ኮቪድ-19 – በዕውቀትና በዕውቀት ብቻ የሚዋጉት ጠላት ነው!

Views: 246

ኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭቱን ቀጥሎ ዘግይቶ የጎበኛትን አፍሪካም እያስጨነቀ ይገኛል። ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቋቋም በሚደረግ ሂደት ውስጥ ታድያ በየጊዜው ተለዋዋጭ አካሄዶች ቢታዩም፣ በአፍሪካ ይልቁንም በኢትዮጵያ የሚታዩ ስህተቶች ግን ዋጋ እንዳያስከፍሉ እንደሚያሰጋ ግዛቸው አበበ አንስተዋል። በተለይም ባለሥልጣናትና ሹመኞች ከሙያቸውና ከሕዝብ ደኅንነት ይልቅ የፖለቲካ ጥቅምን ከማሰብ እንዲቆጠቡና፣ ወርሽኙን የመከላከል ሥራም ታስቦበት በእውቀት ሊመራ ይገባል ሲሉ ያስተዋሏቸውን ችግሮች ነቅሰው ጠቅሰዋል።

ኮቪድ-19 ቻይናን ማተራመስ ሲጀምር ሌላው ዓለም በሽታው ከቻይና የማያልፍ፣ ካለፈም ሳርስ እንደተባለው በሽታ ከጥቂት የቻይና ጎረቤት አገራት የማያልፍ ችግር አድርገው ተመልክተውት ነበር። ችግሩን ቻይና ሠራሽና ቻይናን ብቻ የሚቀጣ አድርገው በመመልከትም ጉዳዩን ለፖለቲካዊ ፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ማዋል በሰፊው ታይቷል። ጥቂት የምዕራቡ ዓለም ባለሥልጣናት በተለይም የአሜሪካ ፕሬዘደንትና የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በሽታውን በመጠቀም የተለመደ ጸረ-ቻይና ፕሮፓጋንዳቸውን ሠርተውበት ሚድያዎቻቸውም በዚሁ መንገድ ነጉደዋል።

በዶቸቨለ፣ በቢቢሲና በቪኦኤ አማካኝነት ኢትዮጵያውያንም ፕሮፓጋንዳውን ተጋብዘን ቻይና በበሽታው ስትተራመስ፣ እኛ እንደ ቴአትር እንደምንመለከት እንድናስብ ተደርገናል። የምዕራቡን ዓለም ወሬ ተቀብሎ ያለ ማመዛዘንና ያለ ማስተዋል በቀጥታ የሚያስተጋቡት ጋዜጠኞቻችንም ይህን ጸረ-ቻይና ፕሮፓጋንዳ በመለዱት ወግ ጨፍረውበታል፣ በቻይና ላይ ለመሳለቅም ሞክረዋል። ከዶቸቨለ፣ በቪኦኤና በቢቢሲ በኩል የተጀመረውን ቻይና ውስጥ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አዛኝ ቅቤ እንጓችነት ሥራዎችንም በዚህ አገር ያሉ የሚዲያ ሰዎችም እየተቀባበሉ አሳቢና ተቆርቋሪ ሆነው ለመታየት ሞክረዋል።

ይህን መሰሉ ሥራ በግል ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ጣቢያዎች ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ ግሰቦች ብቻ ሳይሆን በራሱ በመንግሥት ቴሌቪዥን ላይ በተለይም ኢቲቪ መዝናኛ በተባለው ጣቢያ ቀርቧል። ቻይና የሚገኙ የሚያውቋቸውን ኢትዮጵያውያንን በስልክ በማነጋገርና እዚህ ያሉ ቤተሰቦቻውን በማቅረብም ጭምር ወያኔያዊ ጥቃት በብልጽግና ላይ ሰንዝረዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም ወረርሽኙን በመመርኮዝ ከሕክምና ዕውቀት የራቀ፣ ነግ በኔን ያላሰበና ለቻይናውያን ጥላቻን የሚዘራ ሰፊ ሥራ ተሠርቷል። ይህም ከፍተኛ ዋጋን አስከፍሏል። በመሪዎቻቸው፣ በሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንዲሁም በጋዜጠኞቻቸው አማካኝነት ወረረሽኙን ተጠቅመው ጸረ-ቻይና ቁማር እየተጫወቱ ወርቃማ ጊዜያቸውን ያባከኑት አሜሪካና እንግሊዝ፣ ሕዝባቸው ከፍተኛና መራር ዋጋ እንዲከፍል አድርገዋል።

ቫይረሱ ከቻይና አልፎ ዓለማቀፍ ወረርሽን መሆኑ ሲታወጅም ሆነ ኢትዮጵያ መግባቱ ከታወቀ በኋላ፣ በኢትዮጵያም ከዕውቀትና ከምክንያታዊነት የራቁ በርካታ ስህተቶች ተሠርተዋል። በሽታው ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ያለው ስርጭት ደከም ያለ ሆኖ፣ የደረሰው ኪሳራም ዝቅተኛ መሆኑ በጀን እንጂ፣ በሽታው በአሜሪካና በአውሮጳ ጥቃት ባደረሰበት ጥንካሬው አፍሪካንም ደባብሷት ቢሆን ኖሮ፣ በዓለም ጤና ድርጅት፣ በተባበሩት መንግሥታትና በብልጽግና መር ሹመኞቻችን በኩል የተተነበየው እልቂት ይደርስ ነበር።

እነሱ በተነበዩት ልክ መቃብሮች ለመቁጠርም ብቻ ሳይሆን በመንገዶች ዳርና በየሰፈሮች ውስጥ የወደቁ አስከሬኖችን ለማየትም እንገደድ ነበር። ‹ሳይደግስ አይጣልም› ይባላልና፣ ወረርሽኙ እንደ ድህነታችንና እንደ መንግሥት ችላ ባይነት እሱም እንደ ተናቀ ጠላት ተኩሱን ሳያርከፈክፍብን ችላ ብሎናል ማለት ይቻላል። የቫይረሱን ችላ ባይነት በዚሁ ያዝልቅልን!

