ጉዞው ከአንዱ ኮሮና ወደ ብዙ ‹ኮሮናዎች› እንዳይሆን!

Views: 328

ከሰሞኑ በአዲሰ አበባውና በመቀሌው ቡድን መካከል የሚታየው የዛቻ ልውውጥ እንደ ዋዛ መታየት አይገባውም የሚሉት ግዛቸው አበበ፣ ቀድሞ በሕወሓትና ሻእብያ መካከል የነበሩ ተመሳሳይ መልክ ያላቸውን የቃላት ልውውጦች አውስተዋል። በቃላት መተነኳኮሱ አዲስ ነገር ስላልሆነ ቀላል ቢመስልም፣ መዘላለፎች አሁን ወደ ጦርነት ዛቻ እያደጉ መሆኑን ማስተዋል ይገባል ሲሉም ማሳያዎችን ጠቅሰው፣ ለሕዝብ ሌላ ‹ኮሮና› እንዳይሆኑበት በኹለቱም ወገኖች በኩል ሊኖር የሚገባውን ማስተዋል ጠቁመዋል።

‹‹ርክብ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይን ሕዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራን ክብ ንጉሆኡ ጀሚሩ ኣብ ጎይታን ጊላን ዝተመስረተ ርክብ›› ይህ የሕወሐትና የሻእቢያ አሳፋሪ ግንኙነት መግለጫ ጋህዲ በተባለውና በቀድሞው የሕወሐት ኮማንደር በአስገደ ገብረሥላሴ በተጻፈው መጽሐፍ ሽፋን ላይ በጉልህ የሚነበብ ነው። ግርድፍ ትርጉሙ ‹‹የሕወሐትና የሻእቢያ ግንኙነት ገና ከመጀመሪያው አንስቶ ሕወሐት እንደ ባሪያ ሻእቢያ እንደ ጌታ የነበሩበት ነው›› የሚል ነው።

አስገደ ገ/ሥላሴ መጽሐፍ ውስጥ በእርግጥም ሻእቢያ እንደ ፈላጭ ቆራጭ ጌታ፣ ሕወሐት ደግሞ ከጌታው ርቆ መሄጃ እንደሌለው ሎሌ ሆነው መኖራቸውን በሚያስገርም ሁኔታ ያስረዳል። አንዳንዴም የሕወሐት ሎሌነት ዳፋ ለትግራይ ሕዝብም እንደተረፈ ከዚሁ መጽሐፍ መረዳት ይቻላል።

ይህን መሰሉ ውርደትን፣ ግፍንና ንቀትን ችሎ በመኖር የተሞላ ግንኙነት በኹለቱ ቡድኖች መካከል ከፍተኛ ችግር በተከሰተ ጊዜ ወደ መረረ ብቀላ እንዳመራ በባድመ ጦርነት ዋዜማ በወቅቱና በማግስቱ ከተከናወኑ በርካታ ጉዳዮች ማየት ተችሏል። በጦርነቱ ዋዜማ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ኤርትራውያን፣ የኤርትራ ተወላጅ የሆኑ ኢትዮጵያውያን (ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸውን ላለመቀየርና ኤርትራን በሚያስገነጥለው ሪፈረንደም ያልተሳተፉትን) ሁሉ፣ ከሕጻናት እስከ አዛውንቶች በጥድፊያ የተባረሩትና የኤርትራ መንግሥትም ብድሩን በተመሳሳይ የመለሰው የብቀላ ዱላ ስለተነሳ ነው።

በጦርነቱ ከፍተኛ እልቂትና ውድመት በሚያስከትል የጥላቻ ስትራቴጂ የተካሄደውና በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ መቶ ሺሕ የሚጠጉ ወጣቶች የተሰውትና የዚያኑ ያህል ሰው አካሉን ያጣውም ጭካኔ የተሞላበት መበቃቀል ስለተተገበረ ነው። በጦርነቱ ማግስት (የኤርትራ መንግሥት ከተሸነፈ በኋላ) ሕወሐትን ለክፍፍል የዳረገው ለኢትዮጵያ የሚጠቅም አጀንዳ አንስተው ስላልተግባቡ ሳይሆን አስመራ ድረስ ገብተው የኤርትራን መንግሥት በመገልበጥ አሻንጉሊት መንግሥት አስመራ ላይ በመትከል የብቀላ ዘመቻውን ለመደምደም በፈለጉና ይህን በተቃወሙ የሕወሐት አውራዎች መካከል ግጭት በመፈጠሩ ነው።

