‹ሠኔ እና ሰኞ ሲገጥም…›?

Views: 333

ዘንድሮ ሠኔና ሰኞ ገጥሟል። ማለትም ሠኔ አንድ ቀን ሰኞ እለት ውሏል። በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ብቻም ሳይሆን የአውሮፓውያኑ ጁን 1 ወይም ሠኔ 1 በ2020 ሰኞ እለት ውሏል። በአገራችን ደግሞ ሠኔ እና ሰኞ ሲገጣጠም አንዳች ክፉ ነገር እንደሚከሰት የተለመደና የሚታወቅ ብሂል ወይም አነጋገር አለ። ክፉ ነገር የገጠመውም ‹ሠኔ እና ሰኞ ገጥሞብኝ› ይላል፤ በጥቅሉ ሠኔ እና ሰኞ ሲገጥሙ እለቱ ብቻ ሳይሆን ዘመኑን ክፉ የሚሰማበት አስፈሪ እንደሚሆን ብዙዎች ይሰጋሉ።

በእርግጥ ከዚህ ቀደም ባይሆን እንኳ ዘንድሮ ዓለማችን እያየችው ካለው አሳር አንጻር፣ ቀጣዮቹ ሠኔ እና ሰኞ የሚገጥሙባቸው ዓመታት በስጋት ቢታዩ አያስወቅስም። ከዛም ያለፉ ሐሳቦችን ስንሰማ ነበር። በተለይም ዓለም በ2012 ትጠፋለች ከሚል ‹ትንቢት› በመነሳት ዓለም በፈረንጆቹን 2012 እንደምትጠፋ ሲጠበቅ፣ በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ቢሆንስ የሚል። ይህም አሁን ላይ እየታዩ ካሉ አሳዛኝና አስከፉ ኹነቶች በመነሳት ነው።

ብዙዎች ይህ የሠኔ እና የሰኞ መገጣጠምን ከክፉ እድል ጋር ማገናኘት በድሀ አገራት ብቻ ያለ የአመለካከት ድክመት ይመስላቸዋል። በሚገርም ሁኔታ ግን በርካታ የዓለም አገራት ተመሳሳይ በሆነ መልኩ የማይወዷቸው፣ ገዳችን አይደሉም የሚሏቸው የቀናትና የቁጥር ግጥምጥሞሾች አሉ።

ለምሳሌ በአሜሪካ የየትኛውም ወር አርብ እለት ቀኑ 13 ላይ ከዋለ እንደ መጥፎ እድል ይቆጥሩታል። መዛግብት ላይ ተጽፎ እንደሚገኘው ከሆነ ለዚህ ምክንያት የሚቀርበው ከክርስትና ጋር የተያያዘ ክስተት ነው። በተለይም ከአርብ ስቅለት በፊት የጸሎተ ሐሙስ ቀን ክርስቶስን ጨምሮ ከሐዋርያት ጋር 13 ሰዎች ተገኝተዋል። በቀጣዩ ቀን አርብ ቀን ደግሞ ክርስቶስ ተሰቅሏል ። ስለዚህም 13 እና አርብን ገጣጥመው አይወዷቸውም።

ታድያ አለመውደድ ብቻ አይደለም። አርብ እና 13 የገጠሙበት ቀን፣ በእለቱ ከአልጋቸው የማይወጡ፣ ከቤታቸው ንቅንቅ የማይሉ፣ አሞኛል ብለው ከሥራቸው የሚቀሩ ጥቂት አይደሉም። በተመሳሳይ በግሪክ ማክሰኞ እለት 13 ከሆነ፣ በጣልያን እለተ አርብ 17 ላይ ከገጠመ በፍጹም ደስተኛ አይሆኑም።

የኢትዮጵያው ሠኔ እና ሰኞ
በትክክል በኢትዮጵያ የሠኔ እና የሰኞ ከክፉ እድል ጋር የመገናኘት ምክንያት ይህ ነው ብሎ የሚጠቅስ ብዙ አይደለም። የሠኔ እና ሰኞ መጋጠም እንደ ጷጉሜ 7 በርካታ ዘመናትን የሚጠብቅ ክስተት አይደለም። ይልቁንም በ6፣ በ7 እና በ11 ዓመት ልዩነት ሠኔ እና ሰኞ ይገጥማል። ታድያ ለምን ተፈራ?

ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ በ2007 በሸገር ኤፍኤም ራድዮ ሸገር ካፌ ከጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ጋር ባደረገው ቆይታ፣ ስለዚህ የሠኔ እና የሰኞ መገጣጠም ጉዳይ ሰፋ ያለ ጭውውት አድርጓል። ታድያ በዚህም በደስታ ተክለወልድ የተጻፈውን ‹ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት› ጠቅሷል።

ደስታ ተክለወልድ በመዝገበ ቃላቱ በቅድሚያ ሠኔን እንዲህ ሲሉ ተርጉመውታል። ‹‹ሠኔ (ሠነየ) የወር ሥም፣ ዐስረኛ ወር፣ ከመስከረም። ትርጓሜውም ሠናይ ማለት ነው። የእርሻን መለስለስና የዘርን መዘራት ያሳያል። ሠኔ 1 ቀን ሰኞ የመኪና መንገድ በግራ በኩል መኾኑ ቀርቶ በ1933 በፊት እንደነበረ በስተቀኝ ኾነ››
ቀጥለውም ‹ሠኔና ሰኞ› ለሚለው ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ‹የመለኛ የጠንቋይ ፈሊጥ፣ ሠኔ ሰኞ በባተ ቁጥር ማስፈራሪያ ሆኖ ይኖራል› ብለዋል። ዓለማየሁ ታድያ ሠኔ 1 ቀን ሰኞ እለት የመኪና መንገድ በግራ መሆኑ ቀርቶ ወደቀኝ መቀየሩን አንስቷል።

ይህም የሆነው በ1956 ሲሆን፣ በ1933 የኢትዮጵያና ጣልያን ጦርነት ባበቃበት ዘመን፣ ኢንግሊዝ ኢትዮጵያ ሲገባ የመንገድ ስርዓቱን እንደ ሕንድና ኢንግሊዝ አድርጎት ነበር። ታድያ ይህ ከ1933 ሲሠራበት ቆይቶ በ1956 ወደነበረበት እንዲቀየር ተደረገ።

ያ እንዲደረግ የታዘዘበት ቀን በ1956 ሠኔ እና ሰኞ የገጠመበት ቀን ነው። ታድያ መቀየሩን ብዙዎች አልሰሙ ኖሮ ግራ እያዩ ሲሄዱ በቀኝ፣ ቀኝ እያዩ ሲሄዱ በግራ በኩል ባላዩት መኪና ተገጭተዋል። በእለቱም በደረሱ ግጭቶች ብዙ ሰው ሞቷል። እናም ዓለማየሁ ይህን አንስቶ እንዲህ አለ፤ ‹‹እናም ከዛ በኋላ ሰው ምን ሆንክ ሲባል፣ ሠኔ እና ሰኞ ገጥሞብኝ ይላል። ሠኔ እና ሰኞ በማናየው መኪና የምንገጭበት ቀን ሆነ›› ።

ይህ ታድያ በከተማ እንጂ በገጠር እንደዛ አይደለም። መከራ የደረሰበት ገበሬም ቢሆን ‹ሠኔ እና ሰኞ ገጥሞብኝ› ይበል እንጂ፣ አርሶ ለሚበላና ለሚመግብ ገበሬ ሠኔ ከምንም ወይም ከማንም ጋር ይግጠም ተወዳጅ ወር ነው። እንደውም ሠኔ ላይ ወደ ሥራ ሲገባ ከሰኞ ጋር ቢገጥም፣ የተሻለ ነገር አገኛለሁ ብሎ የሚጠብቀው ነው።

