በዘመነ ኮሮና – መልክ ያጣው ትምህርት አሰጣጥ

Views: 407

ኤርሚያስ በለጠ የአዲስ አበባ ነዋሪ ሲሆን፣ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ ነው። ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረገው ቆይታ ዘንድሮ (2012) ተመራቂ እንደሆነና ልምምድ (apparent) ላይ እንደነበር ጠቅሷል። ከዛም ጎን ለጎን የመመረቂያ ጽሑፍ ለማዘጋጀት ከጓደኞቹ ጋር እየተዘጋጀ እንደነበር አስታውሶ፤ ይሁን እንጂ መጋቢት 03/2012 የመጀመሪያው የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ታማሚ በኢትዮጵያ መገኘቱን ተከትሎ ነገሮች እንዳልነበሩ ሆኑ ይላል። የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር በተደረጉ የእንቅስቃሴ ገደቦ ምክንያትም፣ ከጥናት አማካሪ መምህራኖቻቸው ጋር በኢንተርኔት አልያም በስልክ ብቻ እንደሚናገሩ አንስቷል።

ኤርምያስ ምንም እንኳ አዲስ አበባ በመሆኑ በአንጻራዊነት የኢንተርኔት አገልግሎትን ማግኘትና ከመምህራኑ ጋር በኢንተርኔት መገናኘት ቢችልም፣ ኢንተርኔት በቀላሉ የማይገኝባቸው ቦታዎች ያሉ ተማሪዎች ነገር ያሳስበዋል። በቴሌግራም በተከፈተ መገናኛ አውድ ላይም በንቃት የማይሳተፉ እንዳሉና የሚገናኙት የተወሰኑ ተማሪዎች ብቻ መሆናቸውን ተናግሯል። ከዛም በተጨማሪ ቀጥሎ ምን ይመጣል? የውጤት አሰጣጥ ሂደቱ ምን ሊሆን ነው? የሚለው ኤርምያስን ጨምሮ የተማሪዎች ሁሉ ጭንቀት ሆኗል።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮምዩኒኬሽን ዘርፍ ኃላፊ እንግዳወርቅ ፈለቀ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ አሁን ባለው ሁኔታ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎች የትምህርት አሰጣጥ ሂደት ቆሟል። ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ ቀጥተኛ ባለሆነ መልኩ ከተማሪዎቻቸው ጋር ተገናኝተው እውቀትና መረጃ የመለዋወጥ ነገር በአንዳንድ የጊቢው አስተማሪዎች መኖሩን ከትዝብታቸው ጠቅሰዋል።

‹‹እኔ በበኩሌ ግን መደበኛ ትምህርት ከቆመ በኋላ ከተማሪዎቼ ጋር ተገናኝቼ አላውቅም።›› ያሉት እንግዳወርቅ፣ ለዚህም ምክንያታቸው አብዛኛው ተማሪ የኢንተርኔት አገልግሎት ስለማያገኝ በሚደረገው ኢንተርኔትን መሠረት ያደረገ መረጃና እውቀት ልውውጥ ላይ ተሳታፊ አይደለም ብለው በማመን ነው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 6 ኪሎ ዋናው ጊቢ የተማሪዎች ተወካይ ለአዲስ ማለዳ በሰጠችው አስተያየት፣ ትምህርቱ ለኹለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች እና ለማታ ተማሪዎች እየቀጠለ እንዳለ ገልፃለች። ቢሆንም ዩኒቨርሲቲው ያስቀመጠውን የመማር ማስተማር ማስኬጃ ምርጫዎች በማንሳት፣ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ሊሄድ የማይችል ነው ስትል ታነሳለች።

በተመሳሳይ በዘንድሮው ዓመት የ2012 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኹለተኛ ዲግሪ ተመራቂ የሆነ የአዲስ ማለዳ ምንጭ እንደገለፀው፣ ወቅታዊ ሁኔታውን ያገናዘበ ካለመሆኑም በላይ ውሳኔው እንደገና ሊጤን ይገባል ብሏል። የመመረቂያ ጽሑፉን ቤት ውስጥ ለመጨረስ እንደሚከብድ እና የኹሉም ተመራቂ ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሑፍ በአንድ ዓይነት መልኩ ሊሄድ የማይችል በመሆኑ ከባድ ውሳኔ ነው የሆነብንም ሲል አክሏል። ከዛም በተጨማሪ የሚቀርበውን የመመረቂያ ጽሑፍ በየትኛውም ጊዜ ገምግሞ ውጤት ለመስጠት የሚያስችል አይደለም፤ እንደ አስተያየት ሰጪው ሐሳብ።

የአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የተከታታይና ርቀት ትምህርት ቢሮ ከዚህ ቀደም ለተማሪዎቹ ባወጣው ማስታወቂያ፣ በማታና በርቀት ትምህርታችውን ለሚከታተሉ የቅድመ-ምረቃና ድኅረ-ምረቃ ተማሪዎች በየትምህርት ክፍሎቹ ከተመደቡላቸው አስተማሪዎች እና አማካሪዎች ጋር አማራጭ የመገናኛ መንገዶችን በመጠቀም ግንኙነት እንዲያደረጉ ብሏል። በዚህም መንገድ ትምህርት እንዲከታተሉ እና የመመረቂያ ጽሑፍ ሥራዎችን እንዲያዘጋጁ መግለጹም ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ዘንድ መረበሽ መፍጠሩን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማታ ተማሪ እና ዘንድሮ ዓመት ተመራቂ የሆነች የአዲስ ማለዳ ምንጭ ትገልጻለች።
በዩኒቨርሲቲው የውጭ ግንኙነት እና ትብብር ኮምዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ትብብር ዳይሬክተር ደመቀ አቺሳ (ዶ/ር) በጉዳዩ ላይ ቀደም ብሎ የሰጡትን አስተያየት አዲስ ማለዳ በ78ተኛ እትሟ ሽፋን መስጠቷ ይታወሳል። በዛም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ2012 ዓመት በማታ መርሃ ግብር እና በኹለተኛ ዲግሪ የሚማሩ ተመራቂዎችን ሐምሌ 4/2012 ለማስመረቅ ውሳኔ መተላለፉን ገልፀው ነበር።

በተደጋጋሚ ከተማሪዎች ጥያቄ እንደሚነሳ እና ለቅሬታቸውም ደመቀ ምላሽ ሲሰጡ፣ መብራት እና የኢንተርኔት አገልግሎት በማስመረቅም ሆነ በማስተማር ሂደቱ ላይ ተጽዕኖ አለው። ይህንንም ዩኒቨርሲቲው የሚገነዘበው ጉዳይ ነው በማለት አስረድተው ነበር። ነገር ግን ደመቀ ሲናገሩ ዩኒቨርሲቲው ውሳኔውን እንዲወስን ያደረገው የኹለተኛ ዲግሪ እና የማታ ተማሪዎች አብዛኛዎቹ በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ አካባቢ ይሆናሉ በሚል እሳቤ መሆኑን አንስተው ነበር።

ስለ ኢንተርኔት አገልግሎቱ አስተማማኝነት አዲስ ማለዳ ጥያቄ ባነሳችላቸው ጊዜም፣ በተለያዩ ስፍራዎች የሚኖሩ ከሆኑ ለረጅም ጊዜ ሥራቸው እንዳይስተጓጎል በማሰብ የተወሰነ ውሳኔ ስለሆነ፣ ለተወሰነ ጊዜ ጥሩ የኢንተርኔት አገልግሎት ወዳለበት በመሆን ማከናወን እንዲችሉ ታስቦ ነው ብለዋል።

ነጥብ አያያዝ እና መመዘኛን በተመለከተም ከተማሪዎች ከዚህ ቀደም የነበረውን ያህል አቅም እና ውጤት መጠበቅ ባይቻልም፣ ነባራዊ ሁኔታውን አመዛዝኖ የሚኬድበት መንገድ ይኖራልም ብለው ነበር።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ዳኜ ገብሩ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በዘንድሮው የትምህርት ዘመን የስምንተኛ ክፍልን ክልላዊ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች በተመለከተ ፈተና አሰጣጡ እንዴት እና መቼ ይሰጥ የሚለው ጉዳይ ላይ ግን ውሳኔ ላይ መድረስ አለመቻሉ አንስተዋል። ነገር ግን ተማሪዎች ትምህርት የለም ብለው እንዳያስቡ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እየተጠቀሙ ለፈተና እንዲዘጋጁ እያደረጓቸው እንደሆነ አንስተውልናል።

