አዋሽ ባንክ በአበባ፣ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለተሰማሩ የብድር ወለድ ማሻሻያ አደረገ

Views: 92

አዋሽ ባንክ በኢትዮጵያ የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በንግድ እንቅስቃሴው ላይ ያሳደረውን ጫና ከግምት ውስጥ በማስገባት በአበባ፣ በሆቴልና ቱሪዝም ለተሰማሩ የብድር ወለድ ማሻሻያ ማድረጉን አስታወቀ።

ባንኩ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተከሰተውን ወረርሽኝ ተከትሎ የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ በመኖሩ በኢትዮጵያም የተለየ ነገር እንደማይኖር በመገንዘብ በአበባ፣ በሆቴል፣ በአስጎብኚ እና በጉዞ ወኪል ንግድ ላይ ለተሰማሩ የብድር ወለድ ማሻሻያ ማድረጉን ገልጿል።

በዚህም መሰረት አዋሽ ባንክ በሆቴል ንግድ ተሰማርተው ለሚገኙ ከዚህ ቀደም ይሰጥ የነበረውን ከ12 ነጥብ 5 በመቶ እስከ 15 ነጥብ 7 በመቶ የነበረውን የብድር ወለድ መጠን ዝቅ በማድረግ ከዘጠኝ በመቶ እስከ 12 ነጥብ 5 በመቶ እንዲሆን መወሰኑን አስታውቋል። በተመሳሳይም በአበባ፣ በአስጎብኚ እና በጉዞ ወኪል ንግድ ላይ ለተሰማሩት ደግሞ እስከ ሰባት በመቶ የሚደርስ እንደሆነ ይፋ አድርጎ፣ ይህ ማሻሻያም ለሚቀጥሉት ሦስት ወራት እንደሚቆይም አስታውቋል።

አዋሽ ባንክ የብድር ወለድ ማሻሻያ ለማድረግ መወሰኑን በሚመለከት ለብሔራዊ ባንክ በላከው ደብዳቤ እንደገለጸው፤ የብድር ወለድ ማሻሻያ ለማድረግ የወሰነውን ውሳኔ ተከትሎ እስከ 50 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ከብድር ወለድ የሚገኝ ገቢ እንደሚያጣ ጠቅሷል። ይሁን እንጂ ባንኩ ይህን የሚያጣውን ገቢ ሳይሆን በዋናነት ደንበኞቹ ንግዳቸው ላይ የሚያጋጥመውን መቀዛቀዝ እና ተግዳሮት ተቋቁመው መቀጠል የሚችሉበትን መንገድ በማስቀደም እንደሚሠራ ገልጿል።

ከመጋቢት 23 /2012 ጀምሮ ለቀጣይ ስልሳ ቀናት በባንኩ ተግባራዊ የሚደረጉ ተግባራት ውስጥ ከብድር ወለድ ማሻሻያው ቀጥሎ የብድር አከፋፈል ሂደት ማሻሻያ እንዲሁም በባንኩ በኩል በሚከፈቱ ‹‹ኤል ሲ›› ኮሚሽን ማራዘም እና ከባንኩ የአውቶማቲክ የገንዘብ መክፈያ (ኤቲኤም) ገንዘብ በሚወጣ ጊዜ ተቆራጭ ገንዘቦችን በሚመለከት ማሻሻያ ማድረጉን አስታውቋል።

በሆቴል ንግድ ላይ የተሰማሩ በተለይም ደግሞ በአዲስ አበባ 130 አባላት ያሉት አዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማኅበር ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው፣ ብድር መክፈያ ጊዜው እንዲራዘምላቸው እየጠየቁ እንደሆነ እና የሚራዘመው ጊዜም ለአንድ ዓመት እንዲሆን እንደሚጠይቁም አስታውቀዋል። የማኅበሩ ፐሬዝዳንት ቢንያም ብስራት ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ፤ ሠራተኞችን መበተን ከአቅም በላይ ካልሆነ በቀር የሚመረጥ አማራጭ አለመሆኑን እና እንዲያውም የሆቴል ኢንዱስትሪው በዋናነት ተግዳሮት የሆነበት በዘርፉ ብቁ የሆነ የሆቴል ባለሙያ ማግኘት በመሆኑ፣ ከገቢ አንጻር ደሞዝ መክፈል እንደሚያቅታቸው በመታመኑ እንጂ ሠራተኞችን የመቀነስ ፍላጎት እንደሌለ ተናግረዋል።

ኮቪድ 19 በኢትዮጵያ መታየቱ ከታወቀ የመጀመሪያዎቹ ቀናት አንስቶ በርካታ የንግድ ተቋማት በርካታ ሠራተኞችን ከሥራ እስከ መቀነስ ብሎም እስከ መዘጋት የሚደርስ አደጋ እንደተጋረጠባቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎም በርካታ ገንዘብ ተቋማት በዋነኛነት ባንኮች መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሚገኙ ይታወቃል። ይህንም ተከትሎ የንግድ ተቋማቱ ካሉበት ችግር ለመላቀቅ የሚያስፈልጋቸውን የትኛውንም ዓይነት ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል።
በመንግሥትም በኩል በተለይም ደግሞ ለአምራች ዘርፉ እስከ 100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ በማድረግ እና ሠራተኞቻቸውን ሳይቀንሱ ይዘው እንዲቀጥሉ እንዲሁም የምርት መጠናቸውን በተለይም ደግሞ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመመከት በሚደረገው ርብርብ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ግብዐቶችን በአገር ውስጥ እንዲያመርቱ ማበረታቻ ማድረጉን የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገልጸዋል።

በተለይም ደግሞ ድርጅቶች ወረርሽኙን ለመመከት በመንግሥት በኩል ከወጣው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ተያይዞ ሠራተኛ መቀነስም ሆነ ደሞዝ መቀነስ የተከለከለ መሆኑ ከተደነገገ በኋላ ገቢ ሳይኖራቸው በስራቸው ለሚያስተዳድሯቸው ሠራተኞች የወር ደሞዝ መክፈል እየተቸገሩ እንዳሉ አቤቱታቸውን ሲያሰሙ ተስተውለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 80 ግንቦት 8 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com