የሲዳማ የፊቼ ጨምበላላ በዓልን አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መልዕክት አስተላለፉ

Views: 38

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የሲዳማ የፊቼ ጨምበላላ በዓልን አስመልክተው ዛሬ በፌስ ቡክ ገፃቸው መልዕክት አስተላልፈዋል ሙሉ መልዕክቱም እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

እንኳን ለ2012 የሲዳማ የፊቼ ጨምበላላ በዓል በሰላም አደረሰን፣ አደረሳችሁ።

የሲዳማ ፊቼ ጨምበላላ የአዲስ ዓመት በዓል በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ በቅርስንት ከተመዘገቡት አምስት የሀገራችን ቅርሶች መካከል ነው። ኢትዮጵያ ባህለ ብዙ፣ ዕሴተ ብዙ፣ ጸጋ ብዙ፣ መሆኗን ከሚያሳዩ ህያው ምስክሮች አንዱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተስፋ የተሞላ፣ አዲስን ነገር አበክሮ የሚሻ መሆኑን እንደ ፊቼ ጨምበላላ ያሉ አዲስን ዓመት በተስፋና በጉጉት የመጠበቂያ በዓላት በሚገባ ያመለክቱናል፡፡

የፊቼ ጨምበላላ በዓል ከሥነ ፈለክ ጋር የነበረንን ጥንታዊ የዕውቀት ግንኙነት ያመለክተናል፡፡ ሽማግሌዎቹ የበዓሉን ዕለት የሚወስኑት የመሬትን፣ የፀሐይን፣ የጨረቃንና የከዋክብትን ሥርዓተ ዑደት በመመልከትና የእነዚህን አካላት ቅንጅት በማጥናት ነው፡፡
ፊቼ ጨምበላላ በዓል ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ስላሸጋገረን ምስጋና፣ መጪው ዓመት የሰላም፣ የፍቅር እና የብልጽግና እንዲያደርግልን ምልጃ፣ ለፈጣሪ የሚቀርብበት በዓል ነው፡፡ የተጣሉ ዕርቅ ያወርዱበታል፤ ፈጣሪ ለሽማግሌዎች የሰጣቸው እውነት ወይም ሃላሌ ይጸናበታል፤ ሕፃናትና ከብቶች ጠግበው ይዉሉበታል።

በፊቼ ጨምበላላ ጊዜ ሽማግሌዎቹ የሚሰጡት ምክር ሰባት እጅግ ወሳኝ በሆኑ ዕሴቶች ላይ የተመሠረ ነው፡፡ ሕዝቡ ጠንክሮ እንዲሠራ፣ አረጋውያንን እንዲያከብርና እንዲረዳ፣ ሀገር በቀል ዛፎችን እንዳይቆርጥ፣ እንዲከባከብ፤ ሰዎች ከስንፍና እንዲርቁ፣ ልመናን እንዲጸየፉ፣ ከስርቆትና በሐሰት ከመመስከር እንዲቆጠቡ ይመክራሉ፡፡ በዓሉ በዋናነት ተካፍሎ መኖርን ያስተምራል፡፡ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ይጠይቃል፡፡ ማኅበራዊ ትብብርን ያጠናክራል፡፡ በሰላም አብሮ መኖርንና ከሌሎች ጋር መተሣሠርን ያበረታታል፡፡

ከሁሉም በላይ ፊቼ ጨምበላላ ለሕጻናትና ለዕውቀት ሽግግር የላቀ ሥፍራ አለው፡፡ ልጆች የእናት አባቶቻቸው ታሪክና የሕዝቡ ባህል ይነገራቸዋል፡፡ በቃል እየተላለፈ የመጣውን ትውፊት ይወርሳሉ፡፡ በበዓል ቀን በሚደረገው ክዋኔ እንዲሳተፉና ማንነታቸውን እንዲያውቁ ይደረጋል፡፡ ነባሩ ዕውቀት ከወላጅ ወደ ልጅ በሽማግሌዎች ትረካ የሚተላለፈው በዋናነት በፊቼ ጨምበላላ ወቅት ነው፡፡ ይህ መቼም ቢሆን በየቤታችን ልንተገብረው የሚገባ ድንቅ ዕሴት ነው፡፡

ሲዳማዎች ከአሮጌው ወደ አዲሱ ዓመት የመሸጋገሪያ ተምሳሌት በሆነው በ “በ” ቅርፅ በሚሠራው “ሁሉቃ” ልጆቻቸውንና ከብቶቻቸውን በማሳለፍ፣ በአሮጌው ዓመት የነበሩ ችግሮች፣ መከራዎች፣ በሽታዎች ከኋላችን ቀርተው፣ አዲስ ወደ ሆነውና ብሩህ ተስፋ ወደሚታይበት የብልጽግና ጎዳና እኛንም ምራን በማለት ይለምናሉ፡፡ ለዚሁ ዕለት ተብሎ ወደሚዘጋጀው ለምለም መስክ ከብቶቻቸውን ያሠማራሉ። እኛም ዓለማችንን እና ሀገራችንን ሥጋት ላይ የጣለውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ፈጣሪ ከኋላችን አስቀርቶ፣ በአዲሱ ዓመት ወደ ብልጽግና ጎዳና እንዲመራን ከሲዳማዎች ጋር አብረን ፈጣሪን እንማጸናለን፡፡

የዘንድሮውን የፊቼ ጨምበላላ በዓል በደማቅ ሁኔታ ለማክበር ሁላችንም ስንጓጓ ነበር። ይሁን እንጂ በኮሮና ቫይረስ ምከንያት እንደዚህ ቀደሙ በጉዱማሌ ሕዝብ በተሰበሰቡበት ለማክበር የሚቻል አልሆነም። የሲዳማ ሽምግሌዎች ዓለማችን ያለችበትን ሁኔታ በመረዳት በዓሉ በቤት እንዲከበር ያስተላለፉት ወቅታዊ መልእክት ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ኃላፊነት የሚሰማቸው፤ ከምንም ነገር በላይ የሰው ሕይወት የሚገዳቸው መሆኑን ያሳየ በመሆኑ አድናቆቴን ለመግለጽ እወዳለሁ።

የሲዳማ የባህል አባቶች እና ሽማግሌዎች ያስተላለፉትን መመሪያ በማክበር፣ ሁላችንም በየቤታችን በመሆን፣ እጆቻችንን እየታጠብን፣ ርቀታችንን ጠብቀን፣ ሌሎችንም እየረዳን፣ የዘንድሮን የፊቼ ጨምበላላ በዓል እናከብራለን። የፈጣሪ በጎ ፍቃዱ ሆኖ፣ ይህንን ወረርሽኝ አሸንፈን ለከርሞ እንደከዚህ ቀደሙ፣ በአደባባይ በጉዱማሌ ከመላው ሲዳማ ጋር ለማክበር ፈጣሪ ይርዳን ይርዳን።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com