ሰሚ ያጡ አዛውንቶች እና የሴራሊዮን እርስ በእርስ ጦርነት

0
932

በሴራሊዮን የእርስበርስ ጦርነት ላይ ታዳጊ ጦረኛ በነበረው እስማኤል ቢሀ የተጻፈውን ግለ ታሪክ፣ ሙሉጌታ ገብሬ “ታዳጊው ጦረኛ” በሚል ርዕስ ተርጉመውታል። ብርሃኑ ሰሙ ትርጉሙን አንብበው ቅምሻ በማካፈል፣ መጽሐፉ ለኛም መማሪያ ይሆናል ይላሉ። በሴራሊዮን የእርስበርስ ጦርነት ላይ ታዳጊ ጦረኛ በነበረው እስማኤል ቢሀ የተጻፈውን ግለ ታሪክ፣ ሙሉጌታ ገብሬ “ታዳጊው ጦረኛ” በሚል ርዕስ ተርጉመውታል። ብርሃኑ ሰሙ ትርጉሙን አንብበው ቅምሻ በማካፈል፣ መጽሐፉ ለኛም መማሪያ ይሆናል ይላሉ።

 

“አንድ አዳኝ ነበር። ወደዱር ሔዶ ጦጣ መግደል ፈለገ። በፍለጋ ላይ እያለ አንዲት ጦጣ ተመቻችታ ቀረብ ባለ ቅርንጫፍ ላይ ተቀምጣ አየ። ጦጣይቱ ትኩረት አልሰጠችውም፤ ሌላው ቀርቶ በቅርብ ርቀት ደረቅ ቅጠል ቢያንሾካሽክም፣ ከልቧ አልጣፈችውም። በጣም ቀረብ ብሎ ከአንድ ዛፍ በስተጀርባ በግልጽ በሚታየው ሥፍራ በርከክ ብሎ መሣሪያውን አልሞ ቃታውን ሊስብ ሲል ጦጢት፣ ‘ብትተኩስ እናትህ ትሞታለች! ባትተኩስ ደግሞ አባትህ ይሞታል!’ ብላ ካለችበት ሳትነቃነቅ አንዴ ሆዷን፣ አንዴ ጭንቅላቷን እያከከች የያዘችውን ምግብ ማመንዠጓን ቀጠለች።”

ይህ ታሪክ ሴራሊዮናዊው እስማኤል ቢሀ “A Long way gone” (“ታዳጊው ጦረኛ” ብለው ሙሉጌታ ገብሬ ወደ አማርኛ ተርጉመውታል) በሚል ርዕስ ካሳተሙት የግለ ሕይወት ታሪክ መጽሐፍ የተወሰደ ነው። ታሪኩ የሴራሊዮን ሽማግሌዎች ሕፃናትን ሰብስበው ከሚያወሩላቸው ተረቶች አንዱ ነው። አዛውንቶቹ ትረካውን ሲያበቁ “ተረቴን መልሱ አፌን በዳቦ አብሱ” ብለው ብቻም አያቆሙም። “እናንተስ አዳኙን ብትሆን ምን ታደርጋላችሁ?” የሚል ጥያቄ ያስከትላሉ። ጥያቄውን መሸሻ ዘዴ ያገኙ የመሰላቸው አንዳንድ ልጆች “አስብበታለሁ” በማለት፥ አጣብቂኝ ውስጥ መግባት ያልፈለጉ ደግሞ “ጦጣ አልገድልም” የሚል መልስ ይሰጡ ነበር ይላል – ሴራሊዮናዊው እስማኤል ቢሀ።

