በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰበብ ሰብዓዊ መብትን መጣስ ይቁም!

Views: 68

በዓለም አቀፉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በአገራችን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊጣል እንደሚገባ ብዙዎች ቀድመው ሲወተውቱ ነበር፡፡ አዲስ ማለዳም ይህንን ሀሳብ ቀድመው ከደገፉ ወገኖች ውስጥ ነች፡፡ አዋጁ በባህሪው የሰብዓዊ መብቶችን የሚጥስ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የተረጋጋ ሁኔታ ባለበት ጊዜ የማይደረጉ ነገሮች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት እንደሚፈቀዱም ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ የዜጎችን የእንቅስቃሴ መብት እንደ ሰዓት እላፊ ባሉ የተለያዩ መንገዶች መገደብ፣ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቤቶችን መፈተሽ እና ሌሎች ተግባራት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይፈፀማሉ፡፡

በመሆኑም አዋጁ ሲታወጅ እነዚህን ሁሉ ለማድረግ በቂ የሆነ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ስጋት አለ የሚለው እሳቤ አይሎ መውጣቱን ማረጋገጫ ነው፡፡ አዋጁም የሚከለክላቸው ነገሮች የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ የሚጠቅሙ እና ኢኮኖሚያዊ ትግሉን ስርዓት በያዘ መልክ ለመከወን የሚረዱ ናቸው ተብሎ ይታሰባል፡፡
በዚህም መሠረት ሰው በሚበዛባቸው ቦታዎች የፊት ማስክ ማድረግ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በግዴታነት ከተቀመጡ ነገሮች መካከል አንዱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ አብዛኛው ሰው የፊት ማስክ በማድረግ መንቀሳቀሱም የሰሞኑ ለየት ያለ ነገር ሆኗል፡፡ ነገር ግን የፊት መሸፈኛውን የማያደርጉም አሉ፡፡ በማንኛውም የከተማዋ መንገድ ላይ የፊት ማስክ ሳያደርጉ መንቀሳቀስ እንደማይቻል ግን አስቸኳይ ጊዜ አዋጁም በግልጽ አላወጀም፡፡ ይልቁንም በገበያ ቦታ፣ ሱቆች፣ የመጓጓዣ አገልግሎቶች ውስጥ እና ሌሎች የማህበራዊ ፈቀቅታ ሊተገበርባቸው በማይችል ሕዝባዊ ቦታዎች ላይ የፊት ማስክ መደረጉን ያስገድዳል፡፡ ሕዝባዊ ቦታዎች የሚለው ሀረግ ፖሊስ መንገዶችን እንዲያካትት እድል የሚሰጥ ቢሆንም መንገዶች የማህበራዊ ፈቀቅታ ሊተገበርባቸው የማይችል ቦታዎች ናቸው ለማለት ይከብዳል፡፡

ነገር ግን የፊት ማስኮችን ያላደረጉ ሰዎችን የአዲስ አበባ ፖሊስ ባለፉት ጥቂት ቀናት “በቁጥጥር ስር” ያዋለበት መንገድ መቼም የሚሻሻል ኃይል አይደለም ወይ የሚያስብል ነው፡፡ ሰዎችን ከበሽታ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የፊት ማስኩን ማድረግ አስተዋጽኦ ስላለው ግዴታ ቢደረግ ፖሊስ ያላደረጉት ላይ የሚያሳርፈው አካላዊ ጥቃት ጤናቸውን የሚያውክ እየሆነ ነው፡፡ ፊታቸው በፖሊስ የኃይል እርምጃ የበለዘ፣ በዱላ የተመቱ እና ሰውነታቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እንዳሉ የተለያዩ ሪፖርቶች ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡ ሽማግሌዎች ጭምር በዚህ የፖሊስ ወከባ ተጠቂ ሆነዋል፡፡