‹የበላይ እኔ ነኝ!› በሚል የማን አለብኝነት አስተሳሰብ፣ ፖለቲካዊ ትርፍ ለመቃረምና የሥልጣን ዕድሜን ለማራዘም ሲባል የሕክምና ዕውቀትና የሕክምና ባለሙያዎችን ወደ ጎን በመግፋትና አድርባይ የሆኑ የሕክምና ባለሙያዎችን ለፖለቲካዊ ፍጆታ የሚውሉ ጀሌዎች አድርጎ በማሰለፍ፣ አደገኛ የቁማር ጨዋታ በመካሄድ ላይ ነው። የዚህን ለፖለቲከኞች ትርፍ ሲባል የሚካሄድ አደገኛ ቁማር፣ ሕዝብና አገር ዋጋ ሊከፍሉበት ጫፍ ላይ ደርሰዋል። ሕዝብና አገር ኪሳራውን ማወራረድ የጀመሩ መሆኑንም የሚያመላክቱ ፍጻሜዎች እየታዩ ነው።

ግራ አጋቢው ቁማር የተጀመረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ባሉበት እንዲቀጥል በማድረግ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል። መንገደኞችም ወደ አገር ቤት ሲገቡ ሲካሄድ የነበረው የሰውነት ሙቀት ምርመራ አንድ በአንድ ሳይሆን እንደ ጎርፍ የሚተሙትን መንገደኞች በጅምላ ስካን በማድረግ ስለነበረ ብዙዎች ስጋታቸውን መግለጻቸው አይዘነጋም።

ራሳቸው መንገደኞቹ የሰውነትን ሙቀትን ለጊዜው የሚቀንስ ክኒን እየወሰዱ የፍተሻ ቦታውን የሚያልፉ እንደነበሩ ተናግረዋል። በአየር መንገዱ አካባቢ የሚደረገው ጥንቃቄ በእንከን የተሞላ ነበር ማለት ይቻላል። ይህ ሁሉ ችግር እንዲፈጠር ምክንያት የሆነው፣ አየር መንገዱ በረራ ባያቆም እንኳ የተወሰኑ በረራዎችን ለመቀነስ ባለመፈለጉ፣ ቦሌ አየር ማረፊያ በየሰዓቱ የሚያስተናግደው የወጭና ገቢ መንገደኞች ብዛት ከፍተኛ በመሆኑ ነው።

አንድ ለቢቢሲ የሚሠራና በቦሌና በጀሞ ኬንያታ አየር ማረፊያዎች ተገኝቶ የሚደረጉ ጥንቃቄ እርምጃዎችን ለማነጻጸር ዕድል ያገኘ ጋዜጠኛ፣ የቦሌው የጥንቃቄ እርምጃ በለብ ለብ ሥራዎች የተሞላ፣ የይምሰልና የይስሙላ ነው በማለት ገልጾት ነበር። ይኸው ጋዜጠኛ ቦሌና ጀሞ ኬንያታ አየር ማረፊያዎች ላይ የሚደረጉ የመንገደኞች የጉዞ ታሪኮችን የመፈተሹን ወሳኝ ሥራ በሚመለከትም፣ ቦሌ ላይ በተመረጡ በረራዎች የገቡ መንገደኞች ብቻ ስለ ጉዞ ታሪካቸው ራሳቸው ይናገሩ ዘንድ ሲጠየቁ፣ ጀሞ ኬንያታ ላይ ግን የእያንዳንዱ መንገደኛ መፈተሽ የሚችሉ የበረራ ሰነዶች ሁሉ አንድ በአንድ እየተፈተሹ የመንገደኞችን የጉዞ ታሪኮች መሰረት በማድረግ እርምጃዎች ይወሰዱ ነበር ብሏል።

እነዚህ ሁሉ ይደረጉ ነበሩ የሚባሉ የጥንቃቄ እርምጃዎች ጎደሎነት የነበረባቸው እንደሆኑ ማሳያዎች ናቸው። ይህን መሰሉ ጉድለት እንዲከሰት ያደረገው ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጤና አጠባበቅ ዕውቀትና ለሙያው በቆመ የሕክምና ባለሙያ በታገዙ ውሳኔወች ይመራ ስላልነበረ ነው።

አንድም በረራ ለማቋረጥ ፈቃደኛ ያልነበሩት የኢትዮጵያ አየር መንገድና መንግሥት፣ በአውሮፕላን ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎችን ለ14 ቀናት ማቆያ ውስጥ እንዲገቡ ያደረጉት ዘግይተው ነው። ከዛም በላይ ወደ ማቆያ የማስገባት ሥራ ሲጀመርም በዚያው አውሮፕላን ውስጥ ከመንገደኞች ጋር ለሰዓታት በበረራ ላይ የቆዩት

