የእለት ዜና

ሦስት መልክ የያዘው የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

ሞቅ ቀዝቀዝ፣ ጋል በረድ የሚለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በርካታ ውዝግቦችን በየጊዜው ሲያስተናግድ ከርሟል። ከኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጎን ለጎን ርዕሰ ጉዳይ የሆኑ የፖለቲካ ክስተቶችና ኹነቶችም አሁን ድረስ እየተሰሙ ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል አንደኛው በፌዴራል መንግሥት እና በትግራይ ክልል መካከል የነበሩ የቃላት መወራወሮች ሲሆኑ፣ በትግራይ ክልል የሚታዩና የሚሰሙ ያለመረጋጋት ተያያዥ ጉዳዮችም ተጠቃሽ ናቸው።

ግንቦት ወር የመጀመሪያዎቹ ኹለት ሳምንታት ትግራይ ክልል ለወትሮዋ ከሌሎች ክልሎች አንጻር ሲታይ የነበራትን አንጻራዊ ሰላም ያጣችበት ሰሞን ነው። ይህን በኹለቱ አካት መካከል የነበረውን የቃላት መወራወር ተከትሎ በትግራይ ክልል የታየውን አለመረጋጋት በሚመለከትም፣ የክልሉ መንግሥት የፌዴራሉን መንግሥት እየኮነነ ‹የተጋነነ አይደለም› ሲል፣ በተጓዳኝ የፈዴራሉ መንግሥት ውሳኔ የመስጠት አቅም ማነስ ትግራይን ለዚህ ዳርጓል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ።

በአንጻሩ የክልሉ መንግሥት ጥፋተኛና ተጠያቂ የሚያደረጉም የክልሉ መንግሥት እየተጠቀመ ያለውን ኃይል ይኮንናሉ። የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታም አሳሳቢና እድገትንም የሚያመነምን ነው ሲሉም ስጋታቸውን የሚገልጹ ጥቂት አይደሉም። የአዲስ ማለዳው ኤርምያስ ሙሉጌታ የሚመለከታቸውን የመንግሥት ባለሥልጣናትና ኃላፊዎችን እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በማናገር፣ የተለያዩ ምንጮችን በመጥቀስ ጉዳዩን የሐተታ ዘማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

ባለፉት ዓመታት ይልቁንም ደግሞ ባለፉት ኹለት ዓመታት በሰላም ዕጦት ሥሟ ሲነሳ ያልተሰማው እና እንዲያውም በሰፈነባት አንጻራዊ ሰላም ከኢትዮጵያ ክልሎች በይበልጥ ስትሞካሽ የነበረችው የሰሜናዊት የኢትዮጵያ የክልላዊ ፌደራሊዝም የመጀመሪያዋ፣ ተራ ቁጥር አንድ፣ ትግራይ ከሰሞኑ የለመደችው ሰላም ርቋታል።
በተለይም የመልካም አስተዳደር ዕጦትን የተመለከቱ በስፋት ጥያቄ የተነሳባቸው ጉዳዮች እንደሆኑ እና ከዚህ ቀድሞም ይነገርባቸው እንደነበርና አሁን ደግሞ በወጣቱ ዘንድ ተቀጣጥሎ መውጣቱን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ከትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች ይናገራሉ። በእርግጥ መልካም አስተዳደር ዕጦትን በተመለከተ የተባለውን ያህል ባይሆን እንኳን በክልሉ መኖሩን የትግራይ ክልላዊ መንግሥትም እንደሚያምን የክልሉ መንግሥት የኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ሊያ ካሳ በትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ጣቢያ በመቅረብ ሐሳባቸውን ሲያስተጋቡ ተስተውለዋል።

ይሁን እንጂ አዲስ ማለዳ በቅርበት ጉዳዩን ለመከታተል ባደረገችው ሙከራ በርካታ መረጃዎችን ከስፍራው ማግኘት ችላለች። የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደሚገልጹት፣ ለበርካታ ጊዜያት በተለይም ደግሞ አዲሱ የለውጥ ኃይል ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት በክልሉ መነቃቃት ተፈጥሮ በኅብረተሰቡ ዘንድ ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎች በአፋጣኝ መንገድ ሲመለሱ እንደነበር ይናገራሉ። ነገር ግን ነገሮች በፍጥነት መካሄዳቸውን ኅብረተሰቡም አመስግኖ ሳይጨርስ፣ ከቀድሞው በባሰ ሁኔታ መልካቸውን ቀይረው መምጣታቸውን እና ሕዝቡም ቅሬታውን አፍኖ እንዲቀመጥ መደረግ እንደጀመረ ያወሳሉ።