ይህን ጉዳይ መለስ ብሎ ማየት ያስፈለገው ከሰሞኑ በአዲሰ አበባውና በመቀሌው ቡድን መካከል የሚታየው የዛቻ ልውውጥ እንደ ዋዛ መታየት አይገባውም ለማለት ነው። ላለፉት 28 የሕወሐት/ኢሕአዴግ ዓመታት ሕወሐት እንደ ጌታ ሌሎች የኢሕአዴግ አባል እና አጋር የሚባሉ ቡድኖች ሁሉ መሄጃ የሌላቸው ራስ ወዳድ ሎሌዎች ሆነው መኖራቸው የታወቀ ጉዳይ ነው። በዚህ ወቅት ከምርጫው ጋር በተያያዘ በሚደርጉ የቃላት ልውውጦች የቀድሞዎቹ ጌቶች አሁንም ጌታ ነኝ ለማለት ሲሞክሩና ቀድሞዎቹ ሎሌወች በተለይም ኦሕዴዶች ተረኛ ጌቶች ሆነናል እያሉ ብድራቸውን ለመመለስ የፈለጉ መስለው እየታዩ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያልተመረጡ የማስፈራሪያ ቃላትን እየተጠቀሙ ‹የምርጫውን ጉዳይ በእኔ ፍላጎት አስወስነዋለሁ፤ ካልሆነ ግን ዋጋህን እሰጥሀለሁ›› ሲሉ የትግራዩ መሪ ‹‹ለማንም ጫጫታ ተንበርክከን አናውቅም፣ የሚያሳስበን ነገር የሕዝባችን ጉዳይ ብቻ ነው›› ሲሉ ተሰምተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጨረባ ምርጫ እናካሂዳለን በሚሉት ላይ እርምጃ ለመውሰድ አስፈላጊውን ዝግጅት እንዳደረጉ በመናገር ሲዝቱ፣ የትግራዩ ምክትል ፕሬዘደንት ደግሞ ማንንም እንዳመጣጡ ለመመለስ ተዘጋጅተናል፣ በጦርነትም ቢሆን ሲሉ ዝተዋል።

ይህ በቃላት የመተነኳኮስ ነገር አዲስ ነገር ስላልሆነ ቀላል ቢመስልም፣ የመዘላለፍ ዘመቻው ‹የቀን ጅቦች፣ ውስኪ ጠጭዎች፣ ባንዳዎች፣ ተላላኪዎች፣ የአራት ኪሎ ሕጻናት› ወዘተ…. የሚሉ ስድቦችን ከመሰናዘር ወደ ጦርነት ዛቻ እያደገ መሆኑን ግን ማስተዋል ይገባል። ከዚህ በተጨማሪ የአራት ኪሎው ቡድን ታንኩንም ባንኩንም ተቆጣጥሬአለሁ የሚል ስሜት ያለው መሆኑና የመቀሌው ቡድን ደግሞ ከዚህ በፊት አንበርክኬ የገዛኋቸው ስለሆኑ አቅመ ቢሶችና የተከፋፈሉ ናቸው በሚል እሳቤ ራሱን እያደፋፈረ መሆኑ፣ ግልጽ ነውና ትንሽ ስህተት ትልቅ እልቂትን ልትወልድ እንደምትችል በመገመት ኹለቱም ወገኖች ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባቸዋል።
ይህን መሰሉ በነገር የመጎነታተል ጉዳይ ወደ ታችም እየወረደ ነው። በምክር ቤቱ ወስጥ የሕወሐቱ ተወካይ ‘ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ዥግራ ናት ይሏታል’ ብለው በመተረት የዐቢይ ቡድን ምርጫዋን ሊበላት ዘዴ እየቀየሰ መሆኑን ሲናገሩ፣ የቀድሞው ኦሕዴድ የአሁኑ የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ ተወካይ ደግሞ ‘ጅብ በማያውቁት አገር ሄዶ ቆዳ እንጥፉልኝ ይላል’ ብለው በመተረት ሕወሐት ስለ ምርጫ አሳቢና ተቆርቋሪ መስሎ ማታለል የሚችለው የእሱን የምርጫ ታሪክ የማያውቁ ሰዎች ወዳሉበት አገር በመሄድ ሊሆን እንደሚችል በምጸት ሸርድደዋል።

