ኮሮናና ባለሥልጣኖቻችን!

Views: 116

ከመንግሥት የሚጠበቀውን መንግሥት፣ ከሕዝብ የሚጠበቀውን ከሕዝብ፣ ሁሉም የየድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የሚያሳስቡት ግዛቸው አበበ፣ ባለሥልጣናት በራሳቸው ዐይን ብቻ ሳይሆን ከሕዝብ በኩል ያለውን መረዳት ይገባቸዋል ይላሉ። መንገድ ላይ የሚታዩ የሰዎች እንቅስቃሴና በየስፍራው ያልተወገዱ መጨናነቆች፣ ሰዎች ፈልገው የሚያደርጉት ሳይሆን አማራጭ በማጣታቸው እንደሆነ ሊታሰብ ይገባልም ባይ ናቸው። በመንግሥት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችና እገዳዎችም በጥድፊያ የሚጫኑ እንዳይሆኑና የባሰ ጥፋት እንዳያስከትሉ፣ ከወዲሁ ማሰብ ማሰላሰል ያስፈልጋል በማለት ይሞግታሉ።

ሕዝቡ በመሪዎች ብቃትና ሀቀኛነት ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ ባሳደረበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። የግፍና መከራ፣ የዝርፊያና ማንነትን የማጥፋት ዘመን አከተመለት ተብሎ ተስፋ ሲደረግ፣ ጊዜው ‹የተጠለፈ ለውጥ ጊዜ› ሆነና ከ2010 ጀምሮ ብዙ አለቃና አዛዥ ነን ባዮች በየጎጡ ተነስተው ሕዝብ ሰላሙንና ደኅንነቱን እያጣ፣ አስቸጋሪ በሆነ የኢኮኖሚ ችግር እየተገረፈ፣ በእርግጥም ምን እያስተዳደረው መሆኑን ግራ እያጋባው ባለበት ጊዜ ነው ኮቪድ-19 ተጨምሮበት አጣብቂኝ ውስጥ የገባው። ‹ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ሐኪም አለ!› እያሉ ባለሙያ ዜጎችን የሚያቃልሉ መሪዎች በጫንቃው ላይ በተፈናጠጡበት በዚህ ጊዜ፣ ይህ የጤና ችግር ተከስቷልና ‹ታዲያ እነዚህ አለቆች ባለሙያዎችን እየሰሙ ችግሩን በቅጡ ይይዙት ይሆን?› ብሎ መጠየቅ ተገቢ ጉዳይ ነው።

እስከ አሁንም ችግሩን ለመዋጋት የሚደረጉት እንቅስቃሴዎች፣ የዘገዩና ያልተሟሉ ብቻ ሳይሆኑ ለፖለቲካዊ ፍጆታና ገጽታን ለማሳመር ተብለው የሚደረጉ መስለው የሚታዩ ናቸው።

ሕወሐት/ኢሕአዴግ ቁጥርን መዘንጠፉንም ሆነ ማሳበጡን ባህሉ ያደረገ ድርጅት ነበር። ለችጋር፣ ለረሀብ፣ ለድህነትና ለወረርሽኝ (አተት፣ ወባ ወዘተ..) ስለተጋለጡ ወገኖች ጉዳይ ሲሆን ሚሊዮኖችን ወደ ሺዎች፣ ሺዎችን ወደ መቶዎች፣ መቶዎችን ወደ ዐስሮች እየጎመደ ሙግት ይገጥማል። የኢኮኖሚ ዕድገትን ለመግለጽ፣ የድጋፍ ሰልፍ የወጡ፣ ለምርጫ የተመዘገቡ፣ በምርጫ የተካፈሉ፣ ለሕወሐት/ኢሕአዴግ ድምጻቸውን የሰጡ ሰዎችን ብዛት የሚመለከት ጉዳይ ሲሆን ደግሞ ቁጥሮችን ማሳበጥ፣ እስከ መቶ በመቶ መድፈንንም ቢሆን መዳፈር የለመደ ድርጅት ነው።

የእሱ ውላጅ የሆነው ብልጽግና/ኢሕአዴግም ይህንኑ ባህሉን ጠብቆ እንደሚኖር ወይም ከዚህ ባህሉ በቀላሉና በቅርቡ እንደማይላቀቅ መገመት ይቻላል። ሃቁን እየቆየ ጊዜ ይገልጥልናል። አሁን ግን በጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ በጤና ሚኒስትሯ በኩል ኮሮናን በሚመለከት ይፋ የሚደረጉ ቁጥሮችን ብዙዎች በጥርጣሬ እንደሚያዩአቸው ግልጽ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ይህን የሕዝቡን ጥርጣሬ የተገነዘቡ ግለሰቦችና ቡድኖች በስርዓቱ ኢ-ተአማኒነት ላይ ተረማምደው የየራሳቸውን ፕሮፓግንዳ እየሠሩና ኮሮናን በሚመለከት የተለያዩ መረጃዎችን ይፋ እያደረጉ ነው።

