና ዐቢይ አሕመድ እርዳታውን ተቀብለው ለአፍሪካ አገራት ለማሰራጨት ፈቃደኛ በመሆናቸው ጃክ ማ አመስግነዋል ያለው ዥንዋ፣ የሩዋንዳ የልማት ቦርድ እና የሩዋንዳ ባዮ-ሚዲካል ሴንተርም የጃክ ማ ምስጋና የተቸራቸው መሆኑን ዥንዋ ዘግቧል።

ይህ ዜና ፋና ላይ ከቀረበበት መንገድ በሚመሳሰል ሁኔታ በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ፌስቡክ ገጽ ላይም ቀርቦ ነበር። እናም አንዳንዶች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘..እርስዎ ባይኖሩልን፣ እርስዎን አምላክ ባይሰጠን ምን ይውጠን ነበረ…!’ እያሉ ምስጋናቸውን አዥጎድጉደውላቸው ‘የበሬን ምስጋና ወሰደው ፈረሱ…’ አስታውሰውናል።
ሌሎች ደግሞ በዚያው የፌስቡክ ገጽ ላይ ይህን መሰሉ ጨዋታ ቆሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ለመንገር ሞክረዋል። የምዕራብ ኦሮምያ ሕዝብ ከመረጃ መራቅ ያሳሰባቸውና መፍትሔ እንዲሰጣቸው አደራ ያሉም ብዙዎች ናቸው።

ፋና የተባለው የገዥዎች ሚዲያ፣ ተጠምዶበት የነበረው የዐቢይን ፎቶ ይዞ ሰልፍ የመውጣት ወሬዎችን ተጠቅሞ ፕሮፓግንዳ የመሥራት ሱስ በኮሮና ቫይረስ ስለተስጓጎለበት በዚያ ፋንታ ይህን የእርዳታ ዜና በመጠቀም ገጽታ እያሳመርኩ ነው ብሎ ለመስገድ ሊጠቀምበት የፈለገ ይመስላል። በዘመነ ሕወሐት/ኢሕአዴግ እየበለጸጉ የኖሩት ፋናዎች በዘመነ ብልጽግና/ኢሕአዴግም እየበለጸጉ ለመቀጠል የዘየዱ ይመስላሉ። በዚህ ዓይነት የመከራ ወቅትም ጭምር፣ በሕዝብ ሕይወት ቁማር እየተጫወቱ ለገዥዎች እያሸረገዱ ለመበልጸግ መሯሯጥ እስከ መቼ ይቀጥል ይሆን? እስከ መቼስ ነው አዋጭ የሚሆነው?
አገራችንን ሕዝባችንን በሰላም ያቆይልን!
ግዛቸው አበበ / gizachewabe@gmail.com

ቅጽ 2 ቁጥር 73 መጋቢት 19 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com