ትውስታ ዘግንቦት 1997

Views: 281

የሕዝብ ዐይን እና አንደበት የሚባሉ ጋዜጠኞችና መገናኛ ብዙኀን በዓለም ዙሪያ ሥራቸውን እንዲሠሩና እውነትን እንዲያወጡ ቢተጉም፣ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ማለፋቸው አልቀረም። ይህም ስለታወቀ ነው ገለልተኛ አካላት አገራት በሚሰጡት የፕሬስ ነጻነትና የጋዜጠኞች መብት ዙሪያ ደረጃ ሰጥተው፣ ምስጋና እንዲሁም ወቀሳን የሚያቀርቡት። ኢትዮጵያም በዚህ ጉዳይ ከኹለት ዓመት ወዲህ እየተመሰገነች ሲሆን፣ አብርሐም ፀሐዬ ይህን በማንሳት ወደኋላ መመለስ እንዳይኖር ሲሉ ያይወቸውን ወደኋላ ሊመልሱ የሚችሉ ጉዳዮች አንስተዋል።

መታሰቢያነቱ ለነፃነት፣ ለዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በቅንነት ዋጋ ለከፈሉ የአገሬ ኢትዮጵያ ልጆች ይሁንልኝ ያሉት ይታገሱ ዘውዱ፣ ከግንቦት 7/1997 እና ከዛ በኋላ በነበሩት ቀናት የሆነውን ከትውስታቸው አካፍለዋል። ይልቁንም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጊቢ ውስጥና በተማሪዎች ሕይወት ውስጥ ያለፈውንና የሆነውን አውስተዋል። በተለይም እጅግ ትልቅ ተስፋ ተሰንቆበት የነበረው ምርጫውና በፍካት የጀመረው የግንቦት ወር እንዴት በሂደት ተስፋን እንዳለጨለሙ ፍሰቱን በተከተለ መንገድ አንባቢን ወደኋላ ይመልሳሉ።

የግንቦት ነገር
በአገራችን ትውፊቶችና ብሂሎች ውስጥ ለቀናትና ለወራት ተመርጦ የሚሰጣቸው ግምት ከሁኔታዎች እና ከወቅቶች መለዋወጥ ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንዳላቸው መገመት አይከብድም። በአጋጣሚ ይሁን በዕድል፣ በዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ሰሌዳ ላይ ጎላ ጎላ ብለው የሚጠቀሱ ክስተቶች በተደጋጋሚ ከተፈጠረባቸው ጊዜያት ወረሃ ግንቦት ቀዳሚው ነው። ባሳለፍነው ሦስት ዐስርት ዓመታት ውስጥ በግንቦት ወር የሆኑትን ብናስብ፣ ኢትዮጵያን በተስፋና በስጋት፣ በብርሃንና በፅልመት ቀጫጭን መስመሮች ላይ እንድትራመድ ያስገደዷትን ሦስት አንኳር የታሪክ አጋጣሚዎችን መጥቀስ ይቻላል።

ኢትዮጵያን ለዓመታት ከሽንፈት ወደ ድል፣ ከድል ወደ ሽንፈት እየተገላበጡ፣ ለምሳ ያሰቧቸውን ለቁርስ እያደረሱ፣ እንኳን ታይተው ሥማቸው ሲጠራ በፍርሃት እያስበረገጉ፣ በእሳትና በብረት ቀጥቅጠው መግዛትን የተካኑበት ጓድ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምን ድንገት ሳያስቡት ከአገር እንደወጡ ሊያስቀራቸው የሚችል ሴራ በገዛ የጦር ጄኔራሎቻቸው ተወጠነላቸው።

የታቀደው መፈንቅለ መንግሥት ከሽፎ ኮሎኔሉ አገር ቤት ተመልሰው ‹‹መጀመርያ ከጦር ግንባር ሸሹ፣ ቀጥሎ ፊታቸውን ወደ ሚስቶቻቸው አዞሩ፣ አሁን ደግሞ ወደኔ›› ያሉላቸው እነኛ የለውጥ ሴረኞች፣ ለቀናትም ቢሆን አገሪቱን ወዴት ሊወስዷት ይሆን በሚል የተስፋና የስጋት ውዥንብር ውስጥ ከትተው የነበረው በዚሁ ወርሃ ግንቦት ነበር። ግንቦት 8 ቀን 1981። የታሰበው ቀርቶ ያልታሰበው ሆነና እንደ ቆምጫጫው ኮሎኔል አባባል ‹አንዳንዶቹን ማዕረጋቸውን በመቀስ አስቆርጠው አንዳንዶቹን ደግሞ በሳንጃ ቂጣቸውን አሶግተው› የግንቦት ጭዳ አደረጓቸውና አለፈ።

የተነቃነቀ ጥርስ እንደሚባለው፣ ዙፋናቸው የተነቃነቀባቸው ቆራጡ መሪ ቆርጠው ላይመለሱ አገር ጥለው የኮበለሉት ኹለት ዓመታትን አንክሰው ከገዙ በኋላ ግንቦት 1983 ነበር። ግንቦት ሌላ ብርሃንና ጨለማ ይዞ መጣ። በርካታ ሺዎች ድንበራችን ቀይ ባህር ነው ብለው የተሰውለት ጦርነት አብቅቶ ኤርትራ በጓሮ በር ስትሸኝ፣ ጦረኛው ሕውሓት ፀጉሩን አጎፍሮ፣ በአጭር ታጥቆ፣ በሸበጥ ሸገር ላይ ጉብ አለ።