የቀድሞ ሕወሐት/ኢሕአዴጎችን የአሁን ብልጽግና/ኢሕአዴጎችን ለማመን መቸገር በራሱ ሌላ ችግር እንዳያስከትል ያሰጋል። አለማመንና መጠራጠር ደጋግ እርምጃዎችን ጭምር የሽብር መንስኤዎች እንዲሆኑ ሊያደርግ ይችላል። መንግሥት ከተለያዩ ቦታዎች ተጨማሪ የሕክምና መስጫ ማእከላትን፣ መንከባከቢያና ማገገሚያዎችን፣ ከውጭ የመጡ ዜጎች የሚጠለሉባቸው ማቆያዎች ወዘተ እያዘጋጀ መሆኑ ይታወቃል። ይህን መሰሉ ቀድሞ የመጠንቀቅ ሥራ ጥቅሙ ለሁሉም ነው።
ነገር ግን ከእነዚህ ዝግጅቶች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ሆነ ተብሎ እየተጠመዘዙና የጭንቀት መፍጠሪያ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው። እነዚህ ቦታዎች ሲመረጡ ለ100፣ ለ200፣ ለ300 ወዘተ ሰዎች የሚሆን ቦታ ይዘጋጅ የሚለውን ዕቅድ ቀየር አድርገው ተደብቀው የቆዩ 100፣ 200፣ 300 በሽተኞች ሊመጡ ነው እየተባለ ወሬ እየተዛመተ ነው። ለዚህ ወሬ መዛመት ሽብር ለመፍጠር የሚፈልጉ ዕኩያን ብቻ ሳይሆኑ ቦታዎችን በማዘጋጀቱ ሥራ ተሳታፊ የሆኑ ግለሰቦችና የእነዚህ የተመረጡ ቦታዎች አለቆችና ሠራተኞችም ጭምር የሚሆኑባቸው አጋጣሚዎች አሉ።

ስለዚህ በመምረጡ ሥራ የተሰማሩና በተመረጡት ቦታዎች አካባቢ ያሉ ሰዎች፣ ባለሥልጣናትም ጭምር ትክክለኛውን መረጃ በትክክለለኛ መንገድ ማስተላለፍና ራሳቸው ከሚወልዱት ጥርጣሬ ከሚመነጩ አሉባልታዎች እንዲጠበቁ መንገር ተገቢ ነው።

ትልልቅም ሆነ ትንንሽ ባለሥልጣናት አዋቂ ለመምሰል፣ ገጽታን ለማሳመር፣ ለፖለቲካ ቡድን ማስታወቂያ ለመሥራት ወዘተ… ሲሉ አጠያያቂ መረጃዎችን ከማሰራጨት ሊጠበቁም ይገባል። ከመድኃኒትና ከፈውስ ጋር በተገናኘ፣ የፌስቡክ ወሬ ፈጣሪዎች ውዥንብር አልበቃ ብሎ የብልጽግና/ኢሕአዴግ ሚኒስትሮችም ጭምር የኮቪድ-19ን መድኃኒት በሚመለከት ዓላማው የማይታወቅ፣ ጊዜውን ያልጠበቀና ግራ አጋቢ ወሬ መልቀቃቸውም ሌላው ባለሥልጣናቱን ግምት ውስጥ ያስገባ ጉዳይ ነው። ጥቅማቸው የተረጋገጠው የንጽሕና መጠበቂያ ኬሚካሎችን ከየመድኃኒት መደብሮች በበቂ መጠን ማግኘት ያልተቻለበትን ችግር መቅረፍ ሲገባቸው፣ ኮቪድ-19 ወደ ኢትዮጵያ ገባ በተባለ በ10ኛ እና 12ኛ ቀኑ ተስፋ ሰጭ ምርምር ስለመደረጉና ፍንጭ ስለ መገኘቱ የሚያወሩ ሚኒስትሮች ምን ዓይነት አስተሳሰብና ምን ዓይነት ስብዕና እንዳላቸው መገመት በጣም አስቸጋሪ ነው።

ባለሥልጣናት ስለዚህ ችኩል ወሬአቸው ሳይንሳዊ ትንታኔ እንዲሰጡበት ሲጠየቁ፣ ጠያቂዎችን ‹…የሕዝብ ጠላቶችና ምቀኞች፣ መድኃኒት በመገኘቱ የከፋቸው…› ወዘተ እያሉ የሚያጥላሉ ሚኒስትሮች፣ በእርግጥ በአቶ መለስ ዜናዊ መግለጫ ‹ለዘበኝነት የማይመጥኑትን መሾም› የሚለውን መመዘኛ የሚያሟሉ ናቸው ብሎ ለመፍረድ የተመቻቹ ናቸው።