ኹለቱም ቡድኖች በቁጥጥራቸው ስር ባሉና በደጋፊዎቻቸው ሚዲያዎች የየራሳቸውን ሕጋዊነትና ሕዝባዊነት የሌላውን አምባገነንነትና ሕገ-ወጥነት በሰፊው እየሰበኩ ነው። የመሀል አገሮቹ ሚዲያዎች የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እያሉ የሰሜኖቹ ሚዲያዎች ደግሞ የመቀሌ ነዋሪዎች አስተያየት ሰጡ እያሉ የሚሠሩት አሳፋሪ ፕሮፓግንዳ እስከ 2010 ሲፈተፍቱት የነበረውን ወሬ የሚያስታውስ ነው።

ያኔ እነዚሁ ሚዲያዎች በአንድ ድምጽ ጸረ-ሕወሐት/ኢሕአዴግ አመጽ የሚያካሂዱትን ወጣቶች ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን ለመናድ የተሰማሩ አሸባሪዎች እያሉ ይወርፏቸው እንደነበረና በመንገድ ላይ አስተያየት የሰጡ ነዋሪዎች የሚሏቸው ግለሰቦችና ምሁራንም ተመሳሳዩን ውረፋ ይሰነዝሩ እንደነበረ የሚዘነጋ አይደለም። አሁን ደግሞ እነዚህኞቹ የአዲሰ አበባ ዩንቨርስቲ እያሉ እነዚያኞቹ የመቀሌ ዩንቨርስቲ ምሁራን ወዘተ… የሚሏቸው አንዳንድ ግለሰቦች ነገር ሲሰማ፣ ‘ውሻ በበላበት ይጮኻል’ የሚለውን ተረት የሚያስታውስ እየሆነ ነው።

የአዲስ አበባው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትና የመቀሌው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የደብዳቤ ተኩስ ልውውጥ መጀመራቸው እየተሰማ፣ የደብዳቤ ግልባጮች በማኅበራዊ ሚዲያዎች እየተለቀቁ ነው። ‹የእኔ መንግሥት ይበልጣል! አይ የእኔ መንግሥት ይበልጣል!› እያሉ በመከራከር ላይ ናቸው።

ሕዝብ የኹለቱም ተረት ማለትም የጅቡም ሆነ የዥግራዋ ተረት ለኹለቱም ቡድኖች በደንብ እንደሚሠራ ያውቃል። ወደ 28 ዓመታትን አብረውና ተባብረው፣ ጌታና ሎሌ ሆነው በሕዝብና በአገር ላይ የዘመቱ የአገርና የሕዝብ ጠላቶች እንዲሁም የታሪክ ጸሮች መሆናቸውን በደንብ ያውቃል። አሁን የኹለቱም ጎራዎች አውራዎችና ጭፍራዎች ሁሉ በየተገኙበት ቦታ ለሕዝብ ሕይወት አሳቢ፣ ለአገር ሕልውና ተቆርቋሪ መስለው ለመታየት የሚሞክሩት በዚሁ ባልተመረጡበት ቦታ ሆነው ቀጥለው ጥቅማቸውን ለማስከበር መሆኑም ከማንም የተሰወረ አይደለም።