ልክ 14 ዓመት የሆነው ጊዜ ታድያ ግንቦት ለሕውሓት/ኢሕዴግም አስደንጋጭ ድንገቴን ይዞቦት ደረሰ። ምርጫ 1997።

ሃንጎበር
ግንቦት ልደታ እለተ ሰኞ ዋለ። የአዲስ አበባን ውበት ያደመቀው ደመና አልባው ሰማይ ብቻ ሳይሆን የእሁዱ የደስታ ስካር የዞረ ድምር(ሃንጎበር)እና በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የቴዲ አፍሮ ‹ጃ ያስተርያል› የሚለው ሦስተኛው አልበም መለቀቅ ጋር ተደማምረው ሳይሆን አልቀረም። በታኪሲ፣ አውቶብስ፣ በየካፌው፣ በየገበየ ቦታው፣ በየመሥራያ ቤቱ፣ በየመስጂዱና በየደጀ ሰላሙ፣ በየትምህርት ቤቱና ሆስፒታሉ፣ በየጎዳናውና በየቤቱ በግርምትና በሙቀት የሚወሳው ሚያዚያ 30 የታየው አስደናቂ የአዲስ አበባ ትዕይንተ ሕዝብ ነበር።

ማንሾካሾክ ሳያስፈልግ ብዙ ሰው ተስፋውን፣ ምኞቱንና ፍላጎቱን በይፋ ይናገራል። የኢትዮጵያ ሰማይ ስር የለውጥ ንፋስ ይነፍሳል። ይህ ሲሆን አገራዊና ክልላዊ ብሔራዊ ምርጫ ሊካሄድ ስድስት ቀናት ቀርተው ነበር።

ከምሳ በኋላ እንደወትሯችን በተለምዶ አፍንጮ በር በሚባለው የ6 ኪሎ ካንፓስ የዋናው ጊቢ አምስተኛ በር በኩል በሚገኘው ‹ኋይት ሐውስ ካፌ› ተሰባስበን ቡናችንን እየጠጣን የምናወራው ስለ እለተ ሰንበቱ ሰልፍና የታየው የለውጥ ፍላጎት ነው። ጨዋታውን ስንጀምር ለሰልፍ የወጣው ሰው ቁጥሩ ስንት ይኖናል በሚል ግምት ቢሆንም፣ በአመዛኙ ወጋችን ተቀዋሚዎች ቢያሸንፉ ገዢው ግንባር ሥልጣን እሺ ብሎ ይለቅ ይሆን በሚለው ጥያቄ ላይ ሆነ። በእኛ በኩል ኢሕአዴግ እንዳበቃለት ግምት ወስደናል። ግንቦት 1997 እንዲህ መልካም ሆኖ ጀመረ መዝለቂው ባያምርም።

የሱናሚው ነገር
ግንቦት 4 እለተ ሐሙስ ምሳ ሰዓት ግድም ኢ-መደበኛ በሆነ የሰው ለሰው የመረጃ ማስተላለፍያ ዘዴ አዲስ ወሬ ተሰራጨ። ወሬው ከጊቢው አንድ ጥግ ተነስቶ ተመልሶ ወደ ሌላኛው ጥግ የሚነፍስበት ፍጥነት አስገራሚ ነው። ጉዳዩ አሜሪካን ኤምባሲ አካባቢ ባለው የአዲስ አበባ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ በተለምዶ አሴምብሊ በመባል በሚታወቀው ስፍራ ቅንጅቱ ከሰዓት በኋላ፣ ስምንት ሰዓት ላይ የጠራው ስብሰባ ነበር። ጥሪው የተላከው ለአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ቢሆንም፣ ወሬው በዙሪያው ተዛምቶ ኖሮ ከአራት ኪሎ እስከ ሽሮ ሜዳ ባለው ወሰን ውስጥ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የነበሩ ታዳጊ ወጣቶች ታድመውበታል። ከሰዓት የነበረን የትምህርት ክፍለ ጊዜ ሳያሳስበን ምሳችንን በቁም ላፍ አድርገን፣ የበላነው ሽሮ ደረታችን ላይ እየተንተከተከ በፈጣን እርምጃ ወደ ስብሰባ አዳራሹ አቀናን።

ከስብሰባው ቦታ የደረስነው አንድ ሰዓት አስቀድመን ቢሆንም ስፍራው በጎረምሳና በኮረዳ ለውጥ ናፋቂዎች ተጥለቅልቋል። የጊቢው በር አልተከፈተም። በ‹ክፈቱ! አንከፍትም!› ግርግር ፍጥጫው ከአጥሩ በር ጀርባ ባሉ ጎስቋላ የጥበቃ ሠራተኞችና ወሬ ሰምቶ “ቪቫ” እያለ ለማጫብጨብ በቋመጠ ትኩስ ኃይል መካከል ሆነ። ግብግቡም በመጫረሻ በድርድር መቋጫ አገኘ። የቅንጅቱ አስተባባሪዎች ከጥበቃዎቹ ጋር ተነጋግረውና ኃላፊነቱን ሊወስዱ ተስማምተው ለፍተሻ ከዛው ከተማሪዎቹ መካከል መለመሉ።