በአሁኑ ሰዓት ባለሥልጣናቱ በየግላቸው የተለያዩ ወሬዎችን እየዘባረቁ ነገሩን ለመሸፋፈን እየሞከሩ ሲሆን፣ በችኮላ ወሬ አልረጨንም ለማለት ምርምሩ ከኢቦላ ጋር ተያይዞ የተጀመረና ለኮቪድ-19 መፍትሔ ሰጭ መሆኑ ፍንጭ የታየበት ነው ብለዋል። በብዙ ያደጉ አገራት ተስፋ ሰጭ ምርምሮች እየተደረጉና ከ50 በላይ በሚሆኑ ‹የሕክምና ቅመሞች› ላይ ሰፊ ሥራ እየተሠራ ቢሆንም፣ አንዳቸውም እንደ ብልጽግና ሚኒስትሮች ነገሩን አዋጅ ለማድረግ አልደፈሩም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሮና ቫይረስን ችግር ተከትሎ ከታዩባቸው አስተዛዛቢ አቋሞች አንዱ በረራዎችን ባሉበት እንዲቀጥሉ ማድረጋቸው ነው። መቼም እሳቸው እየከለከሉ አየር መንገዱ በገዛ ፈቃዱ በረራ አይቀጥልምና ጉዳዩ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ራስ የሚወርድ አይደለም። በረራው ባለበት ቀጥሎ፣ ኮቪድ-19 ወደ ኢትዮጵያ ገባ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ሕመሙ የተገኘባቸው ሁሉ ከውጭ የመጡና ከእነሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች መሆናቸው በተደጋጋሚ እየታየ በረራዎችን የማቆምም ሆነ የመቀነስ አዝማሚያ ሳይታይ ቆይቷል።

ነገር ግን የአየር ክልላቸውን ለበረራዎች የሚከለክሉ አገራት ቁጥር እየበዛ ሲመጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በረራ ስለመከልከል መናገር ጀምሩ። በቅርቡም ወደ 80 ዓለም ዐቀፍ መዳረሻዎች ሲደርጋቸው የነበሩ በረራዎች መቆማቸውን መንግሥትና አየር መንገዱ ይፋ አድገዋል። ይህ እርምጃ የዘገየ አይደለምን? እነዚህ 80 መዳረሻዎች የውጭ በረራ ወደ አየር ክልላቸው ድርሽ እንዳይል አስቀድመው የከለከሉትን አገራት (መዳረሻዎች) ይጨምራልን? የማይጨምርና እነዚህ 80ዎቹ መንግሥት በራሱ ውሳኔ ብቻ በረራ ያቆመባቸው ከሆኑ የሌሎቹ ዕገዳ ጨምሮ አየር መንገዱ በረራ የማያደርግባቸው መዳረሻዎች ጠቅላላ ቁጥር ስንት ደረሰ?

እዚህ ላይ የመንግሥት ስህተት ግልጽ ነው። በዚህ ላይ ደግሞ በረራዎች አለመታገዳቸው ወይም አለመቀነሳቸውን ዕውቀትና ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ ለማስመሰል ፕሮፓጋንዳ እየተሠራ ነው። ከዚህ አሳፋሪው ፕሮፓጋንዳ ውስጥ በረራዎች ያልተከተከሉት መድኃኒቶችና መሰል የሕክምና ቁሶች በአውሮፕላን ስለሚመጡ በረራ መከልከል እንዳልተቻለ ተደርጎ የተሰጠው መሸፋፈኛ ይገኝበታል። ቀድሞውንም ቢሆን መድኃኒትም ሆነ ሌላው ቁሳቁስ በጭነት አውሮፕላን (በካርጎ) ወይም በጭነት መርከብ የሚመጣ መሆኑ የታወቀ ሆኖ ሳለ፣ እንደገናም በረራ ያገዱ አገራት ሁሉ የጭነት አውሮፕላኖችን አለመከልከላቸውን በግልጽ እየታወቀና እነሱም በገሃድ እየተናገሩ ይህን የመሰለ ምክንያት ማቅረብ አሳፋሪና ሊደገም የማይገባው ነው።

ኮሮና ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ይፋ መደረጉን ተከትሎ ከተካሄዱ ጋዜጣዊ መግለጫዎች በአንደኛው ላይ ጋዜጠኞች ለጤና ሚኒስትሯ በረራዎች ለምን እንደማይከለከሉ ያብራሩ ዘንድ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። ሚኒስትሯም ከአንዲት ባለሙያ የማይጠበቅ መልስ መስጠታቸው ይታወሳል። ‹‹በረራ የከለከሉ አገራትም ከወረርሽኙ አላመለጡም›› ነበር መልሳቸው። ይህ ተራ ሰበብ እንጂ ከሚኒስትር የሚጠበቅ ምሁራዊ አልያም ሳይንሳዊ ማብራሪያ አይደለም።

በእርግጥ ይህን ምላሽ ‹አልታዘዝኩም› ወይም ‹አልተፈቀደልኝም› ወይም ‹ሰሚ አላገኘሁም› ከሚል ኃላፊነት የጎደለው መልስ ለይቶ ማየት ያስቸግራል። ሥልጣንን ላለማጣት ሲባል ሙያዊ ሥነ ምግባርን እንደ መጣስና ወገንን እና አገርንም እንደ መክዳት የሚቆጠር ነው። ምክንያቱም አንድ እውነተኛ ምሁር ወይም ብቁ ባለሙያ ከሙያው ጋር የሚጻረር ሥራን በትዕዛዝ እየሠራ ከመቀጠል ሥልጣኑን አሽቀንጥሮ ቢጥል ይሻላል ተብሎ ይታመናልና።

