አገርን የመዝጋት ዘመቻ – ለዓለም የቀረበ አስጨናቂ ፈተና

Views: 203

የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ መከሰትና ስርጭትን ተከትሎ፣ አገራት በሮቻቸውን ዘግተዋል። የሰዎች እንቅስቃሴ የተገታ ሲሆን አብሮት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያው እንቅስቃሴም ወደመቆሙ ተቃርቧል። ታደሰ ጥላዬ ይህን ነጥብ በማንሳት፣ በቫይረሱ ምክንያት ዛሬ የተገታው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ነገ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል ባይ ናቸው። እናም አውሮፓና አሜሪካ እንዲሁም ሌሎች አገራት ከወሰዱት ‹አገር የመዝጋት› እርምጃ የተሻለ እርምጃ መውሰድ አንችልም ነበር ወይ በማለት ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል።

ዓለም ፈተና ውስጥ ነች፤ ከባድ ፈተና። የሰውን ሕይወት አልያም አጠቃላይ የዓለምን ሥልጣኔ ፍጹም ከሆነ ውድመት የመታደግ ምርጫ ነው።
የኒዮርክ ታይምስ ጸሐፊዎች ኤድዋርዶ እና ጂም ‹‹ሕይወትን ለማዳን የሚከፈል ኢኮኖሚያዊ ዋጋ›› በሚል አንድ ጽሑፍ አዘጋጅተዋል። ‹‹ለመሆኑ አገርን ከማንኛውም እንቅስቃሴ ዘግቶ የሚደረግ የሰውን ሕይወት ማዳን ያለውን ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ መለካት ይቻል ይሆን?›› ብለውም ይጠይቃሉ።

የተለያዩ ሞዴሎችን በመጠቀም የተሠሩ ጥናቶችን መነሻ የሚያደርገው ይህ ጽሑፍ የአገሪቱን አስተዳደር ስጋት መልክ ለማስያዝ ይሞክራል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ላይ የገለጹትን ሐሳብም ያነሳል። ‹‹በሽታውን ለማስቆም የምናደርገው እርምጃ ከበሽታው በላይ ጎጂ መሆን የለበትም›› ነበር ያሉት።

የትራምፕን ስጋት እውነትነት የሚያረጋግጡ ጥናቶች መኖር አለመኖራቸውን ሲፈትሹም፣ ከዚህ በፊት በአሜሪካን የአካባቢ ጥበቃ ኤጄንሲ አካባቢን ከበካይ ነገር ስለማፅዳት በተደረገ ጥናት መሰረት፣ ‹‹ከበካይ ነገር ከሚመጣ ሞት፣ የአንድን ሰው ሕይወት ለማትረፍ አሜሪካ 9.5 ሚሊዮን ዶላር ማጣት አለባት የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሶ ነበር›› ይላሉ። በተጨማሪም የቺካጎ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ባለሞያና የትራምፕ አስተዳደር ውስጥ የረጅም ጊዜ አማካሪ ካሴይ ሙሊጋን ሲናገሩ፣ ‹‹ሞት የሚመጣው በበሽታ ብቻ አይደለም፤ ሰዎች ሥራ ሲያጡም`ኮ ይሞታሉ›› ይላሉ።

ሰዎች ሥራ ሲያጡ በተስፋ መቁረጥ ራሳቸውን ሊያጠፉ ይችላሉ። በበሽታ ጊዜም መታከሚያ ካላቸው ሰዎች ይልቅ መታከሚያ የሌላቸው ሰዎች ይበልጥ ይሞታሉ በማለት ይሞግታሉ። እንዲያውም ባለሞያው እንደሚሉት ‹‹የሰውን ሕይወት ለማዳን ኢኮኖሚውን ብናቀዛቅዘው ኢኮኖሚው መቶ ሚሊዮን ዶላር ሲያጣ ከዚህ ጋር በተያያዘ ብቻ አንድ ሰው ይሞታል›› በሚል የጉዳዩን ውስብስብነት ለማሳየት ይሞክራሉ። በዚህም ሰው ለማዳን ሁሉንም መስዋዕትነት ማድረግ ተገቢ ቢሆንም፣ የምንወስዳቸው እርምጃዎች አንዱን አድነው ሌላውን ለሞት የሚዳርጉ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ነው።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ዓለም በ2020 በአራት ትሪሊዮን ዶላር ገደማ እድገት አስመዘግባለሁ ብላ ትንበያ አስቀምጣለች። እንደ ብሉምበርግ ዓይነት ተቋማት ግን በ2020 ዓለማችን 2.5 ትሪሊዮን ዶላር ሀብት ታጣለች ብለው ተንብየዋል። ይህ ታዲያ ልታመርት የነበረውን ሀብት ብቻ የሚመለከት ነው። በሽታውን ለመቆጣጠርና እንደገና ወደ መስመር ለመመለስ ግን ከዚያ በላይ እንደሚያስፈልግ እያየን ነው።

