“ጣና” ትኩረት የተነፈገው ሕመምተኛ-እንደ አረል ሐይቅ

Views: 414

በዓለማችን በልዩ ልዩ ምክንያቶች ባለፉት 60 እና 50 ዓመታት ብቻ በሰው ልጅ ለተፈጥሮ በማይስማማ ተግባርና በአካባቢያዊ የአየርን ብረት ለውጥ ምክንያት በርካታ የውኃ አካላት እንዳልነበር ሆነዋል። ከእነዚህ ውሰጥ በስፋቱ ከዓለም 4 ደረጃ ላይ የሚገኘው በቀድሞዋ ሶቬየት ኅብረት ይገኝ የነበረው አረል ሐይቅ አንዱ ነው።

አረል ሐይቅ በዓለማችን ከሚገኙ ሐይቆች በግዝፈቱ 4ኛ የነበረ ሲሆን ዛሬ ላይ በነበር ቢቀርም፤ የሐይቁ ተፋሰስ ካዛኪስታን፣ ኪርጊስታን፣ ታጃኪስታን፣ ተርኪስታን እና ኡዝቤኪስታን የተባሉትን ከሶቬት ኅብረት የተገነጠሉ አምስት አገራትንም የሚያካትት ነበር። ይሁን እንጅ እ.ኤ.አ. ከ1960 ወዲህ በገጠመው፣ በተለይ በሐይቁ በቅርብ እርቀት ከሚገኙ፣ የኪዚልኩ፣ የካራኩም እና የኡስተርት በረሃዎች በሚነሳ ነፋስ ሐይቁን በጨዋማ አፈር እየሞላ በ60 ዓመታት እንዳልነበረ አድርጎታል።

ሐይቁ ከመጥፋቱ በፊት በሐይቁ ላይ ይርመሰመሱ የነበሩ የመጓጓዣ እና የንግድ መርከቦች አሁን ላይ አሸዋ ላይ ተተክለው፣ ለትዝብት ቀርተዋል። ወደ ሐይቁ ይመጡ የነበሩ ወቅታዊ አእዋፍት (migratory birds) ባልተገመተ ጊዜ ዳግም ላይመለሱ ተሰናብተውት ቀርተዋል። ዓሣ ማስገር እና በደማቅ ሰማያዊው የአራል ባሕር በዋና መዝናናት፣ በሐይቁ ዙሪያ መስኖ ማልማት ተረት ሆኖ ያ የተንጣለለው ውብ ተፈጥሮ አስፈሪ ሀሩር በርሃ ሆኗል።

ህመምተኛው ጣና ሐይቅስ? እንደ አረል ሐይቅ ላለመሆኑ ዋስትና የሚሆኑ ሥራዎች የትአሉ። የጣና ሐይቅ ከየት መጣህ የማይሉት ህልውናውን የሚፈታተን ድንገተኛ ክፉ ባላጋራ ከተጋረጠበት ድፍን ስምንት ዓመታት አልፈዋል። እንቦጭ በጣና ሐይቅ ላይ በውል መከሰቱ የታወቀው በ2004 ነበር።