በትግራይ ክልል የተፈጠረው ምንድነው?
በትግራይ ውስጥ ምን እየተፈጠረ ነው ለሚለው እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ፣ የትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢ ነዋሪዎች፣ በክልሉ መንግሥት እንዲሁም በብልጽግና ፓርቲ እና በክልሉ በሚንቀሳቀሱ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ዘንድ ያለውን ምላሽ አጠናቅራለች።

ሥማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ እና በሽረ እንዳሥላሴ ነዋሪ የሆኑ የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደሚገልጹት፣ ለበርካታ ጊዜያት በመልካም አስተዳደር ዕጦት ነዋሪው ሲሰቃይ መቆየቱን እና በተደጋጋሚም በሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በግንባር ኅብረተሰቡ በመገናኘት ውይይት መካሔዱን ነው። ነገር ግን በጠመንጃ የሚተገበር ምላሽ እንጂ በትክክል ለሚፈልጉት ነገር ምላሽ እንደማይሰጣቸው ይናገራሉ።

‹‹በዚሁ ብሶት ነው የተነሳሳነው። ዛሬ የመጣ ጉዳይ አይደለም፤ በተለይም ደግሞ ከኹለት ዓመታት ወዲህ ጠንክረን ለመውጣት እና ድምጻችንን ለማሰማት ጥረት አደረግን እንጂ ከዚህ ቀደም በነበሩት ዓመታት ድምጻችንን ያላሰማንባቸው ዓመታት አልነበሩም›› ሲሉ ይገልጻሉ። በርካታ ጊዜያት ያልተመለሱት ሕዝባዊ ቅሬታዎች ታዲያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብቅ ብቅ እያሉ መምጣታቸውንም ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

“ፈንቅል“ የሚል እና የሜጀር ጄነራል ሓየሎም አርአያን የትግል ሥም በመያዝ በሓየሎም የትውልድ ስፍራ ዐዲነብርኢድን ጨምሮ በሌሎችም የትግራይ ክልል አካባቢዎች የተነሳው ሕዝባዊ እምቢተኝነት፣ መላው ትግራይን አዳርሶ ሕወሓትንም ከመንበረ ሥልጣኗ ካልፈነቀላት አይመለስም ብለዋል፤ ለውጡን በሕይወታችንም ቢሆን ለውጠን እናገኘዋለን የሚሉ በአካባቢው የሚገኙ የአዲስ ማለዳ ምንጮች።

ለረጅም ጊዜ የቆየው እና በትግራይ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የነበረው የመልካም አስተዳደር ዕጦት ታዲያ ከሰሞኑ በተደረገው እና ከመንግሥት ወገን በተወሰደው እርምጃ አንድ ደረጃ ከፍ እንዲል አድርጎታል የሚሉም የትግራይ ክልል በአዲግራት እና በመቐለ የሚገኙ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ገልጸዋል።

ምንጮች ጨምረው እንደሚገልጹት፣ ከዚህ ቀደም ባሉት ጊዜያት ምናልባትም ከወራት እምብዛም በማይዘለው ጊዜ ከመቐለ በአጭር ርቀት ላይ በምትገኘው ሳምራት በምትባል ስፍራ ከኅብረተሰቡ የተነሳው ጥያቄ ለረጅም ጊዜ ምላሽ አጥቶ የቆየ በመሆኑ ወደ መቐለ የሚያስገባው መንገድ ለቀናት ዝግ ሆኖ መሰንበቱን እና ልዩ ኃይሉም በግድ እንዲከፈት እንዳደረገው ጨምረው ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በመቐለ በቅርቡ በክልሉ ልዩ ኃይል የፖሊስ አባላት ተወሰደ የተባለው እርምጃ ይጠቀሳል። በዚህም ‹በከተማው ተሰብስበው ጠላ ሲጠጡ ተገኝተዋል፤ በዚህም መሰረት በክልሉ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተላልፈዋል› በሚል አንድ ወጣት ተገድሎ ኹለት ሰዎች የቆሰሉ ቢሆንም፣ ከቆሰሉት ኹለት ሰዎች ውስጥም አንደኛው በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ግንቦት 15/2012 ሕይወቱ ማለፉን አዲስ ማለዳ ከስፍራው አረጋግጣለች።

