በቀለ ገርባ እና ‘ስቶኮልም ሲንድሮም’ ምን አገናኛቸው?

Views: 355

በየሳምንቱ በማኅበራዊ ትስስር መነጋገሪያ የሚሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ብዙ ናቸው። ይሁንና አንዳንዶች ደግሞ ከሌሎቹ ጎልተው የብዙዎችን ቀልብ ይስባሉ። ከሰሞኑ መነጋገሪያ ጉዳዮች ጎልቶ በመውጣት የኦሮሞ ፌደራሊስት ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር በቀለ ገርባ ለአንድ ሚዲያ የሰጡት አስተያየትን ያክል ትኩረት የሳበ ጉዳይ አለ ለማለት አያስደፍርም።

በቀለ ገርባ በሕወሓት ዘመን በእስር ቤት ውስጥ ምንም ዓይነት የግርፋትና የድብደባ ስቃይ አልነበም ሲሉ ራሳቸውን አብነት አድርገው መናገራቸው ከግራና ከቀኝ ከፍተኛ የሐሳብ ልዩነቶች፣ ሙግቶችና ትችቶች እንዲሁም ወቀሳዎችን አስነስቷል። ብዙ አይሁኑ እንጂ የበቀለን ሐሳብ የደገፉና ያራገቡም አልታጡም።

ከዚህ ቀደም በቀለን በከፍተኛ ደረጃ ይደግፉ የነበሩ የማኅበራዊ ትስስር ተጠቃሚዎች ለዘብተኛ በሆነ ነገር ግን ግልጽ ባልሆነ መልኩ በቀለ ገርባ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ጉዳዩን ባያነሱት ይመርጡ እንደነበር ጠቅሰው ያለፉ ሲሆን ሌሎች በዚሁ ጎራ የሚመደቡት ሰዎች የበቀለ ገርባን ንግግር ቀለል አድርጎ መመልከት ይገባል በማለት ያላቸውን አጋርነት ገልጸዋል፤ በቀለ ቀደም ሲል የከፈሉት መስዋዕትነትን በምንም ተዓምር አያደበዝዘውም ሲሉ ድጋፋቸውን ቸረዋል።

በተለይ የሕወሓት ደጋፊ የሆኑ የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ተጠቃሚዎች “ይኸው ንጽሕናችን በአደባባይ ተረጋገጠ” ሲሉ ጮቤ የመርገጥ ያክል ደስታቸውን የገለጹ ሲሆን ወሬውም እንዲናፈስ እና መነጋገሪያ እንዲሆን ሐሳባቸውን በማጋራት የራሳቸውን ድርሻ ተወጥተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ እሳት ጎርሰው እና እሳት ልሰው ይህ የተለየ ዓላማ (motive) ለማስተላለፍ ተፈልጎ የተላለፈ መልዕክት ነው ሲሉ የበቀለ ገርባን ንግግር ያለማወላወል በማውገዝ አቋማቸውን ያንጸባረቁም አሉ። ሕወሓት በዘመኗ በዜጎች ላይ በእስር ቤቶችም ውስጥ ሆነ ውጪ ፈጽማዋለች የሚባለውን እንግልት፣ ስቅየት፣ መደፈር፣ ግድያ እና ደብዛ መጥፋት፤ በአጠቃላይ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት በይፋ እውቅና ወይም ይቅርታ ባልሰጠችበት ሁኔታ የበቀለ ገርባ ለሕወሓት የድጋፍ ምስክርነት መስጠት ስውር ዓላማ በሥልጣን ላይ ያለውን የዐቢይ አሕመድን መንግሥት ለመታገል ስልታዊ ትብብር ለመመስረት የተሰጠ አረንጓዴ የይለፍ ፈቃድ ነው ሲሉ ጠንከር ያለ ትችታቸውን ሰንዝረዋል። በአንድ ክፍል አብረዋቸው የታሰሩ የእስር ዘመን አጋሮቻቸው ጭምር የበቀለን ንግግር ከመታዘብ አልፈው ሸንቆጥ በሚያደርግ መንገድ አውግዘዋል፤ እውነታውንም ክደዋል ብለዋል።

ሦስተኛ ወገኖች ግን የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ሐሳባቸውን ሳይሰነዝሩ የበቀለን ንግግር እንደ ምሳሌ በመጥቀስ ከዚህ በፊት በተለይ ከፖለቲካ ወይም ከሰብኣዊ መብቶች አያያዝ ጋር በተያያዘ እንቅስቃሴ በማድረጋቸው በተደጋጋሚ ለእስር የተዳረጉ፤ በእስር ቤትም አካላዊ ጥቃት እንዲሁም ሥነ ልቦናዊ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ምንም የሥነ ልቦና ክትትል እና ምክር (counsel) አገልግሎት ስለማይደረግላቸው የሥነ አእምሮ ቀውስ ሊፈጠርባቸው ይችላል ሲሉ ሙያዊ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ሌሎች ባለሙያዎች ደግሞ ዳቦ የተቆረሰለትን ሳይንሳዊ መጠሪያ በመጠቀም በ‘ስቶኮልም ሲንድሮም’ የመጠቃት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው በማለት በዚህ ዓይነት የሥነ ልቦናዊ ቀውስ የሚሰቃይ ሰው በአብዛኛው ለበዳዮቹ ወይም ላሰቃዮቹ የማዘን እና ድጋፍ የማሳየት ባህርይ ያሳያሉ ሲሉ የአዕምሮ ቀውሱን መገለጫዎች ጠቅሰዋል።
እንደዚህ ዓይነት ሙያዊ ገለጻዎች አንዳንድ የማኅበራዊ ትስስር ተጠቃሚዎች ያስፈገገ ሲሆን ሌሎች ግን መላምቱ በቁም ነገር መታየት አለበት ሲሉ ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል። ይሁንና ኢትዮጵያ ውስጥ ከባድ ስቃይ ያሳለፉ ሰዎች ከስቃያቸው ለማገገም ወይም ለመገላገል የባለሙያዎች እገዛ እምብዛም እንደማያገኙ የአደባባይ ሚስጥር መሆኑ ግልጽ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 80 ግንቦት 8 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com