የአውሮፕላኑ ሠራተኞች (ፓይለቶችና አስተናጋጆች) በቀጥታ ወደ ቤተሰቦቻቸውና ወደ ኅብረተሰቡ ይቀላቀሉ ነበር። ስለዚህም ጥንቃቄው ምሉዕነት የጎደለው ነበር።
ከውጭ የመጡ መንገደኞች ገንዘብ እየከፈሉና በአጥር እየዘለሉ ከማቆያው ቦታ መጥፋታቸው በተደጋጋሚ መነገሩ አይዘነጋም። ከዚህ ሌላ ከውጭ የመጡ መንገደኞች በማቆያዎች ውስጥ ናሙናዎች ለምርመራ ተወስደው መንገደኞቹ ውጤቱን ከማወቃቸው በፊት 14 ቀናቱ ተገባድደው፣ መንገደኞቹም ወደ ኅብረተሰቡ ከተቀላቀሉ በኋላ ውጤቱ ይደርሳቸው እንደነበረ ከመንገደኞች አንዳንዶቹ ተናግረዋል። ይህም ሌላው ግራ አጋቢና የሕክምና ዕውቀትን የሚጻረር አሠራር ነበር።

የሕመም ስሜት ተሰምቷቸው ራሳቸውን በቫይረሱ ተጠቂነት የጠረጠሩ የበረራ አስተናጋጆች ቤተሰቦቻቸውን ለአደጋ ላለማጋለጥ ሲሉ አየር መንገዱ በገለልተኛ ቦታ እንዲያስቀምጣቸው ወይም ራሳቸውን ለማግለል ሙከራ ሲያደርጉ፣ የአየር መንገዱ ባለሥልጣናት ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ ግፊቶች ያደረጉባቸው እንደነበር መዘገቡ አይዘነጋም። ቆየት ብሎ ጥቂት አስተናጋጆች የኮቪድ-19 ተጠቂዎች ሆነው መገኘታቸውን አየር መንገዱ ማሳወቁ ይታወሳል። በድምሩ አየር መንገድ በሽታው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ያደረገው የመከላከል እርምጃ ጎዶሎነት ሰፋ ያለ ነበር ማለት ይቻላል።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይህን አሳሳቢ ጉዳይ በሚመለከት የዳር ተመልካች ሆነው ለመታየት መሞከራቸው፣ ብዙ እሮሮዎችና ጫጫታዎች ሲሰሙ ያልሰሙ መስለው ማለፋቸው እንዳለ ሆኖ፣ ጉዳዩን በሚመለከት ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖችን ሁሉ ፊት ለፊት የመጋፈጥ ግዴታ ውስጥ የገቡት የአየር መንገዱ ኃላፊ፣ ወደ ቻይና የሚደረጉ በረራዎች ለምን አይቆሙም የሚለውን ጥያቄ በመለሱበት አንድ አጋጣሚ፣ ‹‹ቻይናን ማግለል አይገባም›› የሚል ምላሽ ሰጡ። የጤና ሚኒስትሯም በረራ መቀጠሉን የሚመለከት ጥያቄ ሲቀርብላቸው፣ ‹በረራ ያገዱ አገራትም በበሽታው እየተጠቁ ነው› በማለት በረራ በመከልከልና ባለመከልከል መካከል ልዩነት የሌለ የሚያስመስል መልስ ሰጥተዋል።

ሆኖም ሌሎች በርካታ አገራት በረራዎችን በማገዳቸው መሄጃ እያጣ የመጣውን አየር መንገዱ ከበረራ ውጭ በመሆን ግዴታ ውስጥ ገብቶ፣ በሌሎች መንግሥታት ተዘዋዋሪ ጫና ምላሽ አግኝቷል። ያም ሆነ ይህ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያችን በአውሮፕላን እና በምድር (ከጅቡቲ፣ ከኬንያ፣ ከኹለቱ ሱዳኖችና ከሶማሊያ) ድንበር አቋርጠው የሚገቡ መንገደኞች በሽታውን ይዘው የመጡባት አገር ከመሆን አልፋ በሽታው በአገር ውስጥ ንክኪወችም የሚሰራጭባት አገር ሆናለች።

የኮቪድ-19 ምርመራ ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው በሽታው ገብቶ ጥቂት ጊዜ ከተቆጠረ በኋላ ነው። ምርመራው አስፈላጊና አይቀሬ መሆኑ ታምኖበት ቀድሞ መዘጋጀት የነበረበት ጉዳይ ቢሆንም፣ ይህ አልተደረገም። መንግሥትም ሆነ ጤና ሚኒስቴርንና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን የመሳሰሉ ነገሩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሽታው እንደተገኘባቸው ያሳወቁ አገራትን ጨምሮ የተለመዱ በረራዎቹን በሙሉ መቀጠሉ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ምርመራ ለማካሄድ የሚያስችሉ መሰረታዊ ቁሶችን ለማሟላትና ለጤና ባለሙያዎቹም ሥልጠና ለመስጠት ዳተኞች ሆነው ቆይተዋል። ለዚህስ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ተቀባይነት ያለው ምክንያታውን ማስረዳት ይችሉ ይሆን?