ይሁን እንጂ በዚህ መልኩ የሚሰጡ ትምህርቶች እንደ ከዚህ ቀደሙ የትምህርት ተደራሽነት እና ጥራት ይኖራቸዋል ተባሎ እንደማይታሰብ አልካዱም። እስከ አሁን እያየን ባለነው ከቀን ወደ ቀን የሚከታተሉት የተማሪዎች ብዛት እየጨመረ መምጣቱን ነው። ትምህርቱ በዚህ ሁኔታ መሰጠት ያስፈለገው ትምህርት የለም ተብሎ በስንፍና መዘናጋትና የቸልተኝነት ሁኔታ እንዳይኖር በማሰብ ነው። ወቅቱም የአገር ዐቀፍም ሆነ በክልል ደረጃ የሚደረጉ ፈተናዎች የሚኖሩበት ጊዜ ስለሆነ፣ ለፈተና እንዲዘጋጁ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የሞዴል ፈተናን በቴሌግራም እንዲሰጣቸው ተደርጓል፤ እንደ ዳኜ ማብራሪያ።

አያይዘው እንዳነሱት ‹‹ትምህርት በቤቴ›› በሚለው መርሃ ግብር ተማሪዎች በቤታቸው መሆናቸውን ተከትሎ ምንም እንኳን መጽሐፍት ቢኖሯቸውም ከዛ በተጨማሪ የመምህራን እገዛ ስለሚያስፈልጋቸው በሬዲዮ እንዲሁም በአፍሪ ኸልዝ የቴሌቭዥን ጣቢያ ከ7ኛ እስከ 12ተኛ ክፍል ድርስ ላሉ ተማሪዎች ትምህርቱ እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።

ከዛም በተጨማሪ የተመረጡ የትምህርት ዓይነቶች ደግሞ በቴሌግራም እና በዩትዩብ ቻናሎች እየተከታተሉ እንደሆነና፣ ያም ውጤት ይኖረዋል ብለው እንደሚያስቡ አንስተዋል።

እንደ ምክትል የቢሮ ኃላፊ ገለፃ፣ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ትምህርት ነክ ጉዳዮችን ማስተላለፍ ያስፈለገበት ምክንያት ትምህርት ስርዓቱ እንዳይቋረጥ በማሰብ ነው። ከዛም በተጨማሪ ሞዴል ፈተናውን በቴሌግራም መስጠት ያስፈለገው ተማሪዎቹ ለሚቀጥለው ክልላዊ ፈተና እንዲዘጋጁ ሲሆን፣ ለ12ኛ ክፍሎች ደግሞ ብሔራዊ ፈተና ስላለ ምን ያህል እራሳቸውን አብቅተዋል የሚለውን እራሳቸውን እንዲገመግሙ ለማስቻል ነው።

ነገር ግን ይላሉ ኃላፊው፣ ትምህርት ቢሮው በትክክለኛው ሰዓት እና ጊዜ ሞዴል ፈተናውን በቴሌግራም ቻናል ወደ ተማሪዎች ያደረሰ ቢሆንም፣ ተማሪዎቹ ጋር ግን ለመመለስ ለረጅም ሰዓት እየቆየ ነው ሲሉ ገልፀዋል። ይሄም ካለው የኢንተርኔት አገልግሎት መወሰንም ሊሆን ይችላል ብለዋል።

‹‹እንደኛ ግን ተማሪዎቹ ላይ ግርታ ተፈጥሮ ወይንም በጥልቀት እየመረመሩት ሊሆን እንደሚችል በመገመት፣ ከባድ ብለን ላሰብነው ጥያቄ በአፍሪ ኸልዝ ማብራሪያ እና መልስ እየሰጠን እየደገፍናቸው ነው›› በማለት አክለዋል።

እንደ ዳኜ ገለጻ፣ ይሄ ይደረግ እንጂ ተማሪዎች ራሳቸውን ከማዳበር እና ከመመዘን ባሻገር በቴሌግራም ቻናል የተላለፈው ሞዴል ፈተና ውጤት የሚሰጥበት እንዳልሆነ ተናግረዋል።

‹‹በተጨማሪም ትምህርቱ እና የፈተናው ስርአት ለኹሉም ተደራሽ ይሆናል ወይ›› የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ እየመጣብን ነው ያሉት ዳኜ፣ አሁን የኮሮናን ስርጭት ለመከላከል እና ያለውንም ንክኪ ለመቀነስ ታስቦ ይሄ መደረጉን አስረድተዋል። ‹‹እንደ ቀድሞው ሊሆን አይችልም። ነገር ግን እኛ በራሳችን አብዛኛውን ተማሪ ተደራሽ ለማድረግ እየሠራን ነው።›› ብለዋል።

በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 አካባቢ የሚገኝ ማርች 8 የተባለ ትምህርት ቤት ልጃቸውን የሚያስተምሩ ወላጅ ‹‹የዘንድሮ ፈተና ልጄ እንዴት እንደሚፈተን አላውቅም። እስከ አሁንም ቤት እንዲቀመጡ በታዘዙት መሰረት ቤት ሆኑ እንጂ እያጠኑ አይደለም። የተለያዩ ፈተናዎች እና ትምህርት ነክ ጉዳዮች ይሰጣሉ ይባላል። ልጆቹ ጋር ግን እየደረሰ አይደለም›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እንደ እርሳቸው ገለፃ፣ የዘንድሮ ፈተና እንዴት መዝነው እንደሚያሳልፉም ግልፅ ባለመሆኑ ልጆቹም ጭንቀት ላይ እንደሆኑ እና ቢቻል ተላልፎ ለሚቀጥለው እንደ መደበኛው ተምረው ቢፈተኑ መልካም እንደሆነ አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ተጨማሪም ወረዳ 01 ቃለ-ሕይወት ትምህርት ቤት ነው ልጄ የሚማረው የሚሉት ወላጅ፣ ትምህርት ቤቱ የግል መሆኑን ጠቅሰዋል። ‹‹ልጆቻችን ቤት ውስጥ ስለሚውሉ መንግሥት በሚዲያዎች የሚያስተላልፈውን ትምህርት እንደ ከዚህ ቀደሙ በትኩረት እየተከታተሉ አይደለም። እና ሌላ አማራጭ ወደ መውሰድ ቢኬድ ጥሩ ነው፣ ልጆች እውቀቱንም እያገኙ ለውጤትም መሥራት እንዲችሉ›› በማለት ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ክፍል ኃላፊ የዓለም ሎሬት ጥሩሰው ተፈራ (ፕሮፌሰር)ን አዲስ ማለዳ አነጋግራለች። እርሳቸውም ይሄ ችግር መከሰቱ ብዙ አሉታዊ ተፅዕኖዎች አሉት ብለዋል። ከነዛም መካከልል ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበረሰባዊ ተግዳሮቶች ሲሆኑ በተማሪዎቹ ላይ ደግሞ የሥነ ልቦና ቀውስ እስከማስከተል የሚዘልቅ ተያያዥ ችግሮች ያስከትላል ብለዋል።

በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በኢኮኖሚ ደካማ አገራት እንደዚህ አይነት ችግሮች ሲከሰቱ ጎን ለጎን በቴክኖሎጂ በመታገዝ የችግሩን ከባድ ሚዛን ለማቅለል ስለማይችሉ ከባድ ይሆንባቸዋል።

ነገር ግን አሁን እየተጀመሩ ያሉት እንቅስቃሴዎችን ውጤታማነት ለመመዘን ከፍተኛ የሆነ የዳሰሳ ጥናት በተማሪዎቹ ዘንድ እና ባለው ማኅበረሰብ ዘንድ መደረግ አለበት፣ የሎሬት ጥሩሰው አስተያየት ነው። ቀጥለውም አሉ፤ ‹‹ትምህርት ነክ የሆኑ ማንኛውም አይነት ውሳኔዎች ከመወሰናቸው በፊት በጥሩ ጎኑ እና በተቃራኒ ጎኑ የሚያመጣው ተፅዕኖ መታወቅ ይኖርበታል። በየትኛውም ደረጃ ያሉ ተማሪዎች የመመዘኛ ፈተና ሊወስዱ የሚገባው በቂ ዝግጅት ማድረጋቸው ከተረጋገጠ በኋላ ነው። ነገር ግን አሁን ትምህርት ቤቶች በተዘጉበት ወቅት ምን አይነት ፕሮግራም ነበራቸው፣ የክትትል ሂደቱ እንዴት ነበር? ለምን ያህሉ ተማሪዎች በቅጡ ተደራሽ ይሆነናል? የሚለውን በሚመለከት ዳሰሳ ማድረግ አስፈላጊ ነው።››

በኢንተርኔት የሚደረገውን እና ‹ትምህርት በቤቴ› የሚለው የማስተማር ሂደት ትምህርት ለከተማ ልጆች ብቻ ባለመሆኑ፣ ሊከታተል የሚችለውን ተማሪ በመቶኛ በመለየት መታወቅ ይኖርበታልም ብለዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ ይሄ ባለመታወቁ ምክንያት ብዙ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው ተማሪዎችን ያገለለ ከመሆኑም ባሻገር ውጤታማነታቸውን ለመቀነስ ጉልህ አስተዋፆ ይኖረዋል። ስለዚህም ትምህርት ሚኒስቴር በዋነኛነት አጠቃላይ በክልል ቢሮዎች ጭምር የዳሰሳው ጥናት ተደርጎ ግልፅ የሆነ መረጃ ከሌለ የትምህርት መድረኩ የተወሰኑ ተማሪዎችን ብቻ ነው የሚያስተናግደው በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ያለውን ሁኔታ ያኘሱት ሎሬት ጥሩሰው፣ አንደኛ ዓመት ተማሪዎች ትምህርት ሲከታተሉ አልነበረም። ኹለተኛ ዓመትም እንደዛው። ስለዚህ ማዘዋወር አይቻልም፣ ቦታም አይኖርም። የእነዚህ ሽግግር ወቅትን ጠብቆ ካልተተገበረ ከ12 ተመዝነው የሚመጡ ተማሪዎችን የመቀበያ ቦታም አይኖርም። ከሁሉም በላይ ጥራት ያለው ትምህርት እና ትውልድ ግን ጥያቄ ውስጥ ይገባል ብለዋል።

