ኦሞ ኩራዝ ቁጥር ኹለት ስኳር ፋብሪካ በኮሮና ምክንያት ሥራው ተቀዛቀዘ

Views: 103

የኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካ ኮቪድ 19 የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያም መከሰቱን ተከትሎ ሠራው መቀዛቀዙን እና ሠራተኞች ሥራ እንዲያቆሙ መደረጋቸውን በፋብሪካ የሚሠሩ የአዲስ ማለዳ ምንጭ ተናገሩ።

ከዛም በተጨማሪ ከኦሞ ኩራዝ ቁጥር ኹለት ስኳር ፋብሪካ ጋር ኮንትራት ይዘው ይሠሩ የነበሩ ‹ኢታኖል› ያመርቱ የነበሩ ድርጅቶች በፋብሪካው ማቆም ምክንያት ከፋብሪካው ያገኙት የነበረውን ምርት ማግኘት ባለመቻላቸው ሥራ ካቆሙ ኹለት ወር እንዳለፋቸው ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

ጉዳዩን በሚመለከት ለአዲስ ማለዳ ምላሽ የሰጡት የኢፌዴሪ ስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ወዮ ሮባ፣ ኦሞ ኩራዝ ኹለት ሥራ እንዳላቆመ እና ነገር ግን በኮሮና ምክንያት መቀዛቀዝ እንዳለ ጠቅሰዋል። ወዮ ጨምረውም ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ሥራ አቁሟል እየተባለ የሚወራውም መሠረተ ቢስ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ዋና ሥራ አስኪያጁ ለተፈጠረው መቀዛቀዝ እንደ ምክንያት የሚገልጹት ከውጪ የሚመጡ ባለሙያዎች ያሉበት ቦታ ላይ እንቅስቃሴ መገደቡን ነው። ኃላፊው አያይዘውም ከውጭ በሚመጡ ሰዎች ላይ ከተከሰተው የእንቅስቃሴ መገደብ ውጭ ‹‹የስኳር ፋብሪካው ስር የሚሠሩ መደበኛ ሠራተኞች ሥራ አላቆሙም፣ ጊዜያዊ የሆኑትም ቢሆን እንደዛው። ሠራተኛ የመቀነስም ሁኔታም የለም።›› በማለት ተናግረዋል።

ይህን ይበሉ እንጂ ዋና ሥራ አስኪያጁ በስኳር ፋብሪካው ውስጥ በሸንኮራ አገዳ መፍጨት ቦታ (operation) ላይ ያሉት ግን ሥራ ማቆማቸውን አንስተዋል። የዚህ ምክንያቱም ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳይሆን በዝናብ ምክንያት ሸንኮራ አገዳ መፍጨት ስላልተቻለ መሆኑንም የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ወዮ ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።

በስኳር ፕሮጀክቱ በ100 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ የሚለማ የሸንኮራ አገዳ ተጠቅመው በቀን 60 ሺሕ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ያላቸው አራት ስኳር ፋብሪካዎች እየተገነቡ መሆኑን፣ በሙሉ አቅማቸው ማምረት ሲጀምሩ ሦስቱ እያንዳንዳቸው በቀን 12 ሺሕ ቶን አገዳ በመፍጨት በዓመት 2 ሚሊዮን 500 ሺሕ ኩንታል ስኳር እና እያንዳንዳቸው በዓመት 28 ሚሊዮን ሊትር ኤታኖል ያመርታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

እንዲሁም እያንዳንዳቸው ከሚያመነጩት 45 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ 29 ሜጋ ዋቱን ወደ ብሔራዊ ቋት ይልካሉ ተብሎ እንደነበር የሚታወስ ነው።
በዚህም በተመሳሳይ አንደኛው ፋብሪካ በቀን 24 ሺሕ ቶን አገዳ በመፍጨት በዓመት 5 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር እና 56 ሚሊዮን ሊትር ኤታኖል እንደሚያመርት ታሳቢ እንደተደረገ የሚታወስ ነው።

የኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን ሰላማጎ እና ኛንጋቶም ወረዳዎች፣ በቤንች ማጂ ዞን ሱርማ እና ሜኢኒትሻ ወረዳዎች እና በካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ የተመረጡ አካባቢዎች እየተካሄደ የሚገኝ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 80 ግንቦት 8 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com