ተማሪው እርስ በርስ እየተፈታተሸ፣ እየተጋፋና እየተሽቀዳደመ በአዳራሹ ተሰገሰገ። ከመቅስፈት አዳራሹ ሞልቶና ተርፎ ጊቢው በሰው ተጨናነቀ። በአራት ቀን ልዩነት በድጋሚ አዲስ አበቤ ለለውጥ ያለውን ጥማት የሚያሳይበት መልካም አጋጣሚ ሆነ።

መድረኩ በአንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ይመራል። የቅንጅቱ አውራ መሪዎች በመድረኩ በክብር ተሰይመዋል። ብዙዎቹን በአካል ባቃቸውም አዳዲስ ፊቶችም ነበሩ። ለምሳሌ እንደ ሽመልስ ተክለፃዲቅ (ዶ/ር) እና ሌሎችም በቅርበት የማላቃውቸው ሰዎች ነበሩ። የስብሰባው ዓላማ ስለ ሚያዚያ 30 ደማቅ ተሳትፎ ምስጋና በማቅረብ ሥም ሕዝቡ እንዲመርጠን ተቀስቅሳችሁ ቀስቅሱልን ነገር ነው።

በመድረኩ የታደሙት የቅንጅቱ ሰዎች በተሰጣቸው አጫጭር ደቂቃ እየተጠቀሙ ምስጋናን ከምረጡን ጋር ቀላቅለው በውብ የሐሳብ ፍሰት አስጨበጨቡን። ከተናጋሪዎቹ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ ሽመልስ ተክለፃዲቅ (ዶ/ር)፣ ኃይሉ አርአያ (ዶ/ር)፣ ሙላለም ታረቀኝ (ዶ/ር)፣ ልደቱ አያሌው እና ብርሃኑ ነጋ (ዶ/ር) እንደነበሩ አስታውሳለሁ።

ከተናጋሪዎቹ ደግሞ ሦስቱን በልዩ ትዝታ አስታውሳቸዋለሁ። ሙላለም ‹የኢሕአዴጉን የሰልፍ መአበል የቅንጅቱ የሰልፍ ሱናሚ ዋጠው› ያለችውን፣ ልደቱ ወደ መድረኩ ሲቀርብ ‹ልደቱ ማንዴላ! ልደቱ ማንዴላ!› እየተባለ አዳራሹ እስኪናጋ በደማቁ ሲዘመርለት እና አንድ ጓደኛችን ከተስብሳቢዉ መካከል ዘሎ ወደ መድረክ ወጥቶ እግሩን ስሞ በጁ የያዘውን ባንዲራ ሲያለብሰው ትዝ ይለኛል።

በኋላ ነገር ተበላሽቶ ቅንጅቱ ሲፍረከረክ ‹ኢፍቲን› የተባለ ጋዜጣ ‹ማንዴላቸው ካንዴላ ሆነ› ብሎ ጽፎ ያላገጠብንንም አልዘነጋም። እንደዛ ስሜት ፈንቅሎት ዘሎ መድረክ ላይ ወጥቶ ልደቱን ሰንደቅ ዓላማ ያለበሰው ልጅም መከራ ደርሶበት ትምህርቱን አቋርጦ፣በስደት ዛሬ በአገረ አሜሪካ እንደሚገኝ አውቃለሁ።
በስብሰባው ፍፃሜው አካባቢ ተናጋሪ የነበረው ብርሃኑ ነጋ (ዶ/ር) ነው። ‹የተማረ ይገደለኝ› እያለ የነበረውን ታዳሚም፣ ‹አይገድላችሁም። ለምንድን ነው የተማረ የሚገላችሁ?› በሚል ንግግር ሲጀምር፣ ሳቅና ጫብጫባ ሆነ። ‹የተማረማ ሁሉ ሰው ግደል ከተባለ ነገ እናንተ ትምህርት ስትጨርሱ አገሩን ልትፈጁት አይደል እንዴ?› ሌላ ሳቅና ጭብጫባ። ‹… እኛ የምንታገለው የተማረም ያልተማረም ሰው የማይገልበትን ስርዓት ለማምጣት ነው። የምንታገለው የተማረም ያልተማረም የማይታሰርበትን፣ የማይሳደድበትን እና የማይገደልበትን አገር ሕያው ለማድረግ ነው። ማንም ሰው በአገሩ ተከብሮና ነፃነቱ ተጠብቆ ከአሳፋሪና አሸማቃቂ ድህነት ተፋቶ በኩራት የሚኖርበት ጊዜ እንዲመጣ ነው ጥረትና ምኞታችን።›

በየአረፍተ ነገሩ በጭብጨባ የሚቋረጠው የዶክተሩ ንግግር ቀጥሎ ማብቂው ላይ የአንድነት ጉዳይ ተነሳ። ‹እኛ ኢትዮጵያውያን የጋራ ታሪክ፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ የጋራ ችግሮች እና መጻኢ እድል ያለን ሕዝብ በመሆናችን፣ ሰዎችና ሁኔታዎች ሊበትኑት የማይችሉት ጠንካራ ትስስር ያለን አንድ ሕዝብ ነን። ለእኔ ኢትዮጵያዊነትን በደንብ የሚያስረዳልኝ ማን እንደሆነ ታውቃላችሁ? አዲሱን የቴዲ አፍሮን ዘፈን ሰምታችሁታል? ሼ-መንደፈር የሚለውን። ኢትዮጵያዊ አንድነትን በፍቅር ተዜሞ እሱ ውስጥ ታገኙታላች።›