ስለዚህም እዚህ ላይ ፈጥኖ ወደ ውሳኔ ከመግባት በፊት የትኛው ውሳኔ የተሻለ ይሆናል የሚለው ከተለያዩ ምሁራኖች የተውጣጣ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በመረጃ መረብና ኢንተርኔት ዙሪያ የሚሠሩ ባለሞያዎችንም አካትቶ ከፍተኛ ውይይት መደረግ ይኖርበታል።

አለበለዚያ ግን ለቁጥር እና ሽግግሩን ለመጠበቅ ካልሆነ በስተቀር ጉዳቱ ያመዝናል ብለዋል። ከዛ በተጨማሪ በምዘናው መሰረት አላለፋችሁም የሚባሉት ተማሪዎች ደግሞ ከፍተኛ ተጎጂ የሚሆኑት እነርሱ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ነባራዊ ሁኔታ እንኳን ተማሪዎች መምህራን ባሉበት ቦታ እንኳን በቂ የኢንተርኔት አገልግሎት የላቸውም። በዛም ሳቢያ የተማሪ እና የአስተማሪ ግንኙነት ይገደባል። ‹‹ለምሳሌ እኔ በግሌ የማማክራቸው ተማሪዎች አሉኝ›› ያሉት ሎሬት ጥሩሰው፣ ‹‹ልጆቹ ባህርዳር እና አዲሰ አበባ ናቸው። ነገር ግን ብዙ ጊዜ ተጨናንቀው ነው ሐሳባቸውንም ጥያቄያቸውንም የሚልኩልኝ›› ሲሉ የችግሩን ስፋት አስረድተዋል።

‹‹በዚህ መልኩ የግዴታ መሟላት ያሉባቸው መሠረታዊ ቴክኖሎጂዎች ሳይሟሉ በድሮው ሕግ ፕሮግራም ፈተናውን እናካሂዳለን ማለት ትክክለኛ ውሳኔ አይደለም›› ሲሉ አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ ሰጥተዋል።

በፌዴራል ቴክኒክ እና ሙያ ማሠልጠኛ፣ የሥነ ልቦና መምህር እና አማካሪ አታለል ካሳ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ሐሳብ፣ የትምህርት ስርዓቱን እና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን ማስቀጠል በማይቻልበት ጊዜ ሌሎች አማራጮችን መከተል ያስፈልጋል ብለዋል። አያይዘውም አሁን ያለው ሁኔታ በተማሪዎች ላይ ከሚፈጥረው ሥነልቦናዊ ቀውስ አንፃር ወረርሽኙ እስከ መቼ እንደሚቆይ ስለማይታወቅ፣ በትምህርት መስመር ውስጥ የነበሩት ልጆች ከመስመሩ ይወጣሉ። መልሶ ወደዛ ሂደት ማስገባት እና ውጤታማ ለማድረግ ከባድ ያደርገዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ከዛ ውጪ ግን በትኩረት ሊታይ የሚገባው 85 በመቶ የሚሆነው ተማሪ በገጠሩ ከፍል የሚገኝ እንደመሆኑ ለምን ያህል ተማሪ መድርስ እንችላለን የሚለው ነው ይላሉ። ለአብዛኛው ተማሪ ለመድረስ ለመቻል በገጠሩ ክፍል ለሚገኙት ተማሪዎች መጽሐፍ ስለሚኖራቸው ፕሮግራም እና ደረጃ በማውጣት በዛ ፕሮግራም እንዲሄዱ በማድረግ አብዛኛውን የትምህርቱን ኅብረተሰብ ማካተት ይቻላል። ይህ ካልሆነ ግን የትምህርትን ጥራት ከመጠበቅ አንፃር እና የተማሪዎችን ሥነ ልቦና ለመጠበቅ አዳጋች ይሆናል ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 82 ግንቦት 22 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com