የቤት ሠራተኞችን በማሰብ…

Views: 227

የቤት እመቤት የማይከፈላት የቤት ውስጥ ሠራተኛ ስትሆን፣ ተከፍሏቸው በየሰው ቤት የሚሠሩትም የቤት ሠራተኛ ይባላሉ። መሥሪያ ቤት ተቀጥረው የሚሠሩትም በተመሳሳይ የድርጅት ሠራተኛ ናቸው። ቃሉ ለምን እንደ ‹ነውር› እንደሚቆጠር ባላውቅም፣ የቤት ሠራተኛ ሲባል ሰው ድንግጥ ይላል። ሥራ ሁሉ ሥራ መሆኑን ለሚያውቅና ሥራን ለሚያከብር ሰው ግን አዲስ ነገር ያለው አይመስለኝም።

አንድን ቤተሰብ ወይም ላጤ የሆኑ ሰዎችን በተለይም በተመላላሽነት የሚያገለግሉ የቤት ውስጥ ሠራተኞች፣ አሁን የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሥራቸውን ስጋት ላይ ጥሎባቸዋል። ቤተሰቦችም እየተንቀሳቀሱ የሚሠሩት እነዚህ ሴቶች የተለያየ ቦታ የሚንቀሳቀሱ በመሆኑ ተጋላጭ ናቸው ብለው በማመን ከሥራ ያባርራሉ።

ያም ብቻ አይደለም። ቤተሰብ በሚሰባሰብበትና በአንድ ቤት እንዲቀመጥ ግድ በሚልበት ጊዜ፣ ሴቶችም በቤቱ ስለሚገኙ በቤት ውስጥ የተከፋይ ሠራተኛ መኖር እንደ ትርፍና አላስፈላጊ ወጪ የሚቆጠር በመሆኑ ነው። በዚህ መካከል ታድያ የነዛ ሴቶች ሕይወት ለፈተና ተላልፎ ይሰጣል። የራሳቸው ቤተሰብና ልጆች ያሏቸው ከሆኑ ደግሞ ፈተናው እጥፍ ድርብ ይሆናል።

ነገሩ ታድያ ቀላል በሆነ መንገድ በመተሳሰብ የሚዘጋ ነው። ‹ይቅር እንድላችሁ ይቅር ተባባሉ› እንዲል፣ ወይም ‹በጎ የተደረገለት በጎ በማድረግ ይመልስ› እንደሚባለው፣ ቋሚ ደሞዝ ያላቸው ሰዎች መሥሪያ ቤታቸው ደሞዝ እየከፈለ ቤታቸው ሆነው ክፉውን ቀን እንዲያሳልፉ ለማድረግ የሚያስችል በጎነትን አሳይቷል።
‹አያዋጣኝም፤ ስለማትሠሩልኝ አልከፍልም። እንደውም ለእናንተ እከፍል የነበረውን አሁን እቆጥበዋለሁ፣ ትርፍ ወጪ ነው የሚሆነው› ያላለ ብዙ ድርጅት አለ። ደኅና ገቢ ያለው ሥራ ላይ ያሉ ሰዎችም በዚህ ወረርሽኝ ሥራውን እንደ ልብ እንዳይሠሩ ተገድበው ይሆናል እንጂ ደሞዛቸው ግን አልቀረባቸውም።

በአንጻሩ አነስተኛ ገቢ የሚያገኙ በርካታ ሠራተኞች ያሉባቸው ድርጅቶች በእርግጥ ሠራተኞችን ለመቀነስ ተገደዋል። እንዲህ ባለ አጋጣሚ ሁኔታውን ለመረዳት ከባድ ባይሆንም፣ በቤተሰብ ደረጃ ሲሆን ግን ትዝብት መሆኑ አይቀርም። ምክንያቱም ይህ ቀን ማለፉ አይቀርምና መልካም መልካሙን ተለዋውጦ ማሳለፍ ተገቢ ነው።
እናም ተመላላሽ የሆኑ የቤት ሠራተኞችና ቋሚዎቹንም ቀጣሪዎች እንዳያስርቡና በመልካምነት የተሰጣቸውን ቢሰጡ ጥሩ ይሆናል። በተለይም እንደ ኢትዮጵያዊ የመረዳዳት ባህላችንን በዚህ ማሳየት ያስፈልጋል። ክፉ ቀናት እውነተኛ መልኮችን ያሳያሉና፣ ለራሳችንም መልካችንን ለመታዘብ ይረዳናል።

በተመሳሳይ የማይከፈላቸው የቤት ሠራተኞች አሉ፤ የቤት እመቤቶችና እናቶች። ‹የቤት እመቤት› የሚለው ሐረግ አገባቡና አተረጓጎሙ ላይ መጻሕፍትን ማገላበጥ የሚጠይቀን ይመስለኛል። በዚህ አውድ ግን የቤት ውስጥ አድካሚ ሥራን ሲሠሩ የሚውሉ ሴቶች ለምን ‹የቤት እመቤት› እንደሚባሉ ግልጽ አይመስለኝም።
ይሁን! እነዚህ የቤት ውስጥ ብርቱ ሠራተኛ ስለሆኑና ሥራውንም ስለፍቅርና ስለሚወዱት ቤተሰብ እንጂ ስለክፍያ የማያደርጉት፣ ከጥቃት ሊጠበቁ ግድ ይላል። በአንድ ቤት ውስጥ ጥንዶች ተስማምተው የሥራ ድርሻ ተከፋፍለው፣ የቤቱን ወጪ ለመቀነስ ሴቷ፣ ከውጪ ገቢ ለማምጣት ወንዱ ሊሰማሩ ይችላሉ። ይህን ግን ኹለቱንም ሚዛን ላይ ሊያስቀምጥ የሚገባ አይደለም። እናም አንዱን አጥቂ ሌላውን ቻይ የሚያደርግ አንዳች ነገር የለም።

ይህን ክፉ ቀን በመተጋገዝ እንለፈው። በብርታትና በመተዛዘን እንሻገረው። እርግጥ ነው! ማናችን ለመመስከር እንቆያለን የሚለውን አናውቅም። ግን ይህ በትክክል ማለፉ አይቀርም።
ሊድያ ተስፋዬ

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com