ግንቦት ሰባት
የ1997 ግንቦት ሰባትን በየዓመቱ ከነበረው ግንቦት ሰባት የሚለየው በኢትዮጵያ የነፃ ማርጫ ሙከራ ታሪክ ውስጥ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ለመረጠው ፓርቲ ለመጀመርያና ምናልባትም ለመጨረሻ ጊዜ በፍላጎቱ ድምፅ የሰጠበት ቀን በመሆኑ ነው።

የዩንቨርስቲ ተማሪዎች በፍርድ ቤት ተከራክረው የመምረጥ መብታቸው የተረጋገጠላቸው በዚሁ ታሪካዊ ምርጫ ወቅት ነው። 6ኪሎ ዋናው ጊቢ ለነበርነው መራጮች የምርጫ ጣቢያችን ባህል ማእከል ውስጥ እንዲሆን ተደርጓል። ምርጫው ከጠዋቱ 12 ሰዓት የሚጀመር ቢሆንም በእኔ ቤት ማልጄ 11 ሰዓት ስደርስ አርፋጅ ነበርኩኝ። ከኔ አስቀድመው ጥንድ ከድርብ ሰልፎች ተደርድረዋል። በበኩሌ ምርጫ ሳጥን ውስጥ የድምፅ መስጫ ወረቀት ስዶል የመጀመርያ ልምምዴ መሆኑ ነው። ይመስለኛል ሁሉም መራጭ ዘንድ የተለየ ጉጉት ነበረ።

ጣታችንን አስጠቁረን ድምፃችንን ለመረጥነው ከሰጠን በኋላ፣ ከአንድ ሳምንት በፊት አላማ ያሰባሰበን ልጆች ስምሪት አወጣን። አዲስ አበባን ተከፋፍለን ልንቃኛት። ምርጫው በምን አይነት ሁኔታ እየተከናወነ እንደሆነ የታዛቢ ልዑክ መላካችን መሆኑ ነው። ቁርስ የምቀማምሰውን ቀማምሰን በስምሪታችን መሰረት በየአቅጣጫው ተበታተንን። ቀጠሯችን ለምሳ ተመልሰን የግምገማ ውጤታችንን መወያየት ነበር።

እንደ አጋጣሚ እኔ የነበርኩበት ቡድን ከ6 ኪሎ አንስቶ እስከ ቁስቋም ማርያም ድረስ ያሉትን የምርጫ ጣብያዎች እንዲቃኝ ተመደበ። ትራንስፖርት ሳያስፈልገን በእግራችን መንደር ማሰስ ጀመርን። ከመነሻችን አንስቶ ያሉት የምርጫ ጣቢያዎች በሰው ተሞልተዋል። በሁሉም ድምፅ መስጫ ስፍራዎች እጅግ የረዘሙ ሰልፎች ይታያሉ። አዛውንቶች በሰው ተደግፈው፣ እናቶች ሕፃናት ልጆቻቸውን በጀርባቸው አዝለው፣ ጎልማሶች ባርኔጣቸውን ደፍተው፣ ባልቴቶች ጃንጥላቸውን ዘርግተው፣ ወጣቶች ቡድን ሠርተው ተራቸው ደርሶ ድምፃቸውን እስኪሰጡ ድረስ በጉጉት ወደፊታቸው ይመለከታሉ።

አብዛኛው ሰው ድምፅ ሰጥቶ ሲወጣ በሰልፍ ተራውን ከሚጠብቀው ወዳጁ ጋር ሰላምታ የሚሰጣጠው ኹለት ጣቱን በማውጣት ነው። ያ ምልክት ማንን እንደመረጡና ማንን ሊመርጡ እንደሆነ ጠቋሚ ነው። ቆይተን ስንሰባሰብ ልጆቹ በየሄዱበት አካባቢዎች ሁሉ ተመሳሳይ ስሜትና መነቃቃት ይታይ እንደነበር መስክረውልናል። ሰልፍ የሚጠባበቀውን መራጭ ገና ከማርፈጃው ላይ ክርር ብላ የወጣችው የግንቦት ፀሐይ አልበገረችውም። ይልቅ ሰው እርስ በርሱ ይደጋገፋል። ጃንጥላ የዘረጋው ከጎኑ ያለው ሰው በፀሐይ እንዳይጎዳ አብረው እንዲጠለሉ ይጋብዛል። ውሃና ሌሎች ፍራፍሬዎችን ይገባበዛል።

ኢትዮጵያዊ መንፈስ የተላበሰ ቅንነት እና ወገናዊነት ይስተዋላል። ተመሳሳይ ድርጊቶችና ስሜቶች በተዟዟርንባቸው ጣቢያዎች ሁሉ በሚገርም ሁኔታ ተደጋግመው ይስተዋላሉ። የኢትዮጵያ ትንሳኤ የደረሰ መሰለን።

