ኮቪድ 19 በሕጻናት ዓለም

Views: 321

ልጆችና ሕጻናት ባለንጹህ ነፍስ ናቸው። የአዋቂዎችን ያህል በዙሪያቸው ያሉ ነገሮችን አይረዱም። የራሳቸው ዓለም አላቸው፣ በራሳቸው መንገድ ነገሮችን ይተረጉማሉ። እንደ ንጹህ ወረቀት የሚያርፍባቸውን ይከትቡና ይይዛሉ። ለአዋቂነት መሠረት፣ ለልምድ መጀመሪያ ለጸባይና ለአመል መሠረት በዚህ የልጅነት እድሜ ይጣላል። ታድያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽ መከሰት በዚህ የልጆች ንጹህ ዓለም ላይ ምን ዓይነት ተጽእኖ ያሳርፋል እንዲሁም ከወላጆችና አሳዳጊዎችስ ምን ይጠበቃል የሚለውን በሚመለከት መቅደስ (ቹቹ)ሐሳባቸውን እንዲህ አካፍለዋል።

በማኅበራዊ ድረ ገጽ የተሰጨ አንድ ተንቀሳቃሽ ምስልን እናስታውስ። የሕክምና ባለሞያ የሆነ አንድ ሰው የቤቱን በር ከፍቶ ይገባል። ኹለት ዓመት በቅጡ እንዳልሞላው የሚያስታውቅ ትንሽ ልጁ አባቱ ስለመጣለት ደስ ተሰኝቶ እንደ እንቦሳ እየቦረቀ አባቱን ለማቀፍ ይንደረደራል። ነገር ግን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ውጪ ሥራ የዋለው አባቱ ልጁን ማቀፍ አይገባውም ነበርና፣ ልጁ እንዳይጠጋው ሲል በርቀት በእጁና ከፍ ባለ ድምጽ ከለከለው።

በዚህ ቅጽበት የሕጻኑ ልጅ ድንጋጤና ሁኔታ የአባትየው ልጁን ማቀፍ አለመቻልና መሰበር፣ በገጽታው ላይ የሚነበበው የጥልቅ ሐዘን ስሜት፣ ያንን ቪድዮ ለተመለከተ ሁኔታው ከዐይነ ልቡና የማይጠፋ ያደርገዋል።

ኮቪድ 19 የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በልጆች ሥነ ልቦና ላይ ያሳደረው ጫና ቀላል አይደለም። ሥራ ውለው የሚገቡ ወላጆች ልጆቻቸውን ‹አትሳሙኝ፣ አትቀፉኝ፣ አትጠጉኝ› ሲሉ ልጆች ግራ ይጋባሉ። ወላጆቻቸው የጠሏቸው ሊመስላቸውም ይችላል። ልጆች ምን ሊያስቡ እንደሚችሉም አዋቂዎች ሊገምቱ እንኳ አይቻላቸውም።
ይህም በቫይረሱ ምክንያት ብቻ አይደለም። በቤተሰብና ወላጅ፣ እንዲሁም አሳዳጊ ሰዎች ለቫይረሱ በሚሰጡት ግብረ መልስ ውስጥ ልጆች አጥልለው የሚወስዱትና በመረዳታቸው ልክ የሚቀበሉት ፍርሃትም አለ።

ሮይተርስ ከለንደን ባወጣው ዘገባ፣ ‹‹ልጆች ከዚህ ቀደም ሰምተዋቸው የማያውቁትን ቃላት እየሰሙ ነው›› በማት ዘገባውን ይጀምራል። ወረርሽኝ፣ አካላዊ መራራቅ፣ ከቤት አለመውጣት፣ አለመጨባበጥ ወዘተ ለልጆ አዲስ ጉዳይ ነው። ቫይረሱ ምንም እንኳ በልጆች አካል ላይ የሚያደርሰው ጉዳትና ምልክቶቹ መለስተኛ ቢሆኑም፣ በሥነ ልቦና ግን ከዛ የበለጠ ተጋላጭ ናቸው። ወረርሽኙና የሰዎች ግብረ መልስ በልጆች አእምሮ ውስጥ የሚፈጠረውም የማይረሳ ጠባሳ መሆኑ አይቀርም።
የጤና ስጋትና ፍርሃት ያለበት ትውልድ እናፈራለን የሚል ፍርሃትም በብዙ ሰዎች ዘንድ እንዳለ ሮቶርስ በዘገባው ጠቅሷል። ይልቁንም በቅርበት የልጆችን ጉዳይ የሚከታተሉትን ይህን ስጋት ከማንም በላይ ወርሰውታል።

