“8ኛው የኢትዮጵያ ንጉሥ” እና “ንግሥቲቱ” አንድም ኹለትም ይሆኑ?!

Views: 251

ከባለፉት ጥቂት ወራት ጀምሮ በዘመነኛው ኮሮና ምክንያት ያዝ ለቀቅ፣ ቦግ እልም፣ መቅ ድብዝዘ እያለ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮችን ትኩረት የሳበ አንድም ኹለትም የሆነ ጉዳይ ነበር። ይሁንና ባለፈው ሳምንት ማብቂያና በዚህኛው ሳምንት የብዙዎችን ቀልብ ሰቅዞ በመያዝ ሲያወያይ፣ ሲያከራክር እና ሲያነታርክ ከርሟል። ይህ አንድም ኹለትም የሆነ ጉዳይ “የ8ኛው የኢትዮጵያ ንጉሥ” እና “የንግሥቲቱ” ጉዳይ ነው።

በተለይ “የኢትዮጵያ 8ኛ ንጉሥ”ን ሰይፉ ፍንታሁን በሚያዘጋጀው የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ፕሮግራም እንግዳ እንዳደረገው ካስታወቀ በኋላ ዝግጅቱ በብዙ ተመልካቾች ጥያቄና ግፊት ምክንያት እንደማይተላለፍ ወዲያውኑ ማስታወቁ የንጉሡ ጉዳይ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ዐቢይ ርዕሰ እንዲሆን አድርጎታል።

“8ኛ የኢትዮጵያ ንጉሥ” የ26 ዓመት ወጣት የሆነው አቡዬ በላቸው ይባላል። “እጩ ንጉሥ” አንድ አፍታ ከተባለው የድረገጽ ቴሌቪዥን ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ውልደቱ እና እድገቱ ጎጃም፣ አዊ ዞን ዳንግላ ወረዳ እንደሆነ፤ የኹለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንደጨረሰም ጥሩ ውጤት በማምጣት በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርቱን መከታተል ከጀመረ በኋላ ከመንፈሳዊ ዕይታ አንጻር አብሮ አልሔድ ሲለው ሜካኒካል ምህንድስና ትምህርት ክፍል በመዘዋወር ጥቂት መማሩን ገልጿል። እርሱ እንደሚለው “በእግዚያብሔር ስለተጠራ” ከአባቶች በረከት ለማግኘት ትምህርቱን እርግፍ አድርጎ በመተው ጉዞውን ወደ ገዳማት አድርጓል።

ንግሥናው የአሁኑንም ሆነ የወደፊቱን የማየት ጥብብ ባላቸው የገዳም አባቶች የተረጋገጠ መሆኑን የሚገልጸው አቡዬ፣ ፈጣሪ በረቀቀ መንገድ ለራሱም ራዕይ እንዳሳየውና ምልክትም እንደሰጠው ተናግሯል። በቃለ ምልልሱ ላይ የኢትዮጵያን ትንሳኤ የማመጣው እኔ እንደሆንኩ ተበስሮልኛል ሲል በልበ ሙሉነት ገልጿል።

ይሁንና የአቡዬ ቃለ ምልልስ የብዙዎች መነጋገሪያ ከመሆን አላመለጠም። በተለይ ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኒያን ዘንድ ከፍተኛ ነቀፌታ የተሰነዘረበት ሲሆን ብዙዎች ግን መሳቂያና መሳለቂ አደርገውታል፤ የስድብና የእርግማን ውርጅብኝ አድርደውበታል። ይሄ “8ኛው ንጉሥ ሳይሆን የ8ኛው ሺሕ መቃረብ አንድ ማሳያ ምልክት ነው” ሲሉም ያመረሩበትም ነበሩ። ሌሎች በበኩላቸው ደግሞ ይህ ራሱን 8ኛው የኢትዮጵያ ንጉሥ አድርጎ የሚቆጥረው ግለሰብ ክፍኛ በአእምሮ ህመም የታወከ ነው ሲሉ ሐዘኔታቸውን ከመግለጽ ባሻገር ከሚያሳየው ምልክት በመነሳት የያዘው በሽታ ይሔ ነው በማለት ሥም ጠርቶ እስከመናገር እና በአስቸኳይ የሕክምና እርዳታ እንዲደረግለት ሲሉም ወትውተዋል።