ጣናን በእንቦጭ ተወሮ ከመጠፋቱ በፊት ህልውናውን ለመታደግ እስካሁን በሰው ኃይል ለማስወገድ በአካባቢው ያሉ በ30 ቀበሌዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች እየጣሩ ቢሆንም እስካሁን መፍትሔ አልመጣም። የማሽንና ሌሎች ሥነ ሕይወታዊ ዘዴዎችም ለጣና ፈውስ አላመጡም። የዓባይ ቀዳሚ ተጠቃሚዎቹ ግብፅና ሱዳን ግን ጉዳዩ አሳስቧቸው አያውቅም። ለግብጾችና ለሱዳኖች ዓባይ ከምንጩ መታመመኑ እስካሁን አንድም ጊዜ አስበው እንደማያውቁ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ጣናን ለማዳን የስምንት ዓመት ክንውንና ውጤቱ
እምቦጭ በጣና ሐይቅ ላይ መከሰቱ ከተሰማ ጊዜ ጀምሮ እስካውን ያለማቋረጥ የተሰራው ሥራ በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮችን በማስተባበር በሰው ኃይል እንቦጭን ከሐይቁ ላይ ወደ ውጭ ማስወገድ ከተሰሩት ሥራዎች ቀዳሚው ነው። የጣና ሐይቅና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃ ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ አያሌው ወንዴ (ደ/ር) እንደሚሉት ስምንት ዓመታት ሙሉ እቦጭን ከጣና ሐይቅ ላይ ለማስወገድ በስፋት የተሰራው ሥራ በሰው ሐይል ለማስወገድ መሞከር መሆኑን በመግለጽ፣ እንቦጭን ከጣና ላይ ለማስወገድ በሰው ሀይል የተሰራው ሥራ የውጤታማነት ደረጃ ፋይዳቢስ መሆኑንና እምቦጭን ከሐይቁ ላይ ለማጥፋት እንዳላስቻለ ይናገራሉ። ለዚህም ዋነኛ ምክንያት ነው የሚሉት አያሌው የእምቦጭ ስነ-ሕይወት በባህሪው በትንሽ ነገር እራሱን የማዛመትና በቶሎ መድረቅ አለመቻሉ በየጊዜው እየሰፋ መምጣቱን እንደሆነ ተናግረዋል። እንደ አያሌው ገለጻ እምቦጭ በስምንት ዓመታት ውስጥ በጣና ሐይቅ ላይ አራት ሺህ ሔክታር ሸፍኖ እንደነበር ገልጸዋል። አሁን ላይ እንቦጭ በሐይቁ ላይ እስከ አንድ ሺህ 500 ሔክታር የሚሆን ቦታ እንደተቆጣጠረ እና ኹለት ሺህ 500 ሔክታር የሚሆን እንቦጭ ከሐይቁ ላይ እስካሁን በሰው ሀይል ለማስወገድ መቻሉን አያሌው አክለው ጠቁመዋል። ይሁን እንጅ የአረሙ በፍጥነት የመዛመት አቅም እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ጣናን እስካሁን ከእንቦጭ ነፃ ለማድግ ፈታኝ እንደሆነ አያሌው ይናገራሉ።

የ“ዓባይ ፖለቲካ እና የባዕዳን ተልዕኮ” መጽሐፍ ደራሲ ጋዜጠኛ ስላባት ማናየ በመጽሐፉ ላይ “አዲሱ የዓባይና እና የሌሎች ወንዞች ራስምታት የእምቦጭ አረም” በሚል ርዕስ ባሰፈረው ጽሑፍ ላይ “እስካሁን የእንቦጭ አረምን መቶ በመቶ በቆጣጠር የተቻለበት ብቸኛ የሆነ ዘዴ የለም” ሲል ገልጿል። ስላባት እንደሚለው እቦጭን አስካሁን ለመቆጠር ያልተቻለው ዘላቂ ስትራቴጂክ የሆነ አሰራር የተከተለ ሥራ ባለመሰራቱ ነው ይላል።

የጣና ጉዳይ በተለይ በ2010 የወቅቱ አጀንዳ ነበር። ያኔ ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከቦታው ድረስ በመሔድ ጣናን ተባብረን እናድነዋለን ብለው ቃል ገብተው እንደነበር የአደባባይ ሐቅ ቢሆንም፣ በገቡት ቃል መሰረት እስካሁን የተሰሩ ሥራዎች እንደሌሉ አያሌው ተናግረዋል። ይልቁንም ይላሉ አያሌው(ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትሩ አርቲፊሻል ሐይቅ ለመገንባት ሲታገሉ እናያቸዋለን እንጅ ለጣና ከቃል ያለፈ ሥራ መሥራት አልቻሉም ሲሉ በፌደራል መንግሰቱ በኩል ያለውን ለጣና የተሰጠ ትኩረት ማነስ እንደ መንግስት እስካሁን ምንም ተጨባጭ ሥራ አለመሰራቱን ያነሳሉ።

በዚያው በ2010 ስለ ጣና ሐይቅ መታመም ብዙ የቅስቀሳ ሥራውዎች በኪነ-ጥበብ ሳይቀር “ስንት ጎበዝ ሞልቶ ጦር የማይመልሰው፣ እንደት ጣና ያልቅስ እንባ አውጥቶ እንደሰው” እየተባለ የማንቂያ ሙዚቃ ተዜሞለታል። በጊዜው በአካባቢው ከሚኖሩ አርሶ አደሮች በተጨማሪ በጣናን እንታደግ ቀስቀሳ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ወጣቶች በመደራጀት እቦጭን ከጣና ለማስወገድ ወደ ባህር ዳር በወኔ ተመው ነበር። ያም ቢሆን ከአንዲ ሰሞን አጀንዳ ማለፍ ባለመቻሉ ጣና መታመሙ ተዘነጋ።