ዘመነ ውዥንብር
እሁድ ማታ አገር ሰላም ብለን እንደተለመደው የኢቲቪን የአማርኛ ዜና ለማየት በየ‹ቲቪ ሩሙ› ተሰይመናል። የጠበቅነው ዜና እንደወትሮው “የአገራዊና ክልላዊ ምርጫ ድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ሰላማዊና ስኬታማ ነበር› ምናምን የሚሉ አሰልቺ ወሬዎችን ቢሆንም ያልታሰበ ነገር ድንገት ተከሰተ። ከሳምንት በፊት በነበረው የሚያዚያ 29ኙ የመስቀል አደባባይ የድጋፍ ሰልፍ ላይ እንደዛ ፊታቸው በደስታ በርቶ ከሕዝብ ጋር አብሬ ልጨፍር በማለት ለጠባቂዎቻቸው አስቸግረው የነበሩት የኢሕአዴጉ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስተር፣ ምሳውን እንደተቀማ ሕጻን አኩርፈው የእለቱ አዋጅ አንባቢ ሆነው ተከሰቱ።

‹‹ሁሉም የፀጥታ አስከባሪዎች በሙሉ በአንድ እዝ ስር ገብተው፣ ተጠሪነታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን ተደርጓል። ከነገ ጀምሮ ለአንድ ወር ሰልፍና ከቤት ውጪ የሚደረግ ሕዝባዊ ስብሰባ የተከለከለ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለማሳወቅ እወዳለሁ። የሕዝቡን ውሳኔ በትእግስትና በፀጋ ለመቀበል ባለመፈለግ ይህንን መመርያ ተላልፎ በሚገኝ ክፍል ላይ የፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች ጥብቅ እርምጃ እንዲወስዱ መመርያ ተላልፏል።›› አሉ።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የጦርነት አዋጅ እንደሆነ ወዲያው ተከስቶልናል። ሰኞ ግንቦት 8 ጠዋት ከግቢ ስንወጣ ከተማዋ በአጋዝያን ተወጥራለች። በክፍት ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ላይ መትረየስ የደቀኑ ሬንጀር ለብሰው ቀይ መለዮ የደፉ ቁጡ ወታደሮች ከተማዋን ወረዋታል። አይቼ የማላውቀው ሃመር መኪና የመሰለ ሌላ አስፈሪ ወታደራዊ መኪና በከተማዋ ሲርመሰመስ ‹ያለነው ዳር ፉር ነው ወይስ አዲስ አበባ?› ያስብል ነበር።

በየምርጫ ጣብያው የተለጠፈው ውጤት ሲታይ ለማመን የሚከብድ ነበር። የቅንጅቱ እጩዎች ተፎካካሪዎቻቸውን ለአስራ ምናምን ሺሕ ይመሯቸዋል። ከምሳ በፊት ቅንጅቱ የሕዝብ ተወካዮችን 23 መቀመጫዎችና የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ምክር ቤት ወንበር ጥርግርግ አድርጎ ወስዷል ብለን አረጋገጥን። ፌሽታ ሆነ። ቅንጅቱ አዲስ አበባ ላይ እንዳሸነፈ መረጃ ከመስጠቱ አስቀድመን ውጤቱን አውቀን እኛ ቡና ተገባብዘናል።

ሲመሽ ደግሞ ሌላ ሃዘን፣ ሌላ ግራ መጋባት፣ ሌላ ብስጭት ሆነ። ኢሕአዴግ በቃል አቀባዩ አማካይነት ‹ድርጅታችን ኢሕአዴግ በፌዴራል እና በሚያስተዳድራቸው 4 ክልሎች መንግሥት መመስረት የሚያስችለውን ድምፅ በምርጫው ማግኘቱን አረጋግጠናል። አባል ደጋፊዎቻችን እንኳን ደስ አላችሁ!› የሚል መግለጫ በኢቲቪ መስኮት ይዞ ቀረበ። ከዛም ምሽት አንስቶ እነሆ ውዥንብር ሆነ።

የጋዜጦች ዘገባ፣ የየተፎካካሪ ፓርቲዎች መግለጫና የሕዝብ ጫጫታ ምርጫው ተጭበርብሯል ሆነ። ተቀዋሚዎቹ ‹ምርጫውን አሸንፈናል፣ የጥምር መንግሥት እንመሰርታለን› የሚል መግለጫ ሲሰጡ፣ ጋዜጣዎቹ በግል ተወዳድረው ዳግም ፓርላማ የመግባት እድል ያገኙትን የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ነጋሶ ጊዳዳን (ዶ/ር) እና የቅንጅቱን ሊቀመንበር ኢንጅነር ኃይሉ ሻወለን መጪዎቹ ፕሬዝዳትና ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው በፊት ገፃቸው ላይ ይዘው ወጡ።

