የሴቶች ሚና በአገራዊ ምክክር መድረክ

0
988

‹ጤና ካለ› እንደሚባለው ኹሉ፣ ‹ሠላም ካለ› ኹሉም እንዳለ ይቆጠራል። ኹሉም ባይኖር እንኳ በተቻለ አቅም አስፈላጊው ነገር እንዲኖር ለማድረግ መንቀሳቀስ ይቻላል። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት በቅድሚያ ሠላም የሚያስፈልጋቸው ለዛ ነው። ሠላም ካልቀደመ፣ መረጋጋት ከሌለ እንኳን ዕድገት ሊታሰብ ቀርቶ ከነበረውን ደረጃ ወደኋላ መራመድ መከሰቱ የማይቀር ነው።

ኢትዮጵያ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ መግባቷን ተከትሎ በሕዝቦች መካከል የተፈጠሩትን ነገሮች በጋራ መግባባት መፍታት በማስፈለጉ አገራዊ ምክክር ለማካሄድ ተወስኗል። በዚህም አገራዊ ምክክሩን የሚመራ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተሰኘ ተቋም በዐዋጅ የተመሠረተ ሲሆን፣ የካቲት 14/2014 ደግሞ ኮሚሽኑን የሚመሩ አስራ አንድ ኮሚሽነሮች ተሰይመዉለታል። አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን እንዲመሩ ከተመረጡት ሰዎች መካከል ምክትል ሰብሳቢዋን ጨምሮ ሦስት ሴቶች ተካተዋል።

አገራዊ የምክክር መድረክ አዲስ ነገር አይደለም። ጥቂት የማይባሉ የፖለቲካ ችግር የገጠማቸው አገራት ተጨማሪ ችግሮችን ለማስቀረት ወይም ለማርገብ ተጠቅመዉበታል። በዚህ መሠረት አገራዊ ምክክር ካደረጉ 17 የዓለም አገሮች መካከል አንዷ የመን ናት። ከተነሳንበት የሴቶች ተሳትፎ አንጻር የየመንን አገራዊ ምክክር መልክና የሴቶችን ሚና በጥቂቱ እናንሳ።

ማሪያ ያሀ ዓለም ዐቀፍ የሴቶችን ሁኔታ እና የየመንን ጉዳይ የሚከታተሉ፣ በአሜሪካ ዓለም ዐቀፍ የልማት ተቋም ውስጥ የፕሮጀክት አስተባባሪ ሆነው የሚሠሩ ሴት ናቸው። እኚህ ሴት በ2013 ‹በየመን ብሔራዊ የምክክር መድረክ የሴቶች ተሳትፊነት/ተካታችነት (Inclusion of Women in Yemen’s National Dialogue) በሚል ርዕስ ጥናት ሠርተዋል። የዓለም ባንክ በገጹ ባስነበበው በዚህ ጽሑፍ ውስጥ፣ በየመን አገራዊ ምክክር ላይ ሴቶች እንዲሳተፉ ዕድል ቢሰጣቸውም የተፈለገውን ያህል ተጽዕኖ ማምጣት እንዳልቻሉ [ሴቶቹ] እና ሥራቸውን እንዳይሠሩ ድምፅ እንዳይሆኑ የተለያየ ትንኮሳ ይደርስባቸው እንደነበር ተገልጿል።

የየመን መንግሥት ለሴቶች አዲስ ዕድል መንገድ ቢከፍትም፣ የመን ላይ ያለውን የሴቶችን መብት ጥሰት አልፈታውም ነበር ይላሉ አጥኚዋ። በዚሁ በየመን አገራዊ ምክክር ላይ 30 በመቶ ሴቶች ይሁኑ ቢባልም፣ ሴቶቹ የተመረጡበት መንገድ አሳማኝ አልነበረም። ስለዚህም አዲሱ የየመን ሕገ መንግሥት ሲረቅ የሴቶችን መብት ከግምት ውስጥ ያስገባ አልነበረም ብለዋል።