የአዲሰ አበባውም ሆነ የመቀሌው ቡድን ለ28 ዓመታት የተፈጸመውን ወንጀልና ዝርፊያ በጥቂት ግለሰቦች ላይ ለጥፎ ዘራፊዎችንና ወንጀለኞችን አቅፎና ተንከብክቦ የሚኖር ስርዓት ዘርግተው፣ ነገር ግን ኹለቱም ጻድቅና ሃቀኛ መስለው በሥልጣናቸው ላይ ለመክረም በማሴር ላይ ናቸው። ኹለቱም ጎራዎች ደክሞና ለፍቶ ፎቆች ያፈራውን፣ ዘርፎና ሰርቆ ባለ ፎቆች ከሆነው ለመለየት ምንም ዓይነት ሥራ ሲሠሩ አልታዩም። ኹለቱም ጎራች በጭንቅላት ብቃቱ ጥሮና ግሮ ባለ ዲግር፣ ባለ ማስተርስና ሦስተኛ ዲግሪ የሆነውን፣ በሕሊና ቢስነት የትምህርት ማስረጃ ዘርፎና ገዝቶ ምሁር ነኝ ከሚለው ለመለየትም አንዳችም ፍላጎት የላቸውም።

ኹለቱም ጎራዎች እንዲህ ሆነው ነው ለአገርና ለወገን ተቆርቋሪ መስለው የሚታዩት። በጣም የሚገርመው ነገር አንዱ ጎራ የሌላውን ጎራ ወንጀል ለማጋለጥ እንኳ ድፍረት የሌለውና በአንዱ ጎራ ያለ ወንጀለኛ ታሪክ መጋለጥ በሌላው ጎራ ያለ መሰሉን ጉድ የሚዘከዝክ በመሆኑ ወንጀላቸውን ለመሸፋፈን የተማማሉ ዓይነት መሆናቸው ነው።
ከዚህ በፊት የሲዳማን ሕዝብ የራስን ክልል የማግኘት ጥያቄ ለማፈን ሲባል ሕገ-መንግሥቱ ወደ ጎን ሊጣል ብዙ ጥረት ተደርጎ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ገዥው ቡድን የምሁራን የተባለ ኮሚቴ አቋቁሞ ለደቡብ ክልል የሚበጅ በማለት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፍላጎት ብቻ ያማከለ ሐሳብ አቀረበ። ከዚህ በላይ ደግሞ የሰላም ምኒስቴር ከዚህ በፊት የሲዳማ ሕዝብ ጥያቄ ተሰሚነት እንዲያገኝና ሕገ-መንግሥታዊ መፍትሔ እንዲሰጠው ግዴታቸውን ለመወጣት በሚጥሩ በክልልና በዞን አመራር ቦታ ላይ በሚገኙ ሰዎች ላይ የሽብር ሚኒስቴር ሆኖባቸው እንደነበረ የሚረሳ አይደለም።

በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስመራ ሄደው ሳለ ሲዳማ ውስጥ ደም መፋሰሰ ተከስቷል። ስለዚህ አሁንም ቢሆን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ ቡድኖች አቋቁሜ፣ አጥንቼና አስጠንቼ በአራት ጠቃሚ ነጥቦች ላይ ደርሻለሁ ማለት ያስቆጣው፣ ምርጫ እናካሂዳለን የሚሉ ወገኖችን ብቻ አለመሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። ምርጫው መካሄድ የለበትም ከሚሉና የሲዳማ ክልል የመሆን ሕዝባዊ ጥያቄ ያለፈበትን ሂደትና አሁን የደረሰበትን ግራ አጋቢ ደረጃ ያጤኑ ወገኖችም ናቸው ብዙ ምክንያታዊና አሳማኝ ቅሬታ እያሰሙ ያሉት።

ጠቅላዩ እንደ ሕጻናት ሊያጃጅሉን እየሞከሩ ነው። ጠቅላዩ ጠብ የምትለው ሐሳብና ውሳኔ ሁሉ የእኔን የሥልጣን ዕድሜ ለማስቀጠል የምትጠቅም መሆን አለባት ባይ ሆነዋል። እንደ ሌሎች የአፍሪካ መሪዎች የሥልጣን ዕድሜን ለማስቀጠል በሕገ-መንግሥቱ ላይ ልዩ ጨዋታ ጀምረዋል። ኢትዮጵያ የውስጥ ሰላሟን ስታጣ ሕግን ለማስፈን ደካማ ሆነዋልና በብቸኛ ወሳኝነት በሥልጣን ላይ መክረማቸው የበለጠ ችግርን ያስከትላል። ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች አግኝታቸው የነበሩትን ዲፒሎማሲያዊ የበላይነቶችና ተደራድራ ጥቅሟን የማስከበር እቅሞች አውድመዋቸዋልና ብቸናኛና ዋና መሪ ሆነው መቀጠላቸው አገርን ይጎዳል ወዘተ…. የሚሉ ወገኖችም ናቸው ተቃውሞ እያሰሙ ያሉት።

