የእለት ዜና

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በዘጠኝ ወራት 30 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር አገበያየ

• ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 20 በመቶ ብልጫ አለው

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 602,823 ቶን ምርት በ30 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በማገበያየት የእቅዱን 97 በመቶ ማሳካቱን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገረው በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ውስጥ 231 ነጥብ 885 ቶን ቡና፣ 211 ነጥብ 772 ቶን ሰሊጥ፣ 69 ነጥብ 760 ቶን አኩሪ አተር፣ 46 ነጥብ 914 ቶን አረንጓዴ ማሾ፣ 39 ነጥብ 286 ቶን ነጭ ቦሎቄ እና 3 ነጥብ 201 ቶን ቀይ ቦሎቄ ማገበያየቱን አስታውቋል።

እንደ ምርት ገበያ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ነጻነት ተስፋዬ ገለጻ፣ ይህ ግብይት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ100 ሺሕ ቶን ብልጫ ወይም 20 በመቶ ብልጫ አለው። ነጻነት ጨምረው እንደገለጹት፣ የተጠቀሱት ምርቶች አጠቃላይ የግብይት ዋጋ 30 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ከእቅዱ የስድስት በመቶ ጭማሪ አለው። ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀርም በኻያ አንድ በመቶ ከፍ ብሏል።

በምርት ስብጥር ሲታይ የቡና ግብይት የእቅዱን ዘጠና ዘጠኝ በመቶ ያሳካ ሲሆን፣ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንፃር ደግሞ ኹለት በመቶ ጭማሪ እንዳለው ምርት ገበያው ለአዲስ ማለዳ ጠቅሷል።

የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አክለውም በሰሊጥ ግብይት በኩል የእቅዱን 75 በመቶ ያህል ሲያገበያይ ይህም ከ2011 ተመሳሳይ ወቅት ጋር አንፃር አራት በመቶ ጭማሪ አሳይቷል በማለት ገልጸዋል።

አያይዘውም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ20 በመቶ ወይም በ100 ሺሕ ቶን ብልጫ ይኑረው እንጂ፣ ነገር ግን ባለፉት ሦስት ወራት የኮሮና ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ በተለይም በምጣኔ ሀብት ዘርፉ ላይ ተፅዕኖ ያሳደረ እንደሚገኝ አውስተዋል። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ባሉ 23 ቅርንጫፎች እስከ አሁን ምርት እየቀረበ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ቀጥለውም በአቅርቦቱ ላይ ምንም ዓይነት ያጋጠመ ችግር አለመኖሩን ጠቅሰው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ጊዜያት ወጥተው የነበሩ የእንቅስቃሴ ገደቦች በሕዝብ መጓጓዣዎች ላይ በመሆኑ እና ምርትን ለገበያ በሚያቀርቡ መኪኖች ላይ ክልከላ አለማድረጉ ጠቅሟል በማለት አስረድተዋል።
እናም የኮሮና ቫይረስ ስርጭቱን ለመቀነስ አስፈላጊው ጥንቃቄ እየተደረገ ግብይቱ በምንም ዓይነት መቆም ስለሌለበት ባለበት ቦታ ተደራሽ እንዲሆን እየተደረገ ነውም ብለዋል።

ወረርሽኙ የምርት አቅርቦት ላይ ይህ ነው የሚባል ተጽዕኖ ባያደርስም፣ ያለው ግብይት ላይ ግን የተወሰነ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል ተብሎ እንደሚገመት ተናግረዋል።
የተደረገውን ጥንቃቄም ሲያነሱ፣ ‹‹የተከሰተው ወረርሽኝ እንዳይዛመት እና እንዳይስፋፋ ምርት ገበያው የራሱን እርምጃ እየወሰደ ነው። ካሉት ቅርንጫፎች ውስጥ በሦስቱ ማለትም ዋና መሥርያ ቤቶችን ጨምሮ ሐዋሳ እና ሁመራ ያሉ ቅርንጫፍ የግብይት ማእከላት የተገበያዮችን ጤንነት በመጠበቅ፣ ከመጋቢት 17/2012 ጀምሮ በፈረቃ ተደርጎ ነበር። ገዢዎችም በፈረቃ ማለትም በአንድ አንድ ቀን ልዩነት እንዲጠቀሙ እየተደረገ ነበር።›› በማለት አውስተዋል።

ነጻነት ከዚህ ጋር በተያያ እንዳነሱት፣ በተወሰደው የመፍትሔ እርምጃ በግብይቱ ላይ የተወሰነ መቀነስ በማሳደሩ ምክንያት ተጨማሪ ግብይት ማእከል ከፍተው በዛ ማስተናገድ እና የሚገበያዩ ሰዎች በፈረቃ መምጣታቸውን በማስቀረት በየቀኑ መገበያየት የሚችሉበት ሁኔታ እንዲኖር ተደርጓል። ይህም የተጠቃሚውን ቁጥር በእጥፍ ጨምሮታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 81 ግንቦት 15 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!