ግብጽ በአባይ ግድብ ውዝግብ ላይ እንደገና ለመወያየት የቀረበውን ሀሳብ ተቀበለች

Views: 135

በአባይ ተፋሰስ አገራት መካከል ውዝግብ ባስነሳው በህዳሴው ግድብ አሞላልእና አለቃቀቅ ዙሪያ ግብፅ ከሱዳን እና ከኢትዮጵያ ጋር ድርድር ለመጀመር ፈቃደኛ መሆኗን አስታወቀች፡፡

የግብፅ የውጪ ጉዳይ ሚኒሰትር ሰምሃ ሹክሪ እንዳሉት ”ግብፅ ፍትሐዊ ፣ ሚዛናዊ እና አጠቃላይ ስምምነትን ላይ ለመድረስ እንዲሁም ሁልጊዜም ወደ ድርድር ለመግባት እና በቀጣይ ስብሰባዎች ላይም ለመሳተፍ ዝግጁ ናት” ብለዋል፡፡

ሚንስትሩም አክልው ”ስምምነቱ የግብፅን የውሃ ፍላጎት እንዲሁም የኢትዮጵያን እና የሱዳንን ጥቅም ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል” ብለዋል፡፡

የካይሮ ይህ አቋም የተገለፀው የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ከኢትዮጵያው አቻቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ጋር የህዳሴውን ግድብ አስመልክቶ በትናንትናው እለት ማለትም ሐሙስ ግንቦት 13/2012 የቪዲዮ ኮንፍረንስ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው፡፡

“ኢትዮጵያ መገንባት የተጀመረችውን ታላቁ የህዳሴ ግድብን ለመሙላት አትዘገይም” በማለት ዶክተር አብይ አህመድ ከዚህ ቀደም ተናግረው የነበረ ሲሆን፤ በሁለት ዓመታት ውስጥ 18.4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የሚሰበሰብበት “የመጀመሪያ ደረጃ ሙሌት” በሚያዝያ ወር  እንዲጀመር ሐሳብ አቅርበው እንደነበርም ይታወሳል፡፡

ነገር ግን ግብፅ እና ሱዳን ኢትዮጵያ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር አቅም ያለው የውሃ ማጠራቀሚያ ታገኛለች የሚል ስጋት ውስጥ የገቡ ሲሆን ይህም ደግሞ የሁለቱን ሀገራት የውሀ አቅርቦት መጠን ይቀንሳል የሚል ፍራቻን ጭሮባቸዋል፡፡

በግብፅ እና በኢትዮጵያ መካከል የዲፕሎማሲያዊ ክርክር በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት ከደረሰ ወዲህ በሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ  እና አቢይ አህመድ መካከል የተደረገው የትናንቱ  ውይይት የመጀመሪያ ነው፡፡

የግድቡ ሙሌት አተገባበር “የውሃ ደህንነትን ፣ የምግብ ዋስትናን እና በአባይ ወንዝ ላይ ሙሉ በሙሉ ጥገኛ የሆኑትን ከ 100 ሚሊዮን በላይ ግብፃውያንን አደጋ ላይ ይጥላል” ሲሉ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰምሃ ሹክሪ ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት ግንቦት 1/2012 ስሞታ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ .

ይህንንም ተከትሎ የኢፌድሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደጉ አንዳርጋቸው ግንቦት 14 ቀን ለፀጥታው ም/ቤት በፃፉት የምላሽ ደብዳቤ “ግብፅ በግድቡ ግንባታና የሙሌቱ ሂደት ላይ እንቅፋት እየፈጠረች” ነው ሲሉ ክስ ሰንዝረዋል፡፡

አቶ አንዳርጋቸውም ጨምረው “ኢትዮጵያ ግድቡን ለመሙላት ግብፅን ይሁንታ የመጠበቅ የሕግ ግዴታ የለባትም” ሲሉ ለምክር ቤቱ አስታውቀዋል፡፡

ግብፅ በአሜሪካ የግምጃ ቤት ዲፓርትመንት ያቀረበውንው የስምምነት ረቂቅ ኢትዮጵያ እንድትደግፍ እንደምትፈልግ የሚታወቅ ነው፡፡

ነገር ግን ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተደረጉትን እነዚህን ውይይቶች አቋርጣ ማንኛውንም ስምምነት ላይ ከመድረስ መቆጠቧ የሚዘነጋ አይደለም፡፡

ካይሮ ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት ያስገባችው ጠንከር ባሉ ቃላቶች የተሞላው ደብዳቤም የግዱቡን አሞላልና አለቃቀቅ ጉዳይ እንደ አዲስ ወደውዝግብ እንዳይመልሰውም እየተፈራ ይገኛል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com