የእለት ዜና

ትውልዳዊ ዕይታ፡ የፍትህ ስርዓት ለውጡን ‹ባልተሳካላቸው› የለውጥ አራማጆች ትከሻ ላይ ማቆም

በኢትዮጵያ የማኅበራዊ ለውጥ ይልቁንም በሕግና ፍትህ ስርዓት ለውጥ ታሪክ ውስጥ የተከፈሉት መስዋዕትነቶች ግብ ላይ አልደረሱም የሚለው እይታ እውነታ ላይ የተመሠረተ ቢሆንም፣ የተጋነነ እና ሙሉ እውነታን የማያሳይ ነው የሚሉት አባድር መሐመድ እና ፋሲካ ዓለሙ፣ በዚህ ጽሑፉ በአገሪቱ የሕግ ስርዓት ታሪክ ውስጥ የተከናወኑ ወሳኝና መሠረታዊ የለውጥ ተግባራትን ከኢትዮጵያ የሕግና ፍትህ ስርዓት ታሪካዊ አንድምታ አንጻር አጢነዋል። መንግሥት በተቀየረ ቁጥር  የትምህርት ስርዓት ጭምር እየተቀየረ የተከፈለው መስዋዕትነት እንደተጠለፈ እናም አዲስ የመጣው መንግሥት ታሪክን ከአዲስ እንደሚጀምር የሚያስመስሉ ትርክቶችን የሚያጠይቁ የታሪክ ሰበዞችንም መርጠው አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ከ1983 እስከ 2011 በሥልጣን ላይ የነበረውን መንግሥት በመቃወም ለውጥ የፈለገው የአገሪቱ ወጣት ከሐምሌ ወር 2006 ጀምሮ በወቅቱ የነበረውን አስተዳደር ለመለወጥ ወደ ጎዳና ወጥቶ እልህ አስጨራሽ የሆነ ትግል በማድረግ፣ በደሙ ፊርማ በአገሪቱን የለውጥ ጭላንጭል ካየ ሰነባብቷል። የወጣቱ የመብት ትግል ሂደትም አዲስ የፖለቲካ አቅጣጫ የሚቀይስ አመራር እንዲፈልቅ ያስገደደ ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ በአገሪቱ የፖለቲካ ምህዋር ላይ አበረታች ለውጦችን አድርጓል።

ከእነዚህ ለውጦች ውስጥ የረጅም ጊዜና መዋቅራዊ የሆነ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ተብሎ የሚገመተው የሕግ ስርዓት ለውጥ ሥራ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መሪነት እየተከናወነ ሲሆን፣ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ስር የተቋቋመው የሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ የዚህን ሥራ መሪ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። አማካሪ ጉባዔው ከተቋቋመበት ወቅት ጀምሮ በአገሪቱ ውስጥ አሳሪና አፋኝ፣ በተለይም ለሰብአዊ መብት መከበር ሳንቃ የሆኑ ሕጎች ዙሪያ ተገቢነት ያለው ቅድመ-ጥናት በማድረግና አማራጭ የመፍትሄ ሐሳቦችን ከነ ረቂቅ ሕጎቹ ለመንግሥት በማቅረብ ደፋ ቀና እያለ ይገኛል።

የሆነ ሆኖ ግን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተቺዎችና አንባብያን እንዲሁም አማካሪ ጉባዔው መዋቅር ውስጥ ሆነው የሕግ ስርዓት ለውጡ እንዲሳካ በበጎ ፈቃደኝነት እያገለገሉ ያሉ ከ180 በላይ የሚሆኑ ባለሙያዎች፣ ከለውጡ ዋዜማ በፊት የተከፈለው የወጣቱ መስዋእትነትና ልፋት ከንቱ ሊሆን እንደሚችል መጠርጠራቸው ወይም ለውጡን ለሂስ ማቅረባቸው አይቀሬ ነው። ጤናማ የሆነ ጥርጣሬና ሂስ አግባብ ከመሆኑም በላይ እንዲያውም ከታሪክ አንጻር የሚበረታታም ሊሆን ይችላል። ለምን ቢባል፤ በኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ታሪክ ሂደት ውስጥ ዜጎች ፍትሐዊነትና የሕግ የበላይነት እንዲከበር በተለያዩ ጊዜያት መስዋዕትነት መክፈላቸው አዲስ ክስተት አለመሆኑ ነው።

