ኮሮናቫይረስን ከአለማችን ፈጽሞ ማጥፋት ላይቻል ይችላል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስጠነቀቀ

Views: 106

የዓለም ጤና ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ማይክ ሪያን ቫይረሱ ከአለማችን መቼ ጨርሶ ሊወገድ ይችላል የሚለውን መተንበይ እጅግ ከባድ እንደሆነ ተናገሩ፡፡

ዶክተር ሪያን ጄኔቫ ላይ በተደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት “ይህ ቫይረስ ፈጽሞ ላይጠፋና ከሰው ልጅ ጋር አሁን ድረስ እንደቆዩት በሽታዎች አንዱ ሆኖ በኅብረተሰቡ ውስጥ ሊኖር ይችላል በማለት አክለውም ኤችአይቪ አልጠፋም፤ ነገር ግን ቫይረሱን በተመለከተ መደረግ ያለበትን እያደረግን ነው” ሲሉ ምሳሌ ጠቅሰዋል።

ዶክተሩ “የኮሮናቫይረስ መቼ ሊወገድ እንደሚችል ማንም ሰው ሊተነብይ አይችልም” ሲሉ እምነታቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ጊዜ ከ100 በላይ ለኮሮናቫይረስ ይሆናሉ የተባሉ ክትባቶች ላይ ምርምር እየተደረገ ቢሆንም፤ ዶክተር ሪያን እንዳሉት ክትባት በሽታውን ላያጠፋው ይችላል ተብሏል፡፡

እንደ ምሳሌም ኩፍኝን አንስተው ምንም እንኳን የመከላከያ ክትባት ቢኖረውም እስካሁን ድረስ ሊጠፋ እንዳልቻለ ተናግረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም በሽታውን ማጥፋት ባይቻል ጥረት ከተደረገ መቆጣጠር እንደሚቻል ጠቁመው ነገር ግን ለበሽታው ክትባት ቢገኝ እንኳን፤ ቫይረሱን ለመቆጣጠር “ግዙፍ ጥረት” ማድረግን ይጠይቃል ብለዋል።

ሌላኛዋ የድርጅቱ ኃላፊ ማሪያ ቫን ኬርኮቫ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ “ከዚህ ወረርሽኝ ለመውጣት የተወሰነ ጊዜ እንደሚወስድብን ማሰብ ይኖርብናል” ብለዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

እስካሁን በዓለም ዙሪያ ወደ 300 ሺህ የሚጠጋ ሰው በኮቪድ-19 ምክንያት የሞተ ሲሆን ከ4.3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ በበሽታው መያዛቸው የሚታወቅ ነው፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com