የአመፃ ልጆች
ሕይወት ፖለቲካ ሆነች። ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሚያሰላስለው፣ የሚያወራው፣ የሚተነብየው አገራችን ምን ትሆን ይሆን የሚለው ጉዳይ ላይ ሆነና ግንቦት ተጋመሰ። የ6 ኪሎው የፖለቲካ አየር የቁጣ ነፋስ ይነፍስበት ጀምሯል። ጀንበር ስታዘቀዝቅ፣ የቀኑ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ሲያበቃ ተማሪው እንደ ወትሮው ወደ መመገቢያ አዳራሹ ከመሮጥ ታቅቦ በየጥጋ ጥጉ ሬድዮ ከቦ ያዳምጣል። በ11 ሰዓት ይጀምር የነበረውን ከቦን ከተማ የሚተላለፈውን የጀርመን ድምፅን ትንፋሹን ዋጥ አድርጎ ይሰማል። ሲመሽ ከየማንበብያ ስፍራው ይወጣና ዳግም ከምሽቱ 3 ሰዓት ላይ የሚጀምረውን የአሜሪካ ድምፅ በፅሞና ያዳምጣል። ቅንጅቱና ኅብረት መገለጫ ያወጣሉ፣ ኢሕአዴግ ያስፈራራል። የተቃዋሚዎቹ እጩዎቻችን ታሰሩ፣ ተገደሉ፣ ታዛቢዎቻችን ተንገላቱ፣ ደጋፊዎቻችን ተሳደዱ እያሉ ያማርራሉ፣ ኢሕአዴግ በድርሻው ጣት እንቆርጣለን እያለ ሽብር ይነዛል። አየሩ በጭንቀትና በሰቆቃ መሞላት ጀምራል።

ኢሕአዴግ ሰሞነኛውን ጫጫታ በሌላ ፕሮፖጋንዳ ለመተካት በእጁ ያሉትን መገናኛ ብዙኀን ሁሉ ተጠቅሞ አየሩን በግንቦት 20 ወሬዎች ለመሙላት ጥረት አደረገ። ምን ብናደርግ ይሻላል በሚል መላ ሲቋጥር ሲፈታ ለነበረው ተማሪ፣ ተቃውሞውን ለማሰማት ግንቦት 20ን እንደ ምቹ አጋጣሚ ወሰደው። ተቃውሞው ሰላማዊና ተምሳሌታዊ እንዲሆን በማሰብ የምግብ ማቆም አድማ እንዲመታ ተወሰነ። ውሳኔውና መረጃው ወዲው በየጊቢው ተሰራጨ። ሕዝብም እንዲያውቀው ሲባል ወሬውን ጋዜጦች እንዲሰሙት ተነገራቸው።

ቅዳሜ ቀን በዋለው ግንቦት 20/1997 ሙሉ ቀን ከዩንቨርስቲው ካፌዎች ያለመመገብ አድማ ተመታ። ኢሕአዴግም አድርጎት የማያውቀውን የኢቲቪ ጋዜጠኞችን ካሜራ አሸክሞ ወደ ጊቢ ላካቸው። አድማው ለምን ዓላማ ተመታ ሊሉ አልነበረም፣ ይልቁንም ጥቂት የሕውሃት ደጋፊ እንደሆኑ የሚታመኑ የትግራይ እህቶቻችን እና ወንድሞቻችን ከየመመገቢያ አዳራሹ በአንድ ላይ ተጠራርተው ‹ልደት ካፌ› ተሰባስበው ሲበሉ ባዶ ወንበሮች እንዳይታዩ ጥንቃቄ አድርጎ ቀርፆ ለመሄድ ነበር።
የኢቲቪ የምሽት ኹለት ሰዓት ዜናው ግንቦት 20 ሆኖ፣ ተቀዳሚው ወሬ ሆኖ የቀረበው ‹የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች የግንቦት 20ን አስራ አራተኛ ዓመት በምሳ ፕሮግራም በደማቅ ሁኔታ አከብሩ› ብሎ የለቀቀው ወሬ ሆነና አረፈው። ቲቪ ሩሞቹ በጫጫታና በስድብ ተሞሉ። ከመራባችን ይልቅ እርር ድብን ያደረገን ኢሕአዴግ የሠራት የአድማ ወሬ ማርከሻ አሻጥር ነበረች። ሳምንቱን ሙሉ ጋዜጦች የርሃብ አድማ ሊመታ ነው ሲሉ ከርመው ኢቲቪ ኹለት መቶ የማይሞሉ ልጆች ሲጎራረሱ አሳይቶ፣ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ጥጋብ በጥጋብ ሆኖ ዋለ አለና የመራባችንን ፋይዳ ፉርሽ ያደረገው መሰለ።

ደግነቱ ኢቲቪ ከዛም ቀን አስቀድሞ አይታመንም ነበር። ነገር ግን በዛ ዘገባው የተነሳ ለሚከተሉት አመፃዎች መንስኤ የሚሆን ከባድ ፋዎል ሠራ። የዛኑ ምሽት ቪኦኤ የአማርኛው ፕሮግራም ባቀረበው ዜና ‹የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የምርጫው ውጤት ተጭበርብሯል ሲሉ የርሃብ አድማ መተው ዋሉ› አለና የተራበውን እና የተቃጠለውን አንጀታችንን አራሰው። ጊቢው በፉጨትና በጭብጨባ ለአፍታ ደመቀ።