ማሪያ የጥናቱ ውጤት ያሳየው ነው ብለው በጽሑፋቸው ባቀረቡት ገለጻ፣ አገራዊ ምክክር ላይ የገቡትም ሴቶች ቢሆኑ የሴቶች መብት በሕገ መንግሥቱ እንዲከበር ያደረጉት አስተዋጽኦ አናሳ ነበር ብለዋል። የየመን አገራዊ ምክክር መድረክ ኹሉን አካታች ነው ተብሎ በአደባባይ ቢነገርና እንደዛ እንደሆነ ቢታመንም፣ ሴቶች ፍላጎታቸውን በግልፅ እንዳይናገሩና እንዳያሳዩ፣ መብታቸው በሕግ እንዳይከበር ዕድል ነፍጓቸዋል ሲሉ የሴቶቹን ሚና እንዳቀጨጨው ይገልፃሉ። አገራዊ ምክክር ሲደረግ ምን ጊዜም ቢሆን ኹሉን አካታች መሆን እንዳለበት ማሪያ በጥናታዊ ጽሑፋቸው አመላክተዋል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሴቶች ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑ ብዙ ጊዜ ይነሳል። ይህ ደግሞ በሴቶች ላይ ያለው ተጽዕኖ፣ በፆታ አድሎአዊነት እንዲቀጥል እና እኩል ተጠቃሚነት እውን እንዳይሆን፣ ሴቶችም በአገራቸው ዕድገት ላይ እኩል ተሳታፊ እንዳይሆኑ፣ ብሎም በሚወጡ እና በሚፈጸሙ ሕጎች ላይ ድምጽ እንዳይኖራቸው አድርጓል። በአንጻሩ የሴቶች የጎላ የፖለቲካ ተሳትፎ ሴቶችን ለአገር ጉዳይ ጠቃሚም ተጠቃሚም ለማድረግ ጥሩ የሚባል አማራጭ ነው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ከገባችበት ውስብስብ ችግር ለመውጣትና ለማለፍ ይጠቅማል የተባለው መንገድ ሲጀመር፣ በዚህ ላይ የሴቶች ሚና ምን መሆን አለበት? አዲስ ማለዳ ይህን ጥያቄ በማንሳት የኢትዮጵያ ፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሊቀ መንበር ራሔል ባፌን (ዶ/ር) አናግራለች።

ራሔል የሴቶች ሚና ከዚህ በላይ ከፍ ማለት ከቻለ፣ ጠቃሚ ነው ብለው እንደሚያስቡ ይናገራሉ። ነገር ግን በኢትዮጵያ ባለው ሁኔታ የምክክር ኮሚሽኑ ውስጥ ያሉ ቀዘሴቶች ብዛት በጣም አነስተኛ መሆኑን አውስተዋል። ሕዝብ መርጦ ካቀረባቸው በኋላም ተለይተው ከቀረቡ 42 ሰዎች መካከል 11 የኮሚሽኑ አባላት በምን መስፈርት እንደተመረጡ እንኳ ግልጽ እንዳልሆነም ጠቅሰዋል።

የሆነው እንዳለ ሆኖ ግን፣ በዚህ ጉዳይ የሴቶች ሚና ምንም ምትክ የለውም ሲሉ አስረግጠው ገልጸዋል። ሴቶች በቤተሰባቸው ውስጥ ያላቸው ሚና፣ አስታራቂነታቸውም ጉልህ ትኩረት ሊሰጠውና ቦታ ሊያገኝ የሚገባው ነው ብለዋል።

ከዚህ በተጓዳኝ መለስ ብለው በኮሚሽኑ የሴቶች ተሳትፎ ያነሰበት ምክንያት ለሴቶች የተለየ ቦታ ባለመሰጠቱ ነው ብለዋል። ‹‹እኛ ቦታ እንዲሰጥ ጥረት ሳናደርግ ቀርተን አይደለም። የሙያ ማኅበራትም ሳይጠይቁ ቀርተው አይደለም። ነገር ግን ከነበረው የኢሕአዴግ ሥርዓት ያልተላቀቀ መንግሥታዊ ሥርዓት ስላለን፣ ከዛ ነፃ መውጣት ስላልቻልን ቦታው አልተሰጠንም። አላካተተንም እንጂ ዕድሉ ከፍ ቢል ጠቃሚ እንደሚሆን አምናለሁ›› ሲሉም ቅሬታና ትዝብታቸውን ተናግረዋል።

ጉዳዩ አማራጭ የሌለው እንደሆነም ነው የጠቀሱት። ‹‹የአገራችን ኹኔታ ሲታይ፣ ጦርነቱም ይሁን መፈናቀሉ፣ መደፈሩም ይሁን መገደሉ፣ ኹሉም ነገር በቀጥታም ሆነ ዞሮ ዞሮ ጉዳቱ ሴቶች እና ሕጻናት ላይ ነው። በአብዛኛው ደግሞ ሴቶች ላይ ነው የተፈፀመው። ግን ያንን ‹እኔ ነኝ የማውቀው። በወንዶች በኩል ነው እንጂ ተወካይ የማቆምላችሁ እናንተ ማውራት አትችሉም። ስለ ጉዳያችሁ ማንሳትም እንደዛው› በማለት የመጨቆን ነገር [በመንግሥት በኩል] ይስተዋላል›› ሲሉም ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
ሴቶች ተጠቂ ብቻ ሳይሆኑ የመፍትሔ አካልም ናቸው የሚሉት ራሔል፣ ነገር ግን የመፍትሔ አካል እንዳይሆኑ ከፍተኛ ተጽዕኖ እና ያለአግባብ የመጫን ነገር ይስተዋላል ብለዋል።