በደቡብ ኢንግሊዝ የቤተሰብ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ኒኪል ቾፕራ፣ ለሮይተርስ በሰጡት አስተያየት ስለራሳቸው ልጆች አንስተዋል። የኹለት እና የአራት ዓመት ልጆች ያሏቸው ኒኪል፣ ይልቁንም የአራት ዓመት ልጃቸው ‹እጃችንን ካልታጠብን እንሞታለን› ማለቱንና ይህም በአእምሮው የሚመላለስ ሐሳብ ስለመሆኑ ይናገራሉ።
ታድያ የሥነ ልቦና ባለሞያዎች እንደሚሉት፣ አዋቂ ሰዎች በፈሩና በተጨነቁ ቁጥር ልጆችም ተመሳሳይ ስሜትን ያሳያሉ። ምክንያቱም ይጠብቁናል ብለው የሚተማመኑባቸው አዋቂዎችና ወላጆቻቸው ፍርሃት ውስጥ ሲገኙ፣ ልጆች ደኅንነት አይሰማቸውም። እናም ታድያ የሚያሰጋው የአዋቂዎች ፍርሃት እንጂ የልጆች ብቻ አይደለም ሲሉም የሕክምና ባለሞያው ይጠቅሳሉ። ወደ ልጆች የሚተላለፈው የአዋቂዎች ስጋት ነውና።

ልጆች ከወዲሁ ቅጥ ያጣ ፍርሃትና ጭንቀት ውስጥ ይገኛሉ። ገና ልጅ በመሆናቸውን ምክንያታዊ ሆኖ ነገሮችን ተረድቶ አገናዝቦ መልስ ለመስጠት አእምሯቸው የዳበረ ባለመሆኑ፣ በአእምሯቸው እድገት ላይ ፍርሃት ይዘራል። እናም የማረጋጋት ሥራ የቤተሰብ ኃላፊነት ነው። ልጆች ፍርሃት እንዳይሰማቸውና ደኅንነት እንደሌላቸው እንዳይቆጥሩ ቤተሰብና ተንከባካቢ ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ።

የዓለም ጤና ድርጅትም በተመሳሳይ ቫይረሱ በአእምሮ ጤና እና በሥነ ልቦና ላይ ላለው ተጽእኖ ትኩረት እንዲሰጥ ብሏል። አካላዊ ርቀትና ማኅበራዊ ፈቀቅታ ግድ ያሉበት ጊዜ በመሆኑ፣ እርስ በእርስ መጠያየቅን ማብዛት ያስፈልጋልም ብለዋል። ከዛም ደግሞ ፍርሃትና ጭንቀትም ደብቆ እንደጀግና መሆን ሳይሆን ሰዎ የሚሰማቸውን ስሜት አውጥተው በመነጋገር ሊያቃልሉት ይገባል ሲሉ ይመክራሉ። በተለይ ልጆች ባለበት ቤት ይህ ለልጆችም የሚጠቅም ነው።

ታድያ ቫይረሱ በልጆች ሥነ አእምሮ ላይ ምን ያስከትላል የተባለ እንደሆነ፣ የዓለም ጤና ድርጅት በተለይ የሕጻናት መንፈስ በእጅጉ ይረበሻል ብሏል። የሕጻናት ፍርሃትም ከአዋቂዎች ጋር ተመሳሳይ ነው ያለው ድርጅቱ፣ ይህም እንዳልሞት እንዲሁም ከዘሞዶቼ መካከል አንድ ሰው እንዳይሞት የሚል ስጋት ሲሆን ሕክምና ቦታ መገኘትንም መፍራት ሌላው ነው።

እንዲያም ሆኖ ይህ ስጋት የሚሰማቸው በአዳጊ የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉት ናቸው እንጂ ትንንሽ የሆኑ ሕጻናት እየሆነ ያለውንም በቅጡ ላይረዱት ይችላሉ። ለዚህም መፍትሔው ለልጆች ፍቅርና እንክብካቤ መስጠት፣ ትኩረትም አለመንፈግ ነው፣ እንደ ሕክምና ባለሞያዎች ምክር። እውነቱንም ለልጆች በግልጽ መንገር ወሳኝ ሲሆን፣ ይህም የሚደረገው ልጆች ሊገባቸው በሚችል ቀላል መንገድ ሊሆን ይገባል።

ምን ይደረግ?
ከላይ በየመካከሉ ምን መደረግ እንዳለበት የሚለውን በተበታተነ መልኩ አንስተናል። ይህም ባለሞያዎች የሚመክሩት ነው። ታድያ ምክረ ሐሳቦችን ወደ አንድ ወደዚህ እንሰብስባቸው።