ዛቸውም ምርጫ እናካሂዳለን የሚሉትን ወገኖች ብቻ ሳይሆን የተለየ ሐሳብ ያላቸውን ሁሉ ምርጫ ይካሄድ ብለው እንደሚሟገቱ ቆጥሮ የተሰነዘረ ነው። እዚህ ላይ ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛቻ ለአንዱ አንበሳ ሆኖ ለመቦጫጨቅ ለሌላው ደግሞ ፒኮክ ሆኖ ከማሽካካት ያለፈ እርምጃ እንደሚሆን የሚጠብቁ ብዙዎች ናቸውና፣ ብልጽግናዎች መሪአቸውን አደብ ግዙ ቡሊ ተመራጭ ነው።

ከዚህ ቀደም 43 ወታደሮች (ብዙወች ኮማንዶወች ናቸው ይሏቸዋል) ከዋና እና ምክትል አዛዦቻቸው (ኮማንደርና ምክትል ኮማንደር) ጋር ሆነው ወደ መቀሌ በአንቶኖቭ ሄደው እዚያው መቀሌ አየር ማረፊያ ውስጥ ተከበው፣ ኮማንደርሩና ምክትል ኮማንደሩ ተጠርተው እጅ ስጡ ወይም በተኩስ እንጨርሳችኋለን የሚል ምርጫ ቀርቦላቸው ኮማንደሮቹም ለወታደሮቻው የገቡበትን ስጋት ገልጠውላቸው እጃቸውን ሰጥተው ሕይወታቸውን አትርፈዋል። እስረኞች መሆናቸውንም የትግራዩ ምክትል ፕሬዘደንት ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ጋዜጠኞችን ጠርተው በአማርኛ በሰጡት መግለጫ አሳውቀዋል።

ደብረጽዮን ትግሬ በመካከላቸው እንዳይኖር ተደርጎ ተመራረጡ ያሏቸው ወታደሮችና አለቆቻቸው ወደ መቀሌ የሄዱበትን ግዳጅ ይፋ ባያደርጉትም፣ በትግራይ ሕዝብ ላይ ጦርነት ለማካሄድ ታስቦ በአስተዋይነታችን አክሽፈነዋል፣ አቀዝቅዘነዋል ብለዋል። ለመሆኑ የጦር ኃይሉ አንድ ክፍል አገራዊ ግዳጅ ተሰጥቶት መደ ቀመሌ ተልኮ ከሆነና ተልዕኮውን መወጣት ላይ ዕንቅፋት ገጥሞት፣ በምርኮ ተይዞ፣ ትጥቁን ፈትቶ፣ እስረኛ ተደርጎ ከሆነ በዚያ የሚገኙት ሰሜን ዕዝንና ማዕከላዊ ዕዝን የመሳሉት ኃይሎች እገዛ ያላደረጉለት ለምንድን ነው?

ድብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ይህን መቀሌ የገባ ጦር ብንመታው በሌላ ቦታም ተመሳሳዩ ነገር የመከሰት ዕድሉ ሰፊ ስለሚሆን ታግሰን መጠነ ሰፊ ጦርነት አስቀርተናል ካሉ በኋላ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ‹ሳንጠይቃችሁና ያለ ፈቃዳችን ጦር ወደ ክልላችን ለምን ትልኩቡናላችሁ?› ስላቸው ጠቅላዩ ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ነግረውኛል ብለዋል።