ቫይረሱ ኢትዮጵያ መግባቱ የተረጋገጠውና ከዚያም ከተጠርጣሪዎች የተወሰደ ናሙና ምርመራ የሚካሄድለት ወደ ደቡብ አፍሪካ እየተላከ እንደነበረ አይረሳም። ምርመራው ኢትዮጵያ ውስጥ ዘግየት ብሎ ከጀረመ በኋላም አዲሰ አበባ ውስጥ በአንድ ተቋም ብቻ ተወስኖ እንደነበረ፣ ምርመራውን ወደ ክልሎች ለማውረድም ሌላ ረዥም ጊዜና ብዙ እሮሮ ማሰማቶችን እንደጠየቀ አይዘነጋም። በመንግሥት ባለሥልጣናትና ጉዳዩ በሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት በኩል ምርመራውን ወደ ክልሎች የማውረዱ ጉዳይ መነጋገሪያ መሆን የጀመረው፣ የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ከአይደር ዩንቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ጋር በመተባበር በቀን እስከ 250 ሰው መመርመር የሚያስችለውን ቁመና እንደፈጠረ ማወጁን ተከትሎ ነው።

ከዚህ የትግራይ ጤና ቢሮ ዜና መሰማት በኋላ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲና የኦሮምያ ክልል መንግሥት ድንጋጤ የፈጠረው የሚመስል ምርመራ በማካሄድ የዝግጁነት ወሬዎችን በሰፊው መልቀቃቸው፣ ከዚያም ሌሎች ክልሎችና ዩኒቨርሲቲዎችም ተመሳሳዩን የወሬ ዘመቻ ማካሄዳቸው ግልጽ ነው።

ቫይረሱ ኢትዮጵያ መግባቱ በተነገረ ማስግት ጀምሮ ብዙ ሰዎች ማስክ አድርገው ታይተዋል። በዚሁ ዕለት ወደ ጉልቶች ብቅ ያለ ሰውም በዚያ የሚሸቅጡ በርካታ ሰዎች በተለይም እናቶች አፍንጫቸው ላይ የተላጡ የነጭ ሽንኩርት ፍሬዎች ሰክተው ባህላዊ ዕውቀታቸው በፈቀደላቸው መንገድ ራሳቸውን ከበሽታው ለመጠበቅ ጥረት ማድረግ መጀመራቸው ታይቷል። የማስኩ ገበያም ደርቶ ነበር። በሚያስገርምና በሚያስደነግጥ ሁኔታ መገናኛ ብዙኀን ላይ የሚቀርቡ ብዙ ሰዎች ማስክ ያደረጉ ሰዎችን ሲኮንኑና ሲያጣጥሉ ተደምጠዋል።

ማስክ ማድረግ የሚገባቸው የሕክምና ባለሙያዎች፣ ታማሚዎችና አስታማሚዎች ናቸው የሚል አደናጋሪ ምክር ወደ ሚድያ የመቅረብ ዕድል ባገኙ ሰዎች ይሰነዘር ነበር። አሁን ደግሞ ማስክ ማድረግ በአዋጅ የተጣለ ግዴታ የሆነበት፣ ማስክ ያላደረጉ ሰዎች እየታፈሱ የሚታሰሩበት፣ በሕዝብ ትራንስፖርት ከመሳፈር የሚከለከሉበት፣ ከገዛ መኪናቸውም ሆነ ከታክሲና ከአውቶብስ እየተጎተቱ የሚወርዱበት፣ በአደባባይ በዱላ የሚነረቱበት ጊዜ መጥቷል።

እነዚህ ኹለት ተቃራኒ ፍጸሜዎች ሲከናወኑ በተለይም ያም ይህም እየተነሳ ማስክ መጠቀምን ሲያጣጥል የጤና ሚኒስትርና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንደ ቴያትር ተመልካች መሆናቸው አስገራሚም አሳዛኝም ነው። ይልቁንም ምርጫን በሚመለከት ፖለቲከኞች ኮሮናን በተቃራኒ አስተያየቶች እያዩ በተጻራሪ ውሳኔወች ላይ ለመድረስ ሲፍገመገሙ፣ የፌዴራልና የትግራይ የጤና ተቋማት የየፖለቲከኞቻቸው ሐሳብ አራማጆች የመሆን አዝማሚያ አሳይተዋል። ወረርሽኙን በማስታከክ የሚደረጉ አደገኛ የፖለቲካ ጨዋታዎችንም በዝምታ እያዩ ነው።

በዚህ በያዝነው ግንቦት ወር ፋና ብሮድካስቲንግ ጨምሮ አዲሰ አበባ የሚገኙ መንግሥት የሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎች እንደ ዋና ዋና ዜናዎች አድርገው ይዘዋቸው ከከረሟቸው ወሬዎች መካከል ‹ትግራይ ላይ ጽሕፈት ቤት የለውም› የሚባለው የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ አዲስ አበባ ላይ ስብሰባ ማካሄዱ አንዱ ነው። የፌዴራልና የክልል ባለሥልጣናት ወይም ወኪሎቻቸው በተገኙበት ለምስኪን ቤተሰቦች ዕርዳታ ተሰጠ የሚሉት ዜናዎች ደግሞ ሌሎቹ ናቸው። ዕርዳታ በመስጠት ሥም የሚፈጠረው የባለሥልጣናትና የሚዲያዎቹ ግርግር ነገሩን ምስኪኖችን በሰብዓዊነት ተነሳስቶ መርዳት ነው ከማለት ይልቅ፣ የብልጽግና ቡድን የምርጫ ቅስቀሳና ገጽታን የማሳመር ሥራ በመሥራት ላይ ነው ቢባል ከሃቁ መራቅ አይሆንም።

