ደም ይፈለጋል! ያስፈልጋል!

Views: 72

የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በየዘርፉ ቀላል የማይባሉ በርካታ ቀውሶችን አስከትሏል። ይህም ያደጉ አገራት ወይም ደሃ አገራት ብሎ ሳያደላ፣ ሳይለይ ሁሉንም በእኩል ነው ያጠቃው። ታድያ በየዘርፉ ጽኑ መሠረት ላይ እንገኛለን ያሉ አገራት እንዲህ ከተናወጡ፣ የእኛዋ አፍሪካ እንደምን ትሆን?

እንደሚታወሰው ቫይረሱ ገና ስርጭቱ ከቻይና ውጪ ታየ ሲባል አውሮፓና አሜሪካ የሰጉት ለአፍሪካ ነበር። ድህነቷ ይታወቃላ! ምንም እንኳ ከጥንቃቄና ከስጋት የሚገላግል ባይሆንም፣ በእውኑ ግን ቫይረሱ በአፍሪካ ከታየ ኹለት ወር ገደማ አልፎም ስርጭቱ የተፈራውን ያህል የሆነ አይመስልም።

ከአቅሙ በላይ የተጫነው የጤና ስርዓቷ ኮሮናንም ቀድመው አብረዋት የኖሩትንም በሽታዎች ተሸክሞ እስከመቼ ይቆያል? ይህ የሁሉም ጥያቄ ነው። እንዲያም ሆኖ ከተለያዩ ባለጸጋ አገራት የተገኙ ድጋፎችንና በእጇ የተረፈውን ሀብት አራግፋ ኮሮና ላይ አውላለች። በዚህ መካከል ሌላው በሽታ ደግሞ አለ? ኮሌራና ኩፍኝ ጨርሶ ያልተላቀቋት ናትና፣ ከወቅት ጋር የሚፈራረቁትን እነዚህን በሽታዎች ‹አንዴ! ኮሮና ስለመጣ ታገሱ!› ብላ ልታቆያቸው አትችልም። ከብዙ ጉልበተኛ ጋር ትግል እንደገጠመ በብዙ ፈተና ታጥራለች።

ታድያ በአገራችን በኢትዮጵያ እየሆነ ያለውን ስናይ፣ ይህን ችግር ለመጋፈጥና ሌሎች ወቅትን ጠብቀው የሚከሰቱ በሽታዎችን፣ ተላላፊ ያልሆኑ የጤና እክሎችንና የመሳሰሉት እንዳይዘነጉ አደራ እየተባለ ነው። ሁሉም ትኩረቱን ኮሮና ላይ ያድርግ እንጂ ሌሎችም ከዛ የከበዱ ሕመሞች የበለጠውን ዜጋ እያጠቁ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ በወሊድ ጊዜ የእናቶችን ሞት ቀንሳ አልጨረሰችም። የሕጻናት መቀንጨር ገና ከአጀንዳነት አልወረደም። ዘመናዊና ጤናማ ሕክምና ያልገባባቸው፣ የጽንስ ክትትል ለማድረግ ብዙ ኪሎሜትሮችን አቋጠው እንዲሄዱ የሚገደዱ እናቶች አሁንም ጥቂት አይደሉም። አሁንም በወሊድ ጊዜ ደም የሚያስፈልጋቸው፣ ከታደሉ በሩጫ የሚገኝላቸው እናቶች አሉ።

እንዲህ ባለ የወረርሽኝ ጊዜ ደግሞ ነገሩ ምንኛ እንደሚከፋ መገመት ነው! በተለይም የደም እጥረት እንዳለና በወረርሽኙ ምክንያት በጎ ፈቃድ ለጋሾች በመቀነሳቸው ደም እንደሚያስፈልግ መልእክት ሲተላለፍ ነበር። ታድያስ መለገስ የምንችል ሰዎች ምን እየሠራን ነው?

የመብትና የእኩልነት ትግል በንግግርና በሙግት ብቻ ሳይሆን በተግባር ሊገለጥ የሚገባ እንቅስቃሴ እንደሆነ አምናለሁ። እንደ ሰው፣ እንደ ኢትዮጵያዊ፣ የሰው ሕመም እንደሚሰማው ሰው፣ እንደ ሴት የደም ልገሳው ላይ መሳተፍ ግድ ይለል። ይህም ለሚችሉ ሰዎች ብቻ ነው።

ይልቁንም ዘጠኝ ወር በማኅጸናቸው ልጅ ተሸክመው፣ ደፋ ቀና ብለው፣ በወሊድ ጊዜም ምጥ ላይና በወሊድ ሂደት በሚደርስ ጉዳት ከፍተኛ ደም የሚፈሳቸውን ሴቶች/እናቶች እናስብ። አዎን! የተለያዩ አደጋዎችም የሚደርሱባቸው ሰዎችም ደም ሊያስፈልጋቸው ይችላል። እነርሱንም ወደ አእምሯችን እናቅርብ። እናም ከቻልን እንለግስ።
ቀይ መስቀል ደም ሊሰጡ ለሚመጡ በጎ ፈቃደኞች ከኮሮና ጋር በተገናኘ ስጋት አይግባችሁ ብሏል። የጤና ባለሞያዎች ናቸውና ተገቢውን ጥንቃቄ ከማድረግ አይቆጠቡም። ርቀታችንን ጠብቀን፣ ንክኪን በመቀነስና ንጽህናን በመጠበቅ ከኪሳችን የሚወጣ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ከማያልቀው ተፈጥሮ ካደለን ደም እንለግስ፣ እንስጥ። ለእናቶቻችን በደም እንድረስላቸው!

ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 80 ግንቦት 8 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com