የሠኔ በረከቶች
ካሕሳይ ገብረእግዚአብሔር (ነፍስ ሔር) ‹ኅብረ ብዕር› ተከታታይ ካሳተሟቸው ሦስት መጻሕፍት ውስጥ በኹለተኛው መጽሐፍ ላይ፣ ወራትን ዘክረዋል። በዛም መሠረት የሠኔ ወር ቀናቱ ረዥም ናቸው ይላሉ። ‹‹የሠኔ ትርጉምም እንደ ሥሙ ትንሽ ነው። የዘር ወር፣ ሠናይ ማለት ነው። ሠኔ ጸደይ ጊዜውን ለክረምት የሚያስረክብበት ወቅት ነው። በኢትዮጵያ አቆጣጠር ክረምት የሚገባው ሠኔ 26 ቀን ነው።›› ሲሉም አብራርተዋል።

ምንም እንኳ በከተሞች ለሚገኙ መሥሪያ ቤቶች ሠኔ የበጀት መዝጊያ ወር ቢሆንም፣ ለገበሬው አዲስ የሥራ ዘመን መጀመሪያ፣ የዘርና የእርሻ ጊዜ ነው። ሰነፍና ጎበዙ፣ ጠንካራውና ደካማው የሚለይበት የፈተና ወርም ነው፣ ሠኔ።

ካሕሳይ ይህን ነገር እንዲህ ሲሉ አስቀምጠዋል፤ ‹‹ሠኔ ለገበሬው የጥድፊያና የሽሚያ ወቅት ነው ብለናል። የአገሬ ገበሬ ወቅቱን ጠብቀው፣ ሰዓቱን ዐይተው ካልዘሩ አዝመራው የሚያመልጥ መሆኑን ለማመልከት በዘይቤያዊ አነጋገሩ ‹ሽልና ዘር በሞፈር ቀዳዳ ያመልጣል› ይላል። እያንዳንዷ የሠኔ ቀን ለገበሬው ወርቅ ናት። ከዚህ የተነሳ ይመስላል ከዐፄ ኃይለሥላሴ በፊት በነበሩት የነገሥታት ስርዓት ወቅት ገበሬን በፍርድ ቤት ለሠኔ ወር መቅጠር ክልክል ነበር። በሠኔ ወርና በሥራ ቀን የሚሞት ሰውም ቢሆን ቀባሪው እስከዚህም ነው የሚሆነው። አንድ ዘመዱ በሠኔ ወር በሥራ ቀን የሞተችበት አልቃሽ

‹አንቺስ አበዛሽው ቅዳሜ መሞትሽ
እሁድ አትሞችም ወይ እንደ ድህነትሽ!› በማለት ያንጎራጎረው ለዚህ ነው።››
በመጽሐፉ ተጠቅሶ እንደምናገኘው በሠኔ ሌሎች ተግባራትም አሉ። በበልግ ወቅት የተዘራው እህል የሚታጨደውና የሚወቃው በሠኔ ወር ነው። በሸዋ ኦሮሞዎች ዘንድም ሠኔ የሰርግ ወር ነው። ይህም የሆነው ሰርግ ከልምላሜ ጋር ሲሆን መልካም ይሆናል ተብሎ ስለሚታመን ነው። በመከር የተጠቁት የቤት እንስሳት መውለድ የሚጀምሩበት ወቅትም ይኸው ሠኔ ነው።

ካሕሳይ በዚህ መጽሐፍ እንደጠቀሱት ከሆነ፣ የተለያዩ ፍጥረታትም ክረምትን እንዴት እንደሚያሳልፉ መሰናዶአቸውን የሚያጠናቅቁባት ወር ናት፣ ሠኔ። ‹‹እንደ ጉንዳን እና ንብ የመሳሰሉት ትጉሀን ፍጥረታት በበጋ ያዘጋጁትን ወይም ያጠራቀሙትን ቀለብ እየተመገቡ ክረምቱን ከሞቀ ቤታቸው ውስጥ ሆነው ለማሳለፍ ወደየሰፈራቸው የሚያቀኑበት፣ አእዋፍም ከፊሎቹ ወደ ሩቅ ቦታ የሚሰደዱበት ጊዜ ነው።›› ብለዋል።