ምንጮች እንደሚሉት ታድያ ግለሰቡን ለመግደል የሚያበቃ ምንም ምክንያት እንዳልነበረ እና አዋጁን ተላልፈውም ከሆነ በእስር ወይም በገንዘብ ቅጣት መታለፍ የሚገባው ጉዳይ ነው። በሰው ልጅ ክቡር ሕይወት ላይ እንዲህ አይነት ጭካኔ እርምጃ መውሰድ አይገባም፣ አግባብነትም የለውም ሲሉ ተናግረዋል። አያይዘውም በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ፣ በስፍራው ሌሎች ሰዎች ቢኖሩም የተገደለው ወጣት ላይ ልዩ ኃይሎች የተለየ ትኩረት በማድረግ ከተሰበሰቡበት ሲበትኗቸው በጸባይ ተነስቶ ሊሄድ ሲል ተኩሰው እንደገደሉት ነው።

ይህንንም ተከትሎ በአካባቢው የነበሩ ወጣቶችም ሆኑ በሌላ አካባቢ ጉዳዩን የሰሙ ሰዎች በስፍራው ተሰባስበው ተገኝተዋል። ከልጁ መገደል በኋላም ሌሎች ተይዘው ወደ ጣቢያ ከመወሰዳቸው ጋር ተያይዞ ‹ልጆቹ ይለቀቁ› የሚል ቁጣ የቀላቀለ ጥያቄ እንዳሰሙ እና በፖሊስ ኃይል እንደተበተኑ ታውቋል።

በትግራይ እየሆነ ያለውን አለመረጋጋት እና በተለይም ደግሞ በሕወሓት ላይ ከወጣቶች ዘንድ የሚነሳውን ተቃውሞ በተመለከተ የብልጽግና ፓርቲ የትግራይ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ነብዩ ስሑል ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ስልክ ቆይታ እንደተናገሩት ‹‹መጀመሪያ ከትግራይ ሕዝብ ታሪክ መነሳት ይኖርብናል፤ ሕዝቡ ጠያቂ ሕዝብ ነው። ይህን ስንል ሌላው ሕዝብ አይጠይቅም ማለት አይደለም›› ሲሉ ይጀምራሉ።

አያይዘውም በክልሉ የቆየ እንቅስቃሴ መኖሩን እና በተለይም ደግሞ በወጣቶች ዘንድ ያለው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ መምጣቱንም ያስረዳሉ። ‹‹ሕዝቡ ለውጥ ከመፈለጉ እና የተሻለ ስርዓትን ከመሻቱም በላይ ሕወሓትን አምርሮ መገላገል እንደሚፈልግ ይታወቃል።›› ብለዋል።

አክለውም እንዲህ አሉ፤ ‹‹መጀመሪያ ጥያቄዎቹ ሕወሓት አሰራሩን እንዲያሻሽል ከሕዝቡ ጥያቄ ቀርቦለት ነበር። ነገር ግን ማሻሻል አልቻለም። ስለዚህ እንዲቀየር ከፍተኛ ግፊት ማሳደር ጀመረ፤ ሕዝቡ። በአሁኑ ሰዓት የትግራይ ሕዝብ እያንጸባረቀ የሚገኘው ነገር ሕወሓት ከአሁን በኋላ መንግሥት ሆኖ ማንንም ማስተዳደር የማይችልበት ደረጃ ላይ እንዳለ እና በአዲስ ሐሳብ እና በአዲስ ትውልድ መቀየር እንዳለበት እየተናገረ ነው ያለው።

እንዲያውም የማእከላዊ መንግሥቱ በቂ የሆነ ትኩረት ስላልሰጠው ነው እንጂ ከዚህ በፊት የነበሩ ናቸው። አንድ ዓመት እና ኹለት ዓመት ወደ ኋላ ብንሄድ እንዲህ ያለ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። እናም አሁን ትኩረት ስለተሰጠው አዲስ መሰለ እንጂ ወጣቶች እንቅስቃሴ በተለይም ደግሞ ‹ፈንቅል› የሚለው ቡድን ከዚህ ቀደም የነበረ እና የሚደግፈው ስላልነበረ የተዳከመ የመሰለ እንቅስቃሴ ነው። እኛም ወደ ብልጽግና ስንመጣ ሕዝባችን የትግራይን ጥቅም እና አጀንዳ ይዘን ነው የመጣነው። ሕዝባችን እንዲሰማም እንፈልጋለን›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ነብዩ ቀጥለውም በተለያዩ አካባቢዎች እንቅስቃሴው መቀጣጠል እና ለውጥ መፈለግ ከዚህ በኋላ ወደ ኋላ ይመለሳል ብለው እንደማያስቡ እና በተለይም ደግሞ ከሕወሓት ወገን የሚወሰደው አሰራር ከዘመኑ ጋር የሚሄድ ባለመሆኑ ሊወገድ የሚገባው እንደሆነም ያወሳሉ።