በወረርሽኙ ምክንያት ምርጫ እንዲራዘም በማድረጉ ራሱን እንደ ትልቅ ባለውለታ አድርጎ በማቅረብ ላይ ያለው የአዲሰ አበባው መንግሥት፣ ወረርሽኙ ዓለማቀፍ መሆኑ ታውጆ በነበረበት ጊዜ የጀመረውን የገጽታ ማሳመሪያና የቅስቀሳ ሰልፍ/ስብሰባ በሽታው ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከተረጋገጠ በኋላም አንዳንድ ካድሬዎቹ ከሚያሰሙት ‘ብልጽግናን ኮሮን አይበግረውም!’ ከሚል ቀረርቶ ጋር ቀጥሎበት እንደነበረ አይዘነጋም። በሽታው በኢትዮጵያ አድማሱን ማስፋቱን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቶ ቅስቀሳዎችና ሰልፎቹ ቢገቱም፣ ብልጽግና ቅስቀሳውንና ገጽታውን የማሳመሩን ሥራ ለየት ባለ መንገድ እያካሄደ መሆኑን መረዳት ይቻላል።

በዕርዳታ ማሰራጫ ጊዜያት ዕርዳታ ለመቀበል ከመጡት የቤተሰብ ተወካዮች ውስጥ እናትን ከኹለትና ሦስት ልጆቿ ጋር፣ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ዕርዳታውን ከሚሸከሙላቸው ኹለትና ሦስት ሰዎች ጋር ወዘተ… ማየት ይቻላል። በአጭሩ ከአንድ ቤተሰብ አንድ ሰው ብቻ የሚገኘው በጣም በውስን ቁጥር ነው ማለት ይቻላል። እንደዚህ ተሰባስበው የመጡት ተረጅዎች ወዲያውኑ ዕርዳታውን ተቀብለው ወደየቤታቸው እንደማይሄዱም መታወቅ አለበት። በቦታው ተገኝተው ንግግር የሚያደርጉና ለዜና ፍጆታ የሚሆን ምስል ለማስቀረት ሲባል ብቻ ዕርዳታውን ለሦስትና ለአራት ሰው እየሰጡ በየተራ በካሜራ የሚቀረጹ ባለሥልጣናት በቦታው እስኪገኙ መጠበቅ የግድ ነው።

ምስሎቹ ሲቀረጹም ሆነ ዜና ሲሠራባቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ስለሚደረግባቸው አደገኛውን ዕውነታ በሚዲያዎቹ ላይ በሚቀርቡ ምስሎች ማየት ባይቻልም፣ በዕርዳታ ሥም ብዙ ሰዎችን በአንድ ግቢ ሰብስቦ ለረዥም ጊዜ ማቆየቱ በእርግጥም በሰው ልጅ ሕይወት አደገኛ የፖለቲካ ቁማር መጫወት መሆኑና ካድሬዎችና ባለሥልጣናቱም ቸልተኞች መሆናቸው ሊዘለል የማይገባው ሃቅ ነው። ምስሎች ሲቀረጹ ጥንቃቄ በመደረጉ ወይም ምስሎች ዜና ለመሆን ሲስተካከሉ ሃቁን የመሸፋፈን ሥራ ቢሠራም ይህ ጉዳይ አደገኛ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም።

ምስሎች ሲቀረጹ ሰብሰብ ብለው የመጡ የቤተሰብ አባላት እንዲበተኑ፣ ካሜራ ውስጥ የሚገቡ ሰዎች ርቀታቸውን እንዲጠብቁና በተዘጋጁ ወንበሮች ላይ ብቻ ሆነው እንዲታዩ፣ ካሜራ ውስጥ የሚገቡ ተረጂዎች ማስክ ያደረጉ ብቻ እንዲሆኑ ወዘተ…. በማድረግ አደገኛውን ነገር ለመሸፋፈን መሞከር ችግሮች እንዳይከሰቱ መከላከያ መሆን እንደማይችል ታውቆ እርምት ሊደረግ ይገባል። ይህን መሰሉን ቁማር ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ከአዲስ አበባ ከንቲባ ቢሮ የተላኩ ሰዎች በተገኙበት ጭምር ሲከናወን ስለሚታይ አሳሳቢነቱን ከፍ ያደርገዋል።

ለምሳሌ ግንቦት 2/2012፣ በዕለተ ሰንበት በድር ፋውንዴሽን በተባለ ለጋሽ አማካኝነት የቀረበ ዕርዳታ ለተረጂዎች በተሰጠበት ወቅት የፋውንዴሽኑ መሥራች፣ ኹለት የወረዳና የክፍለ ከተማ ተወካዮች፣ ምክር ሰጭ የተባለ የሐይማኖት ምሁር፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የተወከለ ሰው፣ ከአዲሰ አበባም ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የተወከሉት እንግዳወቅ አብጤ ወዘተ…. በቦታው ተገኝተው ንግግር ማድረጋቸው በተለያዩ ሚዲያዎች ታይቷል።

ይህን መሰል ሰዓታትን የሚወስድ፣ ምስኪኖችን ፀሐይ ላይ እያንቃቁና ብዙ ሰዎችን በአንድ ላይ በአንድ ግቢ አጉሮ የሚሠራ ድራማ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል። ስለዚህ ከመርፈዱና ችግሮች ዐይናቸውን አፍጥጠው ከመውጣታቸው በፊት የብልጽግና ቡድን ካድሬዎችና ባለሥልጣናት ብቻ ሳይሆኑ ዕርዳታ ለጋሽ ወገኖችም ጭምር ሊያስቡበት ይገባል።