ኮቪድ-19 አገራችንንም ማተራመሰ ጀምሮ 15ኛ ቀኑን ሲያስቆጥር ፕሬዘደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በትዊተር ገጻቸው ላይ እንድ አስተያየት ሰንዝረው ነበር። ፕሬዘደንቷ በዚያ ዕለት አዲስ አበባን እየተዟዟሩ መጎብኘታቸውን፣ በየሄዱበትም ሕዝቡ የማይጠነቀቅ፣ ችላ ባይ ሆኖ እንዳገኙት ጽፈዋል። ይህን ሐሳብ ተከለትለው የመንግሥት፣ የድርጅት (የብልጽግና ፓርቲ) እና የግል መገናኛ ብዙኀንም በሕዝቡ ላይ ውርጅብኛቸውን እያወረዱበት ነው። ትንሽ አልኮልና ሳኒታይዘር መምጣቱ ተሰምቶ በየፋርማሲው በር ተሰልፎ በጭንቀት የሚራኮተውን ሕዝብ ጭምር ነው ግድ የለሽ፣ ግንዛቤ የሌለው፣ ለጤናው የማይጨነቅ ወዘተ… እየተባለ የሚዘለፈው።

አትክልት ተራ ማልደው ሄደው፣ ያስፈልጋል ያሉትን ገዛዝተው፣ ወደየሰፈራቸው ወስደው በጉልት ቸርችረው የዕለት ጉርሳቸውን ለማሟላት ደፋ ቀና የሚሉትን ምስኪኖችንም ነው የቤተ-መንግሥትና የስቱዲዮ ባለሟሎቻችን የሚሳለቁባቸው። በጊዜ ወደ ሥራ ቦታው ለመድረስ የሚጣደፈውንና ትራንስፖርት ለማግኘት የሚራኮተውን ሕዝብም ጭምር ነው እንደ ጥጋበኛና ለሕይወቱ ደንታ ቢስ እንደ ሆነ ሰው አድርገው በመቁጠር በነገር የሚዠልጡት።

ክብርት ፕሬዘደንትም ሆኑ ጋዜጠኞች መመሪያዎች ሲወጡ መመሪያውን ለመተግበር የሚያስችል ዝግጅት ማድረግና ሥራ መሥራት የመንግሥት ወይም የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ኃላፊነት መሆኑን መዘንጋት አይገባቸውም። ሃቁን ያገናዘበ የመንግሥት እገዛ፣ ሊሠራ (ሊተገበር) የሚችል ስርዓት ማበጀት፣ ሊተገበር የሚችል አሰራርን መዘርጋት ነው የሚያስፈልገው። በእርግጥ ይህን ለማድረግ የሕዝብ አገልጋይ ለመሆን የሚያስችል የሥነ-ልቦናና የሥነ-አእምሮ ዝግጁነትን ይጠይቃል።

ይህን መሰሉ ነገር በዘመነ ሕወሐት/ኢሕአዴግ አልነበረም። አሁን በዘመነ ብልጽግና/ኢሕአዴግም ለመኖሩ ማረጋገጫ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ለምሳሌ ክልከላዎችና መመሪያዎች ወጥተው በባቡር ጣቢያዎች ሰልፎችን የተራራቁ የማድረግ ችግር ይታይ ነበረ። ይህ ችግር በጦር ኃይሎች መነሻ ፌርማታ ላይ የተቀረፈው የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ተሳፋሪዎች ከባቡር ፌርማታው ውጭ ባለ ሰፋ ያለ ቦታ ላይ እንዲሰለፉ በማድረጋቸው ነው። አትክልት ተራን የመሳሰሉ ቦታዎችን ከሰው ብዛት ለማንጻትም ተመሳሳይ ተጓዳኝ ሥራ ይጠበቃል፤ ለሌሎች ችግሮችም እንደዚያው። ከመንግሥት የሚጠበቀውን መንግሥት፣ ከሕዝብ የሚጠበቀውን ከሕዝብ መጠበቅ ይገባል።

በዚህ ዓይነት የሞትና የሽረት ወቅት ብቻ ሳይሆና በማንኛውም ጊዜ ስርዓትን ለማስከበር ሕጎችና መመሪያዎች ሊወጡ ይገባል። ሕጎችንና መመሪያዎችን ማክበርም የሁሉም ዜጋ ግዴታ ነው። ነገር ግን ሕጎችና መመሪያዎች ባለሥልጣናት የራሳቸውን የኑሮ ሁኔታና የኑሮ ደረጃ ብቻ ተመርኩዘው እያቀረጹ በሕዝብ ላይ የሚጭኗቸው ሊሆኑ አይገባቸውም። ሕዝብ ያልወከላቸውና በተጭበረበር ምርጫ የሕዝብ ተወካዮች የተባሉ ምክር ቤቶችና ሕግ አውጭዎች የተንሰራፉባት የአገራችን አንዱ ችግር ይህ ነው።

በእርግጥ በትዕግስት የለሽነት፣ አውቆ አጥፊነትም ሆነ በአንዳች ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ስለገቡ ‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል› ባይ የሆኑ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ሕዝብን የማይወክሉ፣ ብዛታቸውም ቢሆን እዚህ ግባ የማይባል ከመሆን አያልፍም። እነዚህ ሰዎች ብዙ ባይሆኑም በኅብረተሰቡ ላይ የሚያስከትሉት ችግር መጠነ ሰፊ ሊሆን ይችላልና አካሄዳቸው ወንጀለኞች ስለሚያደርጋቸው ችላ ሊባሉ አይገባም።