እንደሚታወቀው ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ተከትሎ ሕጻናት ልጆች በቤት ይውላሉ። አሁን ልጆች እንደ በፊቱ ውጪና መንገድ ላይ ወጥተው መጫወት አይችሉም። ከጓደኞቻው ተለይተዋል። በቤት ውስጥ ቤተሰብ ሲሰበሰብ ደግሞ ከሚነሳው ርዕሰ ጉዳይ መካከል የወረርሽኙ ነገር አንዱ ነው። ታድያ በዚህ ጊዜ ጥንቃቄ አድርጉ ሲሉ የሥነ አእምሮ ሐኪሞች አዋቂዎችን ይመክራሉ።

ለምሳሌ ከቫይረሱና ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ የሚነገሩ ዜናዎችን ልጆች በስፋት እንዳያዩ ማድረግ ያስፈልጋል ወይም እንዲያዩ መፈቀድ የለበትም። በተለይም እድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች የሆኑትን ከዜናዎችም መጠበቅ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ቴሌቭዥን ባለበት ቤት የልጆች መርሃ ግብሮች አሉና ያንን እንዲያዩ ማድረግ ነው። ቢያንስ በእነዛ መርሃ ግብሮች ልጆች በእኩዮቻቸው ስለወረርሽኙ በሚግባቡበት ቋንቋ ስለሚነግሯቸው፣ ለመረዳት ይችላሉ።
ታድያ በዚህ ጊዜ ከአዋቂዎች የሚጠበቀው የቴሌቭዥን ጣቢያዎችን ራሳቸው እንደፈለጉት ሳይሆን ልጆችንም ተሳቢ ባደረገ መልኩ መቀየር ነው።

በተጓዳኝ ጉርምስና እድሜ ላይ ያሉ ልጆችን ደግሞ በራሳቸው መወሰንና ማሰብ ቢችሉም፣ ለብቻቸውና ከኢንተርኔትና ማኅበራዊ ሚደያ ጋር ለረጅም ሰዓት መተው እንደሌለባቸው ባለሞያዎች ያሳስባሉ። ማኅበራዊ ሚድያው እንደ ቴሌቭዥን ጣቢያ በመቆጣጠሪያ ወላጅ ሊቀይረው የማይችል ስለሆነና ብዙ አስጨናቂ ወሬዎች ሊቀርቡበት ስለሚችሉ፣ ከዛም አዳጊ የሆኑ ልጆችን መጠበቅ ያስፈልጋል።

ይህ ቅጥታ ወደ ልጆች አእምሮ ሊገባ የሚችል ሲሆን፣ አካላዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የተደረጉ ለውጦ ደግሞ ግራ ሊያጋቧቸው ይችላሉ። በተለይም አሁን በኢትዮጵያ ቫይረሱ ስርጭቱ እንደ አጀማመሩ ቀላ ባልሆነበት ጊዜ፣ ከሥራ ይቀሩ የነበሩ ሰዎችም አማራጭ አጥተው ወደ ሥራ መግባት በመጀመራው፣ ጥንቃቄ በከፍተኛ ሁኔታ የግድ ይላል። እናም በአካል ተራራቁ፣ አትቀራረቡ የሚለው ማስጠንቀቂያ ልጆች በእነርሱ ጥፋ የሆነ እንዳይመስላቸው፣ ከዚህ ቀደም ሆኖና ሰምተውት የማያውቁት በመሆኑም፣ እንዳይጨነቁ ለማድረግ፣ የሆነው ሁሉ በእነርሱ ላይ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ያሉ ልጆች ሁሉ ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ እንዲያውቁ ማድረግ ጠቃሚ ነው የሚል ምክረ ሐሳብን ባለሞያዎች ይሰጣሉ።

ታድያ ልጆች ያሉበትን ሁኔታ መረዳት እንደተባለው ወሳኝ ነው። በመሰልቸት ቸል ማለት አያስፈልግም። ጥያቄያቸውንም በእርጋታና በንቃት ታግሶ መመለስ ይጠቅማል። ሲናገሩም ሥራዬ ብሎ ማዳመጥ እንደዛው።