ምርጫው የተራዘመው ብዙዎችን እንደዚህ መሰብሰቡ፣ ሰብስቦም የፖለቲከኛና የካድሬ ዲስኩር እያሰሙ ለረዥም ጊዜ በአንድ ቦታ ማቆየቱ ሕዝብን ለወረርሽኙ ያጋልጣል ተብሎ ስለተፈራ ነው። በዚህ ጊዜ ይህን የመሰለ ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት በድሆች ላይ መፈጸም የብልጽግና ባለሥልጣናትንና ካድሬዎችን ብቻ ሳይሆን እነዚህን ፖለቲከኞች እየጠሩ ዕርዳታውን ለፖለቲካዊ ቁማር ቴአትር መሥሪያ የሚያደርጉ በጎ አድራጊዎችም ትዝብት ላይ እየወደቁ መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል።
በዚህ የኮሮና ወቅት ምርጫ አለመካሄዱ ተገቢ መሆኑን በተለያዩ ቦታዎች እየተገኙ ሙያዊ ምስክርነታቸውን በመስጠት ላይ ያሉት የጤና ሚኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ቁንጮ ባለሥልጣናት፣ በእርግጥ ለኅብረተሰቡ ደኅንነት አስበው የምርጫውን መራዘም ተቀብለውት ከሆነ፣ ይህን መሰሉን ቤተሰብን በገፍ እየሰበሰቡ ድራማ የመሥራቱን ነገር የማይተቹት ብሎም የማያስቆሙት ለምን እንደሆነ ማብራሪያ መስጠት አለባቸው።

ማንም ሊያውቀው የሚገባው ነገር እነዚህ ፋና ቲቪ፣ ኢቲቪ፣ አዲስ ቲቪ ወዘተ… ላይ የቀረቡ የዕርዳታ ወሬዎች በመገናኛ ብዙኀኑ ላይ የሦስት ወይም የአምስት ደቂቃ ዜናዎች ሆነው ቢታዩም፣ እነዚያ የዕርዳታ ፕሮግራሞች በጣም ብዙ ሰዎችን ለሦስትና ለአራት ሰዓታት በአንድ ቦታ በማጎር የተሠሩ ድራማዎች መሆናቸውን መገንዘብ ተገቢ ነው። በአንዳንዶቹ ዜናዎች ላይ ንግግር ያደረጉት ኹለትና ሦስት ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ተደርጎ ዜናው ቢሠራም፣ ተናጋሪዎች ብዙዎች መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል።

ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ሆኑ ጉዳዩ በባለቤትነት የሚመለከታቸው የጤና ሚኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሹማምንት፣ ወረርሽኙ የዋዛ አይደለምና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ታዛዥና ታማኝ ሆኜ ጥቅሜን አስከብሬ እኖራለሁ እያሉ ቁማር የሚጫወቱበት ጉዳይ አለመሆኑን ቆም ብለው ማሰብ ይገባቸዋል።
የተቋማቱ ቁንጮ ኃላፊዎች ሹመኞች ቢሆኑም፣ በሙያቸው ተመርጠው በቦታው ላይ እንደሚገኙ ይገመታልና ከሙያቸው ጋር የሚጻረሩ ፖለቲካዊ ውሳኔዎችና ትዕዛዛት የሚበዙ ከሆነ ሥራውን ቦታውን በመልቀቅ ለሕዝብ እንደሚያስቡ ማሳየት ይገባቸዋል። ማናቸውም የተቋማቱ ሰዎች ፖለቲካውን፣ ፕሮፓጋንዳውንና ገጽታ መሳማሩን ወደ ጎን ብለው የዕውቀት ሥራ ቢሠሩ መልካም ነው። ዕውቀት ያልታከለባቸው ሥራዎች መዘዛቸው ከፍተኛ መሆኑ አጠራጣሪ አይደለም። ችግሮችን በሐሰተኛ ወሬዎችና እኔ አላውቅም በሚሉ መሸፋፈኛዎች ለማድበስበስ መሞከርም ሊያቆም ይገባል።

በዚህ በኩልም ወረርሽኙ እንደ ዋዛ እየታየ እንደሆነ የሚያሳብቅ ድራማ እየታየ ነው። የትግራዩ ገዥ ሕወሐት ምርጫውን በሚመለከት የያዘው አቋም የሚዋዥቅና ፈራ ተባ በማለት የተሞላ ቢሆንም፣ ደቡብ ኮርያ ምርጫ አካሂዳለችና ትግራይም ለየት ያለ መመሪያና አሠራር አዘጋጅታ ምርጫውን ማካሄድ ትችላለች የሚለው አዝማሚያ ሕወሐት በእልከኝነት ወደ ምርጫ ማካሄድ ሊገባ እንደሚችል የሚያስጠረጥር ነው።

ሕወሐት በየቤቱ እየተዞረ መራጭና ተመራጭ የሚመዘገብበት፣ በመገናኛ ብዙኀን ቅስቀሳዎች የሚካሄዱበትና ድምጽ ማስጫ ኮረጆዎችንም በተመረጡ የምርጫ አስፈጻሚ በተባሉ ሰዎች በየቤቱ እያዞረ ድምጽ ተሰጠ ብሎ እልኩን ሊወጣ ካልሆነ በስተቀር፣ እንደ ደቡብ ኮርያ የተለመደው የምርጫ አካሄድ ከሚጠይቀው በጀት በአምስትና በስድስት እጥፍ የሚበልጥ ከፍተኛ በጀት መድቦ፣ መከላከያ ቁሶችን (ማስክ፣ ጓንትን የመሳሰሉ) ለእያንዳንዱ ግለሰብ አድሎ፣ ለየምርጫ ጣቢያው በመቶ ሊትሮች የሚለካ ሳኒታይዘር ወይም በቂ እጅ መታጠቢያ ውሃና ሳሙና አስቀምጦ፣ የምርጫ ጣቢያዎችንና አካባቢያቸውን በተገቢው ኬሚካል ረጭቶ፣ በጋራ ጥቅም ላይ የሚውሉ ቁሶችን (ብዕር፣ ቀለም፣ ጠረጴዛዎች፣ ኮረጆወች ወዘተ…) በሙሉ ከአደጋ ነጸ አድርጎ ምርጫ አካሂዳለሁ ማለት ዘበት ነው።