‹‹ሕዝቡ ለውጥ ይፈልጋል ሕወሓት ደግሞ ለዚህ ኹሉ የሕዝብ ጥያቄ መልስ መስጠት እና የሥልጣን ዘመኑን ማስቀጠል የሚችልበት ሁኔታ ላይ አይደለም ያለው። ከዚህ በኋላ ምንም ተስፋ የለም። ከዜሮ በታች ያለ ተስፋ ነው ያለው። ስለዚህ መተካት ይኖርበታል። በዚህም ረገድ ብልጽግና የተሻለ ቦታ አለው። እኛ ወጣቶች ነን፣ የተሻለ ሐሳብ፣ የተሻለ የአገር አንድነት አለን። ስለዚህ የሕዝብ ችግር መፈታት አለበት። ሕወሓት ደግሞ መፍታት አቅም የለውም። ስለዚህ ሌላ መፍታት የሚችል አካል መምጣት አለበት›› ሲሉ ያክላሉ።

አዲስ ማለዳ ቀጣዩን የትግራይን ዕጣ ፋንታ እና ክልሉ በቀጣይ ሊኖረው የሚችለውን መልክ ምን እንደሚመስል ላቀረበችው ጥያቄ፣ ነብዩ ምላሽ ሲሰጡ ‹‹ኢሕአዴግ ይወድቃል ብሎ የገመተ አልነበረም። በአጭር ጊዜ በሰላማዊ መንገድ ሕዝቡን አሳምነን ሕዝቡ የሚፈልገውን ነገር አሟልተን፣ ሕዝቡ ይብቃህ ሲለው ሕወሓትም ያበቃለታል። ምክንያቱም መላው ኢትዮጵያ ሕዝብ በቃህ ሲለው እኮ አብቅቶለታል። ስለዚህ የክልሉ መጻኢ ዕድልም ብሩህ ይሆናል።

አገራዊ ለውጡም ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ይሆናል ብለን ነው የምናምነው። ምክንያቱም ለውጡ አገራዊ ነው። ትግራይም የኢትዮጵያ ክፍል ነው። ለውጡ ከየትኛውም አካባቢ ቢመጣ ማክበር ስለሚኖርብን እውቅና እየሰጠን እና እየተደጋገፍን ለለውጡ ተግባራዊነት መትጋት ይኖርብናል። በየሚዲያው የምትሰማው ሽለላ እና ቀረርቶ የሚያሳስብ አይደለም። በሰላም የሚፈታ ጉዳይ ነው›› ሲሉ ምላሻቸውን ይሰጣሉ።

በቅርቡ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት መናገሻ ውስጥ ስለተፈጠረው እና የአንድ ሰው ነፍስ ወዲያው ሲጠፋ ሦስት ሰዎች የቆሰሉበት (ከቀናት በኋላ ቆስሎ የነበረው ግለሰብ ሕይወቱ ቢያልፍም) ሁኔታ በተመለከተ ነብዩ ምላሽ ሲሰጡ ‹‹በእርግጥ ወጣቶቹ እንደተባለው ጠላ ሲጠጡ እንደነበር መረጃው አለኝ። ነገር ግን መዋያ የሌላቸው እና አካባቢውም ከጠላ ባለፈ ስፖርትም የሚሠሩበት አካባቢ በመሆኑ ወጣቶች በስፋት ይስተዋሉበታል። ነገር ግን የተገደለው ልጅ እንደሌሎች ወጣቶች ለውጥን አጥብቆ ይፈልግ የነበረ እና ጠንካራ ወጣት ስለነበረ ነው። ይህ ደግሞ የግል ጉዳይ ሳይሆን ሆን ተብሎ የትግራይ ወጣቶችን ለማሸማቀቅ እና ለማስፈራራት የተወሰደ እርምጃ ነው›› ሲሉ ሐሳባቸውን ይሰነዝራሉ።

ነብዩ አያይዘውም በሐውዜን ከተማ ተፈጠረ ስለተባለው እና ‹‹እኔም ትግራይም ለዚህ አልነበረም የታገልነው›› የሚል ንግግር አድርገው ራሳቸውን አቃጥለው ሕይወታቸውን ስላጠፉት ግለሰብም አዲስ ማለዳ ጥያቄ አቅርባ ነበር። በእርግጥ የተከሰተው ክስተት የሚያሳዝን ሲሆን ግለሰቡ በሕወሓት ብልሹ አሰራር ዘመናቸውን ሙሉ ሲበሳጩ እንደኖሩ እና እየባሰ መምጣቱን ተከትሎ የወሰዱት እርምጃ እንደሆነ አብራርተዋል።