ጦጢት ከኹለት አንዱን ወላጅህን ማጣትህ ስለማይቀር አስብበትና መርጠህ አንዱን ወስን ብላ ለአዳኙ ጥያቄዋን ያቀረበችው፣ የጦር መሣሪያ ከተነጣጠረባት በኋላ ስለሆነ፥ ተጠያቂው መልሥ መስጠት ያለበት በዚያው ቅፅበት ነው። በተረቱ ማስተላለፍ የተፈለገውም መልዕክት በዚህ ውሳኔ ውስጥ የሚገኝ ስለሆነ ነው። ልጆቹ አንዱን መርጠው እንዲመልሱ ወጥረው የሚያዟቸው። “ከጦጣዋ ሳትርቁ ነው መወሰን ያለባችሁ” ብለውም ይሞግቷቸዋል። ልጆቹን እንዲህ የማስጨነቁም ግብ፣ በተረቱ ማስተላለፍ የተፈለገው መልዕክት በአዕምሯቸው እንዲታተም ከመሻት ነው የሚመስለው።

 

“ወደኋላ ተመልሰን ዐሥር ኪሎ ሜትር ተጉዘን ከአያቴ መንደር ደረስን። ባዶ ምድረ በዳ ሆኗል። በአሸዋው ላይ የሚታየው የሰው የእግር ዱካ ብቻ ነው። ከሰፈራችን ማዶ ወዳለው ጥቅጥቅ ያለ ደን ያመለጡ ሰዎች የእግር ፈለግ ብቻ ፈንጠር ፈንጠር ብሎ ይታያል።”

 

በዚህ ተረት ውስጥ ብዙ ቁም ነገር ነው የታጨቀው። ቀድሞ ክፉ አለማሰብ ነው እንጂ፣ ክፉ ነገር ካሰብክ፣ ጊዜው ይርዘምም ይጠር እንደ ሐሳብህ አዎንታዊነትና አሉታዊነት ዋጋ መክፈልህ/መቀበልህ አይቀርም የሚለው ትርጉም አንዱ ነው። ጦጢት ሆዷንና ጭንቅላቷን ማከኳ ለሆድህና ለሕሊናህ ከመኖር አንዱ ምረጥ የሚል ትርጉም ያለው ይመስላል። መሠረታዊውና ዋነኛው መልዕክት ግን ጦጣዋ የወከለችው ምንን ነው? በጦጣዋ ተወክሎ ለልጆቹ ሊነገር የተፈለገውስ ስለምንድን? የጦጣዋ ድፍረት፣ ጅገናና ወኔ ከየት የሚገኝ ነው? የሚለው ነው። በተረቱ ውስጥ ጦጣዋ “ዕውቀት”ን ወክላ ቀርባች።

በሴራሊዮን የእርስ በእርስ ጦርነት ሙሉ ቤተሰቦቹን ያጣ ብቻ ሳይሆን በ13 ዓመቱ ተገድዶ በጦርነቱ በመሳተፍ ብዙ እልቂት የፈፀመና ሲፈፀም ያየው እስማኤል ቢሀ፥ በልጅነት ዕድሜው ብዙ መከራ ካሳለፈ ከዓመታት በኋላ ባሳተመው “ታዳጊው ጦረኛ” ግለ ሕይወት ታሪክ መጽሐፉ፥ የሴራሊዮን አዛውንቶች ስለነገሩት ተረትና የጦጢት ጥያቄ የ7 ዓመት ልጅ እያለ መልሱን አግኝቶ እንደነበር ሲገልጽ፦

“በሰባተኛው ዓመቴ ለጥያቄያቸው መልሥ አግኝቼ ነበር። የግሌ የሆነና እንቆቅልሹን መፍቻ የተሻለ መልሥ ነበር። ዳሩ ግን፣ ለማንም ያልተናገርኩት እናቴን እንዳላሳዝን በመሥጋት ነበር። አዳኙን ብሆን ኖሮ ጦጣይቱን ተኩሼ እገድላት ነበር። ይህንንም ለማድረግ የወሰንኩት ጦጣዋ ከዚያ በኋላ ዳግመኛ ሌሎች አዳኞች ተመሳሳይ ፈተና ውስጥ ለመክተት ዕድል እንዳታገኝ ብዬ ነው” የሚል ምላሽን በመጽሐፉ አስፍሯል።