ይህም እስከዛሬ የምናውቀው ፖሊስ ዋነኛ ባህሪይ ነው፡፡ በአገራችን በአንድ አካባቢ የፖሊስ መኖር የአካባቢውን ሰው የደህንነት እና የመረጋጋት ስሜት የሚሰጥ ሳይሆን የሽብር ስሜት የሚፈጥር ነው፡፡ ይህም የሆነው ፖሊስ ምንም ንግግር ሳያደርግ እንኳን ሰዎችን ሲደበድብ፣ ሲያናግርም ሥነ ምግባር በጎደለው መንገድ እያጓጠጠ እና እየተሳደበ ሲያዋክብ በተደጋጋሚ ሕብረተሰቡ ስለሚመለከት ነው፡፡ በጣም የሚገርመው እንደውም የእኛ አገር ፖሊሶች የሚጠሉት ቃል እንደሆነ በብዙዎች የሚታመነው “መብቴ” የሚለው ቃል መሆኑ ነው፡፡ መሔድ የተከለከለበት መንገድ ጋር በስህተት የደረሰ ሰው በፖሊሶች የሚሰጠው የማንቂያ መልዕክት ለስለስ ያለ የመሆን እድሉ ትንሽ ነው፡፡

በአጠቃላይ ፖሊስ ሰዎችን ሲደበድብ፣ ሲያንገላታ፣ ሲሳደብ እና ሌሎችም አጓጉል ነገሮችን ሲያደርግ መመልከት የዜጎች የዕለት ተዕለት ሕይወት አካል ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቱን እርምጃ በመውሰዳቸውም በተጠቂዎች ክስ ተመስርቶባቸው እርምጃ የተወሰደባቸው ፖሊሶች ቁጥር እጅጉን አናሳ ነው፡፡ በመሆኑም አዲስ የሚመለመሉትም ፖሊሶች ይህንኑ ፀረ-ሕዝብ ድርጅታዊ ባሕል በመላበስ ጥቃት የማድረስ ተግባራቸውን ለመቀላቀል ጊዜም አይፈጅባቸውም፡፡

በፖሊስ የሰሞኑ እርምጃ ዋነኛው ጉዳይ ዜጎች ራሳቸውን እና ሌሎችን ከቫይረሱ እንዲጠብቁ ማድረግ እንዳልሆነ የሚያሳዩም ነገሮች ታይተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል “በቁጥጥር ስር” የዋሉ ሰዎችን በአንድ ላይ አጭቆ ወደሚታሰሩባቸው ትምህርት ቤቶች ወይንም በጊዜያዊነት ተጠብቀው ወደ ሚቆዩበት መውሰድ አንዱ ነው፡፡ በአንድ ኋላው ክፍት የሆነ የፖሊስ መኪና ላይ ስምንት ሰዎችን ከኋላ ጭኖ ፖሊሶች አብረዋቸው እንዲሆኑ ማድረግ የፊት ማስክ ካለማድረግ ይበልጥ ቫይረሱን ሊያስተላልፍ እንደሚችል ለማንም ግልጽ ነው፡፡ በትምህርት ቤቶች ውስጥም በቆዩበት ጊዜ የታየው መጠጋጋት እርምጃው የጤናውን ሁኔታ ለመርዳት መሆኑን ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ነው፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እረቡ ላይ ከ1300 በላይ ሰዎች ርቀታቸውን ሳይጠብቁ እና ያለማስክ ሲንቀሳቀሱ አግኝቷቸው በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው ገልጾ ነበር፡፡ ሐሙስ ደግሞ የልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ 300 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ይህም ሕዝብን በከፍተኛ ሁኔታ ያስቆጣ ከመሆኑም በተጨማሪ በሰብዓዊ መብት ላይ በሚሠሩ ድርጅቶችም ውግዘት እንዲደርስበት አድርጓል፡፡ ለዚህም በዋነኛነት የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዳንኤን በቀለ (ዶ/ር) የሰጡት መግለጫ ነው፡፡ ዋና ዳይሬክቱም “…በየትኛውም ቦታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ የተገኙ ሰዎች ላይ ሁሉ የሚደረግ የዘፈቀደ እስር ከሕግ ውጪ ከመሆኑም በላይ ለነገሩ ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ እና የታለመለትን ዓላማ የሚቃረን በመሆኑ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል፡፡ በዚህ ሁኔታ የታሰሩ ሰዎችም በአስቸኳይ ሊፈቱ ይገባል፡፡” ብለዋል፡፡