አገራት በተናጥል የሚመድቡት ረብጣ ገንዘብ ሳይታሰብ የቡድን ኻያ አባል አገራት ብቻ ባሳለፍነው ሳምንት ለዓለም ማገገሚያ የሚሆን አምስት ትሪሊዮን ዶላር እቅድ ይፋ አድርገዋል። ይህ አሃዝ ብቻውን የዓለምን አጠቃላይ ዓመታዊ ምርት ስድስት በመቶ ያህል ነው። ይህ ሁሉ ሀብት ታዲያ ‹‹ዓለምን አረጋግቶ ዳግም በኹለት እግሯ ያቆማታል” በሚል የፈሰሰ ቢሆንም፣ የተባለው እቅድ ስለመሳካቱ ምንም አይነት ማረጋገጫ የለም።

በተለይ ይህን ያህል ገንዘብ ማምረት ላቆሙ ድርጅቶችና ሠራተኞች የዕለት ከዕለት እስትንፋስ ማስቀጠያ የሚውል ከሆነ፣ የምርት እጥረት እና የመግዛት አቅም በአንድ ላይ መከሰቱ አይቀሬ ነው። በዚህ አያያዝም የዓለም ቀጣይ እጣ የቁልቁለት ጉዞ ነው ማለት ነው። ምክንያቱም የሚያመጣው የተስፋ መላሸቅም ከበሽታው በኋላ እንኳን ኢኮኖሚው በቀላሉ እንዳያገግም ሊያደርገው ይችላል። ይህ ደግሞ ምናልባትም ከበሽታው በላይ ረሃብና ወንጀል ዓለምን እንዲፈትኗት ሊያደርግ ይችላል።

የሰውን ሕይወት ከበሽታው እየተከላከሉ የኢኮኖሚውን ሞተር ማቀጠል?
የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮና ቫይረስን ‹የዓለም ስጋት ነው› ብሎ ከፈረጀ በኋላ በየአቅጣጫው የሚሰጡት ማርከሻ መድኃኒቶች በዋናነት ኹለት ናቸው፤ የጽዳት እና የማኅበራዊ/አካላዊ ርቀት ጉዳይ። ከኹለቱ ውስጥም ዋናውና እንደ አስገዳጅ እየሆነ የመጣው የማኅበራዊ ርቀት የመጨረሻው ምዕራፍ የሆነው ቤት ዘግቶ መዋል ነው።
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ጨምሮ የአብዛኛውን አዳጊ አገራት አቅም በእጅጉ ይፈታተናል ተብሎ የሚጠበቀው ይኸው ማኅበራዊ ፈቀቅታ በሌላ ሥሙ “ሳይሠሩ የመብላት” ዘመቻ ነው። በእኔ እምነት ቤት በመዝጋት ውሳኔ ዓለም ነገ የምታለቅስበትን የቁልቁለት ጉዞ እየተጓዘች ነው። ግን ከዚህ የቁልቁለት ጉዞ አገራችን፣ ገፋ ሲልም አኅጉራችን እንዴት ልታመልጥ ትችላለች?