ሌላኛዋ የሰሞኑ መነጋገሪያ የሆነችው ደግሞ ስንዱ ወይም እህተ ማሪያም ስትሆን እሷም የንግሥና ካባ ደርባለች። ንግሥቲቱ የምትታወቀው በተለይ በዩቲዩብ ቻናል በተለይ “እመቤታችን ድንግል ማሪያም እየተገለጠችልኝ ብዙ ነገር አሳስባኛለች” በማለት መልዕክቷን ለተከታዮቿ በማጋራት በሰፊው ትታወቃለች፤ ትንቢትም ትናገራለች። ንግሥቲቱን ከዚህ ቀደም እናውቃታለን የሚሉት እንደጻፉት ከሆነ እህተ ማሪያም በ2008 ከእንግሊዝ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ ኑሮዋን አዲስ አበባ ላይ ያደረገች፣ ባለትዳር (ባለቤቷ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ በመኪና አደጋ ሕይወቱ እንዳለፈ ይነገራል) እና የአራት ልጆች እናት እንደሆነች እና ባለእንግሊዝ ፓስፖርት ነች።

ንግሥቲቱ የምትታወቀው ማሪያም ተገልጻላት ከምትነግራት መልዕክቶ በመነሳት በኢትዮጵያ ሊከሰቱ ስለሚችሉ ነገሮች በመተንበይ ነው። በተለይ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አባቶችን ከመንቀፍ አልፋ የቤተ እምነቱ መጠሪያ ሥም ዳቦ ሳትቆርስ “ርትዕት ተዋሕዶ” በማለት ለውጣዋለች። ይህን መልዕክት የያዘውም ቪዲዮ በከፍተኛ ደረጃ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል።

የንግሥቲቱ እህተ ማሪያም ጉዳይ መጦዝ የጀመረው ግን ተከታዮቿ ቀደም ብለው ዐቢይ ፆምን እንዲፈቱ ማድረጓና የራሷን የጊዜ ሰሌዳ መጠቀሟ ነው። ከማኅበራዊ ትስስር መድረኮች የመረረ ትችት የተሰነዘረባት ቢሆንም ደጋፊዎቿ ከተለያዩ የድረገጽ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ባደረጓቸው ቆይታ ለትችቶቹ ደፋር ምላሽ እንዲሁም በምንም የማይናወጽ ድጋፋቸውን ሲገልጹ ተሰምቷል።

ከሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እህተ ማሪያም በሥርአተ ቀኖናዬም ሆነ ዶግማዬ ላይ ጥሰት ፈጽማለች፣ በሥሜም ነግዳለች በማለት በመደበኛው ፍርድ ቤት ክስ እንደምትመሰረት ማስታወቋ የነገሮች ጡዘት ጫፍ ማሳያ ሆኖ ተወስዷል። ከቀናት በፊት ደግሞ ፖሊስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጣስ ንግሥቲቱን ዘብጥያ ማውረዱ ሌላ ጉድ ይዞ ይመጣ ይሆን በሚል ብዙዎች ጉዳዩን በአንክሮ እየተጠባበቁት ይገኛሉ።
ንግሥቲቱ የ8ኛው የኢትዮጵያ ንግሥና እውነተኛነት ምስክክርነት መስጠቷን ንጉሡ ራሱ በአንደበቱ የተናገረ ሲሆን የኹለቱም ንግሥና እርስበርስ እንደማይጻረርም ተናግሯል። ይሁንና በተወሰኑ የቀናት ልዩነት ኹለቱም ላይለያዩ በሚመስል መልኩ በፖሊስ ተይዘው ወደ እስር ቤት የተጋዙ ቢሆንም እስካሁን ግን መነጋገሪያነታቸው እንደቀጠለ ይገኛል።

ቅጽ 2 ቁጥር 78 ሚያዝያ 24 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com