የእለት ዜና

ቶዮታ በኢትዮጵያ የመለዋወጫ ፋብሪካ ሊገነባ ነው

የጃፓኑ ግዙፍ የአውቶሞቲቭ ኩባንያ ቶዮታ በኢትዮጵያ የተሽከርካሪዎች ዕቃ መለዋወጫ ማምረቻ ለመገንባት ጥናት ማጠናቀቁ ተገለፀ። የብረታ ብረት ኢንዱሰትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው፣ ቶዮታ ኩባንያ በኢትዮጵያ የተሽከርካሪዎችን ዕቃ መለዋለጫ ለመገንባት ጥናቱን ያጠናቀቀ ሲሆን፣ በቀጣይ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታዎች በማሟላት ወደ ግንባታ እንደሚገባ ገልጿል።

በኢትዮጵያ ከ95 በመቶ በላይ የቶዮታ ምርት የሆኑ ተሽከርካሪዎችን ጥቅም እየሰጡ መሆናቸው፣ ኩባንያው በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ እንደተነሳሳ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዮት ፕላን ዳይሬክተር ጥላሁን አባይ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ኩባንያው ወደ ኢትዮጵያ በሚገባበት ጊዜ እና የተሽከርካሪዎችን መለዋወጫ ማምረት ሲጀምር በርካታ የሥራ እድሎችን ከመፍጠር ባለፈ፣ በዓመት በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚገመተውን የመለዋወጫ ዕቃዎች ግብይት ይቀንሰዋል ሲሉ ይናገራሉ።

በሌላም በኩል ዳይሬክተሩ ሲናገሩ፤ መንግሥት ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ እና ባገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ የኤክሳይስ ታክስ በመጣል ለመቆጣጠር መሞከሩ ተገቢ ጉዳይ መሆኑ የታመነበት ሲሆን፤ ኩባንያው ወደ አገር ውስጥ ገብቶ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ አገር ውስጥ ያለውን የአሮጌ ተሽከርካሪዎች ገበያ በአዲስ ይተካዋል የሚል እምነት እንዳላቸውም ይናገራሉ።

በቅርቡ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የመግባቢያ ሰነድ እንደሚፈራረም የተነገረለት የቶዮታ ኩባንያ፣ ከመስከረም 2012 ጀምሮ ጥናት ሲያካሂድ መቆየቱን እና በቅርቡ መጠናቀቁን አዲስ ማለዳ ብረታ ብረት ኢንዱሰትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጰያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር  መኮንን ኃይሉ እንደተናገረው፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተሽከርካሪ የመገጣጠም ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች ቁጥር ውስን መሆኑንና በዘርፉ እየሰሩ ከሚገኙ ኩባንያዎች መካከል ሃዮንዳይና ሊፋን ሞተርስን ለአብነት ጠቅሷል፡፡ ይሁን እንጂ ከዓመት በፊት በዓለም ከፍተኛ እውቅና ያለው የጀርመኑ ተሸከርካሪ አምራች ግዙፍ ኩባንያ ቮልስዋገን በሃገሪቱ መዋዕለንዋዩን ለማፍሰስ የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ከኢትዮጵያ መንግሰት ጋር መፈራረሙን ተናግሯል፡፡ በአውቶሞቲቭ ዘርፍ የውጭ ኩባንያዎች መዋዕለ-ነዋያቸውን ቢያፈስሱ በሃገሪቱ እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ ካለው ከፍተኛ ፍላጎትና ገበያ በተጨማሪ በአጭር ጊዜ በመሰልጠን ተወዳዳሪ በሆነ ዋጋ ሊሰራ የሚችል የሰው ኃይል ያለ በመሆኑ ኩባንያዎቹ በኢንቨስትመንት ስራቸው ውጤታማ እንደሚሆኑ ተናግሯል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዘርፉ በተለይም በሃገሪቱ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማረጋገጥ ኢንዱስትሪያላይዜሽንን ከማፋጠን አንጻር የጎላ ድርሻ ያለው መሆኑን ተናግሯል፡፡
የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ዘርፉ ይበልጥ ለማሳደግ በመንግስት በኩል ጥረት እየተደረገ መሆኑንና ከዚህም አንጻር በኢትዮጰያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዘርፉን ለማሳደግ የሚረዳ ጥናት እየተደረገ መሆኑን አመልክቶ፣ ጥናቱ በዘርፉ ከፍተኛ ልምድና ቴክኖሎች ያላቸውን እንደ ጀርመን ያሉ የአውሮፓ ሃገራት የካበተ ልምድ መወሰዱን አመልከቷል፡፡ ኢትዮጵያ ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ተመራጭ ከሆኑ የአፍሪካ ሃገራት መካከል በግንባር ቀደምነት የምትጠቀስ ሲሆን፣ በሃገሪቱ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እውቅና ያላቸው የውጭ ኩባንያዎች የአውቶሞቲቭ ዘርፍን ጨምሮ በተለያዩ የማምረቻ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን አቶ መኮንን ተናግሯል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 74 መጋቢት 26 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!