በሰዓት ገደብ ይሁን ከነ አካቴው ይዘጉ የተባሉ የጭፈራ፣ የመጠጥና የመዝናኛ ቦታዎችን በሚያጓጓ ገንዘብ እያማለሉ የጭፈራና የአስረሽ ምችው ሕይወታውን ለማስቀጠል የሚፈልጉ ካሉም አንድ ሊባሉ ይገባል። በእርግጥ እስከ አሁን ባለሥልጣናቱም ሆኑ አብዛኞቹ ጋዜጠኞቹ እነዚህን በመሳሰሉ ግለሰቦችና ቦታዎች ላይ የነገር አለንጋቸውን ሲያወናጭፉ አልታዩም፣ አልተሰሙም።

ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጥይት በማይበሳው መኪና ውስጥ ሆነው፣ ዐይናቸውን ከሕዝብ በሚከልል መነጽር ጋርደው፣ የሕዝብ እሮሮና ችግር ለማዳመጥ ያልተዘጋጀ ጆሮ ይዘው፣ ለአፍታም ቆም ብለው ሕዝቡን ሳያነጋግሩ አዲስ አበባን በመዞር ብቻ በዚህ ድምዳሜ ላይ ደረስኩ ብለው ስለ ሕዝብ መናገራቸው አሳዛኝ ነው። ጋዜጠኞችም ለፕሬዘደንቷ በስልክ ወይም በዚያው የትዊተር ገጽ ጥያቄ ሳያቀርቡ፣ ራሳቸውን በመጠየቅም ነገሩን ሳያመዛዝኑ የሙሾ አውራጅና የሙሾ ተቀባይ ዓይነት ሥራ መሥራታቸው፣ ሕዝብንም ዘላፊ መሆናቸው ወደኋላ መለሰ ብሎ አንድን ጊዜ ማስታወስን ግድ የሚል ነው።

ከግንቦት 7/1997 ቀጥሎ ባሉት ጊዜያት የነበረውን፣ የመንግሥትና የፋና ጋዜጠኞች የሕዝብ ጠላት በመሆን፣ ‹ድምጼ ይከበርልኝ› ብለው አደባባይ ስለ ወጡ ብቻ በስርዓቱ ታጣቂዎች የተገደሉ፣ ታፍሰው ወደ ማጎሪያ የተወሰዱ ወጣቶችና አዛውንቶችን ‹አሸባሪዎች፣ አደገኛ ቦዘኔዎች፣ ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን ለመናድ የተነሱ ወሮበሎች እርምጃ ተወሰደባቸው› እያሉ የተዘባበቱበትን ጊዜ የሚያስታውስ ነው። በዚህ ጊዜ በየሰፈራቸው ሲጫወቱና በቤተሰብ ተልከው ወይም ወደ ጉዳያቸው ሲጓዙ የነበሩ ሕጻናትና ታዳጊዎችም የጥይት ሰለባወች ሆነው፣ የእነዚህ ጋዜጠኞች መሳለቂያዎች ተደርገው ነበር። ሃቁን ሳይሆን የአገዛዙ ባለሥልጣናትና ካድሬዎች የሚያወሩትን ውሸት ብቻ ደግመው ያስተጋቡ ነበር።

የሳሕለወርቅ ዘውዴ አካሄድ የመንግሥታቸውን ደካማ የነገሮች አያያዝ ለመሸፋፈንና የጎላ ችግር መከሰቱ አይቀርም በሚል እሳቤ ከወዲሁ ሕዝቡን ተጠያቂ ለማድረግ የታሰበበት ሥራ እየተሠራ ሊሆን እንደሚችል ለመጠራጠር በር የሚከፍት ነው። በሽታው ተከሰተ በተባለ በጣም በጥቂት ሰዓታት ውስጥ በቂ ዝግጅት እንዳላደረገ፣ አልኮል፣ ሳኒታይዘር፣ አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ በበቂ መጠን ማቅረብ እንዳልቻለ የተጋለጠውን መንግሥታቸውን ከለላ እየሰጡት ሊሆን ይችላል።

በጣም የሚያሳፍረው ነገር ለእነዚህ ወሳኝ ነግሮች እጥረት የተጋለጠው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የሕክምና ተቋማት ባለሙያዎችም ጭምር መሆናቸው መሰማቱ ነው። ችግሩ ከቻይና እየወጣና እየሰፋ መሆኑ መሰማት እንደጀመረ፣ የሚመለከታቸውን ፋብሪካዎች (የጨርቃጨርቅ፣ የመድኃኒት፣ የአልኮል መጠጥ፣ የስኳር ወዘተ…) አቀናጅቶና ቅድሚያ እንዲሰጡ አድርጎ በቂ ማስክና በቂ አልኮል፣ ከአልኮሉም በቂ ሳኒታይዘር እንዲያመርቱ እንዳላደረገ ተጋልጧል። እናም የመንግሥታቸውን የበሽታውን መምጣት በቸልተኝነት መጠባበቅ ቀላል ችግር አስመስለው፣ ራሳቸውንና መንግሥታቸውን የጲላጦስ ዓይነት ከደሙ ንጹሕ ነኝ ባይ ለማድረግ ዝግጅት እያደረጉም ሊሆን ይችላል።