‹‹ስለ ትክክለኛነቱ በመጀመሪያ ደረጃ የአብረሓ ደስታ ምንጮች ናቸው መረጃውን የነገሩት። ከዛም አብረሃ በትግረኛ በግሉ የፌስ ቡክ ገጹ ላይ አሰፈረው። ከዛም እኛም ሌሎችም ተቀባበልነው። ግለሰቡ ራሳቸውን ባጠፉበት ወቅት የተነሱ ምስሎች ቢኖሩም አግባብ ባለመሆናቸው በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ልናጋራቸው አልቻልንም። ነገር ግን በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ የነበረውን ክስተት ማጋራት እንዲቻል አድርገናል›› ሲሉ ምላሻቸውን ገልጸዋል።

ትግራይን እያስተዳደረ የሚገኘው ሕወሓት ምን ያህል አምባገነን መሆኑን ለመረዳት በክልሉ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ከክልሉ እንዳይወጡ በማድረግ እና ቀሪው ኢትዮጵያ ክፍል እንዳያውቃቸው የሚደረጉ መታፈኖች ናቸው ዋነኛው መገለጫዎቹ የሚሉት ነብዩ፣ መረጃዎች ሕዝብ ዘንድ አለመድረሳቸው ከፍተኛ ጉዳት እንዳለው ይናገራሉ።

ነብዩ ስሑል ይህን ይበሉ እንጂ የክልሉ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ባወጣው መግለጫ ተፈጠረ የተባለው ግጭት ከመንደር ግርግር ያለፈ እንዳልሆነ እና በአሉባልታዎች የተሞላ እንደሆነ እና በተለይም ደግሞ በአገር ውስጥ የሚገኙ የመንግሥት እና የፓርቲ ሚዲያዎችን ሥም በመጥቀስ አሉባልታ እያሰራጩ ናቸው በማለት ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ መግባታቸውንም ተናግረዋል።

በመግለጫው እንደተገለጸው ‹‹በእነዚህ በአንድ ሳምባ የሚተነፍሱ ሚዲያዎች በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የፀጥታ መደፍረስ መፈጠሩ ተገለፀ። በተለያዩ አካባቢዎች ማለትም በሽረ እንዳሥላሴ እና በአካባቢው፣ እንዲሁም በዋጅራትና አካባቢው ሰለማዊ ሰልፎች ተካሄዱ። ፍትህ መጓደል አለ ወዘተ። ስለዚህ ይህ ችግር ወደ ከፋ ደረጀ ከመሸጋገሩ በፊት የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ጠየቁ በማለት፣ እንዲሆንላቸው የሚመኙትን ቅዠት፣ ራሳቸው ፈብርከው ሐሰተኛ፣ የበሬ ወለደ ወሬ አሰራጭቷል።›› ሲል ያትታል። ይህን በሚመለከት የክልሉ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ሊያ ካሳ ከአዲስ ማለዳ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፣ በክልሉ መንግሥት በይፋ የተሰጠው መግለጫ በቂ እንደሆነ እና ኹሉንም እንደወረደ መጠቀም እንደሚቻል ገልጸዋል።

ሊያ አያይዘውም ፌዴራል መንግሥት አገርን ሉዐላዊነት እና የሕዝብን ጥቅም ከውጭ ኃይላት ጋር በመደራደር እየሸጠ ስለሆነ የትግራይን የሰሞኑ አለመረጋጋቶችን በማጋጋል የሕዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ለመቀየር የተሠራ ሥራ ነው ሲሉም ተናግረዋል። በተለይም ደግሞ በትግራይ ቴሌቪዥን የትግረኛው ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት ሊያ፣ የመልካም አስተዳድር ችግሮችን ለመፍታት የክልሉ መንግሥት በጥልቀት እየሠራ እንደሆነ እና ኹሉም ነገር ከቀበሌ ጀምሮ የመልካም አስተዳደር እንዲሰፍን እየተሠራ ይገኛል፣ በወረዳዎችም አመራሮች ራሳቸው እንዲመርጡ ነው እየተሠራ የሚገኘው ሲሉ ተናግረዋል።

‹‹ከየአገራቱ ጋር እየተካሄዱ ያሉትን ውይይቶችም ግልፅ አይደሉም። ከውጭ አገራት የማይታወቁ ስምምነቶች እየተደረጉ ናቸው። ምንጩ የማይታወቅ ገንዘብም ለመንግሥት ተሰጥቶታል።›› ሲሉም በቀረቡበት የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ መናገራቸው ይታወሳል።