ነገር ግን ሕወሐት የደቡብ ኮርያውን የመሰለ፣ ነጻና ግልጽ፣ የሕዝብ ድምጽ ወሳኝ የሚሆንበትን ምርጫ ማካሄድ ይችላልን? ይህ የማይመስል ነገር ነው። ሕወሐትም ሆነ የኢሕአዴግ አባል እና አጋር ናቸው እየተባሉ በምርጫ ሲቆምሩ የከረሙት ብልጽግናዎች ይህን የማድረግ ልምዱም፣ ፍላጎቱም ዝግጁነቱም እንደሌላቸው በግልጽ እየታየ ነው። እናም ለሚጭበረበር ምርጫ ተብሎ ተቸኩሎ ወደ ችግር ባይገባ መልካም ይሆናል። በወረርሽኙ ምክንያት በተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ትግራይ ላይ የሚተኮሰውና ወጣቶችን በመግደልና በማቁሰል ላይ ያለው ጥይት ምርጫውን ተከትሎ በሚመጣው አይቀሬ ውዝግብ ተጨማሪ ሕይወት ከመቅጠፍ የተለየ ውጤት የማይገኝበትን ምርጫ ለማካሄድ ባይቸኮል ጥሩ ነው።

የትግራዩ ገዥ ሕወሐትና እዚያው ትግራይ ውስጥ ተመሠረቱ የሚባሉ ሦስት አዳዲስ ተቃዋሚ ነን ባይ ፓርቲዎች፣ በእርግጥ ከሕወሐት ጋር ምንም ልዩነት ስለሌላቸው ቁጥር 2 ሕወሐት፣ ቁጥር 3 ሕወሐት እና ቁጥር 4 ሕወሐት ሊባሉ የሚገባቸው ፓርቲዎች ምርጫው መካሄድ አለበት ባዮች ሆነዋል። ከእነዚህ ድርጅቶች አባላት ብዙዎቹ ወይም ጥቂቶቹ፣ በተለይም ድርጅቶቹ ተለጣፊወች አይደሉም በሚል አስተሳሰብ የተቀላቀሉ አባሎቻቸው በምርጫው እንደሚደሰቱ አይጠበቅምና እንዲህ የቸኮሉለት ምርጫ የእነሱ በጥይት ተደብድቦ መሞቻ፣ መሰንከያ፣ መታሰሪያ፣ መሳደጃና ቤተሰብ መበተኛ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይገባቸዋል።

በዚህም ሆነ በዚያ በኮሮና ሥም የሚሠራው የአላዋቂነት ድራማ እየቀጠለ ነው። ማን ማንን እንደሚያታልል ግልጽ ባይሆንም፣ አዲሰ አበባና መቀሌ ያሉት ገዥዎች ሕዝብ እንደመረጣቸውና ሕዝብ መክሮበት ጸደቀ ለሚሉት ሕገ-መንግሥት ተገዥዎች ስለመሆናቸው እየማሉና እየተገዘቱ በኮቪድ-19 በመነገዱ ጉዞ ላይ ናቸው።
ከፖለቲከኞች ባልተለየ መንገድ የጤና ሚኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ችግሩን የያዙበትን ሁኔታ መመርመር እንደሚገባ የሚያመላክቱ አደጋዎች እየተከሰቱ ነው። አዲሰ አበባ አብነት ወረዳ 3፣ ቀጠና 5፣ መንደር 3 አካባቢ ስጋት እንዲያጠላበት ያደረገው፣ የመረጃ ክፍተት የአካባቢውን ነዋሪዎች ለችግሩ እንዲጋለጡ በሚያደርግ ሁኔታ ውስጥ እንዲገኙ ስላደረገ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪ ለዶቸቨለ ተናግረዋል። በሟች ቤት ለሐዘን የተገኙ ሰዎች ሟቿ በቫይረሱ ሕይወታቸው ማለፉን እንዳላወቁ ነው ከዶቸቨለ መረዳት የተቻለው።

ኮቪድ-19 ባልተከሰተበት ቦታና ሁኔታ ለድንገተኛ ክስተቶች ጥንቃቄዎች አለመደረጋቸው የወረርሽኙን ስርጭት ለመቆጣጠር አዳጋች እንዳያደርገው ማሰብ ያስፈልጋል። በግዥ ወይም በዕርዳታ የተገኙ የሐኪሞች መከላከያ አልባሳትና ቁሳ-ቁሶች የከፋ ችግር እስኪመጣ በሚል በመጋዘን ተቀምጠዋል የሚል የሕክምና ባለሙያዎች እሮሮን ደግሞ ቪኦኤ አሰምቷል። ይህን መሰሉ የሕክምና ባለሙያዎችን ለአደጋ አጋልጦ ቁሳቁሶችን የመቆጠብ አካሄድ፣ ባለሙያዎቹ በገፍ አደጋ ላይ ከመውደቃቸው በፊት ሊታሰብበትና ሊታረም ይገባል።

