በድሬዳዋ የችጉንጉኒያ ወረርሽኝ ተጋርጦባታል

Views: 190

በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ወቅትን ጠብቀው ከሚከሰቱ ወረርሽኞች አንዱ የሆነው የችጉንጉኒያ በሽታ በአሁኑ ሰዓት በከተማዋ ሊከሰት እንደሚችል ምልክቶች እየታዩ እንደሆነ ተጠቆመ።

ከዛም በተጨማሪ ከቺጉንጉኒያ ወረርሺኝ ውጪ ኮሮና ቫይረስን ጨምሮ ወባ እና ዳንጊ ለከተማዋ ስጋት እንደሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ነገር ግን ቅድመ ጥንቃቄ ላይ ትኩረት አድርገን እየሠራን ነው ሲል የድሬዳዋ ከተማ ጤና ቢሮ አስታውቋል።

ችጉንጉኒያ ቫይረስ ድጋሚ ጊዜውን ጠብቆ እንዳይከስት በድሬዳዋ ከተማ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን የድሬዳዋ የጤና ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። ችጉንጉኒያ ቫይረስን ድጋሚ በድሬዳዋ ከተማ እንዳያንሰራራም ከኮሮና ቫይረስ በተጨማሪ የራሱ የሆኑ ባለሙያዎች ተመድበውለት የቤት ለቤት እንቅስቃሴ መጀመሩም ታውቋል።

የድሬዳዋ መስተዳደር ጤና ቢሮ በሽታን መቆጣጠር እና መከላከል ዘርፍ በወባ እና በትንኝ የሚመጡ በሽታዎች መቆጣጠር ዘርፍ አማካሪ ተፈሪ መንገሻ፣ በአሁኑ ሰዓት በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱ ጋር ተያይዞ፣ በድሬዳዋ ተጓዳኝ ሌሎች ወረርሽኞች የመከሰት እድላቸው ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል አንስተዋል።
ቤት ለቤት ምርመራ መጀመሩን እና እስከ አሁን በቤት ለቤት ምርመራ ትኩሳት ታይቶባቸው በተወሰደ ናሙና፣ በድሬዳዋ ኹለት ቺኩንጉኒያ ቫይረስ የተገኘባቸው ግለሰቦች እንዳሉ ተፈሪ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እንደ እርሳቸው ገለፃ ‹‹አሁን የሚያሰጋን ከዚህ ቀደም የችጉንጉኒያ ምልክቶችን እና ኅብረተሰቡ ምን ማድረግ እንደሚኖርበት ወቅቱን ጠብቀን በመኪና ነበር ግንዛቤን እናስጨብጥ የነበረው። ነገር ግን አሁን ለኅብረተሰቡ ያንን ብናደርግ የኮሮና ቫይረስ ምልክት እና የቺጉንጉኒያ ምልክት ስለሚመሳሰል ኅብረተሰቡ እንዳይዘናጋ ፈርተናል›› ሲሉ ስጋታቸውን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። አክለውም ኮሮና ቫይረስ እንዳይሰራጭ ጥንቃቄ በማድረግ ላይ በነበርንበት ሰዓት ችጉንጉኒያ እኩል ቢያንሰራራ፣ ለድሬዳዋ ኹለት ከባድ የቤት ሥራ ይሆናል ብለን እየሰጋን ነው ሲሉም አክለዋል።

የኮሮና ቫይረስን የሚከታተል በሦስት ዘርፍ የተዘጋጀ መዋቅር ሲኖር አንደኛው ግለሰቦችን ለይቶ ማቆያ ውስጥ ማስቀመጥ፣ ናሙና ወስዶ መመርምር፣ ከዛም በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎችን እንክብካቤ ማድረግ ነው። ኹለተኛው ደግሞ ከኮቪድ 19 ውጪ የሆኑትን በሽታዎች የሚከታተል ሲሆን፣ ከዛም በተጨማሪ ወባና ሌሎች በትንኝ የሚመጡ የችጉንጉኒያ ኮሚቴ ለብቻው አለ ሲሉ ገልፀዋል።

እንደ ጤና ቢሮ አማካሪው ከሆነ በችጉንጉኒያ ባለፈው ዓመት ቁጥራቸው በዛ ሰዎች ተጠቅተው እንደነበርና በሽታውም ወረርሽኝ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር አስታውሰዋል። ነገር ግን ወረርሽን ለመቆጣጠር በተሄደበት መንገድ ‹‹የራሱ የሆነ መድኃኒት የለውም። ለታማሚዎች እንክብካቤ በማድረግ እና ቶሎ ቶሎ የሙቀት እና የትኩሳት መጠናቸውን እየለየን ለመቆጣጠር በመሞከር ነበር›› ሲሉ አውስተዋል። ከዛም በተጨማሪ ለችጉንጉኒያ እና ከኮቪድ ውጪ ለሆኑ ወረርሺኖች በአጠቃላይ 15 የሚሆኑ ጤና ጣቢያዎች ተዘጋጅተው እየሠሩ እንደሆነም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ነገር ግን ይሄ በሽታ በጣም ተባብሶ ከቀጠለ ኹለቱንም ለመቆጣጠር ከባድ ሊያደርገው እንደሚችል ተናግረዋል።

ችጉንጉኒያ ‹አዬዴስ› በምትባል ትንኝ የሚመጣ መሆኑን ተፈሪ አስታውቀው፣ ለኅብረተሰቡ ጠቃሚ እና መከላከያ ይሆናል ያሉትን ምክር አስተላልፈዋል። ‹‹ትንኟ ቤቶች ባሉበት እና ያቆረ ውሃ በሚገኝበት አካባቢ ነው የምታዘወትረው፤ የምትናደፈውም በቀን ነው። ስለዚህ ኅብረተሰቡ በመኖርያ አካባቢው ያሉትን ያቆሩ ውሃዎች ማጥፋት ይኖርበታል። ካልሆነ በችጉንጉኒያ የተያዙ ኹለት ሰዎች መኖራቸው ማረጋገጥ እንጂ ቁጥሩ ከጨመረ ከኮሮና ቫይረስ ኮቪድ 19 ጋር በመደምር ወደ ጤና ተቋም የሚመጣው ሰው ስለሚበዛ አካላዊ ርቀትንም ማስተግበር ስለማይቻል የበሽታው ስርጭት ሊጨምር ይችላል›› ሲሉ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ‹‹ኅብረተሰቡ ቅድሚያ በአንዱ በሽታ ከተጠቃ ኹለተኛው ሲጨመር የመቋቋም አቅም ላይኖር ይችላል›› ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ከዛም በተጨማሪም ችጉንጉኒያ ቫይረስ የሚመጣው እና የሚሰራጨው በትንኝ አማካኝነት ሲሆን፣ በሰው ላይ በተከሰተ ከሦስት እስከ ሰባት ቀናት ውስጥ ምልክቶችን እንደሚሳይም የዓለም የጤና ድርጅት አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 80 ግንቦት 8 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com