ሕዝብን ተቺዎች ዓላማቸው ሕዝቡን ለማስተማር፣ ሕዝቡን በሐሳብ ለመርዳት ከሆነ በመጀመሪያ ወደ ሕዝብ ወርደው ሕዝብን መረዳት ተገቢ መሆኑን ማወቅ አለባቸው። ሕዝብን መረዳት የሚቻለው ደግሞ ወደ ሕዝቡ ቀረብ ብሎ ሕዝቡን በማዳመጥ ነው። ከዚህ ውጭ ከሆነ ግን ነገሩ በሕዝብ ላይ በጥላቻ መዝመት ነው። ጋጠ-ወጥነትም ነው። ‹ይህ ኋላቀር ሕዝብ ሊስጨርሰን ነው› የሚል ራስ ወዳድነት የገፋፋው ጭፍን ጥላቻም ሊሆን ይችላል።

ኮቪድ-19’ኝን መዋጋት የሰውን ልጅ በአንዳች መመዘኛ እየመረጡ መዋጋት እንዳይሆን መጠንቀቅ ያሻል። ህንድን የምናውቃት ‹የዓለም ትልቁ ዴሞክራሲ› የሰፈነባት አገር በሚለው በምዕራቡ ዓለም በተቸራት ቁልምጫዋ ነው። ይህ ትልቅ ዴሞክራሲ ብዙ ህንዳውያንን ጨፍልቆ የተገነባ ነጭ ካፒታሊዝም ስርዓትን ያራምዳል። ይህ ጨካኝ ካፒታሊዝም ብዙ ህንዳውያንን ወደ ከፋ ድህነት ዘፍቆ ጥቂቶችን በሃብት ማማ ላይ ያቆናጠጠ ነው። ጥቂቶቹ የህንድ ሃብታሞች ከሕግ-በላይ ሲሆኑ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑት የሕንድ ድሆች ደግሞ በእነዚህ ሃብታሞች ስር ናቸው።

ህንድ በየጊዜው እየሰፋና ብዙዎችን እየዋጠ የሚሄድ ድህነት የሰፈነባት አገር ብቻ ሳትሆን የሰው ልጅ ደረጃ ወጥቶለት የሰው-ሰው እና ሰው መሰል ፍጡር የሚባሉ ዜጎቿን አቅፋ የምትኖር አገርም ናት። እናም ኮቪድ-19 ስጋት ይንጣት የጀመራት ሕንድ ሰው መሰሎቹ ፍጡራን ምርጥ ሰዎቿን እንዳያስጨርሱባት ያለ ምንም ዓይነት መንግሥታዊ ቅድመ ዝግጅት፣ ያለ ምንም የተዘጋጁ ማሳሰቢያ ‹ከየቤትህ እንዳትወጣ!› በሚልና በታወጀ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ተግባር ላይ የሚውል ክልከላ አውጃ ታጣቂዎችን አሰማራች።

የህንድ መንግሥት የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ ግምት ውስጥ ሳያስገባ መተግበር የጀመረው ክልከላ ብዙዎችን ለችግር የዳረገው ሳይቆይ ነው። ለሥራና ለሌላም ጉዳያቸው ወደተለያዩ ቦታዎች ተሰማርተው የነበሩ ህንዳውያን የፖሊሰ ዱላ ሲሳይ ሆነዋል። በዚህ ዓይነት የጀመረው የህንዳውያኑ ምስኪኖች ጣጣ፣ በኮሮና ከሚሞቱ በረሐብ እንዲሞቱ መንግሥታቸው ባስቀመጠላቸው ምርጫ እየተሰቃዩ እንዲቀጥሉ አድርጓቸዋል።

ስቃዩን ያልቻሉት በቤታቸው ተቀመጠው መራቡን ያልፈቀዱ ህንዳውያን ደግሞ ምግብ ፍለጋ ወጥተዋል። በፖሊስ ቆመጥ እየተነረቱም ቢሆን ምግብ ማፈላለጉን የሙጥኝ ብለዋል። ለአንድ አባወራ ሚስትና ልጆቹ በረሀብ እየተሰቃዩ በቤቱ ውስጥ ችሎ መቀመጡ እንዴት ይሆንለታል? ለአንዲት ባል አልባ እናት ልጆቿ በረሀብ አለንጋ እየተገረፉ ለሳምንታት ቤት ውስጥ ችሎ መቀመጡ እንዴት ይቻላታል? የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለተከሰተው ችግር በይፋ ይቅርታ ቢጠይቁም፣ የህንዳውያኑን ምስኪኖች ችግር ስለ መቅረፍ ግን ያቀረቡት ዕቅድ አልነበረም። ነገሩ ባለበት ይቀጥላል ብለዋል።

ጣሊያን ውስጥም በመንግሥታቸው ላይ የሚያጉረመርሙ ዜጎች እየበዙ ነው። ለገንዘብ ወይም ለምግብ ችግር የተጋለጡ ሰዎች ዝርፊያን እንደ አማራጭ አድርገው ማየት በጀመሩባቸው አካባቢዎች፣ የጣሊያን መንግሥት ፖሊስ ለማሰማራት የተገደደ ሲሆን ማፊያዎችም አጋጣሚውን በመጠቀም የተለመደ የውንብድና ሥራቸውን ለመሥራት ዳር ዳር እያሉ መሆኑ ስለተደረሰበት፣ ጣሊያን ሌላ ጠንካራ የጦርነት ዓይነት ዝግጅት ለማድረግ እየተገደደች ነው። በጣሊያን ድንገተኛ አመጽ ተከስቶ በ‹እንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ› የሚሉት ዓይነት ችግር እንዳይመጣ ተሰግቷል።