ብልጽግናዎች ሆይ! ሌላ ውርደት ከመምጣቱ በፊት ጠቅላዩ ማስጠንቀቂያ የሰነዘሩት ደብረጽዮን እና ጃዋር በእኩል ዐይን እያዩ ነውን ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። ለሕዝብ አሳቢ መስላቸሁ ባልመረጣችሁ ሕዝብ ትከሻ ላይ ተፈናጥጣችሁ ለመክረም በማሰብ ብቻ እንደ ጋሪ ፈረስ የአንድን ግለሰብ ሐሳብ ይዛችሁ አትንጎዱ። ከሁሉም ምርጫ ቦርድ ዕውቅና ከሰጣቸው ተቃዋሚዎች፣ ከዘረኝነትና ከአድባይነት የራቁ ምሁራን፣ ሐይማኖታዊ ወገንተኝነት የማያሳዩ የአገር ሽማግሌወች ወዘተ… በተገኙበት ግልጽና ነጸ ውይይት ይደረግ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትግራይ መሪ፣ የኦሕአዴዱ የምክር ቤት አባል ከሕወሐቱ መሰሉ ጋር ደረጉትን የመሰለ ዛቻና ዘለፋ መወራወር እያያችሁ ከማጨብጨብ ባሻገር የመለስ ዜናዊና የኢሳያስ አፈወርቂ በባድመ ጦርነት ዋዜማ ሲወራወሩት የነበረውን ነገር አስታውሱ። ኹለቱም ወገኖች ‘ቀድሞ ነበር እንጅ መጥኖ መደቆስ…’. የሚለውን ብሂል ለማስታወስ የሚገደዱበትን ጊዜ ባይናፍቁ ደግ ነው።

የአዲስ አበባና የመቀሌ ቡድኖች ደሙን እንዲያፈስልንና ሕይወቱንም እንዲሰዋልን ልንልከው የምንችለው ብዙ ወጣት አለ ብለው፣ በወጣቱ ኪሳራና በወጣቱ ዕዳ ከፋይነት ተማምነው እንደ ቀልድ ወደ እሳት እያመሩ መሆኑንም የኢትዮጵያ ሕዝብ (የትግራይን ሕዝብ ጨምሮ ማለት ነው) ሊዘነጋው አይገባም። ዕውቀትና ተሞክሮ ኖሯቸው በከፍተኛ መኮነንነት ማዕረግ በኢትዮጵያ ጦር ውስጥ በአመራር ቦታ ላይ ያሉ ሰዎች ይህ የሥልጣን ሽሚያ የተጠናወተው አካሄድ ጦሩን በዘሩ ብቻ ሳይሆን በሐይማኖቱም ገምድሎ አደገኛ መራኮት ውስጥ እንዳያስገባው፣ ወደዚህ ዓይነት መራኮት ውስጥ ሊያስገቡት የሚፈልጉና እሳት ጭረው፣ በአዲሰ አበባ በመቀሌ ምሽጎቻቸው ውስጥ ሆነው ከሩቅ እሳቱን ለመሞቅ የሚሞክሩት ወገኖችንም አደብ ግዙ ብለው መምከር የሚገባበት ጊዜ አሁን መሆኑም ውል ሊልላቸው ይገባል።

የአራት ኪሎና የመቀሌዎቹ ችግር ‹አወቁሽ ናቅሁሽ› ነው፤ ‹አሁን ጌታዬ አይደለህም – አሁንም ጌታህ ነኝ› ዓይነት ንትርክም ነው። ምርጫ አይካሄድም ባዮቹ ችግሩን ግልጽነት በጎደለውና ብልጥ ነኝ በሚል መንፈስ ለሥልጣን ዕድሜ ማራዘሚያ ለመጠቀም መከጀላቸው ግልጽ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ምርጫ ካላካሄድን ሞተን እንገኛለን ባዮቹ በጀቱና ቁሳቁሱ ተልኮላቸው የራሳችሁ ጉዳይ ቢባሉ ቀጣዩ ጨዋታቸው ምርጫ ማካሄድ ሳይሆን የትግራይ ሕዝብ ለእልቂት እንዲጋለጥ ስለፈለጉ ተጣድፈው ምርጫ አካሂዱ አሉን ብለው ጮኸው የመቀሌ ዩኒቨርስቲና የድጅታል ወያኔ ተከታዮቻቸውን ማጯጯህ ከመሆን የዘለለ እንደማይሆን መገመት ይቻላል።
ኹለቱም ወገኖች አገር፣ ሕዝብ፣ ዴሞክራሲ፣ ፌዴራሊዝም ወዘተ… እያሉ የሚያቅራሩት ለማስመሰል ብቻ ነው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህን ልብ ሊለው ይገባል።
አዲስ አበባና መቀሌ ውስጥ መሽገው ነገር የሚወራወሩት የብልጽግናና የሕወሐት መሪዎች ድርጊት መጨረሻው ጥሩ ላይሆን ይችላል። የጦርነት ልምድ አለኝ የሚለው ወገንም ሆነ የአርሲን ሕዝብ የማያክል ሕዝብ ያለው ጠላት ነው ያለኝ የሚለው ወገን አደብ ካልገዙ ከጀርባው ምንም እንዳይኖር የሚደርግ ነገር በሰላም እና በአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሊሰራ ይገባዋል።