እስማኤል ቢሀ አዛውንቶች በነገሩት ታሪክ ውስጥ፣ ጦጣይቱ ላቀረበችው ጥያቄ የሰጠው መልስ፣ በአስከፊው የእርስ በእርስ ጦርነት እና እሱም በብዙ ሥነ ልቦናዊና ሥነ አእምሯዊ ቀውስ ካለፈ በኋላ ስለሆነ እንዲህ ዓይነት ምላሽ መስጠቱ ብዙም ላያስገርም በቻለ ነበር። አስደንጋጭና አሳዛኝ የሚሆነው ግን ለጥያቄው መልስ “ያገኘሁት የ7 ዓመት ልጅ እያለሁ ነበር” ማለቱ ነው። እስማኤል ቢሀ በዚያ ዕድሜው እናቱ ላይ ሊያስጨክን ያስቻለው ውሳኔ እንዴት በውስጡ ሊፈጠር ቻለ? እሱም ይቅር በብዙ መከራ ውስጥ ካለፈ በኋላ አዛውንቶቹ ይነግሯቸው የነበረው ተረት ትርጉም በምን ምክንያት ሳይገባው ቀረ? ጦጣይቱ የወከለችው “ዕውቀት”ን እንደሆነ፤ ጦጣዋን ካለመግደል፣ መገደሉ የሚበልጠውን ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍል በኋለኛው ዕድሜው እንዴት መረዳት አልቻለም?

የተበላሸውን ፖለቲካ ለማስተካከል፣ ዲሞክራሲ ለማምጣት፣ ሙስናን ለመከላከል… በሚል ሽፋን በሴራሊዮን የእርስ በእርስ ጦርነት ተሳትፈው ሕዝብና አገራቸውን የጎዱት ታዳጊ ሕፃናትና አመራሮቻቸውን ወደጥፋት የመራው ያባቶችን ምክር አለመስማት፣ ነባሩና ባሕልና ስርዓት አለማክበር፣ ከአገራዊ ይልቅ ለባዕድ ዕውቀት ክብርና ዕውቅና መስጠት መፈለግ… ምክንያቶች እንደሆኑ ማሣያነት የቀረቡ የተለያዩ ታሪኮች አሉ። የአገሪቱ በእንግሊዝ ቅኝ መገዛትም የራሱን አንድ አስተዋፅዖ ሳያደርግ አልቀረም።

እስማኤል ቢሀ ከአባቴ የሰማሁት የአገሬ ታሪክ ነው ብሎ ባቀረበው መረጃ መሠረት፥ ሴራሊዮን ከ18ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አንስቶ ለበርካታ ዓመታት በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሥር ቆይታለች። ከነጻነት በኋላ ኹለት ወንድማማቾች በጠቅላይ ሚኒስትርነት አስተዳድረዋታል። በ1960ዎቹ የከሸፈ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከተደረገ በኋላ የአንድ ፓርቲ የሥልጣን የበላይነት እንዲሰፍን መደረጉን ተከትሎ “የነቀዘ ፖለቲካ” በአገሪቱ ሰፈነ። በሙስና የተዘፈቀውን አስተዳደር ማስወገድን ዓላማ ያደረገ “አብዮታዊ ጦርነት” የተጀመረው ይህን መነሻ በማድረግ ነበር። ነጻነትን ለማምጣትና ሙስናን ለማስወገድ የተደረገው ትግል አገሪቷንና ሕዝቧን ለከፍተኛ ምስቅልቅል ዳርጓታል።