የኢትዮጵያ የሕግና ፍትህ ስርዓት ታሪካዊ ዳራ: ከፀሐይ በታች ምንም አዲስ ነገር የለም! 

የኢትዮጵያ የአገር ምስረታ ታሪክ ከሦስት ሺሕ ዓመት በላይ ያስቆጠረ እንደሆነ በኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ታሪክ ያጠኑ የታሪክ ተመራማሪዎች ያትታሉ። በእነዚህ ሺሕ ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩት ብዛት ያላቸው አገረ መንግሥታትና የፖለቲካ ስርዓቶች ስር የተከናወኑ የሕግና ፍትህ ስርዓት ለውጦችና ማሻሻያዎች እንደሚኖሩ መገመት አያስቸግርም።

ለምሳሌ በኢትዮጵያ የነበሩ የተለያዩ አገረ መንግሥታት የፖለቲካ ወይም ማኅበራዊ ለውጥ ውስጥ በሚያልፉበት ጊዜ ወይም ሃይማኖታዊ ጉድኝታቸውን (ለምሳሌ ወደ ክርስትና ወይም እስልምና) በሚቀይሩበት ጊዜ፣ የተለያዩ የሕገ መንግሥታዊና የሕግ ለውጦችን ማድረግ እንደነበረባቸው ግልጽ ነው።

የሕግና ፍትህ ስርዓት ለውጥ በጥንታዊት ኢትዮጵያ

በጥንታዊት ኢትዮጵያ የአገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የስርዓቱ ዋነኛ ተዋንያን ንጉሠ ነገሥቱ፣ የፊውዳል ባለአባቶችና የሃይማኖት ተቋማት የነበሩ መሆናቸውን የኢትዮጵያን ታሪክ ያጠኑ የታሪክ ምሁራን በሰፊው ትንታኔ የሰጡበት ጉዳይ ነው። እነዚህ የሥልጣን ኃይላት (Power Elites) ሥልጣናቸው ቀጣይነት እንዲኖረውና ስርዓትና ተገዥነትን ለማስፈን አንድ ወቅት ጠንካራ የሆነ ማኅበረሰቡን ማእከል ያላደረገ ማእከላዊ መንግሥት በመመሥረት፣ በሌላ ጊዜ ሃይማኖትንና አንዳንድ የሕግ ፍልስፍና ሐሳቦችን በመያዝ የገዢና ተገዢ ስርዓትን በማጠናከር ሕዝቡን በተለያዩ የፖለቲካ ስርዓት ሂደቶች ሲመሩት ቆይተዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥ እንደ ፍትሐ ነገሥት ያሉ የሕግ ሰነዶች ነባራዊ የኃይል መዋቅሮችን ሳይፈታተኑ ነገሥታት ፍርድ መስጠት ያለባቸው በርትዕ መሆኑን፤ እንዲሁም በፍትህ አሰጣጥ ሂደት ለራሳቸው፣ ለልጆቻቸውና ለዘመዶቻቸው ሳያዳሉ መሆኑን በመደንገግ ኃይል በእጃቸው የያዙ ፍትሀዊ በሆነ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ መሞከራቸውን ማየት ይቻላል።