የጀርመኑ የመረጃ ማእከል ስታቲስታ ባወጣው ጥናት መሰረት፣ የአገራችንን ኢኮኖሚ ዘርፎች በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፍላቸዋል። ይህውም ግብርና፣ ኢንዱስትሪና አገልግሎት በማለት ነው። ይህም የተለመደና በየትኛውም አገር የሚተገበር የኢኮኖሚ ዘርፎች አከፋፈል ስልት ነው። በዚሁ ድርጅት ጥናት መሰረት ከአገራችን ዓመታዊ ምርት ግብርና 31.19 በመቶ፣ ኢንዱስትሪ 27.26 በመቶ እንዲሁም አገልግሎት 36.52 በመቶ ለኢኮኖሚው አስተዋፅዖ ያደርጋሉ።

ከሥራ እድል ፈጠራ አንፃር ስናየው፣ አሁንም የአገራችን 65 በመቶ ሕዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከግብርና ጋር የተያያዘ ነው። ይህንን መረጃ መሰረት አድርገን የአገራችንን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ስንቃኘው፣ የግብርናው ክፍለ-ኢኮኖሚ ከሞላ ጎደል መቶ በመቶ በገጠሩና ትናንሽ ከተሞች አካባቢ ያለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሆኖ እናገኘዋለን።

ኢንዱስትሪው በአመዛኙ ከተሞችን ተከትሎ የሚዘወተር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ነው። የአገልግሎት ዘርፉም ቢሆን በአብዛኛው በዋና ዋና ከተሞች ላይ መሰረት ያደረገ ስርጭት አለው። እናም በጊዜያዊ ግፊት ተነሳስተን የከተሞችን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መገደብ ማለት 64 በመቶ ዓመታዊ ምርት (GDP) እና 35 በመቶ የሥራ ቦታን እንደቀላል ነገር መዝጋት ማለት ነው።

ከዚህ መረጃ ተነስተን የሕዝባችንን አሰፋፈር ስናይ፣ አብዛኛው ሕዝብ ኑሮውን የመሠረተው በአገሪቱ ገጠራማና ትናንሽ ከተሞች ውስጥ ነው። ይህ በሰላሙ ጊዜ የ‹ኋላ-ቀርነት› መገለጫ ቢሆንም፣ ለእንደዚህ ዓይነቱ ፈታኝ ወቅት ግን እንደ መልካም አጋጣሚ ሊታይ ይችላል። ምክንያቱም ገጠርና ከተማው ያላቸውን ተፈጥሯዊ መራራቅ ተጠቅሞ ብቻ ብዙም የተለየ ጥበብ ሳያስፈልግ የቫይረሱን ስርጭት በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ ተወስኖ እንዲቀር ማድረግ ያስችላል።

የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ፍጥነትና ጉዳት አስደንጋጭ የሆነባቸው አገሮች፣ ሌሎች ምክንያቶች እንደተጠበቁ ሆኖ፣ ከከተሜነት ጋር ተያይዞ ያለው የሕዝብ ጥግግት ሁኔታ ዋነኛው ጉዳይ ይመስላል። ኢትዮጵያን በተመለከተ ግን ከአዲስ አበባ በቀር ከከተሜነት ጋር ተያይዞ ሊፈጠር የሚችል የወረርሽኝ መስፋፋት ብዙም የሚያሳስባት አይደለችም። ከዚህም አንጻር የምዕራባውያንን አማራጭ እንደወረደ ለመቀበል ከመሞከርና ውድቀትን ከማፋጠን፣ በኛ ሁኔታ ምን ማድረግ እንደምንችል ማሰብ የተሻለ ይሆናል።

ከላይ ከጠቃቀስናቸው እውነታዎች አንጻር ኢትዮጵያ አዲስ አበባን ከሌሎች ክፍለ-አገሮች፣ የክልል ዋና ዋና ከተሞችን ደግሞ ከሌሎች አነስተኛ ከተሞችና የገጠር አካባቢዎች በየደረጃው፣ የሰው እንቅስቃሴ ላይ ገደብ በማበጀት ብቻ ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ ትልቅ ውጤት ማስመዝገብ ትችላለች። ሆኖም ይህንን አማራጭ ስትተገብር ኹለት አደገኛ ፈተናዎች ይገጥማሉ። ይኸውም የከተሞችን ውስጣዊ ስርጭት ለመግታት በሚወሰደው አማራጭ ላይና ከገጠር ወደ ከተማ፣ ከከተማ ደግሞ ወደ ገጠር ከሚደረጉ መሰረታዊ የሸቀጦች ዝውውር ጋር በተያያዘ ነው።