ጣናን ለመታደግ ዘላቂ መፍትሔ በማስፈለጉና እስካሁን የተሰሩ ሥራዎች ስትራቴጂክና ሳይንሳዊ መንገድ የተከተሉ ባለመሆናቸው በስምንት ዓመታት ተጨባጭ ውጤት ካለመገኘቱ ጋር ተያይዞ ባለፈው መስከረም 2012 በአማራ ክልል መንግስት የጣና ሔይቅና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃ ኤጀንሲ ተቋቁሟል። ነገር ግን አዲስ የተቋቋመው ኤጀንሲ እስካሁን ድረስ ከመመስረት ያለፈ የሰው ሀብት መዋቅርና በጀት እንዳልተመደበለት የኤጀንሲው ዋና ስራ አስኪያጅ አያሌው ተናግረዋል። በዚሁ ምክንያት ኤጀንሲው መስራት ያለበትን ሥራ ለመስራት የሰው ሀይል፣ የበጀትና ተንቀሳቅሶ ሥራ ለማስፈጸም የሚያገለግል ምንም አይነት ተሸከርካሪ ባለመኖሩ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ለመግባት ፈተና እንደሆነበት አያሌው ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት በበኩሉ ችግሩን ለመፍታት ራሱን የቻለ ተቋም ማቋቋም በማሰፈለጉ ኤጀንሲው እንደተቋቋመ ገልጿል። በኤጀንሲው በኩል ለተነሱ በርካታ ችግሮች ክልሉ በአንድ ጊዜ ችግሮችን መፍታት አይቻልም በማለት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቻም የለህ ካሳ ምላሽ ሰጥተዋል። አንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ አሁንም ለኤጀንሲው በቂ የሰው ሀይልና በጀት እንደሚመደብለት የሰጡት ጊዜ ገደብ የለም።

በ2012 በጀት ዓመት በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም የሰው ኃይል በመጠቀም ሙሉ በሙሉ ማስወገድ የጣና ሐይቅና ሌሎች ውኃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዕቅድ ነበር። ነገር ግን ከመጋቢት መጀመሪያ ሳምንት አንስቶ በኢትዮጵያ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንቅፋት መፍጠሩን የኤጀንሲው ዋና ሥራ አስኪያጅ አያሌው ወንዴ (ዶክተር) ተናግረዋል።

ማሽኖች ምን ፈየዱ?
እቦጭን ከጣና ሐይቅ ለማስወገድ በወቅቱ ሁነኛ አማራጭ የተባለው ዘዴ ማሽኖችን በማሰገባት እቦጭን ከሐይቁ ላይ በማሽን ማስወገድ ነበር። የጣና ሐይቅና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃ ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ ማሽኖች እቦጭን ከጣና ላይ በማስወገድ ረገድ እስካሁን ውጤታማ እንዳልሆነ ተናግረዋል። እንደውም የማሽኖች ፋይዳ ችግሩን እንዳባበሰውና ማሽኑ አረሙን ከስሩ መንቀል ባለመቻሉ ተቆርጦ ሐይቁ ላይ የሚቀረው አረም ወደ ሐይቅ እንድስፋፋ አድርጎታል ይላሉ አያሌው የማሽኖችን ፋይዳ ሲገልጹ። እንደ ስራ አስኪያጁ ገለጻ ሌላኛው የማሽኖች ችግር በተለይ ውጭ አገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዘፈቀደ ሳይንሳዊ ጥቅማቸውና እቦጭን ለማስወገድ አንፃር ከሚኖራቸው ቴክኒካል ስሪት ተያይዞ አጋዥነታቸው በሳይንስ ሳይመዘንና ቴክኒካል አሰራሩን ሳይገነዘቡ ገዝተው የሚልኳቸው ማሽኖች እቦጭን ለማስወገድ ያላቸው ሚና ዝቅተኛ መሆኑን አያልው ተናግረዋል። በመሆኑም እስካሁን እቦጭን ለማስወገድ ይጠቅማሉ ተብለው የተገዙ አራት ማሽኖች አቦጭን ከስሩ ነቅሎ የማውጣት አቅም እንደሌላቸውና ሚናቸው ዝቅተኛ በመሆኑ እስካሁን የተሰሩ ሥራዎች ሁሉ የሰው ሀይል ውጤቶች መሆናቸውን አያልው ጠቁመዋል።

በመሆኑም ድያስፖራው ለጣና መታመም የሚቆረቆር ከሆነ እና ድጋፍ የሚደርግ ከሆነ በዘፈቀደ ጥቅሙ ያልተጠና ማሽን ገዝቶ ከመላክ ይልቅ ከጣና ሐይቅና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃ ኤጀንሲ ጋር በመነጋገር ስለሚገዙት ማሽን አረሙን ለማስወገድ ያለውን ቴክኒካልና ሳይንሳዊ ጥቅም ያገናዘበ መሆን እንደሚገባው የኤጀንሲው ዋና ሥራ አስኪያጅ ጠቁመዋል።