ኢትዮጵያ ከገጠሟት የለውጥ ሁነቶች ውስጥ አሁን ላለው የለውጥ ሂደት ቀጥተኛ አግባብነት ያላቸው አገሪቱ ከዘመናዊው ዓለምና ከዘመናዊነት ጋር ስትገናኝ የነበሩትን የሕግና የሕግ ሥርዓት ለውጥ ሂደቶች ናቸው። ከነዚህ ውስጥ የአጼ ቴዎድሮስ የባርነት፣ የመሬትና የመንግሥት አስተዳደር ሥርዓትን ለመለወጥ ያደረጉት ሙከራ አጠቃላይ የሆነና ብዙ እመርታዎችን ሊያስገኝ የሚችል ከመሆኑ አንጻር ቢወሳም፣ ተግባር ላይ ግን አልዋለም። ስለዚህ የኢትዮጵያ ዘመናዊ የሕግ ስርዓት ለውጥ ሲነሳ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ስርዓተ መንግሥት በከፊል ተጀምሮ በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ለፍሬ የበቃው ዘመናዊ መንግሥት የመገንባት ሂደትን እንደ መነሻ መውሰዱ የግድ ነው።

በኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካና የሥልጣን ኃይላት የተለያዩ የውስጥና የውጭ የለውጥ ግፊቶችን ለሺሕ ዓመታት የተለያዩ የስርዓት፣ የመሪ ወይም ከፍ ሲል የሥርወ መንግሥት ማሻሻያዎችና ለውጦችን እያደረጉ ያስተናገዱ ቢሆንም፣ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ ኢትዮጵያ ከዘመነ መሳፍንትና ራስን ከውጭው ዓለም የማግለል ፖሊሲ ማብቃቱን ተከትሎ የመጣው የለውጥ ማዕበል ግን በትናንሽ ማሻሻያዎች ሊታለፍ የሚችል አልነበረም።

የውጭው ዓለም በኢንዱስትሪው አብዮት አልፎ እንዲሁም በኢኮኖሚ እና በጦርነት መሣሪያዎችና መንገዶች ኢትዮጵያን ልቆ ነበር የጠበቃት። ኢትዮጵያ በበለጸጉት አገራት ቅኝ ግዛት እንዳትወድቅ፤ ከዚያም አልፋ ከእነዚህ ጋር ሊወዳደር የሚችል ተፎካካሪ ኢኮኖሚ ኖሯት የንግድ ግንኙነቶች ውስጥ መግባት እንድትችል ፈጣንና ስር ነቀል ለውጥ ማድረግ እንዳለባት ግልጽ ነበር። ከውጭ ዜጎች ጋር የሚደረገውን ንግድ ለማሳለጥ እንደ ጊዜያዊ እርምጃ ዳኞች የውጭ አገር ሕግ እንዲተገብሩ አልፎም በውጭ አገር ዜጎች መሃል የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ዳኞች እንዲዳኙ የተፈቀደበት ሁኔታ የነበረ ሲሆን፣ ዘላቂ መፍትሔ ማስፈለጉ የጊዜው ልኂቃንን ያስጨነቀና የማረከ ጉዳይ ነበር።

ጃፓናይዘሮቹ (“Japanizers”) እና የ1923ቱ ሕገ-መንግሥት

‹ጃፓን የሚሉት መንግሥትስ … ወደ ኤሮጳ ኺዶ የሚማርለትን ሲያገኝ በገንዘብ ያግዘው ነበር። የትምህርትን ቤት እከፍታለኹ ብሎ የሚመጣውንም የኤሮጳን ሰው … በገንዘቡ እንዲመጣለት ይዋዋለው ነበር። ስለዚህም ሕዝቡ ዐይኑን ከፈተ፤ ሀብታምም ኾነ፣ በረታም፥ ታፈረም። ቺናና እስያም የሚባሉ ኹለት መንግሥታትም የጃፓንን መንገድ በብዙ ትጋት መከተል ዠምረዋል። …የዛሬው የኢትዮጵያ ንጉሥ የጃፓን መንግሥት እንዴት እንዳደረገ አስመርምረው መንገዱን እንዲከተሉት ተስፋ እናርግ።›

ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ

ዘመናዊ የትምህርት እድል በማግኘታቸው ነባሩን የገዢና ተገዢ ስርዓት የሚደርስበትን የዘመናዊነት ፈተና አስቀድመው በመረዳት ሥርዓቱን ሳይቀናቀኑ፣ እንዲያውም በስርዓቱ ውስጥ ሆነው፣ ዘመናዊ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሞከሩት የመጀመርያዎቹ ኢትዮጵያውያን በተለምዶ ጃፓናይዘሮች (Japanizers) በመባል የሚጠሩት የምሁራን ስብስብ ናቸው። እነዚህ ምሁራን የኢትዮጵያ የፖለቲካና ኢኮኖሚ መዋቅር ኋላ ቀርነት ሊያስከትል የሚችለውን መዘዝ በመረዳት በተዋረድ ከበላይ የሥልጣን ኃይላት ወደታች የሚመጣ አብዮታዊ ለውጥ  እንዲኖር ጥረዋል። ለእንደዚህ ዓይነት ለውጥ ተምሳሌትነት ጃፓንን የመረጡትም ጃፓን በጊዜው በንጉሣዊ ስርዓት የምትመራ፣ አውሮፓዊ ያልሆነች፣ የቅኝ ገዢዎችን የወረራ ሙከራ የመከተች፣ እንዲሁም አገራዊና ብሔራዊ ማንነቷን ሳታጣ የኢኮኖሚና ኢንዱስትሪያዊ ለውጦችን በፍጥነት ማሳካት በመቻሏ ነበር።

በዚህ አመለካከት የተቀረጸው የ1923ቱ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት መሠረቱን ያደረገው እ.ኤ.አ 1889 የወጣውን የጃፓን ሕገ-መንግሥት ሲሆን በወቅቱ በሩስያ የተማሩትን ጥቂት የአገሪቱ ምሁራን በተለይም ጸሐፊና በዓለም መንግሥታት ማኅበር (League of Nations) አምባሳደር የነበሩትን በጅሮንድ ተክለሐዋሪያት ተክለማርያምን በመያዝ የመጀመሪያውን የአገሪቱን ሕገ መንግሥት አርቅቃለች። የሕገ መንግሥቱ አርቃቂዎች መሠረታዊ ዓላማቸው የንጉሣዊ ስርዓቱን በመጠበቅ የኢትዮጵያ አንድነትና ሕዝቡን ከስርዓት አልበኝነት መከላከል ሲሆን፣ በሂደትም በረቂቁ ላይ በንጉሠ ነገሥቱ ጥቂት ለውጦች ከተደረጉ በኋላ ሕገ መንግሥት ሆኖ ሊፀድቅ ችሏል።

በወቅቱ የተዋቀረው የሕገ-መንግሥቱ አርቃቂ የምሁራን ስብስብ በመጀመሪያ የተለያዩ አገራትን ሕገ-መንግሥቶች በማጥናት በተለይም የእንግሊዝን፣ የጀርመንን፣ የጣልያን እና የጃፓንን ሕገ መንግሥቶች ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር በመመልከት ረቂቅ በማዘጋጀት፣ በንጉሠ ነገሥቱ ባለአባቶችና አገር ገዢዎች በማስተቸት ሕገ-መንግሥት ሆኖ እንዲታወጅ አድርገዋል።

አጠቃላይ በወቅቱ የነበሩ ምሁራን የነበራቸው ከፍተኛ ፍላጎት አገራቸው በሕግና ፍትህ ስርዓት በተሻለ እርከን ላይ እንድትቀመጠና የሕግ በላይነት ሰፍኖ የዜጎች ብልጽግና ማስፈን የነበረ ቢሆንም፣ የሕገ-መንግሥት አወጣጥ ሂደት መሠረታዊ መርሆችን ያልተከተለ በመሆኑ የተለየ አመርቂ ውጤት አላመጣም። ለምሳሌ የሕገ-መንግሥቱ በተደራጀ መንገድ የዜጎችን መብቶች ከመዘርዘር አንጻር በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመርያ የሕግ ሰነድ ቢሆንም፣ በተግባር ግን በኢትዮጵያውያን ሕይወት ላይ ምንም ለውጥ አላመጣም።