ነገሮች የተለየ መልክ ሳያሳዩ ግንቦት 24 ደረሰ። ረቡዕ እለት የቪኦኤ ዘገባ እንደ ልማዳችን ትንፋሻችንን ውጠን እናደምጣለን። ቪኦኤ እንግዳ አድርጎ ጋብዞ ያቀረበው ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴን ነበር። ጉዳዩ ቅዳሜ ስለተደረገው የረሃብ አድማና ዓላማው ምንነት ማብራርያ የሚጠይቅ ሲሆን፣ ፕሮፌሰሩ ‹ዐይኔን ግንባር ያድርገው የረሃብ አድማ የሚባል ነገር በየትኛውም የዩንቨርሲቲው ካፌዎች ላይ አልተመታም” ብለው ሽምጥጥ አድርገው ነጭ ውሸት ዋሹ። ይባስ ብለው ‹ይህንኑ ዘገባ ከእናንተ ሬድዮ ሰምቼ እንዴት እንዲህ ያለ ውሸት ለሕዝብ ይነገራል ብዬ እዚህ የሚገኘው ኤምባሲያችሁ ሄጄ አቤቱታ ለማቅረብ እየተሰናዳው ነው› በለው እርፍ።

ቀጠሉናም ‹እንደውም ተማሪዎቻችን ግንቦት 20ን በደመቀ መልኩ አክብረው ውለዋል። ይሄንኑ ምክንያት በማድረግ ኢቲቪ ዘገባ ሰርቷል ጠይቃችሁ መረዳት ትችላላችሁ› በማለት ካፈርኩ አይመልሰኝ መሰል ሙግት ገጠሙ። ከሰውየው ጋር የነበረው ክርክር የመሰለ ቃለ መጠይቅ እንዳባቃ ጊቢው በተቃውሞ ጩኸት ተናጋ። እናም ከሰኞ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የትምህርት ማቆም አድማ እንምታ ተባለ። ካለምንም ማቅማማት አብዛኛው ሰው ተቀበለው። ከዛን ምሽት ጀምሮ የትምህርት አድማን ለመምታት የሚያነሳሱ ቅስቀሳዎች በተለያየ ዘዴ ተሰራጩ።

እሁድ ግንቦት 28 የትምህርት ማቆም አድማው ዋዜማ ነው። ከሰዓት አከባቢ አብዛኞቹ የአዲስ አበባ ልጆች ቦርሳና ሻንጣቸውን እየያዙ ጊቢ ለቀው ሲወጡ ይታያሉ። የጊቢው አየር ውጥረት የተሞላበት ሆኗል። ፀጉረ ልውጦች ጊቢውን አዘውትረው ይመላለሱበታል፣ በደኅንነት ሰዎች ተወሯል። አንዳንዶቻችን በግል እየተጠራን ማስጠንቀቅያና ማስፈራርያ ሽጉጥ ሆድና አፋችን ውስጥ እየተደቀነ ባሩድ አሽተናል።

ፍርሃትና እልህ መሳ ለመሳ ሕይወት ዘርተው ይላወሳሉ። ምሽት አንድ ሰዓት ገደማ የአካባቢው ሁሉ መብራት እየበራ የጊቢው መብራት ድንገት ጠፋ። ይመጣል ብለን ብንጠብቅ ቆየ። አለ ነገር ተባባልን። እስኪመጣ ብለን እንቆይ በሚል አሴ ባር መሸግን። ቆይቶ የጊቢው መብራት መመለሱን ስናረጋግጥ ወደ ጊቢ ገባን። አገር አማን ብለን ለመኝታ ስንሰናዳ በግምት ከምሽቱ አምስት ሰዓት ሊሆን ገደማ የጊቢው መብራት በድጋሚ ጠፋ። ቀድሞም ጠፍቶ ስለመጣ ብዙም ሳያሳስበን የሰላም አሳድረንን ጸሎታችንን አድርሰን ጋደም ከማለታችን ጫጫታ ተሰማ። ለካንስ እነአጅሬ መብራት አስጠፍተው የአድማው ቀንደኛ አስተባባሪ ናቸው የተባሉትን በውስጥ ጠቋሚዎቻቸው በተለይም በጊቢዉ የጥበቃ አዛዥ በሆኑት እነዳኜ እየተመሩ ከየተኙበት ማነቅ ጀምረዋል።

ከነበርኩበት ሕንፃ ቁጥር 501 ላይ የጂኦግራፊ ትምህርት ክፍል ተመራቂ ተማሪ የነበረውን አንዱን ወዳጃችንን ከመኝታ ክፍሉ እያዳፉ ይዘውት ሊሄዱ ይጎትቱታል። መጀመርያ አብረውት የሚያድሩ ልጆች ቀጥሎ የኮሪደሩ ነዋሪዎች ተቀላቅለው በባትሪ መብራት ታጅበው፣ ልቀቁት በሚል ግብግብ የተጀመረው ሁካታ ወዲያው ድምፁን ቀይሮ ‹አትነሳም ወይ! ይሄ ጥያቄ ያንተ አደለም ወይ?› ወደ ሚል ተቀጣጣይ የአድማ ጥሪ ተሸጋገረ።

አብዛኞቻችን በድንጋጤ በሌሊት ልብሳችን ነበር ከሕንጻው የወረድነው። ነገሩ ተጋግሎ በግ ተራው ጋር ሲደርስ ከአጎራባች ሕንጻዎች ያሉ ወንድና ሴት ተማሪዎች ሲቀላቀላቀሉን ድምፃችን ጎላ ማለት ጀመረ። ግርግር ሲበዛ የተደናገሩት አፋኞች ልጁን ትተውት ወዲያው ቢሄዱም የቁጣው ግለት ከመብረድ ይልቅ ጭራሽ እየተቀጣጠለ ተማሪው ከየማደሪያው እየወጣ አጀቡን አሰፋው።