ወረርሽኙን በዋና ዋና ከተሞች ከማገድ አንጻር አሁን መንግሥት እየወሰደው ያለው አቋም ሥራዎችን በማቆም እንቅስቃሴን መገደብ ነው። ይህ አስቀድሜ እንዳልኩት እንደኛ ላለ አገር ‹ራስን ከማጥፋት› የተለየ ውሳኔ አይደለም። ሥራ ማቆም ማለት በመሠረቱ የመንግሥትን ገቢ፣ የባለሀብቱን ቢዝነስ፣ ከእጅ ወደ አፍ የሆነውን ሠራተኛ ጥሪት በአንድ ላይ ማቆም ማለት ነው።

ዛሬ የሚታየው አንዳንድ ባለሃብቶች እያደረጉት ያለው ድጋፍ ኢኮኖሚው ለ15 ቀን ቢቆም፣ የግል ሠራተኛውን ደመዎዝ ይከፍላል ወይስ የመንግሥት ሠራተኛውን ይደጉማል? ዛሬ ጥቂት ሚሊዮንና ቢሊዮን ብሮች ስላየን በስሜት ተነሳስተን ነገሮችን ወደመዘጋጋት ከገባን፣ ከዚያ በኋላ ሁሉም ነገር ይረፍድበታል። የዚያን ጊዜ የኮሮና ወረርሽኝ ዝቅተኛው ስጋታችን ይሆናል።

ሠርቶ መብላት ያልቻለው በሚሊዮን የሚቆጠር ወጣት ወደ ወንጀል ፊቱን ያዞራል። የሚሠራበትን ድርጅት ማቃጠል፣ የግለሰቦችን ቤት መስበር ይጀምራል። ከዚያ በኋላ ቤት መሆን ለጥቂቶቹም ቢሆን የማይቻል ይሆናል። ይህ ችግር መቼ እንደሚያበቃ ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው። ኹለጽ ወራትን ቢቆይስ? የኛ ኢኮኖሚ ያንን መቋቋም ይችላል?

እኛ እንደነ ሩዋንዳ አይደለንም፤ ያለን ኽዝብ 8 እና 10 ሚሊዮን አይደለም። 115 ሚሊዮን እኮ አንዴ ከተነደለ ለማቆም የማይቻል ከባድ ጎርፍ ነው። ሌላው ከዚህ ጋር ተያይዞ መታሰብ ያለበት ጉዳይ መጪው ጊዜ ክረምት መሆኑን ነው። አገራችንን በኢኮኖሚ አሽመድምደን ወደ ክረምት መግባት አንችልም።

በኹለተኛ ደረጃ ከከተማ ወደ ገጠርና ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገውን የሸቀጦች ስርጭት አስመልክቶ በመንግሥት እየተሄደበት ያለው አቅጣጫ ‹‹አስፈላጊ የሆኑ ሸቀጦች እንቅስቃሴ መታገድ የለበትም›› የሚል ይመስላል። ይህ አግባብ የሆነና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ጉዳይ ነው።

ሆኖም ቫይረሱ በእቃዎችም ላይ ለተወሰነ ጊዜ እንደሚቆይ የተረጋገጠ ስለሆነ፣ በሚጓጓዙት እቃዎችና ሸቀጦች ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ ምን አይነት የጥንቃቄ እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ አልተገለጠም። ሸቀጦቹ ከተራገፉ በኋላም በተለመዱት መደብሮች የሚሸጡ በመሆኑ፣ በአጋጣሚ አንድ የመደብር ባለቤት በቫይረሱ ቢጠቃ፣ መደብሩ የወረርሽኙ ማከፋፈያ ሊሆን ይችላል። ይህንንም በሚመለከት የተባለ ነገር የለም።