እስካሁን ጣናን ለማዳን ፈተና የሆኑ ጉዳዮች
እንቦጭ አረም በጣና ሐይቅ ላይ ከተከሰተ ስምንት ዓመታትን ቢያስቆጥርም እስካሁን ማስወገድ ያልተቻለበት ምክንያት የትኩረት ማነስ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። የጣና ሐይቅና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃ ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ አያሌው ወንዴ(ደ/ር) ለጣና እሰካሁን በእንቦጭ አረም መወረር በፈደራልና በክልሉ መንግስት የተሰጠው ትኩረት ማነስ እንቦጭ እስካሁን በጣና ላይ ችግር ሆኖ እንዲቆይ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ይገልጻሉ። በመሆኑም ጣና ስምንት ዓመታት በችግር ውስጥ አቅሙ እየተዳከመ መቆየቱን አያለው በቁጭት ይናገራሉ። አያሌው አክለውም ሌላው ፈተና የሚሉት ጣናን ለማዳን ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቶ በእቅድና በትኩረት አለመሰራቱ ችግሩን እስካሁን እንድዘልቅ ካደረጊት መንስኤዎች ውስጥ በዋናነት የሚጠቀስ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሌላኛው የዓባይንና የተፋሰስ አገራትን ጂኦ ፖለቲካ በመተንተን የሚታወቀው ጋዜጠኛና ደራሲ ስላባት ማናየ ለጣና ችግር እስካሁን መዝለቅ ምክንያቱ በመንግስት በኩል ትኩረት ሰጥቶ ጥብቅ ስትራቴጂክ እቅድ ተነድፎ የተሰራ ሥራ አለመኖሩ መሆኑን በመግለጽ የአያሌውን ሃሳብ ይጋራል። ስለአባት ከዚህ ባሻገር ትልቁ ችግር የሚለው የጣናን ጉዳይ በአንድ ሰሞን “ሆሆታ” ከማራገብ ያለፈ በዘላቂነት ትኩረት ስላልተሰጠው ነው ይላል። ለዚህም መክንያቱ ይላል ስላባት የአገራችን ባህል በአንድ ክስተት ላይ ከአንድ ሰሞን ሆሆታ ያለፈ በዘላቂነት ለችግሩ መፍትሔ ሳናፈላልግ ወደ ሌላ አዲስ አጀንዳ ጥሎ መሄድ ነው መሆኑን አመላክቷል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ጽሕፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቻምየለህ ካሳ እስካሁን ጣናን ከእምቦጭ አረም በታደግ ያልተቻለበት ምክንያት ችግሩ በክልሉ ምንግስት አቅም የሚወገድ ባለመሆነና የፌደራል ምንግስት ትኩረትና ድጋፍ እጦት እና ያለፉት የማስወገድ ሥራዎች ሳይንሳዊ መንገድ የተከተሉና ዘላቂ መፍትሔ የሚመጡ ባለመሆናቸው ነው ይላሉ።

የጣና በእቦጭ መወረር አሁናዊ ጉዳት
ጣና ሐይቅ የኢትዮጵያን 50 ከመቶ የገጸ-ምድር የውኃ ክምችት የያዘ፣ በአቅራቢያው ለሚኖሩ እጅግ በርካታ ሰዎችም የኑሮ መሠረት የሆነ፣ ባህላዊ ታሪካዊ፣ ጂኦሎጂካዊና ሥነ-ውበታዊ እሴት ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው። ጣና በውስጡ ከ37 በላይ ደሴቶች እና በርካታ ታሪካዊ ገዳማትም ይገኙበታል። ነገር ግን አሁን ላይ የገዳማቱ ህልውና ፈተና ውስጥ እንደገባ አያሌው ተናግረዋል።

ዮም የኢኮኖሚ ልማት ተቋም በጣና ሀይቅ ላይ በተከሠተው የእምቦጭ አረም ዙሪያ ያካሄደውን ጥናታዊ ፅሁፍ አረጋግጫለሁ ባለው ጥናቱ እምቦጭ አሁን ላይ በአካባቢው ተጠቃሚ በሆኑ ኗሪዎች ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል። በዚህም የሐይቁ የአሣ ምርት 70 በመቶ፣ የከብት እርባታ 54 በመቶ፣ የሰብል ምርት 25 በመቶ በእምቦጭ አረም ምክንያት መቀነሱ በጥናቱ ተመላክቷል። እንዲሁም የእምቦጭ ቅጠል የተመገቡ ከብቶች ለስጋ እንደማይሆኑ በጥናቱ ላይ ተመላክቷል። የአካባቢው ተጠቃሚዎች ዜጎችን የድህነት ደረጃ በ16 በመቶ ከፍ እንዳደረገው በጥናት ተረጋጧል።