ምን ያጎድላል?
የሴቶች በፖለቲካ ወይም ከላይ እንደተጠቀሰው በምክክር ኮሚሽኑ በሚገባው ልክ አለመሳተፋቸው ምን ያጎድላል? የተባሩት መንግሥታት ከጥቂት ዓመታት በፊት በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ውይይት አካሂዶ ነበር። ውይይቱ በአመራር ላይ የሴቶች አለመኖር ምን አሉታዊ ተጽዕኖ አለው የሚለውን ዋና ማጠንጠኛው አድርጓል። እናም ሴቶች አመራር ላይ ደብዛቸው ከጠፋ ወይም ቁጥራቸው ከአንድ እጅ ጣቶች ካነሰ፣ ዴሞክራሲ ስለመኖሩ ያጠራጥራል ብሏል።

ብዙዎች በዚህ ሐሳብ እንደሚስማሙ የተለያዩ ሠነዶች ያስረዱናል። ከኻምሳ በመቶ በላይ ሴቶች ባሉባት አገር ኢትዮጵያም የሴቶች ተሳትፎ ፍትሐዊና አግባብ ካልሆነ፣ በጠቅላላ ሥርዓቱ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ አይቀሬ ነው። ዴሞክራሲም የአብዛኛውን ድምጽ የጥቂቶችን መብት ሳይነካ የሚያስከብር ነውና፣ በቁጥር የሚበልጡ ሴቶች ድምጽ ሊያገኙና ሊመሩ፣ ሊሳተፉና ውሳኔ ሊሰጡ ይገባል።

ከዛም በላይ የቤተሰብ ነገር ይነሳል። ሴቶቸ በየቤታቸው ያላቸው የማረጋጋት ድርሻ ትልቅ ነው። ብዙ ትዳሮች፣ ብዙ ቤተሰቦች፣ ብዙ ኑሮዎች በሴቶች ብልሀትና ትዕግስት የተነሳ ዘልቀው ታዝበናል። በአገር ጉዳይ ይህ እንዴት ላይሆንና ላይሳካ ቻለ። ብዙዎች እንደሚሉት ለሴቶች በቂ እድል ስላልተሰጠ? ወይስ ሴቶችም የመሳተፍና ሚናቸውን የመወጣት ምንም ፍላጎት ስለሌላቸው? ይህ ለኹሏም ሴት፣ ለየአንዳንዷ የሚቀርብ ጥያቄ ነው።

የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ‹‹የሠላም ግንባታ ማሠልጠኛ›› በተሰኘ ጥናታዊ መድበል ስለ ሠላም ምንነት በዝርዝር አስነብቧል። በዛም ላይ በኢትዮጵያ ለረዥም ዘመናት ጠንካራ የሠላም ባህል እንዲኖር ቤተሰብ ተኮርነት ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል የሚል ነጥብ ይገኛል። እንዲህ ተገልጿል፤

‹‹የሠላም ባህላችንን ውበት ለመግለጽ የማኅበረሰባችን መሠረት የሆነውን የቤተሰብ አስተዋጽኦ ማውሳት እጅግ ጠቃሚ ይሆናል። እኛ ኢትዮጵያዊያን ብዙውን ጊዜ በፍቅርና በመከባበር በጋራ ሠርተን የምንኖረው፣ አደጋን የምንከላከለው፣ ሠላማዊ ሕይወት ለመምራት የምንለማመደውና መተባበርን የምንለማመደው በቤተሰብ መካከል በመኖር ነው። የአመለካከት ልዩነቶችን የምንፈታውና ለቤተሰቡ የጋራ ደኅንነትና ዕድገት ጠቃሚ መንገዶችን የመቀየስ ልምድ የምንማርበት ትልቁ ትምህርት ቤታችን ቤተሰብ ነው ቢባል ከእውነት አያርቀንም።››
የምክክር ኮሚሽኑ ውጤታማ የሆነ ሥራን ሠርቶ ለአገር ሠላም የሚመጣበት መንገድ እንዲመጣ ኹሉም ይናፍቃል። የሴቶች ተሳትፎ ማነሱ ግን፣ በአሁን የማይስተካከል ከሆነ እንኳ ለወደፊቱ ግን በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ልብ ማለት ያሻል።


ቅጽ 4 ቁጥር 178 መጋቢት 24 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here