እንደ መፍትሔ . . .
ኢትዮጵያ ከገባችበት ወቅታዊ ችግር ለመውጣት የተጠቀሱትን አንገብጋቢ ጉዳዮች ከብዙ አቅጣጫ ዐይታ መፍትሔ ማበጀት ይኖርባታል። በከተሞች ያሉ ዋና ዋና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ሳይቋረጡ የቫይረሱን ስርጭት መቆጣጠር የሚያስችል ዘዴ መዘዬድ ይኖርባታል። ከከተማ ወደገጠር የሚጓጓዙ ሸቀጦችና እቃዎች የወረርሽኙ ማጓጓዣዎች እንዳይሆኑና መደብሮችም የቫይረሱ ማከፋፈያዎች ሆነው እንዳያገለግሉ የሚያደርግ መላ መፈለግ ይኖርባታል።

ከዚህ አንጻር ቀጣዮቹን ጥቅል የመፍትሔ ሐሳቦች ለመጠቆም እፈልጋለሁ፤
1ኛ. ከከተማ ወደ ገጠርም ሆነ ከገጠር ወደከተማ የሚደረጉ የዕቃዎችንና የሸቀጦችን እንቅስቃሴ በሚመለከት፣
የእቃዎች እንቅስቃሴ ከሰው ባልተናነሰ ለቫይረሱ ስርጭት ትልቅ ሚና ሊጫዎት ይችላል። ስለሆነም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ የከተማይቱን ዋና ዋና መንገዶች ርጭት በማካሄድ መልካም ሥራ እንደሠራው ሁሉ፣ ይህንን የርጭት ልምድ ለሰውና ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ በብዛት የማጽዳት ዘዴዎች ጋር በማጣመር ከመንገድ በላይ አንገብጋቢ በሆኑት የምግብና የመጠቀሚያ ሸቀጦች ላይ መተግበር ይገባል።

2ኛ. በከተሞች አካባቢ ያሉ ዋና ዋና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ስለማስቀጠል፡-
የቫይሱ ስርጭትን ለመቆጣጠር የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተዘግተዋል። የዚህ መነሻ ደግሞ በቤተሰቡና በመሥሪያ ቤቱ መካከል የተሳሰረ የጥንቃቄ አተገባበር ስርዓት ማበጀት ባለመቻሉ ነው። እኛ እንደዛ ለማድረግ አቅማችን ስለማይፈቅድ፣ የግድም አውሮፓውያኑና ሌሎች አገራት ጋር በዚህ መመሳሰል ስለማይኖርብን፣ ለምን መሥሪያ ቤቶቻችንን ከሰው ነፃ በማድረግ ፋንታ ከቫይረስ ነፃ የማድረግ አማራጭን አንሞክርም? በእኔ አመለካከት ድርጅቶችን እና ቤተሰብን ያስተሳሰረ የጥንቃቄ ዕቅድን በመተግበር ማሳካት ይቻላል።

ይህም የጥንቃቄ እቅድ በሦስት የቁጥጥር ተዋረዶች የሚመራ፣ የመከታተልና የመቆጣጠር እቅድ በመተግበር ልንፈፅመው እንችላለን ብዬ አምናለሁ።
ሀ) ፖለቲከኞች ሳይሆኑ የጤና ጥበቃ፣ የኅብረተሰብ ጤና እና የጤና ተቋማት የተናበበ ቅንጅትን በማድረግ እስከ ቀበሌዎች የሚደርስ የማስተማርና ድጋፍ የማድረግ ሥራ ላይ መሰማራት። በዚህም አቅምን ለመጠቀም እንዲያስችል ከሃይማኖት አባቶች፣ ከእድር መሪዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ጋር በቅንጅት መሥራት።

ለ) በአገሪቱ ውስጥ ያሉ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ከመዝጋት ይልቅ ሠራተኞቻቸውን ከማንም ጋር በማይገናኙበት ሁኔታ ሥራቸውን የሚሠሩበትን ዘዴ መቀየስ። ለምሳሌ አንድ አምራች ድርጅት ያሉትን ሠራተኞች ‹ሄዳችሁ ቤታችሁ ተቀመጡ› ከማለት፣ በትራንስፖርት እና በሸመታ ጊዜ ከማንም ጋር እንዳይገናኙ የመሥሪያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ተንቀሳቃሽ ወይም ቋሚ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብር ማኖር።
ይህም ከገበያ ሊነሳ የሚችልን ለቫይረስ ተጋላጭነት ያስቀርላቸዋል ማለት ነው። ሌላው ተጋላጭነት የሚነሳው መጓጓዣ ላይ በመሆኑ፣ ድርጅቶች በመስፈርቱ መሰረት ለቫይረሱ የማያጋልጣቸው የመጓጓዣ አገልግሎት ማመቻቸት።