ሠኔ እና ሰኞ በታሪክ ማኅደር
በ1956 የተደረገው የመንገድ ለውጥ ሠኔ እና ሰኞ ሲገጥም ክፉ ነው የሚል ስሜት እንዲፈጠር አንድ ምክንያት መሆኑን ከላይ አንስተናል። ታድያ መለስ ብሎ ታሪክን ለቃኘም ትልልቅና በኢትዮጵያ ታሪክ አይረሴ ክስተቶች ሠኔ እና ሰኞ በገጠሙባቸው ዓመታት ሆነዋል። ይህን በሚመለከት ‹ጉዳያችን› የተባለ ገጽ፣ በገጹ አዘጋጅ ጌታቸው በቀለ የተጻፈ አንድ ጽሑፍ ይገኛል።

የ2012/2020ን ሠኔ እና ሰኞ መግጠምን መነሻ አድርጎ በተዘጋጀው በዚህ ጽሑፍ፣ ፀሐፊው የቀደሙ የታሪክ አጋጣሚዎችን ስመለከት ሠኔ እና ሰኞ የገጠሙባቸው ዓመታት ፈተና የመጣባቸው ቢሆኑም ሌሎቹ ደግሞ መልካም ጊዜዎች ነበሩ በማለት አስቀምጠዋል።

የአድዋ ዘመቻ በ1888 ሲደረግ ሠኔ እና ሰኞ ገጥሞ ነበር። ታድያ ዘመቻው ምን ፈተና የበዛበት ቢሆንም፣ የተገኘው ድል ግን አይረሴ መሆኑ ክፉ እድል መሆኑን ያጣፋዋል።

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ያረፉበት እና ልጅ ኢያሱ ወደ ንግሥናው የመጡበት በ1906 ሠኔ እና ሰኞ የተጋጠሙበት ዓመት ነበር። በዚሁም ዓመት የመጀመርያው ዓለም ጦርነት ተጀምሯል።

አፄ ኃይለሥላሴ ከራስ ተፈሪነት አልፈው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሆነው የተሰየሙበት ዓመት ማለትም 1923፣ ሠኔ እና ሰኞ ገጥመዋል። ኢትዮጵያ በፋሺስት ጣልያን የተወረረችበት ዓመት ማለትም 1928 ላይም በተመሳሳይ ሠኔ እና ሰኞ ገጥመዋል።
እነዚህና ሌሎች ታሪኮችም በዛው ጽሑፍ ላይ በተመሳሳይ በስፋት ተነስተዋል።

ታድያ የዘንድሮው 2012 የኮሮና ወረርሽኝ፣ በአሜሪካ የጥቁር አሜሪካዊውን ጆርጅ ፍሎይድ ሞት ተከትሎ የታየው ሁከት፣ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና የአባይ ጉዳይ በኢትዮጵያና በግብጽ መካከል የፈጠረው ውጥረት ወዘተ ‹እውነትም ሠኔ እና ሰኞ!› ሳያሰኝ አይቀርም።

ቀናት ታድያ እንዲህ በግጥምጥሞሽ እይታ መጥፎ ናቸው ብሎ መዝለቅ ይቻላል? ብዙዎች በዚህ ሐሳብ አይስማሙም። የሃይማኖት ሰዎች በፈጣሪ ዘንድ መጥፎ የሚባል ቀን እንደሌለ ሲያነሱ፣ ሳይንሱም ለግጥምጥሞሹ ‹መገጣጠም ነው!› ከማለት ያለፈ ትንታኔ የለውም።

ሠኔን የተመለከቱ አባባሎች
‹አንድ ሠኔ የሳተውን፣ ሰባት ሠኔ አይመልሰውም›
‹ለሞኝ ሠኔ በጋው፣ መስከረም ክረምቱ›
‹አላጋጭ ገበሬ፣ ይሞታል በሠኔ›
‹አንድ ሠኔ የተከለው፣ ከዓመት ዓመት አተረፈው›
‹በሠኔ ካልዘሩ…በክረምት ካላረሙ፣›
እህል የት ይገኛል፣ በድንበር ቢቆሙ›

ቅጽ 2 ቁጥር 83 ግንቦት 29 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com