ከግሪክ ክለብ የሚወጣው ቆሻሻ ወንዞችን እየበከለ ነው

Views: 106

ቅጣቱ እስከ ማሸግ ይደርሳል
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ስር የሚገኘው እና ልዩ ሥሙ ኦሎምፒያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው የግሪክ ማኅበረሰብ ምግብ ቤት ወይም በተለምዶ ሥሙ ‹ግሪክ ክለብ› ደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻዎችን ወደ ወንዝ በመልቀቅ በወንዝ ላይ ከፍተኛ ብክለት እያስከተለ መሆኑ ተረጋገጠ።

አዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ ማረጋገጥ እንደቻለችው፣ ከግሪክ ክለብ የሚወጣው ደረቅ ቆሻሻ ወንዞችን እየበከለ መሆኑን እና ለቆሻሻ ማስወገጃ ተብሎ ወደ ወንዙ መስመር ተስተካክለው የተሠራ አንድ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ እና አንድ ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ መስኮት መሳይ ነገር ናቸው። በዚህም መሠረት አዲስ ማለዳ በአካል እንደታዘበችው ከሆነ፣ የተለያዩ ቆሻሻዎችን በእነዚህ የተለያዩ ማስወገጃ መንገዶች በመጠቀም ከግሪክ ከለብ ደረቅ ቆሻሻ ጨምሮ የተለያዩ ፍሳሾችን ወደ ወንዝ ይለቀቃሉ።

በተመሳሳይም ከግሪክ ክለብ በተጨማሪ በአካባቢው የሚገኙ የግንባታ ሳይቶች ለሕንጻ ግንባታ የሚሆኑ ስፍራዎች በሚቆፈሩበት ወቅት አፈሩን አዛው ወንዝ ውስጥ እንደሚጨምሩት እና ወንዙን ከመበከል ባለፈ በደለል እንዲሞላ እንዳደረጉት አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።

የግሪክ ክለብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ነጋሶ ጫካ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ከወንዞች ጋር የተገናኙ ለቆሻሻ ማስወገጃ ተብለው የተሠሩ ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃዎች እና ፍሳሽ ማስወገጃዎች ይኑሩ እንጂ ለማስወገጃ ተጠቅመውባቸው አያውቁም።

ከዛም በተጨማሪ በግቢው ውስጥ የሚገኙ ደረቅ ቆሻሻዎችን ጨምሮ ለሬስቶራንቱ ከሚውሉት ግብዓቶች ውስጥ ተረፈ ምርቶችን በማከማቸት ሲጠራቀም መኪና መጥቶ ወደ ተገቢው የቆሻሻ ማስወገጃ ስፍራ እንደሚልኩ ሥራ አስኪያጁ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። እንደውም ለወንዙ ፅዳት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሆነ ኃላፊው ጨምረው ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ በጉዳዩ ላይ ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን፣ ‹‹የአካባቢያዊ ቅኝት በማድረግ ነው እንደዚ ዓይነት ተግባሮችን በአብዛኛው የምንይዘው›› በማለት በክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሊያ ግርማ ተናግረዋል። አክለውም በግሪክ ክለብ የሚደረገውን ወንዝን የመበከል ተግባር በሚመለከት እስከ አሁን ጥቆማም እንዳልደረሳቸው እና ጉዳዩን ክፍለ ከተማው እንደማያውቀው ጠቅሰዋል።

እንደ ሊያ ገለጻ፣ እንደዚህ ዓይነት ወንዞችን የመበከል ተግባር የሚሠሩበትን የሥራ ዓይነት ቦታ ከማስቀየር እና ንግዱንም እንዲዘጋ ከማድረግ ባሻገር፣ የእስር ቅጣትን ጨምሮ እንደሚያስከትል ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገለፃ ከሆነ፣ በዚህ ዘርፍ 11 ወረዳዎችን አካትቶ ክፍለ ከተማው እየሠራ ነው። እስከ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ድረስ የተዘረጋ ሰንሰለትም አለ ያሉ ሲሆን፣ ከአረንጓዴ ልማቱ ጋር በተያያዘ የወንዞች ፅዳት ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አውስተዋል።

በተጨማሪም ከግሪክ ክለብ የሚወጣውን ቆሻሻ በተመለከተ ክፍለ ከተማው ክትትል በማድረግ በተቀመጠው ሕግ መሰረት ታይቶ ተገቢውን ቅጣት እንዲቀጡ የማድረግ ሥራ እንሠራለን ሲሉ ሊያ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ዋለልኝ ደሳለኝ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ በዋናነት በተቋሙ እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮችን የሚከታተለው ብክለት ዘርፍ ነው። እንደ እርሳቸው ገለጻ በአዲስ አበባ ያሉት ወንዞች 643 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ርዝመት ያላቸው ሲሆን፤ በዚህም በየአንዳንዱ አካባቢ ማን ከወንዞች ጋር ቆሻሻ ማስወገጃ ትቦዎችን አያያዘ የሚለውን ከምናደርገው ጥናት በተጨማሪ ኅብረተሰቡ የሚታዘበውን ነገር ቢጠቁም መፍትሄ ለመስጠት ሥራውን ያቀለው ነበር ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 80 ግንቦት 8 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com