በአሜሪካና በካናዳ ሕዝቡ ኮቪድ-19 ካጠላው ስጋት በተጨማሪ የደኅንነታቸው ጉዳይ አሳሳቢ የሆነባቸው ዜጎችም በርካቶች ሆነዋል። የአሜሪካዋ የኒው-ዮርክ ባለሥልጣናት የሕክምና አገልግሎትን ማዳረስ ከአቅም በላይ ሆኖባቸው የሌሎች ግዛቶችን ዕርዳታ ለመጠየቅ እንደተገደዱት፣ የትኛውም ግዛትና ከተማ ሕግን የማስከበሩ ጉዳይም ከአቅም በላይ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ብለው በመስጋት ላይ ናቸው። በአሜሪካና በካናዳ የጦር መሣሪያ ግዥ እየተጧጧፈ መሆኑ እየተሰማ ነው። ጀርመንን የመሳሰሉ አንዳንድ አገራት ሕዝባቸውን ለመታደግ በጥበብና በከፍተኛ በጀት የታገዘ ዘመቻ ሲጀምሩ፣ ሌሎች ደግሞ በጉልበትና በጥይት የታገዘ ዘመቻ እንዳይጀምሩ ስጋት ተፈጥሯል።

በኢትዮጵያችን ምግብ ቤቶች፣ ካፌዎች፣ መጠጥ ቤቶችን የመሳሰሉ ሰዎች ዘና የሚሉባቸው ቦታዎች በአብዛኛው ገበያቸው ተቀዛቅዟል። ንግድ ቤቶቹን ዞር ዞር ብሎ ማየት ወይም ባለቤቶቻቸውን መጠየቅ እውነቱን ለመረዳት ያስችላል። ጭር አሉ ባይባሉም እንደ ቀድሞአቸው የግርግር ቦታዎች ሲሆኑ አይታይም። ይህ ሁኔታ ደግሞ ከዕለት ዕለት እየተባባሰ ነው።

የቀን ሠራተኞች ተሰማርተውባቸው የሚውሉ ብዙ የግል ሥራወች እየቆሙ ነው። ብዙዎች በግል ሥራወች ላይ ተቀጥረው ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ ሠራተኞች ‹ምን ሊውጠን ነው?› በሚያስብል ጭንቀት እየታመሱ ነው። በአንዳንድ የሥራ መስኮች በዚህ ሁኔታ ችግር ላይ ሊወድቁ የሚችሉ ምስኪኖችን ቀጣሪዎቻቸው እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ እንደሚረዷቸው ቢታወቅም፣ የችግሩ ወራት በጣም ከተራዘመ ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑ ሊረሳ አይገባውም። የመንግሥት ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።

እነጀርመን የመንግሥት ሠራተኞቻቸውን ብቻ ሳይሆን እነዚህን መሰል የግል ተቀጣሪ ሠራተኞችን እንዲሁም የቀጣሪዎቻቸውን ገቢ ጭምር የሚክስ ዕቅድ አውጥተዋል። ጀርመን ለዚህ ዓይነቱ ጉዳይ ወደ 160 ቢሊዮን ዩሮ ለጠቅላላ ዘመቻዋ ደግሞ 500 ቢሊዮን ዩሮ መድባ ነው ችግሩን በመዋጋት ላይ ያለችው። ህንድ ደግሞ እያንዳንዱ ዜጋዋን ‹በዕድልህ እዘን› የምትል ትመስላለች። ህንድ ያለምንም ቅድመ ዝግጅት፣ በየግላችሁ ተዘጋጁ የሚል ማስጠንቀቂያ እንኳ ሳትሰጥ ሥራዎችንና እንቅስቃሴዎችን አግዳ ገቢያቸው ከእጅ ወደ አፍ የሆኑ በጣም ብዙ ምስኪን ዜጎቿ ለረሀብ ተዳርገዋል። ምግብ ፍለጋ ወጣ ሲሉም ከባለ ዱላ ፖሊሶች ጋር መጋፈጥ ግድ ሆኖባቸዋል። የኢትዮጵያችን አቅምስ ምን እስከ ማድረግ የሚዘልቅ ይሆን?