በጩኸትና በቁጣ ሰልፈኛው አንደኛ በር ላይ ሲደርስ ደግነቱ ሁሉም በሮች ተዘግተዋል። በሮቹ ባይዘጉ ኖሮና እንደዛ በቁጣ የገነፈለ ወጣት ጎዳና ላይ ቢወጣ በዚያ ጨለማና ሌሊት የብዙ ልጆች ደም በከንቱ ይፈስ ነበር። ብቻ ‹‹ወያኔ ሌባ…›› ከሚል ውግዘት አንስቶ የተለያዩ ወኔ ቀስቃሽና ስርአቱን የሚያወግዝ ዜማ ሲቀነቀን፣ እሪ እየተባለ ሲጮኽ ሌሊቱ ተጋመሰ። በአብዛኛው ሲዘፈን እና ሲቀነቀን የነበረው በወቅቱ ዝነኛ የሆነው የቴዲ አፍሮ ጃ ያስተሰርያል የሚለው ሙዚቃ ነበር። ለ12 ሰዓት ሳናቋርጥ ብንጮህም ድካም አልተሰማንም።

ከረፋዱ 5 ሰዓት ሲሆን ውርጭና አመዳይ ሲፈራረቁብን አድረው በደከመ ጉልበታችን ላይ ቅልብ ጦር ተፈትቶ ተለቀቀብን። በዛ ጣዝማ ማር በተባለው የጎማ ቆመጣቸው ይቆምጡን ገቡ። ጊቢ ውስጥ ያገኙትን እያጭዱት ገቡ። የቻለ ነፍሱን በሸሚዙ ቋጥሮ ሲፈረጥጥ ያልቻለው ተማርኪ ሆኖ ይንበረከካል። የቻሉትን ያህል እያፈሱ መኪና ላይ ጫኑት። የሚገርመው አብዛኛው ልጅ ደስ እያለው በፍቃደኝት ነበር መኪና ላይ የሚሰቀለው። አንድ ጓደኛችን በደረሰበት ድብደባ መንቀሳቀስ አቅቶት የወደቀበት የፅድ ዛፍ ስር ጉንዳን ወሮት ከቀመሰው ዱላ ይልቅ የጉንዳኑ ንክሻ አሳብዶት ሲሮጥ ለሌላ ድብደባ እንደተዳረገ አልረሳም። ቀን አልፎ ግብረ ጉንዳንን እየነገረን ያስቀን ነበር።

ግንቦት 29 በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከ6ኪሎ ዋናው ጊቢ ብቻ ተጭነው ጉዞ ማሰቃያ ቦታ ወደሆነው ቀዝቃዛው ሰንዳፋ ፖሊስ ኮሌጅ ሆነ። ይህን የሰሙ የኮተቤ መምህራን ማሠለጠኛ ኮሌጅ ተማሪዎች አጋርነታቸውን ለማሳይት ሲሉ መንገድ ዘጉ። ያን ጊዜ የመጀመርያው ጥይት ጮኸ። ወጣቶች በወጡበት መንገድ ዳር መውደቅ ጀመሩ። ያለምንም እንከን ያሉት ምርጫ መጨረሻው ሳያምር እንከን በእንከን ሆኖ ጎዳና ላይ የንፁን ደም መፍሰስ ጀመረ። ያንን ሁሉ ተስፋ ዳዋ በላው። ያንን ሁሉ የለውጥ ፍላጎት ጽልመት ወረሰው።

የግንቦት 1997 የመጀመርያው ቀን ሰኞ ብሩህና ተስፋ የተሞላበት ደስ የሚል ቀን ነበር። ሲያልቅ አያምር ሆነና ነገሩ የግንቦት የመጨረሻው ሰኞ እጅግ ጨፍጋጋ ቀን ነበር። ግንቦት 29 ሺዎች በግፍ ወደየ ማጎሪያው ለስቃይ ሲጓዙ በርካቶች በግፈኞች ጥይት ተጠብሰው ደማቸው በየአስፓልቱና ጢሻው በከንቱ ፈሰሰ።
የ1997 የግንቦት ጣጣ በስንቶቻችን ልብ ውስጥ ሕመም፣ በመንፈሳችን ላይ የስሜት ቁሰለት፣ በአእምሮችን ላይ ጠባሳ አሳርፎ አልፎ ይሆን? የስንቱስ ቤት ፈረሰ፣ የስንቱስ ጤናና ሕይወት ተቃወሰ? ስንቶቹ ተሰደዱ? ስንቶቹስ በደረሰባቸው የመንፈስ ስብራት ተስፋ ቆርጠው ከማጀት ዋሉ? የነኛን ሰማዕታት ገድል በክብር የምንዘክርበት፣ የነፃነት ተስፋቸውንስ እውን የምናደርገበት ዘመን ቀርቦ ይሆን? የኔን ትውስታ ከነበርኩበት እንቅስቃሴ አንፃር በቅንጣቢ አቃመስኳችሁ። እስኪ ደግሞ እኔ ባጎደልኩ እናተ ሙሉ።

ይታገሱ ዘውዱ ከካቶሎኒያ ስፔን ግንቦት 5/2010 ተጽፎ፣ ከጊዜ አንጻር ማስተካከያዎች ተደርጎበት ለትውስታ የወጣ

ቅጽ 2 ቁጥር 80 ግንቦት 8 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com