የ1950ዎቹ የሕግ አርቃቂ ኮሚሽን 

በኢትዮጵያ የሕግ ስርዓት ለውጥ ታሪክ ውስጥ ተዋናይ የነበሩት ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በጥራትም ሆነ በይዘት የኢትዮጵያን የሕግ ስርዓት ለመለወጥ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርገዋል። በሥልጣን ዘመናቸውም አገራችን እስከ አሁን ድረስ ሙሉ በሙሉና በከፊል እንዲሁም በሂደት የተቀየሩ ሕጎችን በማውጣት አስተዋውቀዋል። እነዚህም የፍትሐ ብሔር፣ የፍትሐ ብሔር ስነ-ስርዓት፣ የንግድ፣ የባህር፣ የወንጀለኛ መቅጫ እና የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ስነ-ስርዓት ሕጎች ናቸው።

በተያያዘም እነዚህ ሕጎች በወቅቱ ከአውሮፓ አገሮች ጠንካራ የሕግ ስርዓትና ልምድ ካላቸው ለአብነትም ከፈረንሳይ፣ ከስዊዘርላንድ እና ከጣልያን በተጨማሪም ከህንድ አገር የተቀዱ ናቸው። የሕግ ምሁራን እነዚህ ለውጦች የማኅበረሰቡን ባህላዊ የሕግ ስርዓትና የሕገ-ልቦና መርሆዎችን ወደ ጎን በመተው ከአውሮፓ አገሮች በተቀዱ ሕጎች እና በአጠቃላይ ሕግ ተኮር “ማኅበራዊ ምህንድስና” ባለው አሉታዊና አዎንታዊ አንድምታዎች ላይ ባይስማሙም፣ አንድ ወጥነት ያለው የመንግሥት ሕግ ስርዐት ከመዘርጋት አንጻር ግን ለውጦቹ በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛ ቦታ እንደሚይዙ አያከራክርም።

በነዚህ ሕጎች መውጣት ሂደት ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ የነበረው በውስጡ 29 አባላት የነበሩት የሕግ አርቃቂ ኮሚሽን (Codification Commission) ሲሆን፣ ይህም ኮሚሽን በዋናነት የተቋቋመው የሕግ አወጣጥ ሂደቱን እንዲያከናውንና በወቅቱ የነበሩት የወጪ አገር ዜግነት የነበራቸው ሕግ አርቃቂዎችን እንዲቆጣጠር ነበር። ኮሚሽኑ የተለያዩ ንዑስ-ኮሚቴዎች የነበሩት ሲሆን፣ እነዚህም ንዑስ ኮሚቴዎች በተመደቡበት የሥራ ቡድን ላይ የሕግ ረቂቅ ከሚሠሩ የውጪ አገር ዜጎች ጋር መሥራትና ሥራውም ሲጠናቀቅ ለሕግ ኮሚሽኑ ማቅረብ ነበር።

ይህ የሕግ አርቃቂ ኮሚሽን በአገሪቱ የሕግና የፍትህ ስርዓት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የሕግ ረቂቅ ከመቅረቡ በፊት የተለያዩ ቅድመ ጥናቶች የሚያካሄዱ ነበሩ። እነዚህ ጥናቶች በሂደት የሕግ አውጪውን ሐሳብ ሊያንጸባርቁ የሚችሉ ቅድመ-ሥራዎች (Travaux Préparatoires) እና እንደ ሁኔታው የሕግ አውጪ ሐተታ ዘምክንያት (Exposé de Motifs) የተሠሩበትም ነበር።