ትግራይ ውስጥ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ሆኗል። የትግራዩ አዋጅ ተግባር ላይ የዋለው የኹለት ቀናት የማስጠንቀቂያና የመዘጋጃ ጊዜ ተሰጥቶበት፣ ሕዝቡ ለኑሮ ውድነትና ለአስፈላጊ ነገሮች እጥረት እንዳይጋለጥ ከከተማ ወደ ገጠር፣ ከገጠርም ወደ ከተማ በየዕለቱ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን የሚመላለሱበት ስርዓት ተዘርግቶ፣ ከመዝናኛና ከጊዜ ማሳለፊያ ጋር በተገናኙ ወሳኝ ያልሆኑ ሥራዎች እንዲዘጉ ተወስኖ፣ በኪራይ ቤት ውስጥ የሚነግዱት ሰዎች እንዳይጎዱም የ15 ቀን ኪራይ እንዲተውላቸው እና የመሳሰሉ ዝግጅቶች ተደርገው ነው።

በሌላ በኩል ግን አዋጁን ተከትሎ ጥይት ወደ ሕዝብ እየተተኮሰ መሆኑ ይሰማል። አዋጁ መተግበር ጀምሮ 24 ሰዓታት ሳይሞሉ አድዋ ከተማ ውስጥ በፖሊስና በሕዝብ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት አንድ ወጣት በፖሊስ ጥይት መገደሉ በትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ተጠሪ በኩል ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ ተመሳሳይ ችግር በትግራይ ናዕዴር አዴት ወረዳ ተከስቶ የሌላ ወጣት ሕይወት በፖሊስ ጥይት መጥፋቱም ከቪኦኤና ዶቸቨለ ተሰምቷል።

አማራ፣ ኦሮምያ፣ ድሬዳዋና ሐረር በክልሎቻቸው የኮቪድ-19 ተጠቂዎች መገኘታቸው እንደተሰማ እንቅስቃሴዎችንና አንዳንድ ሥራዎችን የሚመለከት ዕገዳ ጥለዋል። ሌሎች ክልሎችም እንደዚያው ዕገዳ ጥለዋል። አሁን ዕገዳ ያልጣለ ክልል የለም ማለት ይቻላል። ዕገዳዎቹ የተጣሉት በጥድፊያ ስለሆነ ቅሬታዎች እየተሰሙ ቢሆንም፣ የዕገዳዎች አስፈላጊነት የሚያጠራጥር አይደለም። ነገር ግን ሕዝብን ችላ ያለና ለሌላ አደጋ የሚያጋልጥ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይገባል። አሁን ያለ ዝግጅት ዕገዳ የጣሉ ክልሎችና ከተሞች ነዋሪዎቻቸው ችግር ላይ ሲወድቁ ጥይት ወደመተኮስ እንዳይሮጡ ሊያስቡበት ይገባል።

በአዲሰ አበባም ሆነ በሌሎች ክልሎችና ከተሞች የሚገኙ ባለሥልጣናት ድሃውን ሕዝብ በጭፍን አመለካከት እያዩ፣ ሌሎችን ሊበክል እንዳሰፈሰፈ ኋላቀር ጠላት በመቁጠር ወታደራዊ የመሰለ አዋጅ እንዳይጭኑበት መጠንቀቅ ይገባቸዋል። ምንም እንኳ ዕገዳዎችን በጥድፊያ የጫኑ ቢሆንም ዕገዳው እንዳለ ሆኖ የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ ያገናዘበ ዝግጅት እያደረጉ ሕዝብን ከሌሎች ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ጥቃቶች መጠበቁን ሊሠሩበት ይገባል።

የችግሩ ማብቂያ ጊዜ የታወቀ አይደለም። የችግሩን ትክክለኛ ስፋትም መገመት ከባድ ነው። መጭው ጊዜም ከባድ ሊሆን ይችላል። ከፕሬዘደንቷ የቲዊተር መልዕክት ተነስቶ የተፋፋመው የሚዲያ ዘመቻና የየክልሎቹ አመራሮች የሰነዘሩት ማስጠንቀቂያ ወደ ወታደራዊ ዘመቻ እንዳያመራ፣ በጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ፍላጎትና በፕሬዘደንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ ፊርማ አስገዳጅ ወታደራዊ አዋጅ ታውጆ ለድሆች መርዶ፣ ለባለጸጎች ተስፋ የሚሆን ዜና በሚዲያዎች ከመሰማቱ በፊት ዝግጅት ይቅደም።

ከሕዝቡ አኗኗር አንጻር መደረግ የሚገባው የተሻለው ነገር ምን እንደሆነ ይጠና። ኮቪድ-19ኝን ስለ መከላከል ሲታሰብ ማንንም ችላ ያላለና ሁሉንም ዜጋ፣ ድሃ ይሁን ሃብታም፣ ለብቻው ግቢ ያለው ቤተሰብን ይሁን በተጠጋጉ ዛኒጋባ ቤቶች ተጨናንቆ የሚኖረውን ኅብረተሰብ፣ አዳራሽ መሰል ቤቶችን እንደነገሩ ከፋፍለው የሚኖሩ ቤተሰቦችን ሆነ ቤት የለሽ ወገኖችን ሁሉ ታሳቢ ያደረገ ሊሆን ይገባዋል። ‹‹እነዚህ ድሆች ሊያስጨርሱን ነው፣ ሊበክሉን ነው፣ እድሜአችንን ሊያሳጥሩብን ነው›› በሚል ትዕቢትና ‹የሀብት አፓርታይድ› የመሰለ አሰራር ሊኖር አይገባም። በዚህ ዓይነት የችግር ጊዜ ቆራጥና ደምሳሽ መሪ ለመሆን መሞከር አጥፍቶ ጠፊ እንደመሆን የሚቆጠር ነው።

ግዛቸው አበበ / gizachewabe@gmail.com

ቅጽ 2 ቁጥር 74 መጋቢት 26 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com