‹‹ሶደሬ ሪዞርት በኦሮሚያ ክልል መንግሥት ትዕዛዝ ተዘግቷል›› ዲንቁ ደያሳ

Views: 2032

ከ70 ዓመታት በፊት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የተቋቋመው እና በኋላም ወደ ግሉ ዘርፍ እንዲዞር የተወሰነው የሶደሬ ሪዞርት በኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት ትዕዛዝ ባሳለፍነው ሐሙስ መጋቢት17/2012 መዘጋቱን ሪዞርቱ አስታወቀ።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የድርጅቱ ከፍተኛ ባለድርሻ ዲንቁ ደያሳ እንደገለፁት ‹‹ለጊዜው ሪዞርቱ ለምን እንደተዘጋ አላውቅም። እኔ የማምነው ግን ያለአግባብ ግፍ እየተፈፀመብኝ እንደሆነ ነው›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ከአሜሪካ በስልክ ገልፀዋል። የሪዞርቱ አመራሮች ታስረው እንደነበር ዲንቁ አረጋግጠዋል። ‹‹ከእሱ ጋር ስብሰባ ነበረን። ስብሰባውን ትቶ ወደ አሜሪካ ሄዷል›› በሚል ምክንያት እንደያዟቸው ሰምቻለሁ ሲሉም በሪዞርቱ የሚሠሩ አንድ የሥራ ኃላፊ ተናግረዋል።

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከአገር ሸሽተው ወጥተዋል መባሉን ያስተባበሉት ዲንቁ ‹‹ሥራ ስላለኝ ነው የመጣሁት፣ ለመመለስ ደግሞ ያው ሁኔታ አላስቻለኝም እንጂ መመለሴ አይቀርም፣ ማንንም ፈርቼ አልቀርም›› ብለዋል።

የሪዞርቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቢዮት ተመስገን በበኩላቸው ‹‹በማን ትዕዛዝ እንደተዘጋ እና ለምን እንደተዘጋ የምናውቀው ነገር የለም›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የአዋሽ ወንዝን እና በአካባቢው ያሉ የተፈጥሮ የፍል ውሃ ምንጮችን ተተንተርሶ የተቋቋመው ሶደሬ ሪዞርት 2500 ቋሚ ሠራተኞችን የሚያስተዳድር ነው። ሪዞርቱን ከኹለት ዓመት በፊት ከመንግሥት የጠቀለሉት ዲንቁ ከ304 መኝታ ወደ ኹለት ሺሕ መኝታ ለማሳደግ ማስፋፊያ እያካሄዱ እንደነበርም ገልፀዋል።
በ427 ሔክታር ላይ ያረፈውን ይህንን ሪዞርት ዲንቁ በ370 ሚሊዮን ብር አካባቢ ከባለቤታቸው ከሌንሳ ጳውሎስ ጋር ከፍተኛ ድርሻውን ወስደዋል።
አዲስ ማለዳ ማረጋገጠ እንደቻለችውም ጊዮን ሆቴልን ወደ ግል ለማዞር ወጥቶ በነበረው ጨረታ አሸንፈው የነበሩት ዲንቁ፣ እስከ አሁን ግን ውል አልፈረሙም። ‹‹ያስያዝኩትን 68 ሚሊዮን ብር አልመለሱልኝም ወይም ሆቴሉን አላስረከቡኝም›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።

ሪዞርቱ ወደ ሰንሰለት ሆቴልነት ራሱን በመቀየርም በአዲስ አበባ በአዲሱ ገበያ እና በቦሌ አዳዲስ ሆቴሎችን ወደ ሥራ ማስገባቱ ይታወሳል።
አዲስ ማለዳ በሪዞርቱ ከሚሠሩ አንድ የሥራ ሃላፊ እንደሰማቸው፣ ሆቴሉ እንዲዘጋ የተደረገው በፖለቲካዊ ያለመስማማት ነው። ምንጫችን እንደገለፁት በሆቴሉ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ይሰበሰባሉ የሚለው ምክንያት ለመዘጋቱ ምክንያት ሳይሆን አንዳልቀረም ይናገራሉ።

‹‹ሦሰት የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና በ40 ሚሊዮን ብር መንገድ በነፃ እያሠራሁ ነው›› ያሉት ዲንቁ ‹‹ነገር ግን መንግሥት ሊሸለመኝ ሲገባ መንገላታቴ አግባብ አይደለም›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹የገበሬ መሬትን ነክተሃል ለሚሉትም እኔ ሪዞርቱን የገዛሁት ከመንግሥት ሲሆን፣ መንግሥት በሰጠኝ ልክ ብቻ ነው ያለማሁት። ምንም አይነት የግብር እዳም ሆነ ሌላ ወንጀል የለብኝም›› ሲሉ ዲንቁ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ፣ የናፊያድ ትምህርት ቤቶች፣ ሪፍት ቫሊ ሆቴልን ጨምሮ በተለያዩ የአገልግሎት ሥራዎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙት ዲንቁ፣ በኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት ከሚነሱ ቢሊዮነሮች መካከል ናቸው። በቅርቡም ሀያት ቲቺንግ ሆስፒታልን ከእናታቸው ዳንሳ ጉርሙ ጋር በመሆን መግዛታቸው ይታወሳል። የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ ባለቤት የሆኑት ዲንቁ፣ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ሃብት እንዳላቸው ይነገራል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አብዛኛው የመንግሥት ሠራተኞች ሥራቸውን ከቤታቸው ሆነው እንዲሠሩ መወሰኑ ይታወሳል። በዚህ ምክንያትም የክልሉን የኢንቨስተመንት ቢሮ ኃላፊዎች በስልክ ለማነጋገር ጥረት ብናደርግም ስለጉዳዩ እንደማያውቁ ገልጸዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 73 መጋቢት 19 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com