በክልሉ ይህን ያህል የጎላ ችግር እንደሌለ እና የተባሉ ችግሮችን ከቴሌቪዥን እንደሰሙ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በሽረ ከተማ የሚኖሩ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል። በአንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ የሚሠራ እና ሥሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አስተያየት ሰጪ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገረው፣ አባቱ እና እህቶቹ ከአዲስ አበባ ደውለው ያለውን ችግር እንደነገሩት እና በስፍራው የሚኖረው እሱ ግን ምንም የሚያውቀው ጉዳይ እንዳልነበር ተናግሯል።

‹‹እውነት ለመናገር ምንም አይነት ብጥብጥ እና ግርግር አላየሁም። እንዲያውም ከአሁኑ ይልቅ ከየካቲት 11 በፊት የተወሰነ አለመረጋጋት እንደነበር ነው የማውቀው። የአሁኑ ጉዳይ ግን እውነት ለመናገር ምንም አይነት ግርግር የለም›› ሲል አስተያየት ሰጥቷል። ይኸው የአዲስ ማለዳ ምንጭ እንደሚለው፣ በክልሉ የመልካም አስተዳደር እጦት እንደሚስተዋል በርካታ ጊዜያትም ሕዝቡ ጥያቄዎችን በማንሳት ወደ መንግሥት አቅርቦ ነበር። መንግሥትም ጉዳዩን ተቀብሎ እየሠራበት እንደሆነ እና ምላሽ እስኪሰጥም እየተጠበቀ መሆኑን አውስተዋል።

ይሁን እንጂ በተለያዩ ሚዲያዎች የሚስተዋለው እና የሚሰሙ ዜናዎች ከፍተኛ ውዥንብር እንዳይፈጥሩ መጠንቀቅ እንደሚገባ አስታውሰዋል። ‹‹እኔ በምኖርበት ሽረ ከሥራ መቆም ጋር ተያይዞ በርካታ ሰው ቤት ውስጥ ነው የሚያሳልፈው። በእርግጥ አንዳንድ ወጣቶች እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ሁኔታውን ችላ በማለት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴም ያደርጋሉ። ነገር ግን እንደ ተባለው ወጣቶች ተደራጅተው ይህን የሚያክል ጫና ማድረሳቸውን ግን በእርግጥ እውቀቱ የለኝም። ሽረ ጠባብ ከተማ ናት። እንኳን ሽረ አዲስ አበባ እንኳን እንደዚህ እንደተባለው አይነት ችግር ቢፈጠር በቅጽበት ነው ወሬው የሚዳረሰው። ስለዚህ ሽረ ውስጥ ምንም አይነት ግርግር አልተፈጠረም። ምናልባት እንግዲህ ወጣቶች እርስ በርስ ተጋጭተው ከሆነ እና እሱ ተጋኖ ቀርቦ ከሆነ ሌላ ጉዳይ ነው›› ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል።

በአዲ ነብርኢድ ተነሳ ስለተባለው ጉዳይም ቢሆን አስተያየት ሰጪው ሲናገሩ፣ ከሽረ እምብዛም የሚርቅ ባለመሆኑ የሚደረገው እንቅስቃሴም በአጭር ጊዜ ሽረን ብቻ ሳይሆን መላው ትግራይን ሊያዳርስ የሚችል ጉዳይ ለመሆኑ አይጠራጠሩም።

ከዚህ በተቃራኒው የሚነሱ ሐሳቦች አሉ። በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሰው የአረና ትግራይ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አምዶም ገብረሥላሴ ጋር አዲስ ማለዳ በጉዳዩ አጠር ያለ ቆይታ አድርጋ ነበር። በዚህም ቆይታ አምዶም ለአዲስ ማለዳ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፤
‹‹በአሁኑ ሰዓት በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች የቆዩ እና አዳዲስ ጥያቄዎች ከሕዝቡ በኩል እየተነሱ ነው የሚገኙት። የክልሉ መንግሥትም የሚነሱትን ጥያቄዎች የመመለስ አቅም ላይ አይደለም ያለው። በተለይም ደግሞ በቅርቡ በመቐለ ከተማ 05 ቀበሌ አንድን ወጣት ገድለው ተጨማሪ ሦስት ወጣቶችን ያቆሰሉበት የፖሊስ እርምጃን ተከትሎ ነገሮች እየተካረሩ መጥተዋል። ከዚህም በተጨማሪ በትግራይ ሰሜን ምዕራብ አካባቢ ባድመ እና ሽረ አካባቢ ሕዝቡ ወረዳነት ጥያቄ አቅርቦ የነበረ ሲሆን፣ ተመልሷል ተብሎ እንደነበር ነው መንግሥት የሚናገረው የነበረው። ከዚህም በላይ አስተዳዳሪዎች ከዞን እና ከክልል ነበር ተመልምለው የሚላኩለት። በዚህም ሳቢያ ኅብረተሰቡ ጠንካራ የሆነ ተቃውሞ እና ሰላማዊ ሰልፍ አካሒዷል››

