‹ሙያን መማር…ጾም ላለማደር›

Views: 243

በኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ቀላል የማይባሉ ሰዎች በየቤታቸው እንዲቀመጡ ተገደዋል። ቫይረሱም ስርጭቱና የያዛቸው ሰዎች ቁጥር ከእለት እለት እየጨመሩ መሆኑ ሰዎች ያለማንም ማስጠንቀቂያና ማሳሰቢያ በራቸውን እንዲዘጉና ችግሩ እስኪያልፍ እንዲቆዩ ግድ ብሏቸዋል።

ታድያ ቤት ሆነን ምን እየሠራን ነው? አንዳንዶች ለንባብ ጊዜ ሲያገኙ ሌሎች ፊልሞችን በመመልከት፣ በመጻፍ፣ በማቀድ፣ በመተኛት ወዘተ እያሳለፉት ይገኛሉ። ተማሪዎችም በቤታቸው እየተማሩና እያጠኑ መሆኑ ግልጽ ነው። በጥቅሉ ግን ጠቃሚ እስከሆነ ድረስ የትኛውም ለሰው የተስማማው ተግባር አያከራክርም፣ በሉ በርቱ ነው የሚባለው። የጤና ባለሞያዎች እያሉት እንዳሉት በቤት ውስጥም ቢሆን እንቅስቃሴ ማድረግ መረሳት የለበትም የሚለው ሳይዘነጋ።

ታድያ የወጥ ቤትስ ነገር እንዴት ነው? ከቤት አለመውጣት ይመከር የጀመረበት ሰሞን በማኅበራዊ ድረ ገጽ ከምጣድ ያልወጣ እንጀራ ምስል በብዛት ይታይ ነበር። ይህ ታድያ ‹ቤት ውስጥ ነኝ፣ ሙያ እየተማርኩኝ ነው› ዓይነት መረጃ ለማቀበል ነው። ይህን የሚሉትም ወንዶች ናቸው።

በነገራችን ላይ እንደው ሆነ ብለው ከሰነፉ እንጂ ወንዶች በሙያ ጎበዝ ናቸው። የጓዳ ሲሆንና የእናቶች ኩሽና ጭስ የማይጠፋው፣ በቅጠል ያሸበረቀ፣ የሚሞቅና ጠባብ በመሆኑ እንጂ፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ትልቅ እውቅና ያላቸው ብዙ ወንድ ሼፎች ናቸው። በዘመናዊ አባባል ሼፍ መባል ሲያኮራ፣ በእናት ጓዳ ገብቶ አብሮ ደፋ ቀና ማለት ግን የሚያሳፍር?

በእርግጥ እኛስ አገር በፊት ከደመቀ ግርማ ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜው ሼፍ ዮሐንስ ገብረኢየሱስ ድረስ ወንድ የወጥ ወይም የምግብ ቤት ባለሞያዎችን እናውቅ የለ? እንደውም በተለያየ መልክና ዓይት ምግቦችን ማዘጋጀትም ያውቁበታል። ድሮ ቢሆን ሙያ ያላት ሴት ነበር ለሚስትነት የምትፈለገውም፣ የምትታጨውም። አሁን ግን እንደዛ አይደለም።

ወደፊት እንደውም ሙያ የሌለው ወንድ ጉዱ ነው! ጊዜ የማይቀይረው ነገር የለም።
እንደ ኢትዮጵያ ባሉና ብዙዎች በቀን ሦስት ጊዜ መብላትን ሲባል ብቻ በሚሰሙበት አገር ይህን ማለት ከድፍረት ካልተቆጠረ፣ ምግብ ማብሰል ለአንዳንዶች እንደ ተሰጥኦ ነው። በትርፍ ጊዜቸው ምግብ መሥራት የሚወዱ ሴቶችም ወንዶችም አሉ፣ ሠርተው ማብላት ደስ የሚያሰኛቸውም እንደዛው። ብዙ ጊዜያቸውን ምግብ በማብሰል የሚያሳልፉ ሰዎችም አሁን ላይ ጥቂት አይደሉም።

ለውጦች እንዲህ በሂደት ይመጣሉ፣ ምግብ እንደማብሰል። እንዳልኩትና እንደሚታወቀው ከዚህ ቀደም ወንድ ልጅ ኩሽና ከገባ ‹ተርመጠመጠ› ይባላል። ኩሽናው በድንጋይ ጉልቻ፣ በእንጨት ማገዶ፣ በጢስ የታፈነ መሆኑ ወይም በዘመናዊ መንገድ የኤሌክትሪክ ምድጃ የሚለኮስበት ይሁን፣ ብቻ ሐሳቡ ወንድ ልጅ ምግብ ወደ ማብሰል መሄዱ ነውር ነው የሚል ነበር።

ቀስ በቀስ ግን ነገሮች ሲቀየሩ ወንዶች ማጀት መታየታቸው ተለመደ። ምንም እንኳ አሁንም ያልተለመደባቸው ቤቶች ቢኖሩም፣ በየቤቱ በሚገኙ የቴሌቭዥን መስኮቶች ግን የተለመደው ስርዓት ተቀይሯል። ይህም በሂደት በየቤቱ ለየቤተሰቡ ተጽእኖ ፈጥሮ ለውጥ ማምጣቱ አይቀርም።

እናም ይህን እንላለን፣ ቤት ውስጥ ስትሆኑ አዲስ ነገር መማርን ምርጫችሁ አድርጉ። አንዱም የወጥ ቤት ሙያ ነው። ይህ ለወንዶችም ለሴቶችም ነው። የየቤቱ ሼፍ በመሆን ማገልገልን ማን ቀላል አደረገው!
ሊድያ ተስፋዬ

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com