መ) ሠራተኞቹ ለቫይረሱ ሊጋለጡ የሚችሉበት መንገድ ከሥራ ገብተው ከቤተሰብ ጋር በሚያደርጉት ንክኪ ነው። ይኸውም ምንም እንኳን በመሥሪያ ቤት በኩል የተደረገላቸው ጥንቃቄ ከውጪ ሊመጣባቸው የሚችልን ተጋላጭነት ሊያስቀርላቸው ቢችልም፣ ቤተሰባቸውም በተመሳሳይ መልኩ ካልተጠነቀቀ ቤታቸው ውስጥም ሊጋለጡ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ወደ መሥሪያ ቤትም በሽታው እንዲዛመት ሊያደርገው ይችላል።
ለዚህም እንደ መፍትሔ ‹‹ቤተሰብ ዐቀፍ የጥንቃቄ መመሪያ›› ማዘጋጀት ይቻላል። ይኸውም ሥራ ከሚወጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ውጪ ፍጹም በሆነ መልኩ ቤት ዘግተው እንዲውሉ በማድረግ ነው። ይህንንም ለመቆጣጠር የፖሊስ፣ የመከላከያና ሌሎች የፀጥታ ተቋማትን ከኅብረተሰቡ ጋር ተናበው እንዲያስፈጽሙ ማስተሳሰር ይቻላል።

ከቤት መውጣት የሚያስፈልገው ሠርቶ ገቢ ለማግኘት እንዲሁም ሸምቶ ለመብላት በመሆኑ፣ ኹለቱንም ተናቦ እንዲሟሉ ማድረግና ምርታማ በሆነ መልኩ በሽታውን መግታት ይቻላል።

3ኛ. በትናንሽ ከተሞችና ገጠራማ አካባቢዎች ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ከመሸጫ መደብሮች ሊነሳ ከሚችል የቫይረሱ ስርጭት ስለመከላከል፡-
በአገራችን፣ የገጠሩ ሕዝብና ከፊል ከተሜው ከከተሜው በባሰ መልኩ በብዛት ገዝቶ ለመመሸግ የሚሆን የኢኮኖሚ አቅም የለውም። ስለሆነም አዘውትሮ ወደ ሸቀጣሸቀጥ መደብሮችና ክፍት ገበያዎች መመላለሱ የሚጠበቅ ነው። እናም እነዚህ ገበያዎችና መደብሮች በአገሪቱ ገጠራማ ክፍል ቫይረሱን ለማስፋፋት አይነተኛ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ።

ይህንን አደጋ ከማስቀረት አንፃርም አስቸኳይ የመፍትሄ አቅጣጫ መቀመጥ ይገባዋል ብዬ አምናለሁ። ይህም ላልተወሰነ ጊዜ ክፍት ገበያዎች እንዳይከናዎኑ በማድረግ ሊጀምር ይችላል። ገበሬው ምርቱን የሚሸጥበትንና የሚፈልጋቸውን ሸቀጣ ሸቀጦችን የሚያገኝበትን መንገድ ከመቀየስ አንጻርም፣ እንደቀድሞው የገበሬ ማኅበራት አይነት ጊዜያዊ መጋዘኖችን በማእከላዊ ቦታዎች ላይ በመገንባት፣ ወይንም ያሉትን አገልግሎት በማስጀመር ሊተገበር ይችላል።

