ኢትዮጵያና አሜሪካ የ230 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራረሙ

Views: 137

ኢትዮጵያ እና አሜሪካ 230 ሚሊዮን ዶላር የልማት ትብብር ስምምነት መፈራረማቸው ተገለጸ።
የልማት ትብብር ስምምነቱን አሜሪካ በዓለም ዐቀፉ የዩናይትድ ስቴት ልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩ.ኤስ.ኤይድ) በኩል ከኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስቴር ጋር መፈራረማቸውን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ አስታውቋል።
የ230 ሚሊየን ዶላር የልማት ትብብር ስምምነቱንም የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታ አድማሱ ነበበ እና የአሜሪካ የዓለም ዐቀፍ ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሴያን ጆንስ ፈርመዋል።
ስምምነቱ አሜሪካ በጤና፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በኢኮኖሚ እድገት እና መልካም አስተዳደርን ለማሻሻል የምታደርግውን ጥረት የሚያጠናክር መሆኑም ታውቋል። በአዲሱ የልማት ትብብር ስምምነት ማእቀፍ ውስጥም የአሜሪካ የዓለም ዐቀፍ ተራድኦ ድርጅት ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከሌሎች ዓለም ዐቀፍ እና አገር በቀል ድርጅቶች ጋር በመሆን የጤና ተደራሽነትንና ጥራትን ለማሳደግ፣ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ እንዲሁም በግል ዘርፍ የሚመራ ሞዴል የምጣኔ ሀብት እድገት ለማምጣት የሚሠራ መሆኑም ታውቋል።
ዩ.ኤስ.ኤይድ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሴያን ጆንስ በፊርማው ወቅት፥ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር አጋርነታችንን የሚያድስ ስምምነት በመፈራረማችን ደስታ ይሰማናል ብለዋል።
አዲስ የተፈረመው ስምምነት ከገንዘብ በላይም በኹለቱ አገራት መካከል ለዓመታት የዘለቀውን የሕዝብ ለሕዝብ አጋርነት የሚያጠናክር እና በጋራ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚረዳ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል። ድጋፉ ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ያላት አገር ለመሆንና እድገቷን ለማፋጠን የምታደርገውን ጥረት እንደሚያግዝ በፊርማው ሥነ ሥርዓት ላይ ተገልጿል።
አሜሪካ ባለፉት 20 ዓመታት ለኢትዮጵያ 13 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን ኤምባሲው አስታውሷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 80 ግንቦት 8 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com