ኹለቱም ወገኖች አሁን ኮቪድ-19ኝን ተመርኩዘው እየሠሩት ያለው ድራማ ኮሮና ባይመጣም በቀጥታ ከምርጫ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ወይም ሌላ ሰበብን ተገን አድርጎ ሊከሰት ይችል የነበረ ነው። ኹለቱም ለሕዝብ፣ ለሕግና ለሕገ-መንግሥት የበላይነት የሚያስቡ መስለው ድራማ እየሠሩ መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት አይገባም። ኹለቱም በሥመ ሕወሐት/ኢሕአዴግ ባጭበረበሩት ምርጫ ሥልጣን ላይ የወጡ፣ በሐሰት ሕዝብ ሥልጣን ሰጥቶናል ብለው የሚመጻደቁ፣ ለስርዓታቸው የሚበጅ ሕገ-መንግሥት በተጭበረበረ አካሄድ ያጸደቁ፣ ራሳቸው ይጠቅመናል ብለው ወደ ሥራ ያስገቡትን ሕገ-መንግሥት ራሳቸው ሲሽሩትና ሲረግጡት የኖሩ ቢሆኑም፣ አሁን ደግሞ ሕገ-መንግሥትን ስለማክበርና ስለማስከበር፣ ሕዝብ በአደራ የሰጠን ሥልጣን ጊዜ ስለማክበር ያለ ሀፍረት በማውራት ላይ ናቸው።

አሁን ኮሮና ሕዝብን ሊጨርስ አሰፍስፏል በሚል ሽፋን ጭቅጭቅ እየሰማን ነው። ይህ ጭቅጭቅ ገደብ ካልተሠራለት ቀድሞውንም እንደ ኮሮና የሕዝብ ጸር የነበሩት ሕወሐት/ኢሕአዴጎች አሁን በአዲሱ አደረጃጀታቸው ኹለት ዓይነት ኮሮናዎች ሆነው ቀጥለው። በምርጫ-97 ማግስት የታየውን የሥልጣንን አፈሙዝ በኃይል የመቆጣጠር ሥራ በድጋሜ እንዳይሠሩት ሊታሰብበት ይገባል።

እስከ አሁን ባለው ሁኔታ ኮሮና (ኮቪድ-19) በአሜሪካና በአውሮፓ ያሳየውን ጠንካራ ክንዱንና ጭካኔውን በኢትዮጵያ አላሳየውም። እባካችሁ ሕወሐቶችም ሆናችሁ ብልጽግናዎች፣ ከወረርሽኝ ለሰወረን አምላክ ለምህረቱ በማመሰገን ላይ ባለው ሕዝብ ላይ እንደ ቀድሞው ኮሮናዎች ሆናችሁ እንዳትዘምቱበት አስቡበት። አዎ! የሕወሐት/ኢሕአዴግ ስርዓት ታጣቂዎች፣ ባለሥልጣናትና ካድሬዎች እንደ ኮሮና ወረርሽኝ ሆነው በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ዘምተው ለሞት፣ ለእስራት፣ ለስደት ከሚዳርጉባቸው አጋጣሚዎች መካከል ምርጫ የሚካሄድባቸው ወቅቶች ተጠቃሾች ናቸው።

ግዛቸው አበበ መምህር ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው gizachewabe@gmail.com ላይ ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 80 ግንቦት 8 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com