በቦሌ ክፍለ ከተማ 500 የሚሆኑ የመሥሪያ ቦታዎች በመንግሥት መፍረሳቸው ታወቀ

Views: 177

በአዲስ አበባ በቦሌ ክፍለ ከተማ በወረዳ ሦስት አስተዳደር ቀበሌ 18 አደይ አበባ ስታድየም ዙሪያ በሚገኝ ክፍት ቦታ ላይ እንዲጠቀሙበት ከሰኔ 2010 ጀምሮ ሕጋዊ ፈቃድ ተሰጥቷቸው መጠለያዎች አድርገው ሲሠሩበት ከቆዩበት ቦታ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በድንገት በመንግሥት አካል ፈርሶባቸው ራሳቸውን ለመመመገብ መቸገራቸውን ቅሬታ አቅራቢዎች ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።

ከ2010 ጀምሮ በሥራ አጥነት ተደራጅተው መሥሪያ ቦታቸው እስከፈረሰበት ጊዜ ድረስ ከመንግሥት ባገኙት የሥራ ፈቃድና ሕጋዊነት ማረጋገጫ እየሠሩ የእለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን ይተጉ እንደነበር የገለጹ ሲሆን፤ ከ500 በላይ ሻይ ቡና እና በታሸጉ መጠጦች በመሸጥ የሚተዳደሩበት ስፍራ ሚያዚያ 30/2012 በድንገት በመፍረሱ ካለው ወቅታዊ ችግር አንጻር አብዛኛዎቹ ራሳቸውን መመገብ አቅቷቸው ችግር ላይ መውደቃቸቀውን አዲስ ማለዳ ቢሮ ድረስ በመምጣት ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

‹‹መንግሥት በአንድ ወገን ሰዎችን ከጎዳና እያነሳ በሚገኝበት በዚህ አስቸጋሪና ማንም ማንንም በማያስጠጋበት ወቅት፣ ሠርተን የእለት ጉርሳችንን የምናገኝበት መሥሪያ ቦታ በድንገት በመፍረሱ ለልመናና ለጎዳና ሕይወት እየተጋለጥን ነው።›› በማለት የችግሩ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ብሶታቸውን አስረድተዋል።

የችግሩ ሰለባ ከሆኑት ውስጥ ወጣት ዲንሰፋ ደስታ አንዱ ነው። ዲንሰፋ እንደሚለው ከ2010 ጀምሮ መንግሥት በሥራ አጥ ተደራጅቶ ኹለት ሜትር በኹለት ሜትር ስፋት ያለው የመሥሪያ ቦታ ተሰጥቶት በአሮጌ ጫማ ማደስ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ደካማ እናትና አባቱን ያስተዳድር እንደነበር ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። አክሎም በድንገት የመሥሪያ ቦታው ስለፈረሰበት ደካማ እናትና አባቱን የሚመግብበት ገንዘብ ተቸግሮ እንደሚገኝ ሀዘን ባጠላበት ሁኔታ አስረድቷል።

በመንግሥት አካላት እንዲፈርስ ተደርጓል በተባለው ስፍራ ላይ በብዛት የተሰማሩት ሴቶች ሲሆኑ፣ አንዳንዶች የልጅ እናት ሌሎች ደግሞ ነፍሰ ጡር መሆናቸውን አዲስ ማለዳ ለመታዘብ ችላለች። የልጅ እናት የሆኑ የችግሩ ሰለባዎች ልጆቻቸው ከዚህ በፊት ትምህርት ቤት ላይ በተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ይመገቡ እንደነበር ጠቅሰው፣ አሁን ላይ በተከሰተው የኮሮና ቫይረሰ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ልጆችን መመገብና ማስተዳደር አቅቷቸው በአጭር ጊዜ ለጎዳና እና ለልመና ሕይወት እንደሚጋለጡ አስታውቀዋል።

ተበዳዮች ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ዝግጅት ክፍል ባስታወቁበት ወቅት መንግሥት በዚህ አስቸጋሪ ሰዓት ሕይወታችንን ከአደጋ ሊታደግልን ይገባል ብለዋል። አክለውም በቦታው ላይ ያሉ አመራሮች ሰብዓዊ መብታችንን አላከበሩልንም፣ እንደሰው መቆጠራችን ቀርቶ በማጥላላትና በማስፈራራት ተጽዕኖ እያሳደሩብ ነው የሚል ቅሬታቸውንም አሰምተዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በመንግሥት የተወሰደው እርምጃ ተለዋጭ የመሥሪያ ቦታ ተሰጥቶን ቢሆን ኖሮ፣ ከስፍራው ለመነሳት ፈቃደኞች መሆናቸውን እና ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ግን የመሥሪያ ቦታዎችን አፍርሶ ሜዳ እንድንወድቅ ማድረግ አግባብ አይደለም ሲሉም ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ በአሁኑ ጊዜ የሚደረጉ ከመሥሪያ ቦታና ከመኖሪያ ቦታ ሰዎችን ማፈናቀል ወቅቱን ያልጠበቀ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን ገልጾ፣ ድርጊቱ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ሲታይ አሳሳቢና መሆን የሌለበት ድርጊት በመሆኑ ሊቆም እንደሚገባ አሳስቧል።

500 የመሥሪያ ቤቶችን መፍረስ ተከትሎ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ወደ ተባሉ የወረዳው የሥራ ኃላፊዎች፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ ሦስት ቀበሌ 18 ኃላፊዎች ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪዎች እና ሌሎች ሙከራዎችን አዲስ ማለዳ አድርጋ ነበር። ይሁን እንጂ ስብሰባ ላይ ነን በሚል ሰበብ አዲስ ማለዳ ምላሽ ለማግኘት ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 80 ግንቦት 8 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com