ከዚህም በተጨማሪ አምዶም ሲቀጥሉ በተለያዩ ስፍራዎች የሰላማዊ ሰልፍ ይካሄድ እንጂ በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ መንገድ እስከ መዝጋትም እንደተደረሰ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ወደ ምዕራባዊ ክፍል ወደ ዳንሻ የሚወስደው መንገድ ሙሉ በሙሉ የተዘጋ ሲሆን፣ ‹‹ሕዝቡም መንግሥት ጥያቄዎቻችንን የሚመልስበት አቅም ላይ ባለመሆኑ በዚህ መንገድ ልንታገለው ይገባል የሚል እርምጃ እየወሰደ እንደሆነ ነው የሚናገሩት›› ይላሉ።

ሕዝባዊ እምቢተኝነት እና እንቅስቃሴው ከተጀመረ ከኹለተኛው ቀን በኋላ ትኩረታቸውን እንደሳባቸው የሚገልጹት አምዶም፣ እንደ እርሳቸው አጠራር በሕወሓት ዘንድ ገንዘብ እየተቆረጠላቸው አክቲቪስት ሥራ የሚሠሩትም ቢሆኑ የሕዝብ ድምጽ ስለሆነ ሊሰማ ይገባል የሚል አቋም ይዘው ሲንቀሳቀሱ እንደነበርም ጨምረው ገልጸዋል። ይሁን እንጂ የክልሉ ሚዲያዎች የመሐል አገር ሚዲያዎች ሲዘግቡት መነሳሳት እንዳደረባቸው አምዶም ጨምረው ጠቅሰዋል።

አምዶም በተመሳሳይ ደግሞ ጨርቸር በተባለ ስፍራ ስለተከሰተው እና ይህ ጽሑፍ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ የተቀጣጠለ ሕዝባዊ እምቢተኝነት መኖሩንም ለአዲስ ማለዳ ጨምረው ገልጸዋል። ‹‹ጨርጨር በተባለ ስፍራ የወረዳነት ጥያቄ እና ሌሎች ጥያቄዎችን ተከትሎ ሕወሓት ጥያቄዎችን የማይመልስልን በመሆኑ ከአሁን በኋላ በሕወሓት ስር አንተዳደርም በሚል ራሱ በአካባቢው ኅብረተሰቡ በመረጣቸው ሰዎች እየተዳደረ ይገኛል። በዚህ አካባቢ ጌታቸው ረዳ ከአንድ የሕወሓት አመራር ጋር በመሆን ሄደው ያወያዩ ሲሆን፣ የጥያቄያቸውን መልስ ከመስጠት ይልቅ ልዩ ኃይል ልከው ጥያቄውን ዝም ማስባል ነበር የመረጡት አካሔድ። ነገር ግን ጦርነት ለመግጠም ብትፈልጉም እኛ ግን አንዋጋም በሚል ልዩ ኃይሉን ተመልሶ እንዲሄድ አድርጓል›› ሲሉ አምዶም ይናገራሉ።

ከጨርጨር ባለፈ ወጅራት በተባለ አካባቢም ኅብረተሰቡ ሕወሓትን በግልጽ ከጎኑ እንዳልሆነ እና በአካባቢው ያለው ኅብረተሰብ የራሱ የሚለው እና የሚወክለው ፓርቲ መኖሩን በመግለጽ፣ ከአስተዳደራዊ መዋቅሩ እንዲነሳለት የጠየቀበት አግባብ መኖሩንም አምዶም ጨምረው ገልጸዋል።

ሕዝባዊ እምቢተኝነት በትግራይ ውስጥ አለ ወይም የለም በሚሉ ጎራዎች መካከል ሦስተኛ ሐሳብ ያላቸው እና የትግራይን መጻኢ ዕድል እና ዕጣ ፋንታ በሚመለከት እንቅልፍ የነሳቸው የቀድሞ የሕወሓት ነባር ታጋዮች ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል። ከሚኖሩበት አካባቢ እና ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ከፍተኛ ጫና እንዳይደርስባቸው በሚል ሥማቸውን ከመጥቀስ የተቆጠቡት ምንጮች ‹‹በሕወሓት እና በፌዴራል መንግሥት መካከል ያለው መካረር ሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል አያጠራጥርም። በመጀመሪያ ደረጃ የፌዴራል መንግሥቱ ሥልጣን ይዣለሁ ብሎ ካሰበ እና ኢትዮጵያን የመምራት ችሎታ አለኝ ብሎ መንበሩን ከያዘ በትግራይ ያለውን የተለየ ሐሳብ እና ከሕግ ውጭ የሆነ አካሔድ አስቸኳይ መፍትሄ መስጠት ይኖርበት ነበር።