አገሪቷና ሕዝቧ በእንዲህ ዓይነት መከራና እንግልት ሲያሳልፉም፣ ተረት፣ ባሕልና ልማዱ አብሮ እስከዚህ ዘመን መዝለቁም በ“ታዳጊው ጦረኛ” መጽሐፍ ውስጥ (እንደ ጦጣዋ ተረት) ማሳያ ሆነው የቀረቡ በርካታ ታሪኮች አሉ። ሸረሪት ወገበ ቀጭን የሆነው በአልጠግብ ባይነቱና በስግብግብ ባሕሪው ምክንያት እንደሆነ በሴራሊዮናዊያን ዘንድ የሚነገረው ተረት ሌላኛው ማሳያ ነው።

በአንድ ቀን በስምንት የተለያዩ ቦታዎች ድግስ መዘጋጀቱን የሰማው ሸረሪት ድሩን ወገቡ ላይ በማሰር ከስምንቱም ድግስ ቤቶች ጋር በማያያዝ ዝግጅታችሁ ሲጠናቀቅ ድሩን በሞገተት ምልክት አሳዩኝ የሚል መልዕክት አኑሮ ከጎጆው ይቀመጣል። እንደአጋጣሚ የ8ቱም ቤት ድግስ በእኩል ሰዓት ተዘጋጅቶ ሲያልቅ ስምንቱም በአንድ ጊዜ የሸረሪቱን ድር በመሳብ የመጥራት ምልክት ያደርጋሉ። የዘገየው ስላልሰማ ይሆናል በሚል ድሩን ጠንከር አድርገው ይስቡት ጀመር። ከተለያየ አቅጣጫ የተሳበው ድር ለሸረሪት ወገብ መቅጠን ምክንያት ሆነ ብሎ የሚያበቃው ተረት መልክቱ “አልጠግብ ባይ…” የሚለውን የአገራችንን ተረት የሚያስታውስ ነው።

እናቴን ፈርቻት ነው እንጂ ጦጣዋ መገደል እንዳለባት የ7 ዓመት ልጅ እያለሁ ወስኜ ነበር የሚለን እስማኤል ቢሀ፥ የ13 ዓመት ልጅ እያለ የራፕ ሙዚቃ ተሰጥኦውን መሞከሪያ መድረክ ፍለጋ ከጓደኞቹ ጋር በወጣበት ያስቀረው፣ በአገሪቱ ሌላ ጫፍ ለእሱ የዕድሜ እኩዮች የሚሆኑ ወጣቶች ሕዝብ ሲገድሉና ሲያፈናቅሉ አገሪቱ ታምሳ፣ ወደ ቤተሰቦቹ መመለሻ መንገድና ዕድል ስላጣ ነበር።

የራፕ ሙዚቃ ዝግጅት ወደሚቀርብበት መንደር ከጓደኞቹ ጋር ሲሔድ በቅርብ ርቀት መንደር ይኖሩ የነበሩት አያቱን አግኝቶ የነበረው እስማኤል ቢሀ፥ በአንድ ቀን ልዩነት የተፈጠረውን ትርምስ የቅርብ መሸሻ ማድረግ የፈለገው የአያቱን ቤት የነበረ ቢሆንም የገጠመው ግን ያልገመተው እውነት ነበር። “ወደኋላ ተመልሰን ዐሥር ኪሎ ሜትር ተጉዘን ከአያቴ መንደር ደረስን። ባዶ ምድረ በዳ ሆኗል። በአሸዋው ላይ የሚታየው የሰው የእግር ዱካ ብቻ ነው። ከሰፈራችን ማዶ ወዳለው ጥቅጥቅ ያለ ደን ያመለጡ ሰዎች የእግር ፈለግ ብቻ ፈንጠር ፈንጠር ብሎ ይታያል።”