የፖሊስ ጭካኔ እና ከሕዝብ እራሱን ነጥሎ የሚያስኬደው መንገድን መምረጥ የተለመደው አካሔድ ሆኖ የቆየ ሲሆን የተቃወመን ሁሉ ማጥቃትን እንደመፍትሔ ከማየት ተቆጥቦ ሒስን የመዋጫ ሰዓቱ አልፏል፡፡ በመሆኑም ፖሊስ ለአዲስ አበባ ሕዝብ ግልጽ ይቅርታ ጠይቆ ነገሮች የሚስተካከሉበትን መንገድ መፈለግ እንደሚጠበቅበት አዲስ ማለዳ ታምናለች፡፡ ይህንንም ከመስመር የወጣ ተግባር ከልብ የመቀየር እና ሕዝባዊ የመሆን መጀመሪያ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባዋል፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን እና ሌሎች በዚህ ጽሑፍ ለማካተት ያልተቻሉትን ግን ደግሞ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰበብ በኅብረተሰቡ ላይ እየደረሱ የሚገኙ አካላዊ ጉዳቶች እና ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በአስቸኳይ ሊቆሙ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች። በተለይም ደግሞ ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት በመስራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን ወረርሽ ለመግታት ከመረባረብ ይልቅ በሕብረተሰቡ ዘንድ ታአማኒነት የሚያሳጣ እና ወደ ፊትም ከሕብረተሰቡ ዘንድ አወንታዊ ምላሽ እንዳያገኝ ሚያደርግ ተግባር በመሆኑ እየተባባሱ ከመሔዳቸው በፊት ሳይቃጠል በቅጠል ስትል አዲስ ማለዳ ሃሳብ ታስተላልፋለች።

በሕዝብ ብሶት እና ተቃውሞ እውን ሆኗል ተብሎ ሲነገርለት ነበረው የለውጥ አመራር ይህን ተግባር በአጭሩ መግታት ካልቻለ የተገባው የተስፋ ቃል እና የታለመው ዓላማ ግቡን ሊመታ ካለመቻሉም ባለፈ ተለውጫለሁ ላለው አመራር ከሕዝቡ ዘንድ የሚሰጠው የተሰላቸ ምላሽ መሆኑ አያጠራጥርም። በመሆኑም ይህ ለነገ ሊባል የማይገባው ተግባር በፍጥነት ሊታረም ይገባል።

የፖሊስ አባላትም ወደ ሕዝቡ ከመጠቆማቸው በፊት ለግዳጅ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት በአንድ የኋላ ክፍት ፖሊስ መኪና ከልክ በላይ ተጭነው እና ተጠጋግተው በሕዝብ መሐል እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ የሚታወቅ ነው። በመሆኑም በራሳቸው ውስጥ ይህን የጥግግት እንቅስቃሴ መቅረፍ እንደሚገባቸው አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች። ከዚህም ጋር ተያይዞ ፊት መሸፈኛ አለማድረግን ምክንያት በማድረግ በግለሰቦች ላይ የድብደባ ጉዳት ማድረስ የኮቪድ 19 ተጠቂዎች በሚሆኑበት ጊዜ ሰውነታቸው ቫይረሱን ተከላክሎ የሚድኑበትን አቅም መግደል እንደሚሆንም ሊታሰብበት ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ሀሳቧን ትደመድማለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 80 ግንቦት 8 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com