በኤሌክትሮኒክ መንገድ ግብርን መክፈል የሚያስችል ስርዓት ተግባራዊ ተደረገ

Views: 80

የገቢዎች ሚኒስቴር የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቀነስ እና ግብር ከፋዩ ኅብረተሰብ ግብር ለመክፈል በሚያደርገው እንቅስቃሴ ያለውን መጉላላት ለመቀነስ የኤሌክትሮኒክ የግብር መክፈያ መንገድ ተግባራዊ ማድረጉ ተገለጸ።

የገቢዎች ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኡሚ አባ ጀማል ለአዲስ ማለዳ በሰጡት አስተያየት፣ ኢ-ታክስ ቴክኖሎጂ የተባለው አሠራር ግብር ከፋዮች ወደ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች መሄድ ሳይጠበቅባቸው በቤታቸው ወይንም በመሥሪያ ቤታቸው በመሆን ግብራቸውን ማሳወቅ ወይም መክፈል እንዲችሉ የሚረዳ አሰራር እንደሆነ አስታውቀዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አዲስ ያስተዋወቀው በቴክኖሎጂ የታገዘ የግብር አሰባሰብ ስርዓት ግብር ከፋዮች ወደ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በግንባር በመምጣት በሚያደርጉት መሰባሰብ እና ጥግግት የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ከማሰራጨት አንጻር ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በማመን ነው። ይህን ያስከተለውም ግብር ከፋዮች በወቅቱ ግብራቸውን ለማሳወቅ አለመትጋታቸው እንደ ምክንያት የተቆጠረ ሲሆን፣ ይህንንም ተከትሎ ግብር አሰባሰቡ ስርዓት እንደተፈለገው ያልሄደ መሆኑን ኡሚ ጨምረው ገለጸዋል።

በተያያዘም በቀሩት ኹለት ወራት የታቀደውን ያክል ለማሳካት ሚኒስቴሩ የሚታዩ ክፍተቶችን በማረም እና የተጣራ አፈፃፀም ለማስመዝገብ፣ ግብር ከፋዮች በወቅቱ ግብራቸውን መክፈል እንዲችሉ የኢ-ታክስ ቴክኖሎጂን መሥርያ ቤቱ መጠቀም ስለጀመረ፣ በቀላሉ ግብርን ለመሰብሰብ ከመቻሉም በላይ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቀነስ እንዲያስችለው ሰፊ ድጋፍ ያደርግለታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ታውቋል።

የ2012 በጀት ዓመት እቅድን ለማሳካትም በቀጣይ ወራት እንዲሰበሰብ የታቀደው ገቢ ከፍተኛ በመሆኑ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማት በትኩረት እየሠሩ ነው ሲሉ የገቢዎች ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ ኡሚ አባ ጀማል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከዛም በተጨማሪ የገቢዎች ሚኒስቴር አፈፃፀም ሲታይ፣ በበጀት ዓመቱ 270.2 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሠራ ሲሆን ባለፉት ዐስር ወራት 198.4 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 90 በመቶ ማሳካቱን ኡሚ ጠቅሰዋል። ይህም አፈፃፀም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ35.3 ቢሊዮን ብር ወይም 21.63 በመቶ እድገት አሳይቷል። በተጨማሪም በዓመቱ መጨረሻም 270 ቢሊየን ለመሰብሰብ ታቅዷል ብለዋል።

የሕዝብ ግንኙነቷ እንደሚሉት፣ የተሰበሰበው ከገቢ ድርሻ አንጻር ሲታይ ከአገር ውስጥ ታክስ እና ከጉምሩክ ቀረጥ ሲሆን ይህም በአጠቃላይ በዐስር ወራት ውስጥ 198 ቢሊዮን 477 ሚሊዮን 959 ሺሕ ብር ገቢ በመሰብሰብ የእቅዱን 90 በመቶ ማሳካት ተችሏል።

የተገኘው አጠቃላይ ገቢ በዐስር ወራት ውስጥ በታቀደው መሰረት እኩል ባይሆንም፣ ነገር ግን በኢትዮጵያ ብሎም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ‹‹እንደውም ጥሩ የሚባል ነው፣ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ነው። አቅጣጫዎችን በማስተካከል እና በማሻሻል ለሚቀጥሉት ጊዜያት እንድንሰበስብ ያደርገናልም።›› ብለዋል።

ይሁን እንጂ ይህ በዐስር ወራት የተመዘገበው ገቢ በኮንትሮባንድ የሚያዙትን ጨምሮ እንዳልሆነና የሚያዙት ምርቶች ወደ ገንዘብ ሲለወጡ ምን ያህል እንደሚሆኑ አጠቃላይ ተሠርቶ ባለመጨረሱ እንደማይታወቅ ተናግረዋል።

ሕዝብ ግንኙነቷ አያይዘውም መሥሪያ ቤቱ ባለፉት ስምንት ወራት በታቀደው መሰረት እና ከእቅድ በላይ ሲያሳካ የነበረ ቢሆንም፣ ነገር ግን ባለፉት ኹለት ወራት ኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ በእቅዱ መሰረት መንቀሳቀስ አለመቻላቸውን ተናግረዋል።

እንደ ኡሚ ገለፀ፣ ባለፉት ኹለት ወራት በኮሮና ምክንያት መሰብሳብ ያልተቻለበት ምክንያት ብለው እንዳስቀመጡት ከሆነ አንደኛው እና ዋነኛው ግብር ከፋዮች ተሰማርተው በሚሠሩበት ዘርፍ ባለፉት ኹለት ወራት በተለያየ ምክንያት እንደ ከዚህ ቀደሙ ውጤታማ ባለመሆኑ ግብር ለመክፈል በመቸገራቸው የተፈጠረ ነው ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 80 ግንቦት 8 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com