የሕግ ኮሚሽኑ ጥናት ላይ መሠረት ተደርጎ የቀረበለት ረቂቅ ሕግ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ በማጽደቅ ለሚኒስተሮች ምክር ቤት ያቀርብ የነበረ ሲሆን፣ የሚኒስቴሮች ምክር ቤትም የቀረበውን ረቂቅ ሕግ ከተወያየበት በኋላ በወቅቱ ለነበሩት ለላይኛውና ለታችኛው ምክር-ቤቶች የጋራ ስብሰባ በማቅረብ በንጉሠ ነገሥቱ ሙሉ ፈቃድ አማካኝነት ረቂቅ ሕጉ ሕግ ሆኖ ሊወጣ የሚችልበት የአሠራር ሂደት ነበር። በአጠቃላይ ይህ ኮሚሽን በኢትዮጵያ የሕግ ማውጣት ሂደት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የነበረውና ለዘመናት ተሻጋሪ የሆኑ ሕጎችን የማውጣት ተግባራትን ለማከናወን ያመች ዘንድ መልካም ልምድ ያሳየ ነበር።

የ1948ቱ የተሻሻለው ሕገ-መንግሥት እና የ1966 ረቂቅ ሕገ- መንግሥት

የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት ምንም እንኳን ኢትዮጵያን በሕግ ለውጥ ረገድ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ቢሆንም፤ የፖለቲካ መዋቅራዊ ለውጥ ከማሳካት አንጻር ግን በቂ የሆነና ጊዜውንም የጠበቀ ለውጥ አለማካሄዳቸው እየቆየና እየተደራረበ ሲመጣ ዘርፈ ብዙ የለውጥ ጥያቄዎችን ማስነሳቱ አልቀረም። የ1923ቱ ሕገ-መንግሥት ጥሩ ጅማሬ ቢሆንም በዋናነት ለውጭ አገር ተመልካች ፍጆታ እንጂ በተግባር የለውጥ ዓላማን ሊያሳካ አልቻለም።

የ1948ቱ የተሻሻለው ሕገ-መንግሥትም እጣ ፈንታ ከዚህ የተለየ አልነበረም። ይህኛው ሕገ-መንግሥትም እንዲሁ በውስጡ የነበሩ መርሆች ጥቅምና ጉዳቶች እንደተጠበቁ ሆኖ በዋናነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ መቀላቀል ጉዳይ በሚያደርገው ውሳኔ ተጽዕኖ ከማሳደር ባለፈ በተግባር ብዙ የለውጥ ፈላጊዎችን ያስከፋ ነበር። ስለዚህ በ1948 የተሻሻለው ሕገ-መንግሥት ስር ከላይ የተጠቀሰው አርቃቂ ኮሚሽን ስር ከወጡት ሕጎች ሊጠብቋቸው ከቻሉ መብቶች ውጭ ሕገ-መንግሥቱ ራሱ በመብትና ፖለቲካ ምህዋሩ ላይ እመርታ አላሳየም።

በተጨማሪም የዚህ ሕገ-መንግሥታዊ ሙከራ አመርቂ ውጤት አለማስገኘቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ከዘገምተኛና ከላይ ወደታች ከሚመጣ ለውጥ ይልቅ  ስር ነቀል የሆነ ሕዝባዊ አብዮት እንዲኖር የሚፈልግ የምሁራን ትውልድ እንዲመጣ ወይም እንዲህ አይነት አስተሳሰብ የበላይነት እንዲይዝ መንገድ ከፍቷል።

ሕዝባዊ አመፅ የወለደው አብዬት ሲቀጣጠል 30 አባላት የነበሩት የሕገ -መንግሥት አርቃቂ ቡድን በወቅቱ ለነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ሚካኤል እምሩ ሕገ-መንግሥት አቅርበው ነበር። በዚህ ረቂቅ ሕገ-መንግሥት ውስጥ ቀደሞ በአገሪቱ የሕግና የፍትህ ስርዓት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በተለይም የታችኛው ምክር ቤት  አባላት በቀጥታ ምርጫ ሂደት የሚመረጡበትን፣ የዜጎችን የሰብአዊ መብቶች ሊያስከብር የሚችል የእምባ ጠባቂ ተቋም የሚያቋቋምበትና ዘርዘር ያሉ ሥልጣንና ተግባራትን በአዲስ መልክ ለሚዋቀረው የአገሪቱ ርዕሰ መስተዳደር የሰጠ፣ ይልቁንም የንጉሠ ነገሥቱን የተለጠጠ ልዩ መብትና ሥልጣን በሕገ-መንግሥታዊ ስርዓት የገደበ ታሪካዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚያስችል እድል ነበር።