ነገር ግን ይህ ባልሆነበት ሁኔታ በቅርቡ የተከሰተው በክልሉ የሚታየው አለመረጋጋት እንደቀደመው ትግራይን አድቅቋት እንደሚሄድ አልጠራጠርም። የሚናፈቀው ልማት እና ዕድገት ትግራይ ላይ ሊጓተት ምናልባትም ሊቆም የሚችልበት አዝማሚያው ከፍተኛ ነው። ብቻ የትግራይ መጻኢ ሁኔታ እጅግ መገመት የሚያዳግት እና ውስብስብ ነው። ነገር ግን እንደ አገር አስተዳዳሪ የፌዴራሉ መንግሥት በክልሉ መንግሥት ያልተመለሰውን ችግር የመፍታት ግዴታ ሳይኖርበት የሚቀር አይመስለኝም›› ሲሉ ይናገራሉ።

አዲስ ማለዳ ለዚህ ጽሑፍ ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችን ስታሰባስብ ካናገረቻቸው ትግራይ ክልል ነዋሪዎች እና በአዲስ አበባ የሚገኙ ትግራይ ክልል ተወላጆች አሁንም በሕወሓት እና በሕዝቡ መካከል ያለው መካረር ወይም አለመካረር ሳይሆን ይህ ነባራዊ ሁኔታ ግን ነገ ክልሉን እንዴት አይነት መልክ እንዲይዝ እና ከታቀደው የእድገት ጎዳናም ላያስቀረው የሚችልበት ምንም አይነት ምክንያት እንደማይኖር ስጋታቸው ነው።

በክልሉ አሁንም እምቢተኝነቱ ካለው የወጣ ሥራ አጥነት ጋር ተዳምሮ ከፍተኛ ሆነ ለሕግ ተገዢ አለመሆን እና ስርዓት አልበኝነት እንደማይከሰት ማስተማመኛ እንደሌላቸው ስጋታቸውን በአንድ ድምጽ ለአዲስ ማለዳ ይናገራሉ። ምናልባትም እስከ አሁን የተሔደበት መንገድ ትክክልም ሆነ አልሆነ፣ ብቻ ክልሉ እዚህ ድረስ መድረሱን እና ነገር ግን ከዚህ በኋላ ከሕወሓትም ጋር ሆነ ከሕወሓት ውጭ ክልሉ ምን ሊመስል ይችላል የሚል የጠራ ምስል ማግኘት እንደሚቸግራቸውም አልሸሸጉም።

ከጥያቄዎች መነሳት ጋር ተያይዞም ለቀናት በርካታ ሰዎች ተቃውሟቸውን ገልጸውበታል። መንገድ ዘግተዋል ከተባሉባቸው አካባቢዎች ውስጥ ማይ ሓንሰ የተባለ ስፍራ ነዋሪዎች ከመንግሥት ጋር በሰላማዊ መንገድ ለመነጋገር መግባባታቸውን ቢቢሲ የአማርኛው ዝግጅት ክፍል አስታውቋል። ቢቢሲ በዘገባው በትግራይ ክልል የሰሜን ምዕራብ ወረዳ ቀበሌ ማይ ሓንሰ ነዋሪዎች ከተማይቱ የወረዳው ማእከል እንድትሆን ሲጠይቁ መሰንበታቸው ሲዘገብ መቆየቱን አውስቶ፣ ‹‹የክልሉ መንግሥት መፍትሄ ይስጠን›› በሚልም ለአንድ ሳምንት መንገድ ዘግተው የነበረ ሲሆን፣ ነዋሪዎቹ የክልሉ መንግሥት ቀርቦ ጥያቄያቸው እንዲሰማቸው ጠይቀው ነበር።
በዚህ መሰረት በነዋሪዎቹና በመንግሥት አካላት መካከል በተደረገው ውይይት መንገዱን እንዲከፍቱና ጥያቄያቸውን በሕጋዊ መንገድ ለማቅረብ መስማማታቸውን የወረዳው አስተዳደር ሀብቶም አበራን ዋቢ አድርጎ አረጋግጧል። በዘገባውም ነዋሪዎቹ ጥያቄያቸው ለክልሉ መንግሥት የሚያቀርብላቸው 14 አባላት ያሉት ኮሚቴ ማቋቋማቸውም ተገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 82 ግንቦት 22 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!