ፎክስ ኒውስ ከአንድ የሥነ ልቦና ሐኪም ጋር ባደረገው ቆይታ ካሳው ጥያቄ ውስጥ አንደኛው ልጆች ጭንቀት እንዳለባቸው በምን ይታወቃል የሚል ነው። ባለሙያው ሲስረዱ ልጆች ማለቃቀስ ማብዛት፣ ትኩሳትና ሌሊት መባነን፣ እልህ ማጋባትና መቆጣት ከታየባው ተጨንቀው ሊሆን እንደሚችል ማሳያ ምልክት ነው ብለዋል።
በእድሜ ከሕጻናት ትንሽ ከፍ ያሉ አዳጊዎች ሲሆኑ ደግሞ፣ የምግብና የእንቅልፍ ፍላጎት መቀነስ፣ አቅም ማነስ፣ ትኩሳትና የሆድ ሕመም፣ መርሳትና ግራ መጋባት ምልክቶች ናቸው። አንዳንድ ወጣቶችም ራሳቸውን በቤተሰብ ውስጥም የሚያገሉ ሲሆን ስለጤናቸው መስጋትና ስለወደፊትም መጨነቅ ይታይባቸዋል። እነዚህ ሊከሰቱ እንደሚችሉ የሚታወቁ ምልክቶች ሲሆኑ፣ ወላጅና አሳዳዎች እነዚህን ምልክቶች በማስተዋል ልጆችን እንዲደግፉ ይጠበቅባቸዋል።

ላብቃ! በልጆች ሥም የሚወቅስም ሆነ የሚያመሰግን ተወካይ አካል ስለሌለ እንጂ፣ ብዙ የሚወቀስና ጥቂት የሚያስመሰግን ሥራ በየጊዜው ይታያል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለልጆች ያስተላለፉት መልእክት ደግሞ አንዱ የሚያስመሰግን ጉዳይ ነው። ‹ልጅ ያቦካው…› ዓይነት ብሂሎች ኋላ ሊቀሩ የሚገባና ልጆችን በቁምነገር የማሰብ፣ ትኩረት ሰጥቶ የማነጋገርና የመስማት ባህልም እንደሚያስፈልገን ሊዘነጋ አይገባም።

እናም በዐቢይ መልእክትን እናውሳ! የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያን ሕጻናትና አዳጊዎች ዛሬ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል መንግሥታችሁ ምን እየሠራ እንደሆነ፣ ከእናንተም ምን እንደሚጠበቅ ለእናንተ ለመግለጥ እፈልጋለሁ። ይህ መንግሥት የእናንተ የልጆችም መንግሥት ነውና።

ልጆች! የኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ የመጣ ወረርሽኝ ነው። ከቻይና ተነሥቶ ዓለምን እያዳረሰ ነው። ብዙ አገሮች ዜጎቻቸውን በሞት አጥተዋል። በኢትዮጵያም ብዜ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘውብናል።

አካላዊ ርቀትን መጠበቅ አንዱ መከላከያ ነው። አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ማለት ከሌላ ሰው በአራት የልጆች ርምጃ ርቆ መቆምና መቀመጥ ነው።
እጅን ደጋግሞ በሳሙና መታጠብ ኹለተኛው መከላከያ ነው። ልጆች ጠዋት ስትነሱ፣ ስትጫወቱ፣ ከተጫወታችሁ በኋላ፣ ከምግብ በፊትና በኋላ፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በሳሙና ታጠቡ። ስትታጠቡ ጣታችሁን፣ መዳፋችሁን፣ በጣታችሁ መካከል ፣ የእጃችሁን መዳፍ ፈትጋችሁ በውሃና በሳሙና ታጠቡ።

ትምህርት ቤት ተዘግቶ ቤት ነው ያላችሁት። አደራ ከቤት አትውጡ። ትምህርት ቤት የተዘጋው በንክኪ ምክንያት እንዳይተላለፍባችሁ ብለን ነው። እናንተ ለነገዋ ኢትዮጵያ በጣም ታስፈልጓታላችሁ። ስለዚህ ጤናችሁን ጠብቁ።

ቤት መዋል ሊሰለቻችሁ ይችላል። ግን እንዳትታመሙብን፣ እንዳትሞቱብን ብለን ነው። ቤት ስትሆኑ አጥኑ፣ መጽሐፍ አንብቡ፣ አካላዊ እንቅስቃሴ ሥሩ፣ የልጆችን ጨዋታ ተጫወቱ።

ተጠንቀቁ እንጂ አትጨነቁ። ዐዋቂዎች የተለያዩ መረጃዎችን ሲነጋገሩ እየሰማችሁ ልትጨነቁ ትችላላችሁ። ወላጆቻችሁ ሲወያዩ እናንተን እንዲያስቡ እንነግራቸዋለን። ነገሩን በእናንተ ቋንቋ እንዲያስረዷችሁ አደራ እላቸዋለሁ። አይዟችሁ፤ ይሄን ከባድ ጊዜ እናልፈዋለን፤ ፈጣሪ እናንተን ይሰማልና ለኢትዮጵያ ጸልዩ።

ቅጽ 2 ቁጥር 79 ግንቦት 1 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com