ረቂቅ ሕገ-መንግሥቱ የመተግበር እድል ቢያገኝ እውነተኛ ለውጥ ያመጣ ይሆን ወይ የሚለው ጥያቄ ለግምት ክፍት ቢሆንም፣ የሕዝባዊ ነውጡ አቀንቃኞች ይህ ጥያቄ ራሱን እስኪመልስ መጠበቅ አልቻሉም። የተሻለ የሚሉትን የራሳቸውን መልስ በአፋጣኝ ማስገኘት ስለፈለጉ ወደ እርምጃ አደሉ። በነሱ ‹ዲያሌክቲካዊ› አገላለጽ በምርት ኃይሎች መሃል ያለው ቅራኔያዊ ውጥረት ተባብሶ አብዮቱን በማይቀርበት ደረጃ አድርሶት ነበር – አብዮቱም ሳይታለም ተፈታ።

የሕግና ማኅበራዊ ለውጥ በደርግ ወታደራዊ ሥርዓተ መንግሥት ስር 

ከ1966 ጀምሮ የኢትዮጵያን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ሂደቶችን በመቆጣጠር የተለዪ ፖለቲካ ፍልስፍና በማምጣት አገሪቱን የመራው የደርግ መንግሥት ነበር። ይህ የማርኪሊስት-ሊኒኒስት ወታደራዊ ቡድን በሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ በአገሪቱ የቀደመ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የተለያየ ይዘትና የሕግ ጽንሰ ሐሳብ ያላቸው በርካታ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች በማውጣት ሕዝብን ለተከታታይ 17 ዓመታት አስተዳድሯል።

በዚህ የመንግሥት ስርዓት ውስጥ በወቅቱ ወሳኝ ሕዝባዊ ጥያቄ ከነበሩት መካከል የመሬት ሕግ የለውጥ ሂደት እና የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጥያቄዎች ዋነኞቹ ነበሩ። በወቅቱ የሕዝብን ጥያቄዎች እመልሳለሁ ያለው ደርግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የወሰዳቸው የመሬት ሥሪት ማሻሻያ እርምጃዎች በተለይ ከማኅበራዊ ተጽዕኖ አንጻር በኢትዮጵያ የሕግና የፍትህ ስርዓት ለውጥ ታሪክ በዋናነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው።

የደርግ መንግሥት እከተለዋለው ከሚለው ርዕዮተ ዓለም አንጻር ብዙ እርቃን ጉልበትና ሕግን ያማከሉ የማኅበራዊ ምህንድስና ሥራዎችን እንደሚተገብር መጠበቅ ቢቻልም፣ በተከታታይ ጦርነቶች የተጠመደው ደርግ ከመሬት ሥሪት ማሻሻያው ያለፈ የሕግና ፍትህ ስርዓት ለውጥ ሥራ አልሠራም። በአጠቃላይ በዚህ ዘመን የሕግና የፍትህ ስርዓት ለውጥ ለማምጣት በወቅቱ በመንግሥት የተለየ ተግባራት ያልተከናወኑና ለጉዳዩም ትኩረት ያልተሰጠው የነበረ መሆኑን የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።