ለቫይረሱ ሕክምና ዝግጅት ባላደረጉ የሕክምና ቦታዎች አንድና ኹለት ሰዎች የበሽታው ተጠቂዎች ሆነው በተገኙ ቁጥር 20፣ 40 እና 70 የሕክምና ባለሙያዎችን ወደ ማግለያ ቦታወች ወስዶ መከርቸምን አስፈላጊ ያደርገዋል። ይህም ወረርሽኙን በመዋጋት ረገድ አዋጭና ብዙ ርቀት የሚያስኬድ አይሆንም።

በጎንደር ሆስፒታል ለሌላ ሕመም ወደ ሆስፒታሉ የሄዱ ኹለት ሰዎች ቆየት ብሎ የቫይረሱ ተጠቂዎች መሆናቸው ስለታወቀ 79 የሕክምና ባለሙያዎችና 12 የታማሚዎቹ ቤተሰቦች ወደ ለይቶ ማቆያ ገብተዋል። ‹የውጭ አገር ጉዞ ታሪክ የሌላቸው እና በኮቪድ-19 ከታመመ ሰው ጋርም ግንኙነት የሌላቸው› የሚለው የሕመምተኞች መለያ ዘዴ ለችግሩ መከሰት መንስኤ መሆኑን ከሆስፒታሉ ዳይሬክተር ገለጻ መረዳት ይቻላል።

በጥቁር አንበሳም ግንቦት 17/2012 በተመሳሳይ መመዘኛ ከኮቪድ-19 ጥርጣሬ ውጭ ተደርጋ ሕክምና ላይ የነበረች ግለሰብ ሕይወቷ ካለፈ በኋላ በኮቪድ-19 ተጠቅታ እንደነበረ ስለተደረሰበት፣ በቦታው በሥራ ላይ የነበሩ በርካታ የሕክምና ባለሙያዎች ራሳቸውን አግልለው በሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ ተቀምጠዋል።
እንደ ሆስፒታሉ ዳይሬክተር ገለጻ ወደ 28 የሚሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች መገለል እንደነበረባቸው ጠቅሰው የመከላከያ ቁሶችን በሁሉም ሕክምና ማእከላት ጥቅም ላይ የማዋሉ ጉዳይ ካልታሰበበት መዘዙ አደገኛ መሆኑን ጠቁመዋል። ረቡዕ ግንቦት 19/2012 ምሽት ከተሰማው የቪኦኤ ዜና፣ ስጋት ያጠላባቸው የጥቁር አንበሳ የሕክምና ባለሙያዎች ምርመራ ተደርጎላቸው ከኮቪድ-19 ነጸ መሆናቸው ተረጋግጧል።

ይህ ጥድፊያ የሞላበት ምርመራ ሐኪሞችን በቶሎ ወደ ሥራቸው ለመመለስ ወይም በማቆያ የሚጠየቀውን ወጭ በመፍራት ተብሎ ተካሂዶ ከሆነ፣ በጊዜ ዕርምት ሊደረግበት ይገባል። ሌላው ቢቀር ጥቁር አንበሳን የሚያክል ሆስፒታል ውስጥ የሚሠሩ የሕክምና ባለሙያዎች በጭንብልና በጓንት እጥረት እንዲማረሩ የሚያደርግ ችግር ካለ፣ የሚመለከታቸው ባለሥልጣናትና ተቋማት ሁሉ ራሳቸውን መፈተሸ ይገባቸዋል።

በቂ በጀት አለመኖሩና የቁሳቁሶች በቀላሉ አለመገኘት ተጠቃሽ ችግሮች መሆናቸው ቢታወቅም፣ የእነዚህ ችግሮች በቶሎ አለመቀረፍ የሚያስከትለው መዘዝ የከፋና የሕክምና ባለሙያዎችን ለጊዜው ወይም በቋሚነት የሚያሳጣ መሆኑ ታውቆ ለችግሩ መላ ሊበጅለት ይገባል። ፖለቲከኞችና ሹመኞች ሁሉ ለእኛ ኃይለኛ፣ ለአውሮፓና ለአሜሪካ ምህረት የለሽ ጨካኝ የሆነው የኮቪድ-19 ውጊያ ውጤታማ መሆን የሚችለው በሕክምና ባለሙያዎች ፊታውራሪነት መሆኑን ከልብ አምነው ሊቀበሉት ይገባል።

ትክክለኛ የሆኑ ቁሳቁሶች እስኪገኙ በተመሳሳዮቹ ጥሬ እቃዎች ተፈላጊዎቹን መከላከያዎች በማምረት ጥቅም ላይ ማዋል የሚቻልበትን ዘዴ ማፈላለግ አንዱ ጊዜያዊ መፍትሔ ሊሆን ይችላል። በማስክ ላይ የተሠራው ስህተት በሌሎች የሕክምናና ራስን መጠበቂያ ቁሳቁሶች ላይ ተከፍቶ እንዳይሆን የሚመለከታቸው ተቋማትና ባለሥልጣናት በሙሉ በጊዜ፣ ሳይረፍድ ራሳቸውን መፈተሽ ይገባቸዋል። በእነሱ ጥፋት እነሱ ራሳቸው መልሰው በሌላው ላይ ዱላ ማንሳታቸው በጭንብሉ ይብቃ ሊባል ይገባል።

ግዛቸው አበበ / gizachewgi@yahoo.com

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com