ዓባይ ያለ ጣና
ደራሲ ጋዜጠኛ ስላባት ማናየ “ዓባይ ያለ ጣና፣ ልጅ ያለ ወላጅ ማሰብ እንደማለት ነው” ይላል። ስላባት አክሎም “ዓባይና ጣና የአንድ ሳንቲም ኹለት ገጽታዎች ናቸው። ዓባይን ያለ ጣና ማሰብ አይቻልም” የሚል እምነት እንዳለው ይገልጻል። ሰላበት እምቦጭን ከጣና ሐይቅ ላይ ፈጥኖ ማጥፋት ካልተቻለ ኢትዮጵያውያን እናቶች ከመቀነታቸው ፈተው ያላቸውን በማዋጣት የተገደበው ታላቁን ዓባይን ማሰብ ይከብዳል ይላል። እቦጭ በዚህ ከቀጠለ ነገ ዓባይ ላይ ስለመድረሱ ስላባት አጠራጣሪ አለመሆኑን ያስገነዝባል።

አያሌው እንደሚሉት እምቦጭ የመራባት አቅም ከፍተኛ መሆኑን በመጠቆም በዚሁ ከከጠለ እምቦጭ ዓባይ ላይ መድረሱ አያጠራጥርም ይላሉ። አያሌው አክለውም “ጣና የዓባይ መነሻ ነው። አንድ ነገር መነሻው ከተበላሸ መጨረሻው በመላሸቱ አያጠራጥርም” ይላሉ። እንደ አያሌው እምነት እምቦጭ በአፋጣኝ ካልተወገደ ለአገረም አስፈሪ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጣናን እንደ አረል ሐይቅ ከመሆን ለመታደግ መወሰድ ያለባቸው መፍትሔዎች
እስካሁን ጣናን ለመታደግ የተሄደበት መንገድ ውጤታማነት ሲመዘን ሚዛን አልደፋም። በመሆኑም እምቦጭ አረምን ከጣና ሐይቅ ለማጥፋት የአምስት ዓመት ስትራቴጂ እቅድ መነደፉን የጣና ሐይቅና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃ ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ አያሌው(ዶ/ር) ጠቁመዋል። የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅዱን ለማሳካትም 100 ሚሊየን ብር እንደሚያስፈልግም ዋና ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል። የአምስት ዓመቱ ስትራቴጂክ እቅድ አንደኛው እቦጭን በሦስት መንገድ ማስወገድ ሲሆን፣ በማሽን ፣ በሰው ኃይል፣ በኬሚካል የመጀመሪያው ሥራ መሆኑን አያሌው ጠቁመዋል። እቅዱ ከአምስት ዓመት በኋላ 10 በመቶ ዝቅ ለማድረግ እንደሚያስችልም አያሌው አስረድተዋል።

ስላበት ጣናን ለመታደግ መወሰድ ያለባቸው ከርካታ እርምጃዎች እነዳሉ ይናገራል። ከነሱም ውስጥ የስምንት ዓመቱ ሥራ ወቅታዊና የአንድ ሰሞን ሥራ በመሆኑ ውጤት አላመጣም ሰለሆነም ዘላቂ ስትራቴጂክ ቀርጾ መስራት በትኩረት መስራት የመጀመሪያው እርምጃ ሊሆን እንደሚገባ ስላባት ይጠቁማል። በሌላ በኩል የሐይቁንችግር የሚባብሱ ነገሮችን ማስቀረት ያስፈልጋል። ለዚህም ሐይቁ እየሽሽ በሚሔድበት ጊዜ የሐይቁ ዳርቻዎች እንዳይታረሱ መቆጣተር እና ከባህር ዳር ከተማ ወደ ሐይቁ የሚለቀቁ የቆሻሻ ፍሳሾችን ማስቆም እንደሚገባ ስላባት ጠቁሟል።

የጣና እና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃ ኤጀንሲዋና ስራ አስኪያጁ አያሌው(ዶ/ር) በበኩላቸው ጣናን ለመታደግ የፌደራልና የክልል መንግስታት በትኩረት ተናበው ሊሰሩበት ይገባል ይላሉ። “የተናጠል ሥራ ጣናን አይታደግም” ሲሉ አያሌው በትብብር መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 83 ግንቦት 29 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com