የእምቦጭን አረም የሚያደርቅ ኬሚካል ተገኘ

Views: 485

የአማራ ክልል የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ማድረቅ የሚችል በአካባቢ ሥነ-ምህዳር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሌለው ፀረ አረም ኬሚካል ማግኘቱን አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ በጣና ሐይቅ ላይ ተከስቶ ከባድ ፈተና ሆኖ በፍጥነት ሐይቁን የተቆጣጠረውን እንቦጭ አረም ለማጠፋት በሚደርገው የምርምር ሥራ በኬሚካል የእንቦጭ አረሙን ሕይወት ዳግም እንዳያንሰራራ አድረጎ ባለበት የሚያጠፋና ዳግመኛ እንዳይራባ ማድረግ የሚችል መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኤርሚያስ አባተ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ምርምር ኢንስቲትዩቱ በጥናት አረጋግጫለሁ ያለው ፀረ አረም ኬሚካል አረሙን ለማጥፋት በሚረጭበት ጊዜ በአካባቢ ሥነ ምህዳርና በአካባቢው የሚኖሩ ነፍሳት ማለትም ዐሳ እና ሌሎችም በውሀ ውስጥ የሚኖሩ ነፍሳት ላይ ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት እንደሌለው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ይህ የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ውጤት የሆነው ፀረ አረም ኬሚካል ከሌሎች መሰል ኬሚካሎች ልዩ የሚያደርገው በጣና ላይ የተከሰተውን እንቦጭ አረም ባለበት በሰዓታት ልዩነት ማድረቅ መቻሉና በውሃ ውስጥ የሚኖሩ ነፍሳትን እንዲሁም በአካባቢው ሥነ ምህዳር ላይ የከፋ የጎንዮሽ ጉዳት እንደማያመጣ መረጋገጡ መሆኑን ኤርምያስ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የምርምር ሥራውን የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ አዲስ ግብርና ምርምርና የክልሉ ውሃ ሀብት ልማት በጋራ በመሆን ያካሄዱት ሲሆን፣ የምርምር ውጤቱን ለማረጋገጥ አንደ ወር መፍጀቱን ኤርሚያስ ገልጸዋል። ኤርሚያስ የምርምር ሂደቱን ለአዲስ ማለዳ ሲያስረዱ፣ አረሙን በውሃ ገንዳ ላይ በማኖርና ዐሳዎችን ውሃው ውስጥ በማድረግ በተለያየ ጊዜ የተለያየ መጠን ያለው ኬሚካል በመጨመር ሙከራው ተደርጓል።

በዚህም በሰዓታት ልዩነት አረሙ የመድረቅ ጸባይ ማሳየቱን እና ለአንድ ወር በቆየው የማረጋገጫ ጊዜ አረሙ በምንም ሁኔታ ዳግም ሊያንሰራራ እንደማይችል ማረጋገጣቸወን ጠቅሰዋል። ለሙከራ በተዘጋጀው ቦታ ላይ የነበሩ ዐሳዎችም ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰባቸው በጥናቱ የሙከራ ጊዜ መረጋገጡን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ባህር ዳር ዩኒቨርሰቱ የእምቦጭ አረምን የሚመገብ የጢንዚዛ መንጋ እያረባ እንደሆና የእርባታ ስራው እንደተጠናቀቀ ጢንዚዛዎቹ አረሙን እንዲመገቡ ይደረጋል መባሉ የሚታወስ ነው። ነገር ግን ኤርሚያስ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት የጢንዚዛ እርባታው ምን ደረጃ ላይ እንዳለ እንደማያውቅ ተናግረዋል።

አረሙን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ የሆነበት ምክንያት እንቦጭ በሥነ-ሕይወት ተፈጥሮው ከውሃ ላይ ከተወገደም በኋላ የመድረቅ አቅሙ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑና ባለበት ዳግም ማንሰራራቱ ነው። እንደ ኤርሚያስ ገለጻ አሁን ላይ የኢንስቲትዩቱ ግኝት በቅርቡ ይሄን ችግር ይፈታል ተብሎ እንደሚታሰብ አመላክተዋል።
ኢንስቲትዩቱ ያገኘው የኬሚካል መፍትሔ በሚመለከታቸው አካላት ተመዝኖ የትግበራ ፈቃድ ከተሰጠው፣ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በሐይቁ ላይ የተጋረጠውን ከባድ ፈተና ለመቆጣጠር እስከ አሁን ሲወሰዱ የነበሩ እርምጃዎች በአካባቢው የሚገኙ ሰዎች በስፋት በማስተባበር አረሙን ከውሃው ላይ ወደ ዳር የማስወገድ እና ላለፉት ኹለት ዓመታት ያህል አረሙን በመፍጨት የሚያስወግዱ ማሽኖችን በመጠቀም ለማስወገድ ሲሠራ ተቆይቷል። ሆኖም እስከ አሁን አመርቂ የሚባል ውጤት አለመገኘቱን ተናግረዋል።

የጣና ችግር መጠነ ሰፊ መሆኑን እና አፋጣኝ መፍትሔ ካልተገኘ አሳሳቢ መሆኑን ኤርሚያስ ጠቁመዋል። በመሆኑም እምቦጭን በሰው ኃይል ለማስወገድ እንደማይቻል ለዓመታት ስለታየ፣ ሌላ የትኩረት አቅጣጫ እንደሚያስፈልግ ኤርሚያስ አክለው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ካሏት ጨው አልባ የተፈጥሮ ውሃ ውስጥ ሃምሳ በመቶ ያክሉን የያዘው የጣና ሐይቅ ለመጀመሪያ ጊዜ በእንቦጭ አረም መወረሩ የተስተዋለው በ2009 ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ አረሙ የሐይቁን የገዳማት ቦታዎች እንዲሸፈኑ እያደረገ እንደሚገኝ ታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 80 ግንቦት 8 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com