በመጋቢት ወር 1978 የተቋቋመው እና በውስጡ 343 አባላት የነበሩት የሕገ-መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን የ1979ኙን የኢትዮጵያ ሕዝባዊ የዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥትን ያረቀቁ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የሕግና ፍትህ ስርዓት ግንባታ ታሪክ ውስጥ በረቂቁ ላይ በመላው አገሪቱ በ25,000 የተመረጡ ከተሞችና ስፍራዎች ሕዝባዊ ውይይቶች ከመደረጋቸውም በላይ ሕዝበ ውሳኔን (Referendum) መሠረት ተደርጎ የፀደቀ ሕገ-መንግሥት ነበር።

ይህ ሕዝበ ውሳኔ በኢትዮጵያ ከተካሄዱ ምርጫዎች ጋር ሲወዳደር በዴሞክራሲያዊነት ቀመር በእርግጠኝነት የሚልቀው የ1997ቱ ምርጫ ብቻ ቢሆንም፣ በወቅቱ በነበረው የእርስ በእርስ ግጭት ምክንያትና የደርግ ታሪክ ሲወሳ ቀይ ሽብርና መሰል ሁነቶች ጎልተው መውጣታቸው የሕገ-መንግሥቱ አወጣጥ ሂደትም ሆነ የአሰራር ስርዓቶች ታሪካዊ ውይይቶች ውስጥ እንዳይካተቱ አድርጓቸዋል።

ባልተሳካላቸው የለውጥ አራማጆች ትከሻ ላይ መቆምን አምኖ መቀበል

በኢትዮጵያ የሕግ ታሪክ ውስጥ አንድና ጠንካራ የሆነ እንዲሁም የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብቶችና የሕግ የበላይነት የሚያስጠብቅ ስርዓት ገንብቷል ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል የማጣቀሻ ነጥብ ባይኖርም፣ ባለፉት ሰማንያና ከዚያ በላይ ዓመታት በዘገምተኛ ለውጥ ይሁን በስር ነቀል አብዮት መልክ የመጡት ለውጦች ተደምረው አሁን ያለንበት አድርሰውናል። ከዚህ በፊት የነበሩት የለውጥ ሙከራዎች በጊዜው ለነበሩት ትውልዶች የሐሰት ተስፋም ይሁን የሐሰት ጅማሮ ሊመስሉ ቢችሉም፣ በአገራዊና በረዥም ጊዜ ዕይታ ግን ትውልድ ተሻጋሪ ዝግመተ ለውጥ ድሎች መሆናቸውን መገንዘብ እንችላለን።

ለምሳሌ ባለፉት ኻያ ስምንት ዓመታት የነበረው ሕገ መንግሥትና በስሩ የተደረጉት የለውጥ ጅማሬዎች፣ የደርግ የመሬት ስሪት ለውጦች ወይም በ1950ዎቹ የተደረጉት የሕግ ማሻሻልና ኮዲፊኬሽን ሥራዎች ወደድናቸውም ጠላናቸው፣ አሁን ያለው ትውልድ የሚንቀሳቀስበት መረማመጃ መድረክ ናቸው።

ያም ሆነ ይህ ግን ማናቸውም የሕግና ፍትህ ስርዓት ለውጥ ወይም ማሻሻል ሥራዎች ቀድመው በመጡት ሥራዎችና ትውልዶች ትከሻ ላይ ቆመው ብቻ ነው ሊራመዱ የሚችሉት። ይህን መካድ የቆሙበትን መሬት አይታየኝም ከማለት ጋር ሊመሳሰል የሚችል እውነታን መካድ ብቻ ሳይሆን የቀድሞዎቹን ድሎች በቀላሉ የመድገምና ውድቀቶችን የመሸሽ፣ ራስንም እድሎችን መንፈግ ነው።

አባድር መሐመድ በሕግ ሳይንስ ዶክትሬት (J.S.D.)፣ የሰብዓዊ መብት ጠበቃና መምህር፣ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ።

ፋሲካ ዓለሙ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰብዓዊ መብቶች ትምህርት የኹለተኛ ዲግሪ ተማሪ እና በሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት የሕግ ባለሙያ።

ቅጽ 2 ቁጥር 80 ግንቦት 8 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!