ከዚህ ገጠመኝ በኋላ እስማኤልና ጓደኞቹ በሔዱበት የሚገጥማቸው በልጅ አዕምሮ መቀበል የሚያስቸግራቸው እውነት ነበር። የነጻነት ታጋዮቹ የገደሉትን ሰው ጭንቅላት ቆርጠው በማንጠልጠል ሲዝናኑበት፣ በጀርባዋ አዝላው በጥይት የተመታባን ልጅና እራሷን ለማዳን የምትሮጥ እናት፣ ሰላት ያሰግዱ የነበረ ኢማምን ታጋዮቹ ከመስጊድ አስገድደው በማውጣት በአደባባይ ገድለዋቸው አስከሬናቸውን በእሳት ሲያቃጥሉ፣ የተገደሉበት ሦስት ቤተሰቦቹን በመኪናው ጭኖ ነፍስ አውጪኝ የሚከንፍ አባትን… የተመለከቱት በነጻ አውጪዎቹ ላለመያዝ በየጫከው በመሽሎክለክ ነበር።

በሽፍቶች እጅ ሳንገባ ቤተሰባችንን እናገኛለን የሚል ተስፋ የነበራቸው እስማኤል ቢሀ እና ጓደኞቹ ተስፋቸው እውን ሳይሆን ምርኮኛ ሆኑ። “ለአገርና ሕዝባችን ነጻነት ነው እየታገል ያለነው” ያሏቸው “አማፂያን” እነ እስማኤልን ጭካኔ ለማለማመድ ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም። “ከመኖሪያችሁ ያፈናቀሏችሁ፣ ወላጆቻችሁን የገደሉባችሁን… ግደሉ” ብሎ ማጀገን ዋነኛው ዘዴ ነበር። ጭካኔን እንዴት እንዳለማመዷቸው ሲገልጽ፦

“አምስት ምርኮኞች ከፊት ለፊታችን በልምምድ ሜዳው ላይ እጆቻቸው እንደታሰሩ ተደርድረዋል። እኛም በ10 አለቃው ትዕዛዝ አንገታቸውን ልንቆርጥ ተዘጋጅተናል። በቶሎ የሞተውን ሽፍታ አንገት ፈጥኖ ለቆረጠ የተዘጋጀውን ሽልማት እኔ ወሰድኩ” የሚለው እስማኤል ቢሀ፥ ከዚያ በኋላ ለግድያና ቅሚያ በተሠማሩበት ሁሉ ሞት ማምረት፣ ዘረፋ መፈፀም መዝናኛቸው ሆኖ ነበር። “ሬሳ እያገላበጥን መሣሪያና ጥይት ገፈፍን። ለሞተ ሬሳ የነበረን ፍርሐት ጠፋ። በጥላቻና በንዴት ጦፌ አስከሬኖቹን ሳገላብጣቸው ሁሉ በመርገጥና በማሽቀንጠር ነበር።”

በሙሉጌታ ገብሬ ተተርጉሞ የቀረበልን “ታዳጊው ጦረኛ” የግለ ታሪክ መጽሐፍ ተደራሲያንን የሚያወያይ ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ አንስቷል። በሴራሊዮን የእርስ በእርስ ጦርነት ተሳታፊዎች አብዛኞቹ በዕድሜ ሕፃናት ናቸው። በእስማኤል ቢሀ ታሪክ እንደምናየው ልጆቹ ለፖፕ ሙዚቃ የሰጡትን ክብር ያህል ለአዛውንቶች ተረት ዕውቅና የሰጡ አይመስልም። ለዚህ ነው እስማኤል ቢሀ እና ዘመነኞቹ ምን ቢሆኑ፣ በምን ተፅዕኖ ሥር ቢወድቁ፣ በምንስ ውጤት ይሆን “ጦጣዋን ገድዬ ለእናቴም ሞት ምክንያት እሆን ነበር” የሚል አቋም ለመያዝ መነሻ የሆናቸው? የሚል ጥያቄ መነሳት ያለበት። መልሱን በፍጥነት ማግኘቱ ቢያስቸግር እንኳን የእኛዋን ኢትዮጵያ ጨምሮ እንዲህ ዓይነት ቀውስና ሥጋት ለሚታይባቸው አገራት የችግሩን ምንጭ ለመፈተሽ ዕድል የሚሰጥ ታሪክ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 18 የመጋቢት 7 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here