ይህ ሲደረግ የሽያጭ ስርዓቱ በመንግሥት እጅ ስር እንዳይገባና ነጋዴዎች ከሥራ እንዳይወጡም መደብሮቹን በጊዜያዊነት በመንግሥትና በነጋዴዎች ጥምር ባለቤትነት የሚመሩ እንዲሆኑ በማድረግ ነጋዴውን ማሳተፍ ይቻላል። የመንግሥት መኖር አስፈላጊነት በዋናነት ምርቱ እና የሽያጭ ሂደቱ ለአደጋ የተጋለጠ እንዳይሆን ለመቆጣጠር በመሆኑ ይህ ወረርሽኝ ሲቆም እንዲወጣ ይሆናል።

4ኛ. በከተማ ሆነ በገጠር ሆነው ከሥራ ውጪ ያሉትንና በዚህ ሂደት ደግሞ ከሥራ ውጪ ሊሆኑ የሚችሉትን የኅብረተሰብ ክፍሎች በሚመለከት፤
በአገራችን በከተማም ሆነ በገጠር የዕለት ጉርሱን መሸፈን የማይችል በርካታ የኅብረተሰብ ክፍል እንዳለ ግልፅ ነው። ይህም ክፍል በዚህ ጊዜ ይበልጥ ተጋላጭ ይሆናል። ስለዚህ የመንግሥትና የሌላው ኅብረተሰብ እጅን የመዘርጋት ግዴታ እዚህ ጋር ነው የሚመጣው። በተጨማሪም አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ሥራዎች የሚሠሩ እንደ ቀን ሠራተኞች እና ጉሊት ቸርቻሪዎች በዚህ ጊዜ ላይ ህልውናቸው አደጋ ላይ መውደቁ ስለማይቀር ለነሱ የተለየ ፓኬጅ ያስፈልጋል።

እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎችን አነስተኛ በሆኑ የመንግሥት መዋቅሮች በመጠቀምና ሌሎች ማኅበረሰባዊ መዋቅሮችን በመጠቀም መለየት፣ ብሎም መመዝገብ ያስፈልጋል። ከዚያም ላልተወሰነ ጊዜ ከቤት እንዳይወጡና የመኖሪያ ቤትና የምግብ ወጪያቸው በመንግሥትና ሌሎች ግብረ-ሰናይ ደርጅቶች እንዲሸፈን ሊደረግ ይችላል።

እንደማጠቃለያ
ይህንን የተቀናጀ ተግባር ለመፈጸም ትልቅ የሆነ ዲሲፕሊንና መናበብ እንደሚጠይቅ ግልፅ ነው። ሆኖም በሽታውን ለመከላከል በሚል እየገባንበት ካለው ሥራን የማቆም የቁልቁለት ጉዞ ስለሚታደገንና፤ ከውስጥም ከውጪም ከፍተኛ በጀት እየተመደበለት ያለው በሽታውን የመቆጣጠር ሙከራ አቅም ስለሚሆንልን መሥራት ይችላል ባይ ነኝ።

ይህ የትግበራ ዘመቻ ተሳክቶ ለውጥ የሚያመጣ ከሆነ፣ ለአገራችን የበሽታውን መድኃኒት ከማግኘት ያላነሰ መልካም ሥም የሚያስገኝላት ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን የሠራተኛው የሥራ ሞራል እንዳይሞት እና ምንም ማነቃቃት ሳያስፈልገን እንድንቀጥል ያደርጋል።

አዳዲስ አሠራሮችን በማስተዋወቅ አዲስ የሥራ ባህልን በአገራችን ይፈጥራል። የተናበበና ወጥ የሆነ አገራዊ ዲሲፕሊንን በመፍጠር ሂደት ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫዎታል። የወረርሽኙን ስርጭት በመንግሥት ብቻ ሳይሆን በቢዝነስ ማኅበረሰቡና በእያንዳንዱ ቤተሰብ ደረጃ ኃላፊነት እንዲወሰድበት በማድረግ በአጭር ጊዚ የተሳካ የመከላከል ሥራ እንዲሠራ ያደርጋል።

ታደሰ ጥላዬ የቢዝነስ ትንታኔ የሚሰጡ፣ የኢኮኖሚ ምሩቅና በሔሚስፌር ብሪጅ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው። በኢ-ሜይል አድራሻቸው tadinvela@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 75 ሚያዝያ 3 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com